የዞኑ መስተዳድር በዞኑ ነዋሪዎች የተቋቋመ ‹ነጻ› በሚባል የልማት ማህበርጋር የገንዘብ ማሰባሰቢያ ባዛር ለማዘጋጀት ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ መሆኑን፣ ለዚሁ ባዛር መምህራንን ለማሳመን በየትምህርት ቤቱ ….. በመሰብሰብ ያወያየ ሲሆን ከመምህራን የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸውንና ለዚህም በቂ መልስ መስጠት ባለመቻሉ ለሌላ ጊዜ ሰፊ ውይይት ለማድረግ በመወሰን ስብሰባዎቹ ማብቃታቸውን መምህራን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ት/ቤቶች በተደረጉ ስብሰባዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች የተነሱ መሆኑን እነዚህም፡-
1ኛ/ ከዚህ በፊት በተደረገው ባዛር የተሰበሰበው ገንዘብ አጠቃቀምና በገንዘቡ ለመስራት የተነደፉ ፕሮጀክቶች ክንውን /አፈጻጸም ሪፖርት ሳይቀርብ ስለሌላ ባዛር ማቀድ አግባብ ነውን ?
2ኛ/ ሌላ ዕቅድ ከማሰባችን በፊት ከዚህ በፊት በህዝብ ሃብት የተገዙ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች / ዶዘርና ግሬደር፣ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ/ ያለአገልግሎት የቆሙት ለምን እንደሆን በግልጽ ይታወቅ፤
3ኛ/ ከዚህ በፊት በህዝብ ገንዘብ የተገነባው ስታዲዬም ከፍተኛ ገንዘብ ወጣበት ተብሎ በተነገረ በወራት ውስጥ መደርመሱ/መፍረሱ ይታወቃል፤ ይህ ሁኔታ እንዲጣራ ጥያቄ ቢቀርብም መልስ ባልተሰጠበት እንደምን ሌላ ባዛር ማዘጋጀት ታሰበ ?
4ኛ/ በተመሳሳይ በዕቅድ ተጀምሮ የተቋረጠው የጂንካ ቤቶ-ሜላ መንገድ የተቋረጠበት ምክንያት አሳማኝና ግልጽ ምክንያት ባልቀረበበት በባዛር ስም ከህዝብ ለምን ገንዘብ መሰብሰብ ተፈለገ ?
አንድ መምህር እውነት ዛሬ ላይ ለጂንካ ከተማ የምግብ እህል ነው ወይስ የሽንት ቤት መምጠጫ መኪና– ለመሆኑ ምን ተበልቶ ? የሚል ጥያቄ አንስተው በተሰብሳቢው ከፍተኛ ጭብጨባ ተችሮኣቸዋል፡፡ በመጨረሻም እነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ ባልሆኑበት አሁንስ የሚሰበሰበው ገንዘብ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በማይነሱበት ሁኔታ በሥራ ላይ ይውላል ብሎ ማመን ይቻላል፣ ‹ነጻ› የሚባለው የልማት ማኅበር በገንዘቡ አጠቃቀም ላይ ያለው የመቆጣጠር አቅምና ተጠያቂነትስ ምን ያህል ነው ? የሚሉት ናቸው፡፡
መምህራኑ ‹‹ ማናችንም የዞናችንን ልማት እንፈልጋለን፣ ከፍላጎት ባለፈም በአቅማችን መሳተፍና አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብን እንረዳለን፤ ግን በልማት ስም ገንዘብ እየተሰበሰበ ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የሙስና ደላላና ተጠቃሚ ግለሰቦችና ባለሥልጣናት ኪስ ማደለቢያ ሊውል አንፈቅድም ›› ካሉ በኋላ በሚል አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡ ይህንኑ ባዛር በሚመለከት አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኦህዲኅ የዞን ጽ /ቤት ምክትል ተጠሪ መምህር እንዲሪስ መናን በሰጡት አስተያየት ‹‹ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እርሳቸው በሚያስተምሩበት ት/ቤትም በተደረገ ስብሰባ ላይ መነሳታቸውን አረጋግጠው፣ እንደ ህዝብና የዞኑ ነዋሪ ልማቱን የሚደግፍ ነኝ፣ በመምህራን የተነሱት ጥያቄዎች በቂና አሳማኝ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው አምናለሁ፣›› ከዚህ ባለፈ እንደ ፖለቲከኛ ‹‹ ይህ የአካባቢ ልማት ጉዳይ በቅርብ ጊዜ በዞናችን በኢንቨስትመንት ስም በህወኃት አባላትና ደጋፊዎች የተፈጸመው የመሬት ቅርምት ከተጋለጠና የህዝብ ውይይት አጀንዳ ከሆነ በኋላ እንዴት መጣ (ለሽፋን የታሰበ ፖሮፖጋንዳ ይሆን) ? .