ሰርግና ሰዓት – ዳንኤል ክብረት
ለጊዜ ያለንን አነስተኛ ግምት አጉልተው ከሚያሳብቁብን ክዋኔዎች አንዱ ሰርግ ነው፡፡ ሰርገኛ በጊዜው ከመጣ ትዳሩ ይፈርሳል የተባለ ይመስል አንድና ሁለት ሰዓት ዘግይቶ መምጣት ይቅርታም የማያስጠይቅ ልማድ ሆኗል፡፡ በሰዓት ተለክቶ በሚከፈልበት በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ የሀገሬ ልጆች እንኳን ‹የዘሬን ያንዘርዝረኝ› ብለው ሁለት ሰዓት ካላረፈዱ ያገቡ አይመሰስላቸውም፡፡ አብረዋቸው የሚሠሩ የሌላ ሀገር ዜጎችንና ኢትዮጵያውያንን የሚጋብዙበት ሁለት ዓይነት የጥሪ ካርድ እንዲያሳትሙ ይገደዳሉ፡፡ የሐበሻና የፈረንጅ፡፡ የፈረንጁ ካርድ ከሐበሻው ካርድ ሁለት ሰዓት ዘግይቶ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ሰርጉ ላይ ሁለት ዓይነት ማርፈዶች ናቸው የሚፎካከሩት፡፡ በአንድ በኩል ስድስት ሰዓት የተጠራው ሰርገኛ ሁለት ሰዓት ዘግይቶ ስምንት ሰዓት ላይ ሲመጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ስድስት ሰዓት የጠሩት ሙሽሮች ቢያንስ ሦስት ሰዓት ዘግይተው ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይመጣሉ፡፡ አርፍዶ የመጣው ሰርገኛም፣ አስረፍደው የመጡት ሙሽሮችም በረፈደ ሰዓት በመጀመራቸው ምንም ሳይሰማቸው አዳራሹን በእልልታ ያቀልጡታል፡፡ በርግጥ ለአንዳንድ ሰው ጊዜ ማለት ወር፣ ከዚያም ካለፈ ቀን ማለት ነው፡፡ ጊዜ ማለት ሰዓትና ደቂቃ ያልሆነለት ሰው ብዙ ነው፡፡ የኛ ሀገር ሰዓትና የኛ ሀገር አንድ ሳንቲም የሚያገለግሉት ለአንዳንድ ክፍያዎች ብቻ ነው፡፡
በአኩስም ከምናገኛቸው የጥንት የድንጋይ ላይ ቅርሶች አንዱ የሰዓት መለኪያ ነው፡፡ የፀሐይዋን ‹ጉዞ› ተከትሎ የጥላው ቦታ ላይ ምልክት የሚያሳይ የጥላ ሰዓት ከ2000 ዓመታት በፊት ነበረን፡፡ ሰዓታት የተሰኘው የዝማሬ ድርሰት፣ ጾም የሚገባውና የሚወጣው ስንት ሰዓት ላይ ነው? የሚለው የኖረ ክርክር፤ በፋሲካ እርድ መከናወን ያለበት ስንት ሰዓት ላይ ነው? የሚለው ጥንታዊ ሙግት፣ የባሕረ ሐሳብ ትምህርታችን የእያንዳንዱን ወር ቀንና ሌሊት ርዝመትና እጥረት በሰዓት ለክቶ ማስቀመጡ፣ በሰዓት መጠቀም ነባር ባህላችን እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ቤተ ክህነታዊና መንግሥታዊ ጉዳዮች ከሰዓት ጋር የተያያዙ ቢሆኑም ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ግን ከቀን፣ ከወርና ከዓመት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ለሚያርስ ገበሬ፣ ከድንበር እስከ ድንበር ለሚጓዝ ሲራራ ነጋዴ፣ ጌቶቹ ያዘዙትን መሥራት ብቻ ሳይሆን ጌቶቹ ያዘዙለትን ያህል መኖር ይችል ለነበረው ጢሰኛ፣ በሰዓት እንዲኖር