(ዘ-ሐበሻ) በጋምቤላ “መንግስት የለም ወይ?” ያሉ ነዋሪዎች ሰሞኑን የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝና መንግስትም ይህንን የሕዝብ ሞት ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ አዎሎታል በሚል ሕዝቡ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ሲያሰማ መዋሉን ለዘ-ሐበሻ የደርሰው መረጃ አመለከተ::
“ልጆቻችን ይመለሱ…. በሃገራችን ሰላም አጣን… መንግስት በኛ ሞት የፖለቲካ ድል ማግኘቱን ያቁም…” እና ሌሎችንም መፈክሮች ሲያሰሙ የነበሩት የጋምቤላ ነዋሪ ሰልፈኞች መንግስትን ሲያወግዙ ውለዋል::
ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ከብቤያለሁ እያለ ሲፎክር የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ወታደር እስካሁን ልጆቹን ባያስለቅቅም የትናንቱን ገድያ ተቃውመው ለሰልፍ የወጡትን ኢትዮጵያውያን ግን ዛሬ ጋምቤላ ላይ ሲቀጠቅጥና ለመበተንም ሲሞክር ታይቷል::
በጋምቤላ የተለያዩ ከተሞች በአሁኑ ወቅት መረጋጋት አለመኖሩን የሚገልጹት የአካባቢው ምንጮች ማን ከየት መጥቶ ገድሎ እንደሚሄድ እንደማይታወቅና ሕዝቡም እርስ በራሱ ተፈራርቶ እንደሚገኝ ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል::
በጋምቤላ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የታህሳስ 13 መታሰቢያ ንቅናቄ ተወካይ አቶ ኦዶል ኦዶል ለዘ-ሐበሻ በሰጡት አስተያየት የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት የሰሞኑን ግድያ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ አድርጎታል ብለዋል:: እንደ እርሳቸው አባባል መንግስት እየነገረን ያለው ትንሹን ግድያና በተለይም ሙርሌዎች ያደረሱትን እንጂ ከዛ በፊት ከ15 ቀናት በፊት ስለሞቱት ሰዎች የነገረን ነገር የለም ብለዋል::: እንደ ኦዶል ገለጻ መንግስት በኦሮሚያና በጎንደር የተነሳበትን ሕዝባዊ ቁጣ ለማብረድና ሃሳብን ለማስቀየር የሙርሌዎችን ግድያ ከመጠቀሙ በላይ ምንም ያደረገው ነገር የለም ብለዋል::
በተለይም በትናንትናው ዕለት በጋምቤላ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደሉት 15 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጠይቀናቸው “ገዳዮች ናቸው የተባሉት ሰዎች የገደሉት አማሮችን እና ኦሮሞዎችን ብቻ መርጠው ነው; ይህም ማን ከበስተጀርባው እንዳለ ያሳየናል” ብለውናል::
አቶ ኦዶል ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት የጋምቤላ አክቲቭስቶች ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ መረጃዎችን ለሕዝብ ቶሎ ቶሎ ማድረስ አለባቸው ብለዋል:: ሕዝቡ መንግስት የሚለውን ብቻ በመስማት መንግስት አሸናፊ እንዳይሆን መረጃዎችን ከፎቶዎች ጋር በማውጣት ማጋለጥ ይገባቸዋል ብለዋል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ትናንት ጃዊ በተባለ የስደተኞች ጣቢያ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሏክ ቱት ኩዃት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሞቱትን ቁጥር ወደ 10 አሳንሰውታል:: ለትናንቱ ግድያ መነሻም ሴቭ ዘችልድረን የተባለ የግብረሰናይ ድርጅት መኪና በስደተኞቹ ካምፕ ላይ በደረሰበት አደጋ የሁለት ስደተኞች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ነው ሲሉ ተናግረዋል:: ስደተኞቹ ከመኪና አደጋው ጋር ተያያዥነት በሌላቸው 10 ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውንም ገልጸዋል::
ጋምቤላ ተወጥራለች…. ዘ-ሐበሻ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዳገኘች ትመለሳለች::
Share0 611 1
No comments:
Post a Comment