ይኸው የወርሃ ሚያዝያ 2008ን የመጀምሪያ ሳምንት አገባደድን:: ግንቦት ተንደርድሮ እየመጣ ነው:: ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘበትን 25ኛ ዓመት ለማክበር ደፋ ቀና ማለት ጀምሯል:: ሩብ ምዕተ ዓመታትን በታላቁ ቤተመንግስት ማሳለፍ ቀላል አይደለም:: የአንድ ትውልድ ዕድሜ ነው:: እንኳን በተማሪዎች አብራክ ውስጥ ለተወለደ ድርጅት ይቅርና፣ በነባሮቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሚዛንም ረዥም የሥልጣን ዕድሜ ነው:: ሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ መቆይታቸውን እንደጀብድ ለሚቆጥሩት የኢሕአዴግ ነባር መሪዎች፣ የዘንድሮዋ ግንቦት 20 በተለየ ሁኔታ ጮቤ የሚረገጥባት ናት::
ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ትሩፋት ነው:: ንቅናቄው ከውልደት እስከ ህልፈቱ ከ1953 – 1966 – 13 ዓመታትን አስቆጥሯል:: ከ1966ቱ አብዮት በኋላ፣ የአባላቱ ብርቱ ሕልም ፍሬ አፍርቶ ወደ ተደራጀ የፖለቲካ ትግል ቢያድግም፣ በአንድ ጥላ ሥር ሊያስገባቸው የሚችል መሪ ድርጅት Vanguard Party የሚሉትን መፍጠር ባለመቻሉ ተማሪዎቹ ወደ ተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደጨው ተበትነዋል:: በትህምርት ቤት የነበራቸው መፈቃቀር፣ መተሳሰብ፣ በቅንነትና ተስፋ የውሃ ሽታ ሆኖ፣ ወደ መወነጃጀሉ ፣ ወደ መከፋፈሉ፣ ወደ መካካዱ፣ ወደ መቀኛነቱ፣ ወደ ክፋቱና ወደ መጠፋፋቱ ዓለም ጭው ብለው ገብተዋል::
ይህ ሂደት ብልጭ ድርግም እያሉ የኖሩ በርካታ የፖለቲካ ቃላትን አፍርቷል::: አብዮት፣ ኢምፔሪሊያዝም፣ ፊውዳሊዝም፣ ተራማጅ፣ አድሃሪ፣ በዝባዥ፣ ጨቋኝ ፣ ፋሺስት፣ አናርኪስት፣ ጠባብ፣ ትምክህት፣ አምባገነን፣ ዴሞክራሲ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ አክራሪ፣ ለዘብተኛ፣ ጽኑ፣ ወላዋይ፣ ሐቀኛ፣ አስመሳይ፣ ጀግና፣ ባንዳ፣ ታማኝ፣ ከሃዲ፣ ሃገር ወዳድ፣ ቅጥረኛ፣ ታጋይ፣ ነፍጠኛ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ሊብራል ዲሞክራሲ፣ ቦናፖርቲስት፣ ተንበርካኪ፣ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝቦች፣ ወዘተ::
እነዚህ ቃላት የሚጋሩን የአፍሪቃ ሃገራት ማግኘት በእጅጉ ይከብዳል:: ኢትዮጵያ እንደሃይማኖቶቿ፣ እንደ ምግቦቿ፣ እንደ አላብስቶቿ፣ እንደዜማዎቿ፣ እንደነሥነጽሁፏ፣ እንደ ስዕሎቿ፣ እንደ ታሪኳ፣ እንደ መሬት አቀማመጧ ሁሉ በፖለቲካውም ልዩ ናት::
እንዲህ ዓይነቱን የተለየ ማንነት አሜሪካውያን ኤክሴፕሽናሊዝም (exceptional-ism) ይሉታል:: በብዙ መመዘኛዎች አሜሪካ ኤክሴፕሽናል ናት ብለው ያምናሉ:: በዚህ እሳቤ እስከ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ድረስ ራሳቸውን ከዓለም ፖለቲካ አግልለው ኖረዋል:: በአውሮፓ እንግሊዞች፣ በኤሺያ ጃፓኖች፣ በመካከለኛው ምስራቅ ኢራኖች፣ ይህን ስሜት ይጋሩታል:: በላቲን አሜሪካ “ኤክሴፕሽናል ነኝ” የሚል ሃገር ስለመኖሩ አላውቅም:: ዓለም ላይ ካሉት 200 ሃገራት መካከል በዚህ ምድብ ሊካተቱ የሚሉት ከአስር ቢያንሱ እንጂ አይበልጡም:: ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ፣ ስብሰቡ የጥቂቶች ነው::
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም ከሃገሪቱ ታሪክ ባልተለየ መልኩ ልዩ የሚያደርጉት ገጽታዎች አሉት:: “ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነበር” ማለት ግን አይቻልም:: ይህን መንታ ባህሪ “በ66ቱ አብዮት ላይ ጥሩ መጽሐፍ ነው” የሚባለው የጆን ማርካኪስ (John Markakis) – አናቶሚ ኦፍ ኤ ትራዴሽናል ፖሊቲ ( Anatomy of a Traditional Polity) ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል::
