ሚያዝያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. (April 9, 2016) በ 179 Fairway Boulevard በሚገኘው አዳራሽ ቁጥሩ ከፍ ያለ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የአርማጭሆና ጎንደር ክ/ሀገር ተወላጆች ኢትዮጵያዊያን ስብሰባውን ተካፍለዋል።
በአገር ቤት ሰለተቋቋመው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባብሪ ኮሚቴ እንቅስቃሴና ለፌደረሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ፅሁፍ ተነቧል።
በውጭ አገር ያለው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የአማራ ብሔረትኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ በተናጠል ለብዙ አመታት የተደረገው ጩኸት ውጤት ባለማምጣቱ በዛሬው ቀን የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የጎንደር ሕዝብ ብሎም አማራውና ኢትዮጵያዊ ሁሉ በዚህ ስብሰባ ተገኝቶ በሰፊው እንዲወያይበት መድረኩን ክፍት አድርገዋል።
አባቶችም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማንነት፣ አመጣጡና የዘር ሃረጉ፣ ከጎንደር ጋር ያለው ቁርኝት እንዲሁም ይህ ኩሩ ሕዝብ በልማትና የእናት ሃገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር በተለያዩ ጊዜያት የከፈለው መስዋእትነት ለተሰብሳቢው በስሜት ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ድንበሩን የተከዜ ወንዝን ተሻግረው ከሕዝቡ ፍላጎት ውጭ የተደረገው ማካለል ህገ-ወጥ እርምጃ በመሆኑ ሕዝቡም ይሁንታ ስላልሰጠው ይኸውና ከ37 አመት በኋላ የተዳፈነ ነገር ግን ያልጠፋ እሳት ዛሬ ተቀጣጥሎ ጥያቄው ለም መሬታችን ተቀማን፣ አስተዳደራዊ አድልዎና በደል ደረሰብን የሚል ብቻ ሳይሆን በሆዱ አምቆ ያቆየው የማንነት ጥያቄ በግልጽና ድምፁን ከፍ አድርጎ እኛ ጎንደሬዎችና አማራ ነን ብሏል። አራት ነጥብ!!
በዚህ ደማቅ ስብሰባ ከተሰብሳቢው ብዙ ጥያቄዎች ተነስተው መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ብዙ ሃሳብ ቀርቦ ቤቱ በጥሞና ከተወያየ በኋላ አገር ቤት ከተቋቋመው ኮሚቴ ጐን በመቆም አስፈላጊ የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ በሙሉ ድምጽ ቃል ገብቷል።
ጉባኤው ህዝባዊውን ጥያቄ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካለው የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አስተባባሪ ኮሚቴ በተጨማሪ ሶስት (3) ሰዎች በመምረጥ በጠቅላላው አስር (10) አባላት ያሉት ኮሚቴ ሆኖ እንዲሰራ እና ለወደፊቱ ሰፋ ባለ መንገድ የጎንደር ክ/ሃገር እና አጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ስብሰባ ተጠርቶ በጉዳዩ ጠለቅ ያለ ውይይት እንዲደረግበት ለኮሚቴው ሃላፊነት ሰጥቷል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ተገን አድርገው በዲሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ መንገድ የማንነት መብታቸውን በጠየቁ የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት ህዝቦች በትግራይ ክልል መንግስት እየደረሰ ያለው የአፈና፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ የሞራልና ይስነ-ልቦና ተፅእኖ ባስቸኳይ እንዲያቆም ጠ ይቋል።
በዚሁ የወልቃይት ጠገዴና እና ጠለምት ህዝብ የአማራ ብሄረተኘነት የማንነት ጥያቄ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ጥያቄውን ስላነሱና ሃሳቡን ስለደገፉ በትግራይ ክልል መንግስት በግፍ ታፍነው በእስር ቤት እየተሰቃዩ የሚገኙትን የሕብረተሰብ አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ ጉባኤው ጠይቋል።
በመጨረሻም በአገር ቤት በሰላማዊ መንገድ የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት እንዲሁም ሌሎች ማንነታቸውና መብታቸው ለማስከበር ጥያቄ እያቀረቡ ያሉትን ወገኖችን ለመደገፍ በቅርቡ ሌላ አጠቃላይ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲጠራ በመወሰን ጉባኤው በሰላም ተጠናቋል።
የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት ህዝብ የማንነት ጠያቂ አስተባባሪ ኮሚቴ ኮሎምቦስ፤ ኦሃዮ
Share0 19 0
No comments:
Post a Comment