Tuesday, April 19, 2016

የ86 መንትዮች እናት በምጥ ትሰቃያለች– Girma Bekele


የ86 መንትዮች እናት በምጥ ትሰቃያለች– የአዋላጅ ሃኪሞች ‹‹ ቡድን ›› እየተጣራች ነው፤ በእናት የምትመሰለው አገራችን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተለይም ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ከአንድ ምንጭ በሚቀዱ ህመሞች እየተሰቃየች በመፍትሄ ምጥ/መድሃኒት ፍለጋ/ ውስጥ ነች፡፡ እኛ ልጇቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ የለቅሶ ድንኳን እየቀያየርን ከሃዘን ቤት ወደ ሃዘን ቤት እየተመላለስን እያነባን ነን፡፡
ሁላችንም እንባችንን ለማድረቅ በየፊናችን ችግሩን ለመተንተንና ከደረስንበት ድምዳሜ በመነሳት ትክክልና ያዋጣል ባልነው መንገድ መፍትሄ ከመፈለግ አልቦዘንንም፤ ግን የተናጠል ጥረታችን ህመማችንን አልፈወሰም፣ ከዘላቂ መፍትሄ አላደረሰንም፡፡ ከመፍትሄው ያልደረስነው ችግራችን ቀላል፣ ጉዳታችን የሚረሳ በመሆኑ ሳይሆን በህመማችን ስረ-መሰረት መንስኤና ዘላቂና ቀጣይ መፍትሄ ላይ ባለመግባባታችንና በተናጠል የህመማችን ምልክት እያከምን ህመሙን በቅጡ ማስታገስ እንኳ ባለመቻላችን ነው ሥቃያችን ከለት ወደለት እየበረታ ያለው፡፡
በሽታው በየጊዜው ስሙንና መልኩን ፣ የመግቢያ ቀዳዳውንና ስልቱን እየቀያየረ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ፣ ካቀረብነው የተናጠል ጊዜያዊ የማስታገሻ መድሃኒት እየተላመደና እያላመደን ከዚህ ደርሰናል፡፡ ይህ የአናሳዎች ዘረኛ አምባገነናዊ ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የጥፋት ሴራውን ያላሰራጨበት የኢትዮጵያ ምድርና የልማትና አስተዳደር ሴክተር ፣ በጥፋት በትሩ ያልተገረፈ የኢትዮጵያ ህዝብ/ የማኅበረሰብ ክፍል/ ፣ ያልደረሰብን ተፈጥሮኣዊና መንግስት ሰራሽ የችግር ዓይነት የለም፡፡ ከህጻናት እስከ አረጋዊያን፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከገበሬ እስከ ከብት አርቢው፣ ከመናጢ ድሃው እስከ ባለሃብቱ፣ ከማይም እስከ ምሁሩ ፣ ከባህላዊ እምነት እስከ ኃይማኖት ተቋማት፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ … በየጊዜው እየረሳነው ካልሆነ ችግሩ ያልደረሰበት አይገኝም፣እንዲያውም ችግሩና ህመሙ ድንበራችን አቋርጦ እየተከተለን በውጪም ሥቃያችን አክፍቶታል፡፡
ትምህርት ዓላማውን ስቷል፣ ግብርናው የፖለቲካ መስክ ሆኗል፣…. የኢኮኖሚ እድገትና የአገር ልማት በቴለቪዥን መስኮት እንጂ ለኑሮኣችን ከጓዳችን አልደረሰም፤ በቴለቪዥንና ሬዲዮ ፕሮፖጋንዳ ቁንጣን በምንሰቃይበት፣ባለሁለት ዲጅት ዕድገት ባስመዘገብንበት ከአስር ሚሊዮን ዜጎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ነው፡፡ ዛሬም በሞት ውስጥ ለማለፍ ስደቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ በኦጋዴን ፣በጋምቤላ ፣ በትግራይ ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ፣ በቤንሻንጉል፣ በአፋር፣ …. የዜጎች ደም ያልፈሰሰበትን የእናቶች እምባ ያልተረጨበትን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ዛሬም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወልቃይት -ጠገዴና ቅማንት፣ በኮንሶ…የጣር ድምጾች እየተደመጡ ነው፣ በጋምቤላ የደረሰው ለጆሮና ለማመን ይከብዳል፡፡ ግን መሆኑን ‹ደፋሮቹ› አረጋግጠውልናል ፡፡
