ራሱን ‹‹የደቡብ ሱዳን ቡድን›› በማለት የሚጠራው የሙርሌ ጎሳ ታጣቂ ቡድን የደቡብ ሱዳንን ወታደራዊ ዩኒፎርም በመልበስና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በመታጠቅ መቼ እንደተነሳ እስካሁን ማረጋገጫ ባይገኝም፣ ዓርብ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቅዳሜ አጥቢያ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጋምቤላ ደረሰ፡፡
ታጣቂው ኃይል ከደቡብ ሱዳን ግሬት ስቦር ግዛት ተነስቶ፣ በሁለት መንገዶች (ጆር እና ኦኛላ) 175 ኪሎ ሜትር አቋርጦ በኑዌርና በአኙዋ ዞኖች በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ተሰማራ፡፡
‹‹የደቡብ ሱዳን ቡድን›› እያለ ራሱን የሚጠራው የሙርሌ ጎሳ ታጣቂ ኃይል በወታደራዊ ሬዲዮ መረጃ እየተለዋወጠ በተመሳሳይ ሰዓት በከፈተው ተኩስ፣ ምናልባትም በታሪክ ዘግናኝ የሚባል ግድያ በሰው ልጆች ላይ ፈጽሞ ግዳዩን ይዞ በድል ዜማ ታጅቦ ወደመጣበት መመለሱ ተነግሯል፡፡
ለአራት ሰዓታት በቆየው የሙርሌዎች ዘግናኝ ጭፍጨፋ 182 የኑዌር፣ የአኝዋ እንዲሁም ደገኛ ወገኖች ሕይወት፣ እንዲሁም ከሚያዚያ 7 ግድያ ቀደም ባሉት ቀናት 26 ንፁኃን የተገደሉ በመሆኑ በድምሩ የሟቾች ቁጥር 208 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ጋምቤላ ከእንቅልፏ ሳትነቃ በተከፈተው በዚህ የሙርሌዎች የጥቃት ተኩስ፣ በተለይ እናቶችና ሕፃናት አስከፊ ጭፍጨፋ ተካሂዶባቸው እዚህም እዚያም ወድቀው ታይተዋል፡፡
በግፍ ከተጨፈጨፉት ወገኖች በተጨማሪ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት እስከ ስምንት ዓመት የሚደርሱ ምንም የማያውቁ 36 ሕፃናት በዕለቱ ታፍነው ከመወሰዳቸው በተጨማሪ፣ ቀደም ባሉት ቀናት 72 ሕፃናት ታፍነው በመወሰዳቸው በድምሩ የታገቱ ሕፃናት ቁጥር 108 ደርሷል፡፡
ከዚህ ዘግኛኝና ተቀባይነት ከሌለው ድርጊት በተጨማሪ 72 ንፁኃን ወገኖች ቁስለኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በንብረት በኩል በርካታ መኖሪያ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን፣ ከ2,000 በላይ ከብቶች ተዘርፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በአደጋው 20,000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ደረጃ፣ ጭፍጨፋ የፈጸሙት የሙርሌ ታጣቂዎች ያቀዱትን አሳክተው ሕፃናቱንና ከብቱን እየነዱ ወደመጡበት መመለሳቸው፣ የጋምቤላ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ ክስተት ሆኗል፡፡
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት፣ ጨፍጫፊው ቡድን ያቀደውን ካሳካ በኋላ በዜማ ታጅቦ መመለሱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
‹‹ራሱን የደቡብ ሱዳን ቡድን›› እያለ የሚጠራው ኃይል ዕልቂት ፈጽሞ በድል አድራጊነት ስሜት ወደመጣበት ተመልሷል፤›› ብለዋል፡፡
በእርግጥ አቶ ጋትሉዋክ ባይቀበሉትም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የጋምቤላ ነዋሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ዕልቂት ከመድረሱ በፊት ጫካ ውስጥ ፀጉረ ልውጦች መታየታቸውን ለአካባቢው የአስተዳደር አካላት ከኅብረተሰቡ ጥቆማ ደርሷል፡፡
እኝህ ግለሰብ እንደሚሉት ይህ መረጃ ጥቅም ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ይህ አሳዛኝና በዚህ ዘመን ሊታሰብ የማይገባው ዕልቂት ላይደርስ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ ጋትሉዋክ ፀጉረ ልውጦች ስለመታየታቸው የሚገልጽ ምንም ዓይነት መረጃ ለመንግሥት እንዳልቀረበ አስተባብለዋል፡፡
ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. እና ከዚያ ቀደም ባሉት ቀናት ሙርሌዎች በኑዌርና በአኙዋ ዞኖች በሚገኙት ጅካዎ፣ ላሬ፣ ሙከይ፣ ጆርና ጎግ ወረዳዎች በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ጥቃት ፈጽመዋል፡፡
አቶ ጋትሉዋክ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት የሚፈጽሙ መሆኑ ቢታወቅም፣ ይኼኛው ግን እጅግ የከፋ ነው፡፡
ይህ ጥቃት የከፋ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ሲያስረዱ፣ የመከላከያ ሠራዊት ዕልቂቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ባለመድረሱና የጋምቤላ ልዩ ኃይልና የፖሊስ ኃይል ትጥቅ እንዲፈቱ በመደረጉ ነው ይላሉ፡፡
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የሙርሌ ጎሳዎች ጥቃቱን አድርሰው የተመለሱት በተሽከርካሪዎች አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ከብቶችና ሕፃናት በመያዛቸው ፈጥነው ሊጓዙ አይችሉም፡፡
‹‹መከላከያ ሠራዊታችን በፍጥነት ቢሰማራ አንዳቸውም ሊያመልጡ አይችሉም ነበር፤›› በማለት አንድ ነዋሪ ቁጭታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም የጋምቤላ ልዩ ኃይል ትጥቅ ፈትቶ በመከላከያ ካምፕ እንዲገባ መደረጉንም ለአስከፊውና ለአሰቃቂው ጥቃት መንስዔ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ጋትሉዋክ እንደተናገሩት፣ የመከላከያ ሠራዊት ጦር ሠፈር ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች በግምት 60 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል፡፡
‹‹ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አካባቢዎች የመንገድ መሠረት ልማት የሌላቸው በመሆናቸው መከላከያ ሠራዊታችን መጠነኛ መዘግየት ነበረበት፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ፈጥኖ በመድረስ ዕርምጃዎች እየወሰደ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በጥር 2008 ዓ.ም. በኑዌርና በአኙዋ ብሔረሰቦች መካከል ተከስቶ የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭት ለመቆጣጠርና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣ የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ጋር በመሆን ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች ውስጥ የመጀመርያው ለግጭቱ መባባስ በጋምቤላ ልዩ ኃይል ውስጥ የሚገኙ የኑዌርና የአኙዋ ተወላጆች አስተዋጽኦ አለበት በማለት ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ማስፈታት አንዱ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ምክንያት የፖሊስ ኃይሉም ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሠረት የጋምቤላ ልዩ ኃይል አባላት ትጥቅ ፈተው እዚያው ጋምቤላ ውስጥ በሚገኘው የመከላከያ ጦር ካምፕ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደሮች ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው በወቅቱ ልዩ ኃይሉ ትጥቅ እንዲፈታ መደረጉን ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር የሚዋሰን በመሆኑ ሕገወጥ የጦር መሣርያ ዝውውር መኖሩ መረጃ መድረሱን፣ ይህ ሁኔታ ለጋምቤላ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አካባቢዎች ችግር እየሆነ በመምጣቱ የታጠቀውን ዜጋ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ይህ ዕርምጃ ከተወሰደ ከሦስት ወራት በኋላ የተከሰተው የሙርሌዎች ጭፍጨፋ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ራሱን መከላከል በማይችልበት ወቅት እንደተፈጠረ ይታመናል፡፡
አቶ ጋትሉዋክ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይልና ፖሊስ ትጥቅ እንዲፈቱ መደረጉን፣ በዚህ ምክንያት ጥቃት በተሰነዘረባቸው አካባቢዎች የጥበቃ ኃይል ባለመኖሩ ክፍተት መፍጠሩን አምነዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ለግጭት የተጋለጠ ከመሆኑ በተጨማሪ መረጋጋት ከተሳነው ደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር የሚዋሰን በመሆኑ፣ ዘወትር ትንኮሳ እንደማያጣው ይነገራል፡፡