ንቅናቄዎን ልዩ ከማያደርጉት ባህሪያቱ መካከል፣ በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሃገራትም የተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበረ መሆኑ አንዱ ነው:: በሌላ አነጋገር፣ የተማሪዎች ንቅናቄ የዘመኑ ፋሽን ነበር:: ጆን ማርካኪስ እንዲህ ያስቀምጡታል::
“Radical student agitation was a hallmark of the 1960s in all non-communist Countries Ethiopia Students, eager to imitate western models, naturally became engaged”
“በ1960ዎቹ ( እ.ኤ.አ) ኮሚኒስት ባልነበሩት ሃገራት የተጋጋለ የተማሪዎች ንቅናቄ የዘመኑ መለያ ነበር:: ይህ የምዕራባዊያንን ፈለግ ለመከከተል ጉጉት የነበራቸው የኢትዮጵያ ተማሪዎች የራሳቸውን ንቅናቄ አቀጣጥለዋል” (በcontext የተተረጎመ ነው::)
“Radical student agitation was a hallmark of the 1960s in all non-communist Countries Ethiopia Students, eager to imitate western models, naturally became engaged”
“በ1960ዎቹ ( እ.ኤ.አ) ኮሚኒስት ባልነበሩት ሃገራት የተጋጋለ የተማሪዎች ንቅናቄ የዘመኑ መለያ ነበር:: ይህ የምዕራባዊያንን ፈለግ ለመከከተል ጉጉት የነበራቸው የኢትዮጵያ ተማሪዎች የራሳቸውን ንቅናቄ አቀጣጥለዋል” (በcontext የተተረጎመ ነው::)
ልዩ ከሚያደርጉት መካከል ደግሞ ሦስት ባህሪያቱን ማንሳት ይቻላል:: በቀዳሚነት ተማሪዎቹ ለሥልጣንና ለሹመት የነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት ይገኛል:: ይህ ጥማት በምዕራዊያኑ ተማሪዎች ዘንድ አልነበረም:: ማርካኪስ እንዲህ ያስቀመጡታል:-
“The First Ethiopians who came back with degrees from abroad had become ministers and ambassadors. Students felt entitled to advance as rapidly. Law and Humanities courses were overflowing. Engineering and since were less appealing. Many students disdained and avoided teaching or other forms of social service in the province.”
“ከውጭ ሃገራት ድግሪ ይዘው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት የመጀመሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ሚኒስተሮችና አምባሳደሮች ሆነዋል:: (እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የነበሩት) ተማሪዎችም “በዚያው ፍጥነት የማደግ መብት አለን” የሚል ስሜት ነበራቸው:: (በተማሪዎቹ ዘንድ) ምህንድስናና ሳይንስ ብዙም ተፈላጊ አልነበሩም:: ወደ ክፍለሃገር ሄዶ ማስተማርም ሆነ ማህበራዊ አገልግሎት መስጠትን ይጠሉና ይሸሹ ነበር::”
በዚያ ዘመን የነበረው ቢሮክራሲ ግን፣ እንኳን ሚኒስትርና አምባሳደር ሊያደርጋቸው ቀርቶ ፣ የተመረቁትን ሁሉ ተቀብሎ ሥራ ለመስጠት እየተንገዳገደ ነበር:: የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ፣ “ከምረቃ በኋላ ሥራ እናጣለን” ብለው የሰጉ ተማሪዎች ንቁ ተሳትፎ ያደረጉበት ነበር:: ተማሪው ለሃገርና ለሕዝብ ብቻ ብሎ አልተነሳም::: ከኢትዮጵያ ሌላ ለየትኛውም ሃገር ንቅናቄ ይህን ማለት አይቻልም::
ማርካኪስ፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የነበረውን ነፃነት ለንቅናቄው መወለድና ማበብ እንደ አበይት ምክንያት ያስቀምጡታል:: ይህም የኢትዮጵያን ተማሪዎች ንቅናቄ ልዩ ከሚያደርጉት – በሦስተኛ ዓለም ከነበሩት – ገጽታዎቹ አንዱ ነበር::
ማርካኪስ እንዲህ ብለዋል:-
“With the university, the students succeeded in joining almost complete freedom of expression, and their publications launched quite uninhibited attacks on the regime although they refrain from attacking the person of the emperor”“ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሃሳብን በነጽሳነት የመግለጽን መብት ከሞላ ጎደል ሙሉ ለሙሉ ለማስከበር ችለዋል:: ሕትመቶቻቸውን የአጼውን ስብዕና ከማጥቃት ቢቆጠቡም መንግስትን ግን ያለምንም ፍርሃት ይተቹ ነበር” ((በcontext የተተረጎመ)
የተማሪዎቹን ቀልብ በዋናነት የሳበው ግን፣ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አልሆነም:: ወሳኝ የሆኑትን የሃገራቸውን ታሪክ፣ ፖለቲካና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አልሆነም:: ወሳኝ የሆኑትን የሃገራቸውን ታሪክ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምተው ማርክሲም ላይ አተኩረዋል:: ይህ ሲሆን መንግስት ጣልጋ አልገባባቸውም:: በዚህ ሳቢያ ማርክሲዝም በአደባባይ ከተሰበከባቸው ጥቂት የአፍሪካ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆን በቅታለች:: ይህ እውነታ የተማሪውን ንቅናቄ የአጼው መንግስት የአካዳሚ ነፃነት ውጤት ያደርገዋል:
በሦስተኝነት፣ የኢትዮጵያን ተማሪዎች ንቅናቄ ልዩ ከሚያደርጉት ባህሪያቱ መካከል የአባላቱ ድህነት ጉልህ ስፍራ ይሰጠዋል:: ይህ ክፍተት ንቅናቄው የግድ የውጭ ኃይሎች፣ ጥገኛ አድርጎታል:: የንቅናቄው አድማስ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጥቶ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲዛመት፣ ከተማሪዎች በሚሰብሰብ መዋጮ የተደራረበውን ወጪ የሚሸፈንበት ሁኔታ አልነበረም:: በዚህ ክፍተት፣ በዘመኑ ከነበሩት ሁለት ልዕለ ኃያላን መካከል አንዷ የነበረችው ማርክሲሥቷ ሶቭየት ኅብረት ተማሪዎቹን ስኳር ታልሳቸው እንደነበር ማርካኪስ ጽፈዋል::
“After Haile Selassie expelled several soviet and East European embassy officers in 1968 and 1969 for subversive contacts with students, Moscow refined its techniques. It was less risky to work with Ethiopian students abroad. Hence forth, money, propaganda and advice for student’s agitation in Ethiopia came in large part through Marxist- dominated Ethiopia student organizations in Europe and America. Under the guise of supporting literacy campaigns and welfare projects, these organizations sent far larger sums of money than they would conceivably have collected on their won to their counter parts in Addis Ababa’“እ.ኤ.አ በ1968 እና በ1964 የሶቭየትና የምሥራቅ አውሮፓ ዲፕሎማቶች ‘ከተማሪዎች ጋር ሕገ-ወጥ ግንኙነት አድርጋችኋል’ ተብለው ከተባረሩ በኋላ፣ ሞስኮ ስልቷን ቀየረች:: ውጭ ካሉት ተማሪዎች ጋር መሥራቱ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ተገኘ:: ከዚህ በኋላ ሃገር ውስጥ ለነበረው የተማሪዎች ንቅናቄኤ የሚሰጠው የገንዘብ፣ የፕሮፓጋንዳና የምክር ድጋፍ፣ ማርክሲስቶች በሚመሯቸውና በአውሮፓና በአሜሪካ በነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበራት በኩል እንዲላክ ተደረገ:: እነዚህ ማህበራት ለመሰረተ ትምህርትና ለማህበራዊ ዋስትና ድጋፍ እንሰጣለን’ በሚል ሽፋን ከአባላቶቻቸው ሊያሰባስቡት ከሚችሉት በላይ ገንዘብ ወደ አዲስ አበባ ልከዋል::”