ሥራ አጥነትና ስደት፣ ረሃብና ድርቅ፣ እስራትና አፈና የፍትህ እጦትና የክብር መደፈር፣ … አገራችን ቤታቸው ናት፡፡ በመሆኑም ተፈናቅለናል፣ አካላችን ጎድሏል፣ ሥነ- ልቡናችን ታውኳል፣ ተሰደን (ለአረመኔዎች ሠይፍና ጥይት፣ ለባህር አውሬና ለዱር አራዊት እራት ሆነናል፣አካላችን ተሸጧል፣በእሳት ተቃጥለናል፣… ) ፣ተገድለናል፣ ሙስሊም ክርስቲያኑ ቤተ እምነቱና ትምህርተ-ሃይማኖቱ ተደፍሯል ፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ክብራችን ተዋርዷል፣ ድንበራችንና ሉዓላዊነታችን ተደፍሯል፡፡ የዛሬው የጋምቤላው ግን ከመቼውም የከፋ ነው፡፡ የእስከዛሬው ጥይት በእኛው ከእኛው ፣ ወይም ለስደት በምንጓዝበት መንገድ ወይም በተሰደድንበት ከአገራችን ውጪ ነበር ፡፡
ዛሬ ግን ‹‹ባለቤት የናቀውን …፣ ወይም ባለቤቱን ካልናቁ ….›› እንዲሉ ድንበራችን ዘልቀው እስከቤታችን ገብተው ጨፈጨፉን፡፡ ከመድረሱ በፊት የሚከላከለን ፣ ከደረሰ በኋላ የሚበቀልልን ያለመኖሩን የተመለከቱ ከመንደር መንደር እየተዘዋወሩ ከ200 በላይ ወገኖቻችንን ጨፈጨፉ፣ በመቶ የሚቆጠሩትን ጠልፈው ለባርነት ወሰዱ፡፡ ልብ እናድርግ — ይህ በቤታችን በቀዬኣችን ባለንበት መጥተው ያደረጉት ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንደ አገርና ዜጋ መዋረድ ከቶ ከወዴት አለ፣ በታሪካችን መቼ ተሞክሮብን ተሳክቶ ይሆን ? አዎን እስከዛሬ ችግሩ የእርስ-በርስ የውስጣችን ይመስል ነበር፣ እስከዛሬ ‹‹ ይጨርሱናል፣ ያጫርሱናል ›› ስንል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ደረጃው አድጎ ከመጨረስና ማጨራረስ አልፎ ወደ ‹‹ ማስጨረስ ›› ተሸጋግሯል፡፡ ታዛቢና ጠባቂ እንደሌለን ብቻ ሳይሆን በሞታችንም የሚቆጭ እንደሌለን በተጨባጭ አረጋግጠናል፤ አሁን ጥያቄው ከዚህ በኋላ ምን እስከምንሆንና እስኪያደርጉን ሳይሆን እስኪያስደርጉብን እንጠብቅ ? እስከመቼ በተናጠል በየራሳችን መንገድና ዘዴ (ባህላዊ ሥራ- ሥር ይሁን፣ ዘመናዊ መድሃኒት በሉት የቀዶ ጥገና ህክምና ) የበሽታውን ምልክት እያከምን ፣ በሽታው የበለጠ ስር እንዲሰድና ከማይታከምበትና እናታችንን ከሚገድልበት (የሠይጣን ጆሮ አይስማው) ደረጃ እንዲደርስ እንፍቀድለት? ነው፡፡ የመፍትሄው ጥያቄ እንግዲያውስ ከእስከዛሬው ተምረን ምን ማድርግ እንችላለን ፣ ለዚህስ ምን እርሾ አለን፣ ምንስ ተስፋ ቋጥረን/ሰንቀን እንነሳ ? ነው፡፡
አዎን // ከላይ እናታችን የአዋላጅ ሃኪሞች ‹‹ቡድን›› እየተጣራች ነው ብለናል፡፡ አዎን// እነዚህ አዋላጅ ሃኪሞች የየራሳቸው ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታና አቅም ይዘው በየግላቸው የየራሳችን ላሉት ‹በሽታ› መድሃኒት ያሉትን ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን የየራሳችን ያሉት በሽታ — በሽታ ሳይሆን ምልክት መሆኑን የተረዱበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል፤ በሽታው የሁሉምና የጋራ አንድ ዓይነት መሆኑን፣ ለብቻቸው በሽታውን ከስር-መሰረቱ በዘላቂነት ነቅሎ የሚያወጣ መድሃኒት እንደሌለ ተምረዋል፡፡ በመሆኑም በእያንዳንዳቸው ያለውን የየግል ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታና አቅም በአንድ ዓላማ ሥር ለጋራ ግብ አሰባስበው /አቀናጅተው የሁሉንም የጋራ በሽታ ከሥሩ የሚነቅሉበትንና በውጤቱም ሁሉም የሚጠቀሙበት የጋራ ተግባር የሚፈጽም ስብስብ መፍጠር ላይ መግባባት እየተደረሰ እንደሆነ ጠቋሚዎች አሉ፡፡
