የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
የአንድ አገር ድንበር የሚደፈረው ፣ሕዝቡ ለተለያዩ ጥቃቶች የሚጋለጠው የአገሩን ድንበርና የሕዝቡን ደህንነትና ሰላማዊ ኑሮ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል በሕዝብ፣ለሕዝብ፣የሕዝብ የሆነ መንግሥት በሌለበትና ለጸረ ሕዝብ ሃይሎች አመቺ ሁኔታ ሲፈጠር ነው።
ለአለፉት ሃይአምስት ዓመታት ሥልጣኑን በሃይል የጨበጠው የጎሳ ስብስብ በተደጋጋሚ የአገራችንንና የሕዝባችንን ጥቅምና ደህንነት ለአደጋ እያጋለጠ እራሱም የአደጋው ፈጣሪ እየሆነ መቆየቱን የሥልጣን ዘመን ታሪኩ ይመሰክራል።
የስልጣን ዕድሜውን ለማርዘም በሁከትና በሽብር፣በብጥብጥና በእርስ በርስ ቀውስ አንድ ጊዜ ቀስቃሽ ሌላ ጊዜ ወቃሽ፣አንድ ጊዜ አዘጋጅ ሌላ ጊዜ አሶጋጅና አስታራቂ፣እየሆነ በመቅረብ ለማምታታት ቢሞክርም በየቀኑ እውነተኛ ገጹና ባህሪው እየተጋለጠ ሕዝብን ማታለል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።ውስጡም በቀውስ እየተናጠ ይገኛል።
ሰሞኑን የመንግሥት አልባነት እንዳለ የሚሰማቸው የወራሪና የሽብር ሃይሎች በከፍተኛ ዝግጅትና በዘመናዊ መሳሪያ ከፈጣሪው በቀር የት ደረስክ፣ምንስ ደረሰብህ የሚል መንግሥት በሌለው ኢትዮጵያዊ የጋምቤላ ሕዝብ ላይ የወሰዱት የጭካኔ እርምጃና ጭፍጨፋ ለአገሩና ለሕዝቡ የማይጨነቅና ደንታ የሌለው ፣ ለማንኛውም ጸረ ኢትዮጵያ አጋልጦ የሚሰጥ “መንግሥት” መኖሩን በማወቃቸው ነው።
የአገሪቱን ዳር ድንበርና የሕዝቡን መብትና ሰላማዊ ኑሮ የማያስከብርና የማያረጋግጥ ቡድን በመንግሥት የሥልጣን ቦታ ላይ ሊቀመጥ፣መንግሥትም ተብሎ ሊጠራ አይገባውም። ለአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ ለደረሰው መከራና ጥቃት በአንደኛ ደረጃ ተጠያቂው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ነው።በሥልጣንም ላይ ኖረም አልኖረም ከፈጸማቸውና ካስፈጸማቸው ወንጀሎችና የአገር ክህደቶች ነጻ አይሆንም።በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የፍትሕ መድረኮች ይጠየቅበታል፤ፍርዱንም ያገኛል።መሪዎች ገለውና ዘርፈው የሚደበቁበት ዋሻ እየተደፈነ መምጣቱን ሊያውቁት ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ማወቅና መረዳት ያለብን በሥልጣን ላይ ያለው ስብስብ የሥልጣን ዘመኑ እየተሟጠጠ፣ ከሕዝብ እየራቀና እየተነጠለ እየተጠላም ሲመጣ “ከደነገጠ የቆሰለ ነብር ይከፋል” እንደሚባለው የሞት የሽረትና አልሞት ባይ ተጋዳይ የግፍ እርምጃዎችን ሊፈጽም እንደሚችል ነው።የዚያ ሰለባ ላለመሆንና ለመመከት የግድ መደራጀትና መሰባሰብ አስፈላጊ ነው።የአሁኑም በጋምቤላና በቀረው ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የጥቃት እርምጃ የዚያው የተስፋ መቁረጥ ስሜት አካል ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ለተጎዱት የጋምቤላ ወገኖቻችን ሃዘኑንና የትግል አንድነቱን እየገለጸ ከሌሎቹ ተመሳሳይ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጥቃቱን የፈጸሙት የመንግሥትም ሆነ የውጭ ታጣቂ ሰርጎ ገብ ሃይሎች ለፈጸሙት ጭፍጨፋ፣ሕጻናትን አፍኖና አግቶ የመውሰድ እርምጃ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አቤቱታውን በማቅረብ በሕግ የሚጠየቁበትን መንገድ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ፣ለአገር አንድነት፣ ለዴሞክራሲ፣ለሕግ የበላይነት፣ለሰብአዊና ለዜጎች መብት፣ መከበር የቆሙ ድርጅቶች ይህን አሰቃቂ ድርጊትና አገር አጥፊ መንግሥት ከማውገዝ አልፈው በጋራ ግንባር ተሰልፈው ሊያሶግዱት ይገባል።ለዚህም አገር አድን የጋራ ዓላማ ልንታገልበት የምንችልበትን የጋራ አካል ለመፍጠር እንዳለፈው ጊዜ አሁንም ሸንጎ ጥሪ ያደርጋል። ጊዜውና ሁኔታው እያዘኑና እየተበሳጩ ብሎም እያወገዙ የሚቀመጡበት ሳይሆን በወሳኝ ትግል ላይ የሚሰማሩበት ወቅት ነው ብሎ ሸንጎ ያምናል።
አገራችንንና ሕዝባችንን ከተመሳሳይ ጥቃት በአንድነት ተደራጅተን እናድን! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!
No comments:
Post a Comment