Thursday, April 14, 2016

በኢትዮጵያ የኦሮሚያና በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ብሎምበርግ ዘግቧል፡


ኢንተርኔትን በመጠቀም የጽሁፍና የድምጽ መልእክቶች የምናስተላልፍባቸው አፕሊኬሽኖችን ጨምሮ ፌስ ቡክና ትዊተር በኢትዮጵያ የኦሮሚያና በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ብሎምበርግ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች በመጥስ ዘግቧል፡፡
የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች በስልካቸው የጫኗቸውን አፕሊኬሽኖች በመጠቀም አገልግሎቶቹን ማግኘት አለመቻላቸውን በመጥቀስ የቴሌ ኮም አገልግሎት ለአገሪቱ በመስጠት ላይ የሚገኘውን መንግስታዊ ተቋም ይከሳሉ፡፡በወሊሶ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነው ስዩም ተሾመ በስልክ ለብሉምበርግ ሪፖርተር እንደነገረው ከሆነም የፌስ ቡክ መልእክት መላኪያ ሚሴንጀር፣ትዊተርና ዋትሳፕ ከአዲስ አበባ በ115 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወሊሶ ከተቋረጡ ወራትን አስቆጥረዋል፡፡
ስዩም‹‹ሁሉም መስራት ካቋረጡ ከአንድ ወር ላይ ተቆጥሯል››ብሏል፡፡ አገልግሎቶቹን ማቋረጡ በዋናነት የሞባይል ዳታዎችን እንዳይሰሩ ከማድረግ ጋር የተያያዘ መሆኑንም መምህሩ ጠቅሷል፡፡
ስለሁኔታው በኢ ሜይል የማብራሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው የትዊተር ካምፓኒ ቃል አቀባይና ዋትሳፕን በ2006 የገዛው የፌስ ቡክ ካምፓኒ ምላሽ አለመስጠታቸውን ብሎምበርግ አስነብቧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ይፈጽሟቸው የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማህበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት ሲሰራጩ በመቆየታቸውም የአገልግሎቶቹን መታፈን መረጃዎችን ከመቆጣጠር አንጻር እንደሚሆን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
አገልግሎቶቹን ማፈን የመንግስት ፖሊሲ አለመሆኑን የሚናገሩት የመንግስት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ ‹‹እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ማብራሪያ አላገኘንም፡፡ሁኔታው የተከሰተው ከኮኔክሽን ችግር ነው››ብለዋል፡፡
በቅርቡ ሪፖርተር የቴሌ ኮሙን አስተዳዳሪ አንዷለም አድማሴን በመጥቀስ ባስነበበው ዜና ቴሌ የስማርት ስልኮችን አፕሊኬሽኖች የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂ መጠቀም ለመጀመር መዘጋጀቱን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ክልል በምተገኘው ሐዋሳ ከተማም አፕሊኬሽኖች ባለመስራታቸው በአካባቢው ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን በምስራቅ ለንደን በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚክስ በማስተማር ላይ የሚገኙት ስዩም ሃሜሶ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ ብሉምበርግ

No comments:

Post a Comment