የቪዥን/ራዕይ ኢትዮጵያ እና ኢሳት ያሳዩን መልካም ጅምር ፣ በጽንፈኛ ፖለቲካዊ አመለካከትና ተግባራት መካከል የተደነቀረው የልዩነት ግንብ እየተናደ መምጣቱን የሚያመለክቱ እርምጃዎችና በዲሞክራሲ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በጋራ ለመስራት ከተደረጉ ጥረቶች የተገኘው ተሞክሮና ዛሬም ስላለው ፍላጎት የምንሰማቸው ተስፋን የሚያጭሩ ፣ የቀጣይ ትግላችን ስንቅ ናቸው፡፡ አዎን ይህ የብዙዎች መንታ እናት አገራችን በአንድ ላይ ካላዳንናት ያለእናት( በእናት አልባ) የምንቀረው ሁላችን ነን፡፡ ግማሽ፣ ሲሶ ፣ ሩብ … እናት ለማናችንም አትተርፍም፣ ብሎ ነገር የለም፣አይኖርም፡፡ ስለዚህ ዘላቂ ስር-ነቀል መፍትሄው የአዋላጅ ሃኪሞቹ ‹ቡድን › ‹‹ ይህ በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና በመሳሪያና ደህንነት አፈና የሚያሰቃየን ፣ ግን ከውጪ ጠላት እንኳ የማይጠብቀን የአናሳዎች ዘረኛ አምባገነን ስርዓት መቀየር አለበት፤ ለዚህም በብሄራዊ መግባባት ዕርቅ አውርደን በአካታችና አሳታፊ የሽግግር መንግስት አልፈን አዲስቱን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት በኅብረት መቆም ›› በሚል የጋራ እምነት የተጀመሩትን ጥረቶች አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ አካታች ሰላማዊ የሥርዓት ለውጥ (የሥልጣን ሽግግር አላልኩም) ፣ዘላቂ ሰላምና ልማት ፣ ፍትህና የህግ የበላይነት፣ ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ፣እኩልነትና አብሮነት…. መሪዎቻችን በክብር የምንጦርበትና የምንቀብርበት ሁኔታ የሚቻል አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ በተለመደው አግላይና ጠቅላይ ፖለቲካ የሥልጣን ሽግግር ይቻላል፤ በዚህ ሁሉንም የዛሬ መሪዎች አንድም ወህኒ ፣ ሌላም በስደት አገር እናገኛቸዋለን፣ ይቀበራሉ፣ ወይም ተሳደው ለፍርድ ይቀርባሉ ፡፡
በሽግግር መንግስት ግን ሁሉም ሳይሆኑ ቀንደኛ ወንጀለኞች ብቻ የሚጠየቁበት ስርዓት ሊዘረጋ ወይም ሌሎች የዕርቅ የመፍትሄ አማራጮች ሊቀርቡና በአካታችና አሳታፊ ውይይት መግባባት ሊደረስባቸው ይችላል፡፡ ለዚህ ምርጫው ኳሷ/ እንዳለፉ ጊዜያት በኢህአዴግ እጅ/ሜዳ ብቻ ነው ብዬ አላስብም፤ አዋላጅ ሃኪሞቹ ተግባብተውና ተባብረው ‹ቡድን › ከመሰረቱ በጉዞ ላይ ያለቺውን ኳስ ወደ ሜዳቸው በቅርብ ያመጣሉ ፡፡ ዋናው ነገር –ከዚህ የከፋ ሊደርስብን የሚችል ጥፋት፣ አደጋና ውርደት አለ /የለም ፣ እያንዳንዳችን ለየራሳችን የተናጠል መፍትሄ አለን/የለንም ብሎ ለመከራከር፣ በታሪክ ለመነታረክ …. የምናባክነው ጊዜ የለም ፡፡ ዛሬውኑ ለ ‹‹ቡድኑ›› ምስረታና ለተግባራዊ እንቅስቃሴው መጀመር ሁላችንም እንደዜጋ ተደራጅተን፣ እንደድርጅት በተናጠልና በጋራ አሁኑኑ ወደ ተግባር ፡፡ ባለፈው እንዳልኩት አገራችን ለዚህ የሚበቁ ብቻ ሳይሆን ለሌላ የሚተርፉ ልጆች እናት ናትና ‹‹ ይቻላል ›› ብዬ መሳሳትን እመርጣለሁ፡፡ ለአገራችንና ለልጇቿ ደግ ደጉን ያሳስበን. ፣ ያሰራን፣ ያሰማን ፡፡ በቸር ያገናኘን ፡፡ 10/08/08. UNITE. ( በጋምቤላ ለተጨፈጨፉ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን መታሰቢያ)

No comments:

Post a Comment