የሚደርገው አስገዳጅ ምክንያት አልነበረም፡፡ እንኳን የተወለዱበት ቀንና ሰዓት ቀርቶ መወለድም ትርጉም የማይሰጥበት ዘመን ነበረ፡፡ አሜሪካ የሰማሁት አንድ ቀልድ አለ፡፡ አንዳንዱ የሀገሬ ሰው የተወለደበት፣ ፓስፖርቱ ላይ ያለው፣ አሜሪካ ሲገባ የሞለው የልደት ቀኑ ይለያያል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የፌስ ቡክ የልደት ቀንም የተለየ ሆኗል፡፡ ታድያ እንዲህ ያለው ችግር የገጠመው ወገን የመሥሪያ ቤቱ ሰዎች ‹ሰርፕራይዝ› ሊያደርጉት አሳይለም ሲጠይቅ በሞላው ቅጽ መሠረት በልደት ቀኑ ኬክ አስጋግረው ይመጣሉ፡፡ ልክ ጠዋት ወደ ቢሮው ሲገባ ‹ሃፒ በርዝ ደይ ቱ ዩ› እያሉ ሲያዜሙለት ግራ ይገባዋል፡፡ አሁን የትኛውን የልደት ቀኔን ነው እያከበሩ ያሉት? ብሎ፡፡ በኬኩ ሳይሆን ‹በቀኑ› ሰርፕራይዝ ሆነ፡፡ እንዲህ እንደርሱ ያልተወለደበትን ቀን የሚያከብር ብዙ ነው፡፡
እንዲያውም በእኛ ሀገር የአብዛኛው ሰው የሞቱ መታሰቢያ(ተዝካሩ)እንጂ የልደቱ መታሰቢያ አይከበርም ነበር፡፡ እንዲህ እንደዛሬ የእናቶችን የወሊድ ጊዜ ሞት የሚገቱ ዘመናዊ መንገዶች መጥተው መውለድ ‹አባት ደስ ይለዋል ልጅ ሲወለድለት› የሚል ዘፈን ከማስዘፈኑ በፊት መውለድ መከራ ነበረ፡፡ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድም ሴቲቱ ለብቻ ተነጥላ ጫካ ውስጥ እንድትወልድ ይደረግ ነበር፡፡ በቤት የምትወልደውም ብትሆን እርግዝናው ከድካም ጋር፣ ወሊዱም ሞትን የሚስብ ነበር፡፡ ያንን የመከራ ቀን ለማስታወስ ካለመፈለግ ይመስለኛል የልደታችን ቀን ይረሳ የነበረው፡፡ ቀኑ ለእኛ የልደት፣ ለእናት የመከራ መታሰቢያ ነበርና፡፡ ‹ምጡን እርሺው፣ ልጁን አንሺው› የተባለውም ምጡ መከራ ጭምር ስላለበት ነው፡፡ በምሥራቃውያን ባህል ምጥ ‹የጭንቅ ቀን› (ያውም ከሞት በመለስ) በመሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የመጨረሻው ዘመን ‹የምጥ መጀመሪያ› እስከ መባል ደርሷል፡፡
የአሁን ዘመን ልጆች ናቸው መውለድ ቄንጥ ሲሆን ልደትም ቄንጥ የሆነላቸው፡፡ እኛ ‹እሞታለሁ ብለህ ኑር፣ እኖራለሁ ብለህ ሥራ› እየተባልን አደግን፤ ልጆቻችን ደግሞ መኖርን እንጂ መሞትን ስለማያስቡ የተወለዱበትን ቀን ከወለዷቸው እናትና አባት እኩል ይወዳሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በእነርሱም ዘመን ባህላችን ቀን ላይ እንጂ ሰዓት ላይ ገና አልደረሰም፡፡ በሰዓት ተጀምሮ በሰዓት የሚያልቀውን፤ የባከነች ሰከንድና ደቂቃ ዋጋ ተሰጥቷ የምትጨመርበትን የእግር ኳስ ጨዋታ አፍቃሪና አድናቂ የሆነው ትውልድ፣ ለሰዓትና ደቂቃ ዋጋ ሲነፍግ ማየት የችግሩን አስከፊነት ማሳያ ነው፡፡
