↓
የሰማያዊ ፓርቲ የውስጥ ፍትጊያ ለበጎ ወይስ ለጥፋት ? መልካሙን ማሰብ ከመልካም ያደርሳልና— ጠንካራውን ሰማያዊ እንጠብቅ// (የሰማያዊ የውስጥ ፍትጊያ ለሚያስጨንቃችሁ፣ በተለይ ክፍተቱን ለማጥበብ የነበረኝን ድርሻ በሚመለከት አስተያየት እንድሰጥ ለጠየቃችሁኝ ) በቅድሚያ ይህን ጥረት ለማድረግ ያቀረብኩትን ጥያቄ በሙሉ ልብ ተቀብላችሁ በመተማመን ስሜት ያለምንም ማመንታት በግልጽ ለመወያየት ፈቃደኛ ለሆናችሁና ላደረጋችሁ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ለሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና ለብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ይድነቃቸው ከበደ ፤ ይህ ጥረት መጀመሩን ካወቃችሁበት ጊዜ ጀምሮ በቅርበት ስትከታተሉ ውጤት እንዲያመጣ መሻታችሁን ስትገልጹና ኃሳብ ስትሰጡ፣ በመጨረሻም ጥረቱ የደረሰበትን ደረጃ እንድገልጽ ለጠየቃችሁኝ፣ ስላሳደራችሁብኝ እምነት ከፍ ያለ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ ባለፉት በርካታ ወራት በሰማያዊ ፓርቲ በተነሳው የውስጥ ፍትጊያ ፓርቲው የሚታወቅበት ወቅታዊ ክስተቶችንና ታሪካዊ ኩነቶችን ተከትሎ ህዝብን ለትግል የማነሳሳት ፈጣን ተግባርና ሳምንታዊ የመማማሪያ ፕሮግራም ተሰናክሎ መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው ፡፡ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት ተከትሎ ህወኃት/ኢህአዴግ ስንጥቅ ለመፍጠርና ለመጠቀም የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ለፓርቲው ተቆርቋሪ መስሎ የተንቀሳቀሰ ‹ስውር. ቡድን ከከፈተው የማኅበራዊ ሚዲያ ‹‹የእናድን›› ዘመቻን ጨምሮ አፍቃሪ ኢህአዴግ ጋዜጦችም ክፍተቱን ለማስፋት አስተዋጽኦ አበርክተዋል ፡፡ በመካከሉም ፍትጊያው ጎራ ለይቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ከመጠዛጠዝ ወደ እርስ በርስ መካሰስ ፣ መወነጃጀልና መፈራረጅ ቀጥሎም በአመራር አባላት መካከል ‹የታዳኝና አዳኝ› ጨዋታ ከዚያም አልፎ እስከ መደባደብ ደርሷል፡፡ በዚህ አፍራሽ ግብግብ ውስጥ ለህወኃት የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለመረዳት ምርምር ቀርቶ አንዳች ማሰላሰል አይጠይቅም፣ በጣም ግልጽ ነውና፡፡ በዚህ መካከል ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የፓርቲውን አስፈላጊነትና በእስከዛሬው ትግሉ ባሳየው አበረታች እንቅስቃሴ ቀጣይነቱን የሚሹ ወገኖች ጉዳዩ ጉዳያችን ነው በሚል መንፈስ ክፍተቱን ለመድፈን የተለያየ አስተያየት በማቅረብ አስተዋጽኦ ለማድረግ ሞክረዋል፤ ዳሩ ጥረታቸው አንድም ጎራ የለየ በሌላውም በአደባባይ በመሆኑ ከአዎንታዊ ጎኑ አሉታዊው ያመዘነ ይመስላል ፡፡ በዚህ ሂደት መካከል እኔም እንደ ተቆርቋሪ፣ ባለድርሻ እና የተፋታጊ አመራሮች የትግል ጓድ በአደባባይ የሚታየው ክፍተቱን የበለጠ ከማስፋቱ በፊት አመራሮቹ ተቀራርበው በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሚና ለመጫወት ወይም አስተዋጽኦ ለማድረግ ሞክሬኣለሁ፤ የፓርቲውን ሊቀመንበርና የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ በተናጠልና በጋራ በተደጋጋሚ አነጋግሬኣለሁ፡፡ ይህ ጥረት ሲጀምር ለሁለቱም የተነሳሁበት እሳቤ ‹‹ ችግር ካለ ችግሩን በግልጽ በመነጋገር መፍታት አንጂ ለጠላት በር ላለመክፈት በሚል ለመተቻቸት መፍራት፣ ችግሩን መሸፋፈንም ሆነ በመቻቻል ስም ጥያቄዎችን ማዳፈን ለበለጠ አደጋ ይዳርጋል፤ በተቃራኒው በመረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ስህተትን ለማረም ያለመ ገንቢ ትችት አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ፤ ከተለመደው ትችትን እንደጦር የመፍራት አካሄድ የምንላቀቅበት ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ተቋማዊ አሰራር መጎልበትና ድርጅታዊ ዕድገት በእጅጉ ጠቃሚ ነው…፡፡ ›› የሚል መሆኑን አቅርቤ ሁላችንም ተስማምተንበት ነው ፡፡ ሦስት ሆነን በጋራ ያደረግናቸው