ይህ ሁሉ በጥቂት ተማሪዎች ፈቃድ የተፈጸመ ሲሆን በእኔ ግምት በክሮኮዳይሎች crocodiles ብዙሃኑ ተማሪዎች እስከአሁን ድረስ ምን እንደተደረገ አያውቁም:: ይህ መረጃ ጨለማ፣ በብዙሃኑ ተማሪ በጭፍን ይከተላቸው የነበሩትን የንቅናቄው መሪዎች፣ ማርክሲዝምን የተቀበሉት ለገንዘብ ብለው ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳስነሳ ያስገድደኛል:: የተማሪው ንቅናቄ ከከሰመ በኋላ እንደታየው፣ በመሪዎቹም ሆነ በብዙሃኑ ተማሪ ዘንድ፣ ማርክሲዝም ቅብ ነበር እንጂ ውስጣቸው ሰርጾ የገባ እምነት አልነበረም::
ፈረንጆች “…with the benefit of hindsight…” የሚሉት ነገር አላቸው:: “ግዜው ካለፈ በኋላ በአንክሮ ሲታይ” እንደማለት ነው:: የተማሪው ንቅናቄ በዚህ ዓይነቱ መነጽር ሲቃኝ የውጭ ኃይሎች መሣሪያ መሆኑ ብዙም አያስደንቅም:: የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የታሪክም ደሃ ነበርና:: ጥራዝ ነጠቅ ማርክሲዝምን በተላበሰው ንቅናቄ ዘንድ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ኃይማኖት የመሳሰሉ ነገሮች በመደብ የተከፋፈለ ማህበረሰብ ኋላቀር ቅሪቶች ናቸው ተብለው በመፈረጃቸው በንቀት የሚታዩ ነበሩ:: ለኢትዮጵያ የተለየ ታሪክና ማንነት ቦታ አልነበረውም::
በዚህ ሳቢያ፣ ስለ1984ቱ “ፓሪስ ኮሚውን” (የፓሪስ አመጽ) መወያየትና መከራከር ይወዱ የነበሩት የተማሪው ንቅናቄ አባላት – ልክ የዛሬ ዘመን ወጣቶች ስለ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በአንክሮ እንደሚከራከሩት – እንኳን የጥንቱን የኢትዮጵያ ታሪክ ይቅርና፣ በፓሪስ ኮሚውን የቅርብ ርቀት (እ.ኤ.አ በ1860ዎቹ) የእንግሊዝ ጦር በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመው ወረራና ስላስከተለው እንደምታ ምንም እውቀት ሳይቀራምቱና ሳይመጋገቡ ቀርተዋል::
ተማሪዎች በዚህ መልክ እስከ 1966 ድረስ ከቀጠሉ በኋላ፣ በአብዮቱ ፍንዳታ ማግስት ያቋቋሟቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ወስደዋቸዋል:: ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ያቋቋሙትም ማክርሲዝም ላይ ተቸክለው በመቅረታቸው መንግስታዊ ጭቆናን እስከመጨረሻው ድረስ መቋቋም የሚችሉ አባላትን ማፍራት ሳይችሉ ቀርተዋል:: እነ ኢሕ አፓና መኢሶን በደርግ ጭፍጨፋና አፈና ብቻ አልጠፉም:: በማርክሲዝም ብቻ የታነጹት አባሎቻቸው፣ በድንጋያማ መሬት ላይ እንደወደቀ ዛፍ፣ ጸሃይ ሲበረታባቸው – በመከራ ጊዜ – በቀላሉ ደርቀዋል:: በአንጻሩ፣ የብሄር ድርጅቶች ያቋቋሙት ተማሪዎች – የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ ወዘተ – ሃገራዊውን ታሪክ ከማርክሲዝም ያልተናነሰ ቦታ በመስጠታቸው፣ ብርቱ መከራን መቋቋም የሚችሉ አባላትን አፍርተው – በተለይ የኤርትራና የትግራዮቹ – ደርግን ለመጣል በቅተዋል:: የሕብረብሄራዊ ድርጅቶች ማርክሲስቶች እንደተመኙት፣ ታሪክን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ነቅሎ ማውጣት አልተቻለም::
ተማሪዎቹ እንቅስቃሴያቸውን ከጀመሩ 55 ዓመታት በኋላም ከ1953 – 2003 የዮሐንስና የምኒልክ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ የፈጠረው ሽኩቻ፣ የኢሕአዴግ ቅኝት ጸረ-ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት ግብአቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይገኛል:: የታሪክ ጣጣ የኦሮሞና የተማሪ ብሄረተኞችን ነፍስ እረፍት እንደነሳ ነው:: የታሪክን ህጸጾች የማይቀበሉ ቀላል የማይባል የፖለቲካ ኃይልም አለ:: ይህ ሁሉ ተደማምሮ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው:: መፍትሄው ከአዲሱ ዘመን ዴሞክራቶች ይጠበቃል::
እስክንድር ነጋ፣
የሕሊና እስረኛ፣
ቃሊቲ::
የሕሊና እስረኛ፣
ቃሊቲ::
No comments:
Post a Comment