↓
የዓለም የጤና ድርጅት ሰነድ እንደሚለዉ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን 37 ሚሊየን ሕዝብ HIV ተሐዋሲ በደሙ ዉስጥ ይገኛል። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ላይ 16 ሚሊየኑ ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እንደሚወስዱ ተመዝግቧል። በሽታዉ እስካሁን ከ34 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። የመድኃኒቱ ስርጭት እና የመገኘት ሁኔታዉ በየጊዜዉ እየተሻሻለ በመሄዱም HIV የሚያጠፋዉ የሰዉ ሕይወት ቁጥር እየቀነሰ፤ የተሐዋሲዉ መዛመትም መጠነኛም ቢሆን መሻሻል እንደታየበት ይነገራል።
የመጀመሪያዉ ጸረ ኤች አይቪ መድኃኒት በሙከራ እና ምርመራ የተረጋገጠዉ የዛሬ 30ዓመት ገደማ ነዉ። ያኔ በዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የመድኃኒቶች ባለስልጣን (FDA) የተረጋገጠዉ የመጀመሪያዉ አንቲ ሪትሪዮቫይራል መድኃኒት ከሌላ መሰል መድኃኒት ጋር ተቀናጅቶ እንኳን የHIV ተሐዋሲን መዛመት መግታት እንዳልቻለ በዚህ ረገድ የተከናወኑ ጥናቶች ዛሬም ያስታዉሳሉ። የሟቾች ቁጥርም እንዲሁ ሊቀንስ አልቻለም ነበር። ከዕለት ወደዕለት ምርምሩና ሙከራዉ ቀጥሎ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1996ዓ,ም በጣም ፈጣን -አንቲ ሪትሪዮቫይራል የሚል ቅጽል ታክሎበት የሦስት መድኃኒቶች ጥምረት ህክምና ተጀመረ። እናም በየጊዜዉ መሻሻሎች እና አዳዲስ የሚባሉ ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒቶች እየተዘጋጁ ለገበያ እንደሚቀርቡ መረጃዎች ይዘረዝራሉ።
No comments:
Post a Comment