ውይይቶች ሁሉ የልዩነት ምክንያት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ቀርበው በቂ መልስና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው፣ ገንቢ ኃሳቦች ተነስተው ውይይት አድርገን በአብዛኛው ስምምነት የደረስንባቸው፣ አበረታችና ችግሩ በቅርብ ጊዜ ይፈታል የሚል ተስፋን የሚያለመልሙ ይመስሉ ነበር ፡፡ በተግባር ግን ይመስሉ የነበሩት ሆነው አልተገኙም፤ በተቃራኒው በመጓዝ ክፍተቱን የሚያሰፉ፣ የተጀመረውን መቀራረብ ጥረት የሚያመክኑ ክስተቶች ታዝበናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ክስተቶች የችግሩን መንስኤ ለመረዳትና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ ፈጥረዋል ማለት ይቻላል ፡፡ ጥረታችን ከተሳካ ‹‹ ካልደፈረሰ አይጠራም ›› እንዲሉ፣ ያሊያ ባይሳካና ችግሩ በሌላ መንገድ መፍትሄ ከተበጀለትም ‹‹ የቤቴ መቃጠል ለትኋኔ በጄኝ ›› እንደሚባለው ይሆናል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው፣ አሳሳቢነቱን ተረድተው እንድንነጋገር ከጠየቁኝ የፓርቲው አባላት፣ እንዲሁም እንኳን ይህ ለአደባባይ የበቃ ጉዳይ ቀርቶ ሌላውንም ‹‹ ምናችንን (የተቃዋሚ ፓርቲዎችን) እነማን አያውቁም ብለን እንጠነቀቃለን(?)፣ ይህን ማሰብ ሞኝነት ነው ›› በሚል አደባባይ በወጡት ላይ ከፓርቲው ውጪ ያሉ የፖለቲካ ሰዎችም ጋር ተመካክሬኣለሁ፣ ገንቢ አስተያየቶች አግኝቼአለሁ፡፡ ከዚህ ጋር በቀጥታ የተገናኙ በማኅበራዊ ሚዲያ የቀረቡ አስተያየቶችን ፣ በጋዜጦች የተጻፉ ዜናዎችንና የውጪ የሬዲዮ ጣቢያዎችን ጨምሮ የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ትኩረት ሰጥቼ፣ ጊዜ ወስጄ በጥንቃቄ ለመመርመር ሞክሬኣለሁ ፡፡ ባለፈው ሳምንትና ዛሬ ከሁለቱም አመራሮች ጋር በተናጠል ስለ ጉዳዩ ተነጋግሬኣለሁ፡፡ አሁን ላይ ችግሩ በውይይት በምናነሳቸው ጉዳዮች ካለመስማማት ወይም የልዩነት ነጥቦች ተብለው የተነሱት ጥቄዎች መልስ ባለማግኘታቸው/ ግልጽ ባለመሆናቸው ሳይሆን ለዘላቂ መፍትሄው ወደ ተግባር መግባት ባለመቻሉ ወይም መዘግየቱ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ በመሆኑም ከላይ ተፈጥሯል ያልኩትን የዘላቂ መፍትሄ መልካም አጋጣሚና ባለፈው ሳምንት ካገኘኋቸው ግብኣቶችን በማገናዘብ በእጅጉ ወድቆ ተስፋ ከመቁረጥ ጠርዝ አድርሶኝ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ወስኜኣለሁ ፡፡ ለዚህም ከሁለቱም ወገን ይሁኝታ አግኝቻለሁ ፡፡ በዚህ ውሳኔዬ መሰረት ‹‹ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሰማያዊ ፓርቲም ባሳለፈው የፍትጊያ ሂደት ተፈትኖ ነጥሮ ፣ጠንክሮ ይወጣል፤ አባላቱም ከሂደቱ ተሞክሮ ቀስመውበት፣ ብዙ ተምረውበት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አጠናክረው፣ አመራርና አሰራራቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቆርጠው ፣ ለውጤታማነት በመስራት ፓርቲያቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቃልኪዳናቸውን ያድሳሉ ፤ ይህን ለማድረግና የተሰበረውን የህዝብ ሞራል ለመጠገን የሰማያዊ ወጣቶች አያንሱም (ከዚህ በፊት ሰማያዊ ‹ያለኔ ማን አለ› ባለ ጊዜ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቼ ተሳክቶልኛል) ›› የሚል ተስፋ ሰንቄ ለመጨረሻ ጊዜ ጥረቱን እቀጥላለሁ ፡፡ ጉዳዩ ከጊዜ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነውና በቀጣይ ከሳምንት የማያልፍ ጊዜ ከጥረቱ መጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ በሂደቱ የደረስንበትንና የተረዳሁትን ይዤ እመለሳለሁ፡፡ አስከዚያው ደግ ደጉን፣ ለአገራችንና ህዝቧ የሚበጀውን ያሳስበን፣ ያስፈጽመን፣ ያሰማን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን፡፡ አሜን // ግርማ በቀለ፤ ሚያዝያ 11 / 2008 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment