Wednesday, April 20, 2016

ነአምን ዘለቀ፣ ተሳለቀ ወይስ ዘባረቀ


ከፍያለው ስዩም
ግንቦት ሰባት እ.አ.አ. ከማርች 26 እስከ 27, 2016 ድረስ አካሂዶት በነበረው በባዕዳን ቋንቋ “ቪዥን” በመባል የሚጠራው ቡድን ጥቂት ታዳሚዎች በተገኙበት ስብሰባ አካሂዶ እንደነበር ይታወቃል። የስብሰባው “የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሽግግር፣ የዲሞክራሲና በብሔራዊ አንድነት” የሚል ታፔላ ተለጥፎበት ነበር። ታዲያ የዚህ ስብሰባ ታዳሚዎች ቁም ነገር ይሰራሉ ወይም ቋት የሚሞላ ነገር ይናገራሉ የሚል ግምት ስላልነበረኝና ከመቶ ሽህ ባላይ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት የዋሽንግተን ከተማ አካባቢ ካለው ኢትዮጵያዊ ከአዘጋጆቹ ሌላ በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ ቀልብ የሳበ ስለነበር እኔም ዝም ብዬ አልፌው ነበር።ሆኖም ይህችን አጭር ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሳኝና ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ በድረገጽ በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ነአምን ዘለቀ የተባለው ግለሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በመርገጥ የሻቢያ ተላላኪነቱን ያረጋገጠበትን “ኢትዮጵያ የምትባል አገር” በማለት መናገሩና በዚህም አገራችንን ማዋረዱ እጅግ አስቆጭቶኛል። አገራችን ኢትዮጵያ ከ4,500 ዓመታት በላይ ታሪክ ያላትና የተነሱባትን ጠላቶች ሁሉ አሸንፋ ተከብራና ታፍራ የኖረችው አገራችንን ከሻቢያ ቀለብ የተሰፈረላቸው ቅጥረኞች ሲያዋርዷት መመልከት በጣም ያንገበግባል።
ነአምን ዘለቀ ይህ ብቻ ሳይበቃው “የኢትዮጵያ አንድነት ብቻ ሲባል ‘ሰፎኬት’ ያደርገኛል” በማለት ለኢትዮጵያ ያለውን ጥልቅ ጥላቻ አፉን ሳያደናቅፈው ተናግሯል። የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማምጣት በተለይም ከአጼ ቲዎድሮስ አንስቶ በርካታ የሕይወት መስማዕትነት የተከፈለ መሆኑ ለነግንቦት ሰባት ምናቸውም አይደለም። ይህ የተከፈውን መስዋዕትነትና የወደመውን የአገር ሐብት እንደ ተራ ነገር በመቁጠር ነአምን ተሳልቆበታል። የአገር አንድነት ማለት እጅግ የረቀቀ ጽንሰ ሐሳብ ነው። በእርግጥ ነአምን ከዚህ ቀደም መለስ ዜናዊ ያላገጠበትን አነጋገር በድጋሚ በመጠቀም “ኢትዮጵያ የምትባል አገር” እያለ አገራችን ላይ አሹፏል። ይህ ግለሰብ ይህንን ድፍረትና ንቀት ያመጣው በቅርቡ ሻቢያ ጋር ሄዶ ተግቶት በመጣው የጥላቻ መርዝ ምክንያት መሆኑ አያጠራጥርም።
በዓለም ላይ በርካታ ጦርነቶች የተካሄዱት የአገሮችን ሉዓላዊነትንና አንድነትን ለማስከበር ነው። በ1860ዎቹ አጋማሽ ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በደቡብ የሚገኘው የአገሪቷ ክፍል የአሜሪካንን አንድነትና ሉዓላዊነት በማፍረስ በሌላ አዲስ ስም ተገንጥሎ መንግስት ማቋቋሙን ለማስቆም ባካሄዱ የአንድነት ዘመቻ ከሚሊዮን በላይ የሚቆጠር የሕይወት ዋጋ ተከፍሎበታል። እንዲሁም ናይጀሪያ፣እንግሊዝ፣ ቻይና፣ጣሊያን፣ሩሲያ፣ፈረንሳይ፣ጀርመን፣ ጃፓንና ሌሎችም አገሮች ውስጥ የተካሄዱ አንድነትን የማስጠበቅና የተከፈሉ ግዛቶችን የማስመለስ ጦርነቶች በርካታ የሕይወት ዋጋ ተከፍሎባቸዋል።
ነአምን ዘለቀ ካሻቢያ የምትገኝ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ኢትዮጵያን እያጣጣለና እያጎደፈ በመሄድ ላይ መሆኑንን ብዙዎች አላስተዋሉትም ይሆናል።”ቪዥን ኢትዮጵያ” የሚባለው እንኳንስ “ቪዥን” ይቅርና ጭላንጭል ብርሃን የሌለበት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የተዋጠ የተስፈኞች መድረክ ነው። ከአሁን በፊትም ይኽው “ቪዥን” የሚባለው የሻቢያ ተላላኪ የግንቦት ሰባት ቡድን ኢትዮጵያ የምትባል ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ትልቅና ሰፊ አገርን ከሻቢያ ኤርትራ ጋር ደርቦ “የአፍሪካ ቀንድ” እያለ በተወናበድ ስም ሲጠራት እንደነበር አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ አንድነት ሲባል የሚያንቀው ወይም የሚያፍነው “ሰፎኬት የሚያደርገው” ሰው በምን መስፈርት ነው ከወያኔ የሚለየው? ወያኔም እኮ አገራችንን በዘር ከፋፍሎ ብሔራዊነትን አሰልስሎና የአንድነቱን ገመድ አላልቶ እየከፋፈለ አፍኖ በመግዛት ላይ የሚገኘው የአገራችንን አንድነት ስለሚጠላ ነው። ነአምን ዘለቀ በተለይም ኤርትራ ሄዶ ተጣብቶት የመጣው የኢትዮጵያ ጥላቻ ኮሶ ቀስፎትና ሆዱን ነፍቶት እያንዘፈዘፈውና እያንቀጠቀጠው ስለሆነ ብዙ ይዘባርቃል። ግንቦት ሰባት ሌላው አገኝበታለሁ ብሎ ያሰበው ትርፍ ኢትዮጵያን ካዋረድኩኝ የኢትዮጵያ ጥላቻ ያላቸው ተገንጣይና የጎሳ ድርጅቶች ተቀባይነት ይሰጡኛል ብሎ የሚያደርገው መሸራሞጥ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱን የከፋና የከረፋ ነገር ሳይረዳው ይቀራል ማለት እራስን ማሞኘት ነው።

No comments:

Post a Comment