ይሄ ትውልድ ነው እንግዲህ ሦስትና አራት ሰዓት ዘግይቶ በገዛ ሰርጉ ላይ የሚገኘው፡፡ ኑሮውን በማርፈድ የሚጀምር፡፡ በሰርግ ዘፈናችን ላይ ‹ሰርግና ሞት አንድ ነው› ብንልም የሀገራችን ሰው ከሰርግ ይልቅ የቀብር ቀጠሮ ያከብራል፡፡ ለነገሩ በጥንቱ ባህላችን ድንገት የሚደረሰው ለቀብር እንጂ ለሰርግ አይደለም፡፡ ለሰርግማ ቢቻል ከሳምንት፣ ካልሆነም ከቀናት በፊት ተገኝቶ ሥራውን ማገዝ፣ ዋዜማው መዝፈንና መብላት ተገቢ ነው፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ በሰዓትና በአዳራሽ የተወሰነ ግብዣ አልነበረም፡፡ ሰርጉም ከጠዋት እስከማታ፣ አልፎም እስከ ሦስትና አራት ቀን የሚዘልቅ ነው፡፡ ስድስት ብንመጣ ሰባት፣ አሥር ብንመጣ አሥራ ሁለት ችግር የለውም፡፡ ጠዋት የገባውም አይወጣ፣ ማታ የመጣውም አያጣ፡፡ ችግር የተፈጠረው በገጠር ልቡና ከተማ መኖር ስንጀምር ነው፡፡ የጥሪ ካርድ፣ አዳራሽ፣ የሰሐን ኪራይ፣ የመናፈሻ ኪራይ፣ የመኪና ኪራይ የሚባሉ በሰዓት የሚያስከፍሉ ነገሮች የመጡብን በከተሜነታችን ነው፡፡ እኛ ደግሞ እየኖርን ያለነው በገጠር አስተሳሰብ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ‹በበገና ማኅሌተ ገንቦ› እንዲሉ፡፡ ከተማ እንጂ ከተሜ የለንም ከሚያስብሉብን መገለጫዎች አንዱም ሰርጋችን ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ክፉ አመል ለማረም ግን እንደ አቶ ቢረጋ ያሉ(ስማቸው ተቀይሯል) ቆራጦች ያስፈልጋሉ፡፡ አቶ ቢረጋ ልጃቸውን ዳሩ፡፡ ያውም የሚወዷትን ሴት ልጃቸውን፡፡ የመልሱ ለታ ማስጠንቀቂያ ሰጡ፡፡ ‹እኔን ድፍን የመርካቶ ሰው ያውቀኛል፡፡ በሰዓት ቀልድ አላውቅም፡፡ ልክ በሰዓቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረሱ› አሉና ዐወጁ፡፡ ልጃቸው ቀርቶ እኛ በልጃቸው በኩል የምናውቃቸው ሰዎች እንኳን ‹ሰዓትና አቶ ቢረጋ ምንና ምን ናቸው? የጆሮ ጉትቻ የአንገት ሐብል ናቸው› እንላለን፡፡
ምን ያደርጋል ታድያ፡፡ ወንዶቹ ለመልሱ በግ ሊገዙ፣ ሴቶቹ ፀጉራቸውን ሊፈሸኑ ሄዱ ተባለና የአቶ ቢረጋ ሰዓት የሙሽሮቹ ቤት እያለን ደረሰ፡፡ ‹ኢትዮጵያውያን መንግሥተ ሰማያት የማይገቡት ጽድቅ ስለማይሠሩ ሳይሆን፤ አርፍደው ሲመጡ በሩ ተዘግቶ ስለሚጠብቃቸው ነው› ይባላል፡፡ ‹መጡ፣ እየደረሱ ነው፣ በቃ ጨርሰዋል፣ እንትና ቀርቶ ነው፣ እንትን እረስተን ነው፣ እነ እንትና ጠብቁኝ ብለዋል› ሲባል ሰዓቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሆነ፡፡ እኛም ሙሽሮቹን አጅበን ወደ ኮልፌ በረርን፡፡ የአቶ ቢረጋ ግቢ ግራ ቀኙ በመኪና ተሞልቷል፡፡ ሚዜ በግ እየጎተተ ቀሪው ሆ እያለ ስንገባ አቶ ቢረጋ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ሳይሆን ራሳቸው እሳት ሆነው ይጠብቁናል ብለን ፈርተን ነበር፡፡ እርሳቸው እቴ፤ ዘመኑ አስተማራቸው መሰል የባህል ልብሳቸውን ለብሰው በፈገግታ ነው የተቀበሉን፡፡