የፌደራል መንግሥት ከዚህ በመነሳት በጋምቤላ ክልል ቋሚ የመከላከያ ሠራዊት ጦር ካምፕ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ጥቃቱ በደረሰባቸው ቦታዎች ቀደም ብሎ ኃይል ለማሰማራት ባለመቻሉ፣ አሰቃቂው ጭፍጨፋ ከመፈጸሙም በላይ ሙርሌዎች ሕፃናትንና ከብቶች እየነዱ ተረጋግተው መሄዳቸው ብዙዎችን እንዳስቆጨ እየተነገረ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደቡብ ሱዳን የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም የሰፈነበት አገር ባለመሆንዋ፣ ለኢትዮጵያ ፀጥታ አሥጊ ልትሆን የምትችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በመነሳት በሁነኛ መንገድ ድንበሩ ባለመጠበቁ፣ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት ባሉት ቀናት የንፁኃን ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ባላት ጉርብትና የጎላ ችግር አጋጥሟት አያውቅም፡፡ ‹‹ነገር ግን የከብቶች ዝርፊያ አለ፡፡ መከላከያ ሠራዊት ምላሽ የሚሰጠውም ሪፖርት ሲደርሰው እንደመሆኑ ሪፖርት እንደደረሰው ምላሽ ሰጥቷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከዚህ ውጪ ግን ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው ድንበሩ ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ታጥሮ ይጠበቃል ማለት አይደለም፤›› ብለው ‹‹ሕፃናት የታገቱ በመሆኑም የሚወሰደው ዕርምጃ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መሆን ይኖርበታል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት በወቅቱ በወሰደው ዕርምጃ 60 ያህል የሙርሌ ታጣቂዎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ጋር በጋራ ኦፕሬሽን ለማካሄድ ንግግር መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጉዳዩን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡
የሙርሌ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት ወተደራዊ ዩኒፎርም ለብሰውና ዘመናዊ መሣሪያዎች ታጥቀው ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫው ወቅት እንዳብራሩት በጉዳዩ ላይ የደቡብ ሱዳን መንግሥትና የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎቹ እንደሌሉበት ነው፡፡
አቶ ጋትሉዋክ ‹‹እስካሁን የፖለቲካ አጀንዳ መኖር አለመኖሩ አልተረጋገጠም፤›› በማለት ጉዳዩ ገና እየተጣራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ ጋትሉዋክ የታገቱትን ሕፃናት ሙርሌዎች ምን ያደርጓቸዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የከብት እረኛ ያደርጓቸዋል፡፡ ታጋቾቹ ሕፃናት እንደመሆናቸው የሙርሌ ቋንቋ እንዲለምዱ አድርገው እዚያው የእነሱ አካል ያደርጓቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ጋትሉዋክ ድንበር ሰብረው የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎችን ቁጥር መገመት ባይችሉም ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑን ግን ያምናሉ፡፡ ታጣቂዎቹ ጉዳት ያደረሱባቸውን ነዋሪዎች በማሰባሰብ ድጋፍ ለመስጠት እየተሞከረ መሆኑን ሥጋት ለገባቸው ነዋሪዎችም መንግሥት በማፅናናት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የደረሰውን ግድያና አፈና ኢትዮጵያውያን በማውገዝ ላይ ሲሆኑ፣ መንግሥትም ብሔራዊ የሐዘን ቀን ከማወጁም በተጨማሪ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ መንግሥት ዜጎችን ትጥቅ በማስፈታት ራሳቸውን የሚከላከሉበትን ዕድል ነፍጓል በማለት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ‹‹ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ሁኔታ ለደኅንነታቸው ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው ነው፤›› በማለት ችግሩ እንደተከሰተም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባወጣው መግለጫ የመከላከያ ሠራዊት የአገር ዳር ድንበርና የዜጎችን ሰላም የማስጥበቅ ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን፣ መንግሥት ከአካባቢያቸው ታግተው የተወሰዱትን ዜጎች ሕጋዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርጎ እንዲያስመልሳቸው ጠይቋል፡፡
No comments:
Post a Comment