Thursday, April 14, 2016

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለከፍተኛ የዉኃ እጥረት ተዳርገዋል – ዶይቸ ቬለ


የአፍሪቃ ኅብረት ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ በርካታ ዲፕሎማቶችን የምታስተናግድ ብትሆንም የመብራት ኃይልን ጨምሮ የዉኃ አቅርቦት እጥረት ችግር ላይ መዉደቅዋን አስመልክቶ የተለያዩ ዘገባዎች እየወጡ ነዉ።
የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ በቅርቡ ለዉኃ እጥረት የመዳረጋቸዉ መንስኤ ምንድነዉ ብለን አዲስ አበባ የዉኃና ፈሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ፊቃዱ ዘለቀን አናግረን ነበር። ይሄ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ቦታ ሳይሆን በተወሰነ አከባቢ የዉኃ እጥረት እንዳለ አቶ ፊቃዱ አክለዉ ገልፀዋል። አቶ ፊቃዱ ማብራርያ የዉኃ እጥረቱ የተከሰተባቸዉ አከባቢዎች ሃያት፣ CMC፣ ገርጅ፣ መገናኛ፣ 22፣ ቂርቆስ፣ ለገሃር እና በከፊል ቦሌ አከባቢ መሆናቸውን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።
የዉኃ እጥረቱ መከሰት ከጀመረ ሰንብቷል ያሉን የቦሌ አከባቢ ነዋሪ አቶ ሰፊነዉ አድነዉ ዉኃዉን በፈረቃ በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አካል ጋ ቀርቦ የችግሩን መንስኤ መጠየቅ ወደ ሌላ ጉዳይ እንደሚያመራ ነዉ የገለፁት።
ኅብረተሰቡ የዉኃ አጠቃቀም ችግር እንዳለበት፣ የዉኃ አጠቃቀምን እንደቀልድ ያዩ እንደነበር አቶ ሰፊነዉ ሳይጠቅሱ አላለፉም። በየአካባቢው እየተዘዋወሩ ቁጥጥር የሚያደርጉ የዉኃ ባለሥልጣን መሥርያ ቤት ባለሙያዎች ይሄን ያህል ገንዘብ ክፈል ከማለት ባለፈ ስለ ዉኃ አጠቃቀም የሰጡት ሥልጠና አነስተኛ ነዉ ሲሉም አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል። ይህን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ የዉኃና ፈሳሽ ባለሥልጣን ምን እያደረገ ነዉ ብለን አቶ ፍቃዱን ጠይቀናቸዉ ነበር።
ይሄን ጉዳይ በተመለከተ በዶቼ ቬሌ የፌስቡክ ደረ-ገፅ ላይ ዉይይት አከሂደን ነበር። አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጭዎች ባለስልጣን መሥርያ ቤቱ የዉኃ አገልግሎቶትን ለማድረስ የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ ኋላ ቀር ስለሆነ ቴክኖሎጂዉን ማሻሻል አለበት ሲሉ አስተያየታቸዉን አጋርተዉናል። ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች የመልካም አስተዳደር ጉድልት ሙስናና ፈጣን አገልግሎት መስጠት ያለመቻል ዋናዉ ችግር ነዉ ሲሉ አስተያየተቸዉን አስፍረዋል።

No comments:

Post a Comment