እኛም ሀገር ሰላም በመሆኑ ከጭንቅ ወደ ሳቅ ተሸጋግረን፣ ያረደ እንጂ ያረፈደ ሳንመስል ወደ ዳሱ ዘለቅን፡፡ የምግቡ ሽታ እየጋበዘን፣ የሰው ጫጫታ እየገፋን በራሳቸው በአቶ ቢረጋ አጋፋሪነት ወደ ቦታችን አመራን፡፡ ሙሽሮችም መድረኩን እኛም ወንበሩን ያዝን፡፡ ዘወር ብለን ስናይ ከፊሉ ሰርገኛ በልቶ መጠጡን ያስከነዳል፣ ከፊሉ ሊበላ ተሰልፏል፣ ከፊሉ ደግሞ አንሥቶ ወደ ወንበሩ ይመለሳል፡፡ ለእኛም የጠረጲዛችን ውኃና ለስላሳ ተከፈተልንና ባረፈደ ሆድ እናወራርደው ጀመር፡፡ ሃያ፣ ሠላሳ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ተነሡም፣ አንሡም የሚለን ጠፋ፡፡ ሰዓቱ ሲገፋ በአዳራሹ የሞላው ሰርገኛ ዓይኑ በእኛ ላይ ተተከለ፡፡ አሁን ነገር እንዳለ ገባን፡፡ ዓይኔን ስወረውር አንድ የማውቀው ሰው ሊቀ ምርፋቅ ሆኖ አየሁት፡፡
ጠጋ አልኩና ‹ሙሽሮቹ አያነሡም እንዴ፤ መሸኮ› አልኩት፡፡ ‹ሙሽሮቹንና አጃቢዎቹን የማስነሣው እኔ ነኝ ብለዋል አቶ ቢረጋ› አለኝ፡፡ ‹ቆልፈውናላ› አልኩና በልቤ ወደ ወንበሬ ተመለስኩ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ከማየት ያለፈ አማራጭ አልነበረም፡፡ በመሐል እንዲያውም አንዳንዱ ሰርገኛ እየመጣ ሙሽሮቹን መሰናበት ጀመረ፡፡ ‹ምግብ እያሸተቱ ምግብ እንደመከልከል ያለ ቅጣት የለም› ይል ነበር አጎቴ፡፡ አሁን ሰርገኛው በሙሉ አንሥቶ ገበታው ከሩቁ ወላቃ መስሎ መታየት ጀመረ፡፡ አቶ ቢረጋ ጭራቸውን እያወናጨፉ በመኳንንት ወግ መጡ፡፡ ከዚያም ወደ ሙሽሮቹ አመሩ፡፡ ሁላችንም በዓይን ተከተልናቸው፡፡ ሙሽሮቹን እየመሩ፣ ሚዜዎቹን እያስከተሉ ወደ ማዕዱ ሄዱ፡፡ እኛም በአጃቢ ሞድ ተከተልናቸው፡፡
የቪዲዮ ቀራጮቹና ፎቶ ግራፍ አንሺዎቹ ግራ ተጋብተዋል፡፡ ለቪዲዮ ብላችሁ አንዳንድ ነገር ጣል አድርጉበት ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡ ተራችን ደርሶ ገበታው ጋ ስንደርስ ያለቀ ጥብስ፣ የተፈረፈረ እንጀራ፣ የተሟጠጠ ወጥ፣ ‹ብቻዬን ከምቀር ውሰዱኝ› ብሎ የሚለምን ትራፊ ክትፎ፣ አጥንቱ ከሥጋው በላይ የገጠጠ ቁርጥ፣ በማንኪያ የሚሟጠጥ አዋዜ ቀርተዋል፡፡ አስተናጋጆቹም እፍታ እፍታውን እንደሚያቀርብ ሰው ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ እኔማ አንድ ቁራጭ ዳቦና አንድ ቁራጭ ሙዝ ነው የደረሰኝ፡፡ የአቶ ቢረጋ ወንድም ነገሩ አላስችል ቢላቸው ወደ ግድግዳ ወስደው ‹ምነው ቢረጋ፣ የሰው ሰርግ ለምን ታበላሻለህ› አላቿው፡፡ ‹ሰው የሚጋበዘው እንዳመጣጡ ነው› አሉና ትተዋቸው ሄዱ፡፡
እንዲህ እንደ አቶ ቢረጋ ቆርጦ የሚያርም ሰው ካልተገኘ ቀብር ከሰርግ በላይ የሚወደድበት ዘመን ሩቅ አይሆንም፡፡
No comments:
Post a Comment