በዚህ ጉዳይ የታሰሩ የእነ ዓለማዬሁ/ የድርጅታችን አባላትና የከተማው ነዋሪ / ጉዳይስ በዚህ ወቅት በዝምታ የሚታለፍ ነውን ? …. ከዚህ የልማት ኃሳብና ዕቅድ በፊት በዞናችን የሚታዩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎች / የዜጎች መፈናቀል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሻከር – የቦዲና የኮንሶ ግጭት /፣ የሃመር ወጣቶች ያነሱትን የፍትህ ጥያቄ ተከትሎ ከመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተገባው ቅራኔ ያስከተለው የህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል፣ የንብረት ውድመት፣የወጣቶች ከቀዬኣቸው መሰደድ፣….በአጠቃላይ ከዞኑ ነዋሪዎች የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው ፣ የህዝብ ብሶት ያሰሙ መሪያችን፣ አባልና የከተማው ነዋሪ በሃሰት ውንጀላ ከቤተሰብና ከዞናቸው ህዝብ ተነጥለው በእስር እየማቀቁ ባሉበት ይህን ለምን ? ብለው ሳይጠይቁ ‹ነጻ› ነን በሚል ስለልማት ቢሰብኩ በህዝብ ተቀባይነት ማግኘት አይታሰብም፡፡‹‹ እኛ ተስማማንም አልተስማማን ባዛሩ እንደሚደረግ እናውቃለን ፣ ልማታዊ አርቲስቶች- ሠራዊትና ሙሉዓለም ለመድረክ መሪነት ተመርጠዋል፣ ባለቀለት ጉዳይ ቢያወያዩንም ማድረግ የምንችለው ይሁንታችንና ገንዛባችንን ያለመስጠት ብቻ ነውና በቀጣይ ይደረጋል በተባለው ውይይት ይዘው የሚመጡትን መልስ ከሰማን በኋላ ለህዝባችን ማድረግ ስላለበት አቅጣጫ እናስቀምጣለን ›› በማለት ኃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ የኦህዲኅ ሊቀመንበር በሰጡት አስተያየት ደግሞ ስለባዛሩ የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊ በሰጡት አስተያየት ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙ ገልጸው ይህ ‹ነጻ› የተባለው የልማት ማኅበር በውጪ የሚገኙ የዞኑን ተወላጆች ለባዛሩ ድጋፋቸውን እንዲገልጹና እንዲሳተፉ ጥረት ማድረጋቸውንና እንዳልተሳካላቸው፤ አብዛኞቹ ከህዝብ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ስለማቅረባቸው ተጨባጭ መረጃ እንዳላቸው ገልጸው ፣ እርሳቸውም ‹‹ እንኳን የህዝብ ውክልና ይዘን የምንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ማንኛውም ጤናማ ሰው ልማት አይቃወምም፣ይፈልጋል- ትግላችንም ይህንኑ ያካተተ ነው፤ ግን እንዳየነው ብዙ ከበሮ ተደልቆለት ከወራት በላይ ዕድሜ ከሌለው ድንጋይ ድርዳሮና ሌላ ሌላው በፊት የዜጎች መብትና የሰው ሃብት ልማቱ፣ የባለሥልጣናት ተጠያቂነት መቅደም አለበት፣ ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች መመለስ፤ ሙስናው መገደብ…. አለበት፣ ስለቀጣዩ ብዙ ከማለታችን በፊት ካለፈው ምን ተምረናል ለሚለው ግልጽና በቂ መልስ ማግኘት፣ ፍላጎታችንና የልማት ጥያቄዎቻችን በአግባቡ ቅደም ተከተል ሊቀመጥላቸው ይገባል›› ብለው እንደሚያምኑና እነዚህ በሆኑበትና በተሟሉበት ‹‹ ህዝብ በአንድ ልብ፣በአጭር ጊዜ ተዓምር የመስራት አቅም እንዳለው በጽኑ አምናለሁ›› በማለት ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment