Wednesday, April 20, 2016

ዐውደ ርእዩ ተፈቀደ፤ እኛም “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ” ብለን ተቀበልን

ዲባባ ዘለቀ
በማኅበረ ቅዱሳን ተዘጋጅቶ“ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፣ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማእከል ለ5ኛ ጊዜ ሊያካሔደው የነበረው ዐውደ ርዕይ ለእይታ ሊቀርብ ጥቂት ሰዓታት ሲቀር በቀጭን ትእዛዝ ያገደውንየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ርእይ ፀሐዩመንግሥታችን መፍቀዱን አስታውቋል። “በዚህ ምክንያት ነው ያገድኩት”ለማለት ያልተገደደው የአጼዎቹ መንግሥት ዛሬም እንዲታይ የፈቀደበትንምክንያት መጠየቅ ነውር ሆኖ ይልቁንም ስለፈቀዳችሁልን “እናንተንያቆይልን” ለማለት ዳር ዳር እየተባለ ነው። ወያኔ ላለፉት 25 ዓመታትየሕዝብን ተቃውሞ ሲያስተነፍስ የኖረበትም ስልት ይኸው ነው። ለፓለቲካ ዓላማ ወሳኝ የሆኑ ርምጃዎችንበህገ ወጥነትና በድፍረት ይወስድና ሕዝቡ እንዲንጫጫ ካደረገ በኋላ ትንሽ ዘግየት ብሎ ነገሩን የሚያበርድከፊል ምላሽ ይሰጣል። ሕዝቡም “ኧረ ይህንንስ እነርሱ ቢሆኑ አይደል? እግዚአብሔር ይስጣቸው!” ብሎ አስቀድሞ የጠየቀውን ጥያቄ ዘንግቶት ዝም ይላል። ይህ ስልት ሳይቀየር ለሩብ ምእተ ዓመት መሥራቱበራሱ ኢትዮጵያውያን ለማታለል የማናስቸግር “የዋሕ” ሕዝቦች መሆናችንን የሚያረጋገጥ ይመስለኛል።
ለምሳሌ በምርጫ ሰሞን የምርጫውን አካሄድ ሊለውጡ ምናልባትም አስቀድሞ የተሰላውን ውጤትሊለወጡ የሚችሉ ወሳኝ የፓለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኛች ወይም የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች ይታሠራሉ።የታሰሩበት ምክንያት ተጋኖ እና እንኳንስ ሊፈቱ በሞት ለመቀጣት የሚያበቃ ጥፋትእንደተገኘባቸውበጠቅላይ ሚኒስቴሩ እና በቱባ ባለሥልጣናት ለሀበሻውም ለፈረንጁም ከተነገረ በኋላ(“ብርቱካንን ከምፈታ አዜብን ብፈታ ይቀለኛል ከተባለ በኋላ”) የምርጫው ሒደት ከተጠናቀቀ እና የታሳሪው/ዎቹ ተጽእኖ ፈጣሪነት ከደበዘዘ በኋላ “በምሕረት” ወይም በነጻ በከፊል ይለቀቃል/ሉ። ሐበሻሆዬ ለምን ካለጥፋታቸው እንደታሠሩ ወይም ቢያንስ እንደዚህ ዓይነት “አደገኛ ወንጀለኞች”ተገቢውንሕጋዊ ቅጣት ሳያገገኙ እና ከጥፋታቸው ሳይታረሙ ለምን ወደ ማኅበረሰቡ እንደተቀላቀሉሳይጠይቅ ስለመፈታታቸው ሊያመሰግን ይዳዳዋል። በየዜና አውታሩም እንደዋዛ ይዘገባል። ተፈቺዎቹምለምን እንደታሰሩም ሆነ ለምን እንደተፈቱ እንደማያውቁ ተናግረው ከዚህ የባሰ እንዳያገኛቸው በመስጋትወደ “ሰላማዊ” ኑሮአቸው ይመለሳሉ፤ ወይም ቀጣዩን እንቅስቃሴአቸውን በጥንቃቄ ያከናውናሉ፤ከተቻላቸውም ሀገራቸውን ለወንበዴዎቹ ጥለው ይሰደዳሉ። ልብ በሉ ይህ ሁሉ የሚሆነው ካለምንምጥፋት ሲሆን አጼዎቹን ለምን ብሎ የሚጠይቃቸው የለም። ይህ የሚደረገው በፖለቲካው ላይ ብቻሳይሆን በእምነት ተቋማትም ጉዳይ እንዲህ እንደ አሁኑ ጣልቃ በመግባት ጭምር ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሁሉም የእምነት ተቋማት የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በሀገራችን መዲና በግብረ ሰዶማውያን ሊካሄድ የነበረውን ስብሰባ ለመቃወም ስብሰባ አድርገው የአቋም መግለጫ ለማውጣት በተዘጋጁበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም በሰብሰባው አዳራሽ ሳይጠሩ ተገኝተው መመሪያ በመስጠታቸው የአቋም መግለጫው እንዳይወጣ ተደርጓል። ለየሃይማኖት መሪዎቹ የተገለጸላቸው የነውረኞቹ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ተሰብስበው የፈለጉትን መግለጫ ማውጣት እንደሚችሉ ነገር ግን በመንግሥት የተፈቀደው ስብሰባ እንዳይስተጓጎል ምንም ሳይናገሩ እንዲበተኑ ነበር።ሁሉም “ምንም ማድረግ እንችልም” በማለት ዝም አሉ። ቢያንስ ተግባሩን በመቃወም የዜና ሽፋን ሊገኝበት ይችል የነበረውን ይህን ተግባር መንግሥት ተብዬው ሲያስቆመው ማንም “ለምን?” ብሎ አልተቃወመም።ቆይቶ የሃይማኖት መሪዎቹ (ሲፈቀድላቸው) መግለጫ እንዲያወጡ ተደረገ። በወቅቱ መጠየቅ የነበረበት ጥያቄ “እናንተ ምን አግብቶአችሁ ነው እኛ በሃይማኖት ምክንያት የወሰንነውን ውሳኔ ጊዜና ሰዓት የምትወሰኑለት?” የሚል መሆን ነበረበት። ግና ምን ያደርጋል “ሰማይ አይታረሰ” ሆኖባቸው ተዉት እንጂ።
አሁንም እየተደገመ ያለው ተመሳሳይ ሸፍጥ ነው። ዐውደ ርዕዩ እንዲታይ ከታቀደበት ጊዜ ዘግይቶ መታየቱ ምንም ተጽእኖ የለውም ማለት አይቻልም። ቢያንስ በጾሙ ወራት መደረጉ ምእመናን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲመለከቱት ይረዳ ነበር። በወቅቱ በአዘጋጆቹ ላይ ለደረሰው የኢኮኖሚ እና የሥነ ልቡና ጉዳትስ ለቤተ ክርስቲያኗ ካሣ የሚከፍላት ማን ነው? ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ታግዶስ ከሆነ ሕዝቡ ይህን የማወቅ መብት የለውም?
ዛሬም “ሰማይ አይታረሥ ንጉሥ አይከሰስ” ብለን የምናምን ይመስላል። ለዚያውም ሀልዎተ እግዚአብሔርን ለካዱ እና ቤተ ክርስቲያንን በየቀኑ ለሚያዋርዱ ተራ የዘራፊዎች ቡድን። ለመሆኑ ለመንግሥት የፈለገውን እንዲያደርግ መብት የሚሰጠው ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ሕግ የትኛው ነው? እስከመቼ ነው በዚህ ፍጹም ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን ስንታለል የምንኖረው? ከአሁን በኋላ መንግሥት ተብየው የፈለገውን ነገር እያገደረገና በፈለገው ጊዜ እየፈቀደ የሚሄድበት አካሄድ መቆም አለበት። የቤተክርስቲያኗም ምእመናን መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ የሚወስደውን ርምጃ በአጽንዖት በመከታተል ከመሥመር ያለፈ ነገር ሲያዩም ለምን ሆነ? በማለት በግልጽ መንግሥትን መጠየቅ ይገባቸዋል።በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማይ በሮኬት ይታረሳል፣ ንጉሥም በሕግ ፊት ይከሰሳል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
ዲባባ ዘለቀ dibabazeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment