Tuesday, April 26, 2016

መንድሜ፣ እስክንድር (አይበገሬው) ነጋ፡ ብቻህን አይደለህም እናም እንወድሀለን!


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ወንድማችንን እስክንድር ነጋን እናስታውስ፣
Eskinder Nega 1                                             /ዘ-ህወሀት (የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ) ታላቁ እስክንድር ነጋ ከሕዝብ ትውስታ እና ህሊና ተፍቆ እና ጠፍቶ ከማየት በላይ የሚወደው ነገር የለም፡፡ ዘ-ህወሀት ዓለም እስክንድር ነጋን እንዲረሳው ይፈልጋል፡፡ የእርሱ ትዝታ እየደበዘዘ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ይፈልጋሉ፡፡ እርሱ መታወስ ያለበት ከሆነ ደግሞ የዓለም ሕዝብ እርሱን በአሸባሪነት ማስታወስ እንደሚኖርበት ይፈልጋሉ፡፡
የእስክንድር ጉዳይ እ.ኤ.አ በ1964 በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ አፓርታይድ ኔልሰን ማንዴላን አሸባሪ በማለት በሀሰት በመወንጀል የእድሜ ልክ እስራት በመበየን ወደ ሮቢን ደሴት የማጎሪያ እስር ቤት ወስደው ዘብጥያ ካወረዷቸው ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ማንዴላ ከ27 ዓመታት የአፓርታይድ የእስራት ጊዜ በኋላ ከማጎሪያው እስር ቤት በመውጣት ደቡብ አፍሪካን ከመጥፎ አደጋ አድነዋታል፡፡
አናሳው የደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የበላይነት አገዛዝ አፓርታይድ ማንዴላን ከሕዝብ ትውስታ ሰውሮ በማቆየት ጥረቱ ላይ ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ዘ-ህወሀትም በተመሳሳይ መልኩ እስክንድር ነጋን ከሕዝብ ትውስታ ለማጥፋት ከቶውንም አይችልም፡፡ እስክንድር ነጋ ከማጎሪያው እስር ቤት ይወጣል፣ ወዲያውኑም የእርሱን ቦታ አሳሪዎቹ ተክተው ይወስዳሉ፡፡
የእስክንድር ነጋ ምስል፣ ጽሑፎች እና ሌሎች የትችት ስራዎቹ እና በረከቶቹ ሁሉ በማህበራዊ ሜዲያዎች እና በበርካታ ድረ ገጾች ታላቅ ክብር ባላቸው ዓለም አቀፍ የፕሬስ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጭምር ይወጣል፡፡ ከሳምንት በፊት አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት የእስክንድር እስራት በሕገወጥ መልኩ እና በዘ-ህወሀት አጭበርባሪነት መሆኑን ገልጾ  በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የእስክንድር ነጋ ምስል በማህበራዊ ድረ ገጼ አናት ላይ ይገኛል፡፡ በእኔ ማህበራዊ ድረ ገጽ (https://www.facebook.com/al.mariam) እኔን የማይመስል ምስል እንዳለ ሰው ሳይጠይቀኝ የዋለበት ጊዜ የለም፡፡ አትጨነቁ እያልኩ እንደህ በማለት እነግራቸዋለሁ፡፡ “ያ የወንድሜ የእስክንድር ነጋ ምስል ነው!”
አንባቢዎቼ ጥቂት ውለታዎችን እንድታደርጉልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ይህንን ትችት ከማንበባችሁ በፊት የእስክንድርን የእጅ ጽሑፍ እና የዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር እየተባለ ከሚጠራው እስር ቤት ቤት የተጻፈውን ደብዳቤ እንድታነቡት እጠይቃለሁ፡፡ (ይህንን ደብዳቤ ለማንበብ በእንግሊዘኛ  እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)
(**የእስክንድርን የእጅ ጽሑፍ ደብዳቤ በማያቋርጥ መልኩ በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት ዘበኞች እና ሰላዮች ክትትል ስር ሆኖ ይህንን የመሰለውን ጠንካራ ሀሳቡን ለመግለጽ ባደረገው ልዩ የሆነ ጥረት ምክንያት የኮምፒውተር የፊደላት መክተቢያ ቆልፎችን ሳንጠቀም ለክብሩ ስንል እንዳለ አቅርበነዋል፡፡)
ከዚህም በተጨማሪ በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጠኛ በካርል በርነስተይን (እ.ኤ.አ ነሐሴ1974 የዋተርጌትን ቅሌት ያጋለጠው እና ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰንን ከስልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ያደረጋቸው እና በዓለም ላይ ታላቅ እውቅና ያለው ጋዜጠኛ) እና ሌቭ ሽሬበር (እ.ኤ.አ የ2016 የኦስካር ምርጥ ስዕሎች አሸናፊ የሆነው እና የተከበረ ዳይሬክተር፣ ያዘጋጁትን ተንቀሳቃሽ ፊልም አንባቢዎቼ እንዲመለከቱት እጠይቃለሁ፡፡
(የቪዲዮ ምስሉን ለመመልከት እዚህ ጋ ይጫኑ ፡፡ ካርል በርንስተይን እና ሌቭ ሽሬበር አሸባሪን ለመከላከል ብለው እንደዚህ ያለ በፍቅር የተሞላ መሳጭ ንግግር ያደርጋሉን?) 
ከሁሉም በላይ ደግሞ በእስክንድር ነጋ ላይ በባለቤቱ በሰርካለም ፋሲል (እርሷም የተከበረ የጋዜጠኝነት ሽልማት አሸናፊ ኢትዮጵያዊት ጋዜጠኛ እና ለመብቷ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለፕሬስ ነጻነት መከላከል ከባለቤቷ ጋር ታስራ የነበረችው) አማካይነት (በእንግሊዝኛ ንኡስ ርዕሶች) የተዘጋጀውን እና ልብ የሚሰብረውን የ3 ደቂቃ የቪዲዮ ፊልም አንባቢዎቼ እንዲመለከቱት እጠይቃለሁ፡፡ (የቪዲዮኑን ፊልም  እዚህ ጋ በመጫን  መመልከት ይችላሉ፡፡)
ሰርካለም ልጇን ናፍቆትን በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት እ.ኤ.አ በ2007 ተገላግላለች፡፡
Amnesty 4እስክንድርን ወንድሜ ብዬ ስጠራ እና ሰርካለምን እህቴ ብዬ ስጠራ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በእነርሱ መስዋዕትነት፣ በእነርሱ ድፍረት፣ ጽናት እና አይበገሬ ታማኝነት እና በእነርሱ ግላዊ አርአያነት እራሴን ዝቅ አድርጌ እመለከታለሁ፡፡
እስክንድር ነጋ እና ሰርካለም ለኢትዮጵያ ምርጦች እና ባለብሩህ አእምሮ ጋዜጠኞች፣ ለሰላማዊ አማጺዎች፣ በዘ-ህወሀት ግልጽ እና ድብቅ የማጎሪያ እስር ቤቶች ውስጥ በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት የፖለቲካ እና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አርአያ እና ቀንዲል ናቸው፡፡ እስክንድር ነጋን በማስብበት ጊዜ በቀለ ገርባን፣ አህመዲን ጀቤልን፣ ውብሸት ታዬን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ አንዷለም አራጌን፣ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ እማዋይሽ ዓለሙን፣ ዴልዴሳ ዋቆ ጃርሶን፣ አኬሎ አቆይ ኡቹላን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማርያንን እና በሺዎች የሚቆጠሩትን የሌሎችን የፖለቲካ እስረኞችንም በተጨማሪ አስባለሁ፡፡
እስክንድር ነጋን በምናስብበት ጊዜ ሁሉንም በሙሉ እናስታውሳለን!
የእስክንድር ነጋ የፍርድ ቤት ሂደት እና ስቃይ፣
እስክንድር ነጋ ልዩ የሆነ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እና በኢትዮጵያ ጽኑ የፕሬስ ነጻነት ተሟጋች  ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1993 ጀምሮ የዘ-ህወሀት ፍርሀት የለሽ ተቺ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ እስክንድር እና ባለቤቱ ሰርካለም በዘ-ህወሀት የተዘጉ ጋዜጦችን ማለትም ኢትዮጲስ፣ አስኳል፣ ሳተናው እና ምኒልክን ጨምሮ የተለያዩ ጋዜጦችን እያቋቋሙ መስራት ጀምረው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 በዘ-ህወሀት በቁጥጥር ስር ውሎ ወደማጎሪያው እስር ቤት እስከገባበት ጊዜ  ድረስ እስክንድር እረፍትየለሽ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ዘንድ ሰፊ አንባቢ ያለው ጦማሪ ነበር፡፡ ዘ-ህወሀትን በተለይም አሁን በህይወት የሌለውን መሪውን አምባገነኑን መለስ ዜናዊን ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ጉዳዮች ላይ ግንባሩን ሳያጥፍ ፊት ለፊት ይታገል ነበር፡፡ ዘ-ህወሀት እስክንድር ነጋን ለመቁጠር በሚያዳግት ለበርካታ ጊዚያት በሸፍጥ ውንጀላ ክስ እየመሰረተ በማጎሪያው እስር ቤት ሲያስረው ቆይቷል፡፡
ዘ-ህወሀት እስክንድርን እ.ኤ.አ በ2011 አሸባሪነት የሚል የሸፍጥ ክስ በመመስረት ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ዘብጥያ ወረወረው፡፡ የእርሱ ወንጀል ሆኖ የተቆጠረው፣
1ኛ) በፕሬስ ነጻነት ላይ ጭቆና እያራመደ ያለውን ዘ-ህወሀትን መተቸቱ፣
2ኛ) ዜጠኞች በጅምላ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረጉ ወደ ዘብጥያ መጣልን በመቃወሙ፣
3ኛ) የዓረብ የጸደይ አብዮት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረውን እንደምታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማወያየቱ ነበር፡፡
ዘ-ህወሀት እስክንድር የአሸባሪ ቡድን አባል ነው፣ ለውጭ ኃይሎች ሰላይ ነው፣ እናም በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የአሸባሪዎች ጥቃት ለማሳለጥ የተዘጋጀ አሸባሪ ነው በማለት በእስክንድር ላይ ስም የማጥፋት እና የማጠልሸት ያልተሳካ የፕሮፓጋንዳ ሙከራ ዘመቻውን ለማሳየት ሞከረ፡፡
አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በግል በእስክንድር ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ እንደነበረው ታማዕኒነት ያላቸው መረጃዎች አሉኝ፡፡ መለስ እስክንድር እንደሚያደርገው በተስፋ የተሞላ ንግግር ዓይነት ማድረጉን አይደግፍም፡፡
እስክንድር ለአምባገነኑ ለመለስ ቅንጣት የምታህል ፍርሀት አያሳይም፡፡ እስክንድር ስለመለስ የፈለገውን ያህል የሚመጣ ነገር ቢኖርም ባይኖርም በእራስ መተማመን ስሜት ይናገራል፡፡
አምባገነኑ መለስ እስክንድርን ይጠላዋል ምክንያቱም ይፈራዋል፡፡ አምባገነኑ መለስ የእስክንድርን ብዕር ይፈራዋል ምክንያቱም የእስክንድር ብዕር በመለስ ላይ ያለውን ያልተቀባባውን ደረቅ እውነታ መዞ ያወጣልና፡፡
አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በርካታ ነገሮችን መከላከል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እውነትን መከላከል ፈጥሞ አይችልም፡፡
እ.ኤ.አ በመስከረም 2010 እስክንድር እና ሰርካለም የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ለሊ ቦሊንገር ደብዳቤ በመጻፍ ስለአምባገነኑ መለስ ያለውን እውነታ ተናግረዋል፡፡ በዚያ ደብዳቤ እስክንድር እና ሰርካለም አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእነርሱ ላይ በግል እና በፕሬስ ነጻነት ላይ የሰራቸውን ወንጀሎች በሙሉ ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ለአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጥሪ እንዳይደረግለት እንዲህ የሚል ተመጽዕኖ አቅርበዋል፣ “በሀገሩ የመናገር ነጻነትን በትጋት የሚደፈጥጥ መሪ የእራሱን ሀሳብ በክብር ለመግለጽ በነሐሴ ወር በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሚደረገውን ጉባኤ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡“
እ.ኤ.አ መጋቢት 2011 “ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ” በሚል ርዕስ እስክንድር ለአምባገነኑ መለስ እውነታውን እስከ ጥርሱ ድረስ ነግሮታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አምባገነኑ መለስ ምናልባትም ስሙን መለስ ከሀዲው በሚል በመቀየር ባታላይነቱ እና በከሀዲነቱ ለበርካታዎቹ ለዘ-ህወሀት ለታገሉ እና ለሞቱ ጓደኞቹ እንዲህ የሚል የነብይነት ከሀዲ ዕጣ ፈንታውን በትክክል ይገልጻል፡
“ማናቸውም መሪዎች [ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ወታደራዊው ጠንካራው መንግስቱ ኃይለማርያም እናም ሌሎችም የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች] ኢትዮጵያዊ ወይም ደግሞ አሜሪካዊም ቢሆኑ መለስ ዜናዊ እንዳደረገው ሁሉ በንዴት የሚጦፉ እና ስሜታዊነት የሚያጠቃቸው እና የጓደኝነት ምግባራቸውን ሊመለስ በማይችል መልኩ ሊያቋርጡ ይችላሉ፡፡ በመለስ ዜናዊ እና በስዬ አብረሃእንዲሁም በሌሎች መካከል የጠፋው ጓደኝነት በጣም አስቸጋሪ በሆነው ጊዜ ለሶስት አስርት ዓመታት ዘልቋል፡፡ አዲስ ጓደኞች በጠፉት በሌሎች የሚሸፈነውን ክፍተት ሊሞሉ አይችሉም፡፡ ሆኖም ግን አውሪያዊ ስሜታዊነት እና ከብቸኝነት ሊመጣ የሚችለው ባህሪ ግን ትንሹ የመለስ መገለጫ ነው፡፡“
በዚያ አንቀጽ ላይ የሰፈረው እውነታ የመለስን ውስጣዊ ባህሪ እንዴት እንደሚነጣጥለው ማሰብ እችላለሁ፡፡ አምባገነኑ መለስ በቅርብ ጓደኞቹ እና በወታደራዊ ጓደኞቹ ላይ ያደረገውን ነገር የሚያውቅ እና ጸጸትም የሚሰማው ነው ይባላል፡፡ (መለስ ለተፈጸመ ስቃይ እና መከራ ምንም ዓይነት ጸጸት እና ርህራሄ አለው ብዬ አላምንም፡፡) ሆኖም ግን ጸጸት እና ርህራሄ የሚኖረው ቢሆን እንኳን እንዲህ የሚለውን የሸክስፒርን ጥልቅ የግጥም ስሜት የሚያስብ ከሆነ በጣም የሚገርመኝ ይሆናል፡ “…እራሴን አከበርኩ እናም ለዕጣ ፈንታዬ ቃል ገባሁ፣/በተስፋ አንዱ ዋና ከበርቴ ለመሆን፣/ እንደ እርሱ ለመሆን፣ እርሱ እንዳሉት ጓደኞች ለመሆን…“ አምባገነኑ መለስ ጠላት እንጅ ጓደኞች አልነበሩትም፡፡
በዚያው ደብዳቤ ላይ እስክንድር ለአምባገነኑ መለስ ወደፊት ማለቱን ትቶ ስልጣኑን እንዲለቅ እንዲህ በማለት ነግሮታል፡
“አቶ መለስ ዜናዊ፡ አንተ ከስልጣንህ እንድትወርድ እና ቢሮህን እንድትለቅ ሕዝቡ ይፈልጋል፣ ሕዝቡ አንተን አይፈልግም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህንን ደብዳቤ እየጻፍኩ ባለበት ጊዜ ህዝቡ በሰሜን አፍሪካ እየተፈጸመ ያለውን ክስተት በቅርበት በመመልከት ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ በአፍሪካ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሚኖሩት እንደምታዎች ላይ በመከራከር ላይ ይገኛል፡፡ እናም በተራዎቹ ሊቢያውን ጀግንነት ላይ በመደመም ላይ ይገኛሉ፡፡ ጊዜው ከመምሸቱ በፊት ሕዝቡን አዳምጥ፡፡“
እ.ኤ.አ ሐምሌ 2011 የጭቆና አገዛዝ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ይጣላል፣ እናም ዴሞክራሲ በዘ-ህወሀት አመድ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያብባል በማለት እስክንድር ለመለስ እንዲህ ሲል በአጽንኦ ነግሮታል፡
“ዴሞክራሲ የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ዕጣፈንታ ነው፡፡ ኤስኪሞ ወይም ደግሞ ዙሉ፣ ክርሰቲያን ወይም ሙስሊም፣ ነጭ ወይም ጥቁር፣ የሰለጠነ ወይም በማደግ ላይ ያለ ብትሆንም እንኳ ልታስወግደው አትችልም፡፡ በእርግጠኝነት ይኸ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው፡፡ እናም ከረዥም ጉዞ በኋላ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ትግል እውን ለመሆን በማዕዘኑ አካባቢ በመዞር ላይ ይገኛል፡፡ ሁላችንም በዚያ አካባቢ ነን፡፡ ነጻ እንሆናለን!“
እ.ኤ.አ ነሐሴ 2011 ነገሮች ሁሉ አሁን ባሉበት ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ መለስ የጋዳፊን ዓይነት አስፈሪ ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥመው እንዲህ በማለት አስጠንቅቆት ነበር፡
“የአፍሪካን ግዙፍ አምባገነናዊ አገዛዝ የሚመራው የኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ በርካታዎቹ እንደሚጠረጥሩት በመጀመሪያ ጋዳፊ እንዳደረገው ስሌት በመስራት ጽኑ ማስታወሻ ይይዛል…እናም የዓረቡ ዓለም ታላቋ አምባገነን ግብጽ በሙባረክ የአገዛዝ ዘመን እንደሆነችው የጸደይ አብዮት ወርቃማ ሽልማት እንደሆነችው ሁሉ የሰብ ሰሀራ ታላቋ አምባገነን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ የጸደይ አብዮት ሽልማት ትሆናለች፡፡ ካለግብጽ የዓረቡ ዓለም የጸደይ አብዮት ሊኖር አይችልም ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከኢትዮጵያ ውጭ የአፍሪካ የጸደይ አብዮት ሊኖር አይችልም፡፡“
እስክንድር እ.ኤ.አ መስከረም 2/2011 አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ለሰላማዊ የለውጥ ሽግግር እንቅፋት እንዳይሆን እንዲህ በማለት መክሮት ነበር፡
“ለበርካታ ዘመናት ሰላማዊ ሽግግር ባለመኖሩ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ውድቀት፣ ምናልባትም አደገኛ የሆነ የኃይል እርምጃ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ማለት የተፈለገው የነበረው ሁኔታ በነበረበት መልኩ ሊቀጥል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ሕጋዊ የለውጥ እርምጃ ለማድረግ ጥሪ የሚደረግበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ታሪክ ላልተወሰነ ጊዜ ሊተላለፍ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡“
እ.ኤ.አ መስከረም 14/2011 እስክንድር በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
እ.ኤ.አ ሐምሌ 13/2012 እስክንድር በዘ-ህወሀት የይስሙላ የዝንጀሮው ፍርድ ቤት የ18 ዓመታት እስራት ተበየነበት፡፡
ዘ-ህወሀት በእስክንድር ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ማስረጃ ይሆነኛል ብሎ ያቀረበው በጥራት ያልተቀዳ በአንድ በከተማ አዳራሽ ለተሰበሰበሰ ሕዝብ የዓረቡ የጸደይ አብዮት በኢትዮጵያ ላይ ስለሚኖረው እንደምታ በሚል ርዕስ እስክንድር ያቀረበውን ንግግር ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 20/2012 አምባገነኑ መለስ መሞቱ ይፋ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን እ.ኤ.አ ሐምሌ 20/2012 (እ.ኢ.አ ደግሞ ሐምሌ 13 ቀን 2004) አምባገነኑ መለስ መሞቱን ይፋ አደረገ፡፡
ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ “ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ” ስራውን ይሰራል ይላሉ፡፡
አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እስክንድርን የሚጠላው በሚያሳየው ድፍረት፣ ፍርሀትየለሽነት እና ባለው ጽናት ምክንያት ብቻ ኤደለም፡፡ ሆኖም ግን መለስ በእስክንድር ምሁራዊ ክህሎት ላይ ቅናት ያድርበት እንደነበር ጭምር ያሉኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት በተደጋጋሚ ስናገረው እንደቆየሁት መለስ የእራሱን ልዩ ክህሎት ተጠቅሞ እና የነገሮችን ውልመሰረት አጢኖ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችን ማሳመን የሚችል ጎበዝ አፈ ምላጭ የውሸት ምሁር ነው፡፡ መለስ ፍሬከርስኪ ስለሆኑ እና ምንም ዓይነት እርባና ስለሌላቸው ነገሮች ብዙ የማውራት ተሰጥኦ የነበረው አጭበርበሪ ከመሆን የዘለለ ሰው አልነበረም፡፡ የቀድሞው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ዶናልድ ያማማቶን እንዲህ በማለት በዊኪሊክስ በተለቀቀው መልዕክት የተታለሉ መሆናቸው ግልጽ ሆኗል፣ “በበርካታ አጋጣሚዎች መለስ ዝርዝር የሆኑ ምላሾችን በመስጠት ስለአንድ ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ያለባቸውን ቡድኖች በአንድ መስመር ላይ የማሰለፍ ችሎታ እንዳለው ተመልክተናል፡፡“ ቡድኖችን በአንድ መስመር ማሰለፍ እና በቀላሉ የሚሞኙ የምዕራብ ሀገሮች ዲፕሎማቶችን ማቅረብ የመለስ ዋናው ድብቅ ሚስጥር ነው፡፡ መለስን በሚገባ ለሚያውቁ የለየለት አታላይ መሆኑን በውል ይገነዘባሉ፡፡ እስክንድርም ይህንን ነገር አሳምሮ ያውቃል፡፡ መለስ እንደሚበሳጭ የውኃ ተርብ ዓይነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይቆጣል፣ ወዲያው ወዲያው በፍጥነት ይተነፍሳል እናም በላይ ያሉት የአካል ክፍሎቹ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ሆኖም ግን ከተቃዋሚዎቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በመከራከር እና በመወያየት ተግባራት ላይ አይሰማራም፡፡
ለመሆኑ እስክንድር ነጋ ማን ነው?
እስክንድር ነጋን ለመግለጽ ቀላል እና እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ እስክንድር የኢትዮጵያ ታዋቂ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ እስረኛ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2013 አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እስክንድር ነጋ “የህሊና እስረኛ” ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ በተመሳሳይ መልኩ እስክንድር የህሊና እስረኛ ለመሆኑ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የፕሬስ ድርጅቶች ተመሳሳይ የሆኑ መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እስክንድር በጽናት፣ በምክንያታዊነት እና የፕሬስ ነጻነትን በመከላክል ረገድ በርካታ የሆኑ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማቶችን አሸናፊ ነው፡፡
እስክንድር ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ እና ሌላም ተጨማሪ ነገር ነው፡፡
እስክንድር ነጋ ለእኔ ልዩ ጀግናዬ የሆነው በርካታ ጽሑፎች መጻፍ በመጀመሩ፣ የፕሬስ ነጻነትን ለማስከበር ፍርሀት የለሽ በመሆኑ፣ ወይም ደግሞ ለእርሱ የሚገባውን ዓለም አቀፍ ክብር እና ዝናን በመጎናጸፉ ምክንያት አይደለም፡፡
እስክንድር ለእኔ ልዩ ጀግናዬ ነው ምክንይቱም የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ የነጻነት ታጋይ ነው፡፡ ለመታገል ግን ጠብመንጃ፣ ቢላዋዎችን ወይም ሽብርን አይዝም፡፡
የእርሱ ምርጡ መሳሪያዎቹ ቁራጭ እርሳስ ወይም ደግሞ ብዕር ናቸው፡፡ የእርሱ ብዕር  እውነትን ዘክዝኮ በመትፋት ዘ-ህወሀትን ሽባ የሚያደርግ እና ግራ የሚያጋባ ክስተትን መፍጠር ነው፡፡ የእርሱ ሀሳቦች ተፈጥሯዊ ኃይል አላቸው፡፡
እስክንድር ውሸትን፣ ሙስናን፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ስልጣንን መጠቀምን እና ሕገወጥነትን በእውነት ጎራዴ በመጠቀም የሚመትር ጀግና ነው፡፡
ብዕርን ብቻ በመታጠቅ እስክንድር ጨለምተኝነትን በተስፋ፣ ፍርሀትን በድፍረት፣ ቁጣን በምክንያታዊነት፣ እብሪትን በትህትና፣ ድንቁርናን በእውቀት፣ አለመቻቻልን በትዕግስት፣ ጭቆናን በጽናት፣ ጥርጣሬን በእምነት እና ጥላቻን በፍቅር ይዋጋል፡፡
ሆኖም ግን እስክንድር በብዕር ከመዋጋትም በላይ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እስክንድር የደፋርነት ንጉስ ነው፡፡ እስክንድር በቀልተኛ የሆኑትን የዘ-ህወሀት አውሬ ዓይኖች ከተመለከተ በኋላ እንዲህ አለ፡
“ለስምንተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር ልታውሉኝ እና ልታስሩኝ ትችላላችሁ፡፡ ልትደበድቡኝ፣ ልታሰቃዩኝ እና ከሌላው እስረኛ ለብቻ ነጥላችሁ ልታስሩኝ ትችላላችሁ፡፡ መከራ ልታደርሱብኝ እና የሸፍጥ ክስ በመመስረት በተንዛዛ ቀጠሮ እያመላለሳችሁ ፍዳ ልታሳዩኝ ትችላላችሁ፡፡ በሚከረፋው የማጎሪያ እስር ቤታችሁ በረሀብ እንድቀጣ እና የሕክምና አገልግሎት እንዳጣ ልታደርጉ ትችላላችሁ፡፡ ስሜን ልታጠፉ እና ባሕሪዬን ጠላሸት ለመቀባት ትችላላችሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ባለቤቴን ልታዋርዷት እና የእናንተ ወሮበሎች በእኔ ላይ የሚያደርሱትን በደል እየተመለከተ ልጄ እንባ አውጥቶ ሲያለቅስ እናንተ ልትስቁ ትችላላችሁ፡፡ እኔን እና ቤተሰቤን ልታስፈራሩ፣ ልታሸማቅቁ እና ለእኛ ህይወት በመሬት ላይ ገሀነም እንድትሆን ልታደርጉ ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም ግን ለእናንተ የጭቆና አገዛዝ፣ ለእናንተ የበከተ ሙስና፣ ለእናንተ የጭካኔ ፌሽታ፣ ለእናንተ አረመኒያዊ ድርጊት እና እንስሳዊ ኋላቀርነት ባህሪ በፍጹም በፍጹም በፍጹም አላጎበድድም፡፡ እስክንድር ነጋ እንደመሆኔ መጠን የእራሴ ዕጣ ፈንታ አዛዥ እና የህይወቴ መርከብ ነጂ/ካፒቴን ሌላ ማንም ሳይሆን እኔው እራሴ ነኝ!“
ከእስክንድር ነጋ እና ከእርሱ ባለቤት ከሰርካለም ፋሲል የበለጠ የማከብራቸው፣ የማደንቃቸው እና የማወድሳቸው በጣም ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱን ለማክበር የምስጋና ደብዳቤ ጽፊያለሁ፡፡ እስክንድር፣ ሰርካለም እና ልጃቸው ናፍቆት (ቀኑ ሳይደርስ በእስር ቤት የተወለደ እና በአረመኔው በቀልተኛ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ የህይወት ማዳኛ ኢንኩቤተር የተከለከለው) ናቸው፡፡
እኔ ማድረግ የምችለው ቢሆን ኖሮ እነዚህን የተከበሩ እንቁዎች የሌላ የማንም ሀገር ወይም ደግሞ ተቋም የእኔ ናቸው ብሎ እንዳይጠይቅ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄራዊ እሴቶች ናቸው በማለት አውጅ ነበር፡፡ በዚያ ጉዳይ ላይ ሌላ ምርጫ አይሰጣቸውም!
እስክንድርን የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ተሟጋች አድርጌ ለመናገር አልፈልግም፡፡ ከእኔ ይልቅ ስለዚህ ሁኔታ የበለጠ ግልጽ በሆነ መልኩ ሊናገሩ የሚችሉ በርካታዎቹ አሉ፡፡
እስክንድር በዓለም ሁሉ ካሉ የፕሬስ ነጻነት ጀግናዎች ሁሉ ጀግና ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ሰላማዊ አመጸኛ ጋዜጠኞች ሁሉ ስለእርሱ ተናግረዋል፣ በአስቸኳይ ከእስር ቤት እንዲለቀቅም ጠይቀዋል፡፡ ከበርካታዎቹ ጥቂቶቹ የሚከተሉትን ያካትታል፣ ኬኔት ቤስት ከላይቤሪያ፣ ሊዲያ ካቾ ከሜክሲኮ፣ ጁአን ፓብሎ ካርዲናስ ከችሌ፣ ሜይ ችዲያክ ከሊባኖስ፣ ሰር ሀሮልድ ኢቫንስ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ አክባር ጋንጂ ከኢራን፣ አሚራ ሀስ ከእስራኤል፣ ዳውድ ክታብ ከዮርዳኖስ፣ ግዌን ሊስተር ከናሚቢያ፣ ሬይሞንድ ሎው ከደቡብ አፍሪካ፣ ቬራን ማቲክ ከሰርቢያ፣ አዳም ሚችንክ ከፖላንድ፣ ፍሬድ ሜምቤ ከዛምቢያ፣ ኒዛር ኔዩፍ ከሶርያ፣ ፓፕ ሳይኔ ከጋምቢያ፣ ፋራጅ ሳርኮሂ ከኢራን፣ ኔዲም ሴነር ከቱርክ፣ አሩን ሻውሬ ከሕንድ፣ ሪካርዶ ኡሴዳ ከፔሩ፣ ጆሴ ሩቤን ዛሞራ ከጓቲማላ ናቸው፡፡ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች እና የፕሬስ ድርጅት መሪዎች ደግሞ የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡ ማርክ ሀምሪክ የናሽናል ፕሬስ ክለብ ፕሬዚዳንት ከዋሺንግተን ዲ.ሲ፣ አርየህ ኔይር የኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽንስ ፕሬዚዳንት፣ ኬኔዝ ሮት የሂዩማን ራይተስ ዎች ዋና ዳይሬክተር፣ ጆኤል ሲሞን የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ ዋና ዳይሬክተር፣ ዊሊያም ኢስተርሊ በኒዮርክ ዩኒቨርሲሰቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡
እስክንድር ነጋ፡ አይዞህ ብቻህን አይደለህም!
እስክንድር ነጋ ያልተረሳ መሆኑን እንዲያውቅ እፈልጋለሁ፡፡ ሰርካለም እና ናፍቆት እስክንድር በፍጹም የማይረሳ መሆኑን እንዲያውቁት እፈልጋለሁ፡፡ ለክብራችን እና ለነጻነታችን ሲል ከዘ-ህወሀት ግንባር ለግንባር ገጥሞ እየተፋለመልን ያለውን እንቁ ጀግና እንደምን ልንረሳው እንችላለን?
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሕዝብ በኢትዮጵያ በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ እየማቀቁ ያሉትን እስክንድር ነጋን እና ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንዲያስታውስ እፈልጋለሁ፡፡
እስከንድር ነጋን እናስታውሳለን፣ ሁልጊዜ፡፡ እስክንድር ነጋን እናደንቃለን፣ እናከብራለን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አስደናቂ እና አፍቃሪ ባል እና አባት በመሆኑ እስክንድር ነጋን እንወደዋለን፡፡
ከሁሉም በላይ እስክንድር ነጋ የኩሩዋ ኢትዮጵያ ልጅ በመሆኑ እናከብረዋለን፣ እናስታውሰዋለን፡፡
የሚካኤል ጃክሰንን የግጥም ስንኞች ትንሽ ለወጥ በማድረግ እኛ የእስክንድር ነጋ ወንድሞች እና አህቶች ስለእርሱ ምን እንደሚሰማን ያለንን ስሜት እንዲህ በማለት ለመግለጽ እንወዳለን፡
ብቸኛ አይደለህም አለን ከጎንህ፣
ሌት ከቀን በማሰብ የምንሳሳልህ፣
ስለውሎ አዳርህ ጤናና ምግብህ፣
ስለጥልቅ ሀሳብህ የሕዝብ ፍቅርህ፡፡
አንተ ለኛ ብለህ፣
ባፋኞች ተወግረህ፣
ስቃይ ተሸክመህ፣
ከደስታ ርቀህ፣
ባጥር ተከልለህ፣
በሸፍጥ ተይዘህ፡፡
ብትኖር በስቃይ፣
ሁሉን ነገር ሳታይ፣
ቢደረመስ ሰማይ፣
ወይ ንቅንቅ ካላማህ ነጻነትን ሳታይ፡፡
በአካል ሩቅ ሆነን ካንተ ጋር ባንሆንም፣
የስቃይ ተጋሪህ ጓደኞች ባንሆንም፣
እኔ ልተካልህ የማንል ብንሆንም፣
በመንፈስ አንድ ነን ልዩነት የለንም፣
ብቸኛ ነኝ ብለህ ፍጹም እንዳትቆዝም፣
በጀግናው ጽናትህ ከቶ አንረሳህም፡፡
ፍቅርህ ቤቱን ሰርቶ በልባችን ውስጥ፣
ሌት ቀን እንድንተጋ ለወሳኙ ለውጥ፣
ለሕዝቦች አርነት ለእድገት መሳለጥ፡፡
አንደበተ ርትኡ የጠላት መጋኛ፣
የሕገወጥነት ታጋይ አመጸኛ፣
የዘር ናፋቂነት የአድልኦ ቀበኛ፣
ሙስናን ተዋጊ ተፋላሚ ዳኛ፣
የፍትህ መሀንዲስ የጠራ እውነተኛ
ፍትህ ሳያሰፍን ከቶ የማይተኛ፣
ብቸኛ አይደለህም ከጎንህ ነን እኛ::
አረመኔ ስርዓት በሸፍጥ ተነስቶ፣
በዘር በኃይማኖት ልዩነት መስርቶ፣
ጥላቻና በቀል በሀገር አስፋፍቶ፣
ነጻነትን ገፎ ፍቅርን አጥፍቶ፣
የሀገሪቱን ሕዝብ ረግጦ አደህይቶ፣
ጉልብትና ኃይሉን ሸፍጡን ተመክቶ፣
ለመጥፎው ድርጊቱ ህይወቱን ሰውቶ፣
በኢትዮጵያ ላይ አይቀር እንዲህ ተንሰራፍቶ፡፡
እኔ እስክንድር ነጋ ነኝ! 
አይበገሬው እስክንድር ነጋ! 
እስክንድር ነጋ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም የፖለቲካ አስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  
ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም 

No comments:

Post a Comment