Friday, April 15, 2016

በካድሬዎች ስር የወደቀችው ቤተ ክርስትያን (አምዶም ገብረስላሴ

 


ARENA candidate Mekonen Asfawኣቶ መኮነን ኣስፋው በምርጫ 2007 ዓ/ም በተካሄደው ምርጫ ዓረና-መድረክን ወክለው በኣላማጣ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ተወዳድረው ህወሓትን ኣምበርክከዋል ዳሩ ድምፃቸው ተዘረፉ እንጂ።
ኣቶ መኮንን በ1974 ዓም ወደ በረሃ ወጥቶ ያታገሉ ሲሆኑ ከነ ሓየሎም ኣርኣያና ገብሩ ኣስራት ጎን ተሰልፈው ደርግ በመደምሰስ ታላቅ ድርሻ የተጫወቱ የህዝብ ልጅ ናቸው።
ኣቶ መኮነን በህወሓት ካድሬዎች ከግድያ ዛቻ ጀምሮ እስከ የሃይማኖት ኣባቶችና የኣገር ሽማግሌዎች ሽምግልና የሚደርሱ ተፅእኖዎች ሲደርስባቸው ነበር።
ኣቶ መኮነን ኣስፋው ግን ሁሉንም ዓይነት የዓፈና መንገዶች ተቋቁመው በዓረና_መድረክ ስር ሆነው እየታገሉ መጥተዋል።
በመጋቢት ወር ያጋጠማቸው ገጠመኝ ግን ለራሳቸውም እጅግ ያስደነገጠና ያስገረማቸው ነበር። ገጠመኙ የማርያም ባላ ኣስተዳዳሪ ቄስ ኣፅበሃ ኣሰፋ ያሳወቋቸው ጉዳይ ነው።
ቄስ ኣፅበሃ ኣሰፋ ለታላቅ ጉዳይ እፈልገሃለው ብለው ቀጠሮ ያዙላቸው።
በቀጠረው መሰረት ሲገናኙ የሰሙት ንግግር ግን በፍፁም ለማመን ኣልቻሉም።
ቄስ ኣፅበሃ “… ኣንተ ኣሁን እየሰራኸው ያለው ስራ ሰው፣ መንግስትና ቤተ ክርስትያን የማይቀበሉት ተግባር ነው። ከዚህ በፊትም የክርስትናና የሙስሊም ሃይማኖት መሪዎችና ያገር ሽማግሌዎች ምክርና ተግሳፅ ኣልሰማ ብለሃል። ይሄ ዓረና የሚል የጠላት ኣላማ ይዘህ በቤተ ክርስትያናችን መቆየት ኣትችልም። ከዓረና የማትወጣ ከሆነ፣ ብትወልድ ኣናስጠምቅህም፣ ብትሞት ኣናስፈታህም፣ በቤተ ክርስትያናችንም ኣናስቀብርህም፣ ከቤተ ክርስትያንም እንደወጣህ ይቆጠራል።…” በማለት ከዓረና ኣባልነቱ ካልወጣ ክርስትያናዊ መብቱን እንደሚነጥቁት ተነግሯቸዋል።
“……ኣንተ የቤተ ክርስትያን ኣገልጋይ ነህ። ማገልገል ያለብህ ለቤተክርስትያን ብቻ መሆን ነበረበት። ኣሁን ያንተ ተግባር ግን የህወሓት ካድሬ እንጂ የቤተ ክርስትያን ኣገልጋይ እንዳልሆንክ ያመላክታል። እኔ እማውቀው ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆናቸው ነበር።
ቤተ ክርስትያንዋ በህወሓት ካድሬዎች የምትመራ ከሆነች ግን ከስርዋ ኣይደለሁምና እናንተም ሙቼ መቃብር ከልክሉኝ እኔም የምሰራውን ራሴ እወስናለው……” በማለት ራሳቸው ዓፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ሂደው ወደ እስልምና ሃይማኖት ተከታይነት መቀየራቸው በይፋ ኣሳውቀዋል።
የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በከፍተኛ ደረጃ የህወሓት ተፅእኖ ስር ወድቃ ትገኛለች።
በየ ደብሩ የሚገኙ የህወሓት ቄስ ካድሬዎች በዓረና ኣባላት ላይ ከዓረና ኣባልነታቸው እንዲወጡ የግዝት፣ለልጆቻቸው የጥምቀት ክልከላ፣ የኣባት ንስሃ ክልከላና ከሞቱ በኋላ የፍትሃትና የቀብር ስርዓት እንደማይፈፀምላቸው ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተፅእኖ በማድረስ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ተፅእኖ ጥልቅ የሃይማኖት ተከታይ የሆነው የትግራይ ህዝብ ላይ የፖለቲካዊ ተፅእኖ ስር እንዲወድቅና ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ የሚያስገድድ ነው።
ቤተ ክርስትያንዋ ከህወሃት ቀጥተኛ ተፅእኖ ካልወጣች ኣማኝዋ እያስከፋችና ሞራሉ እያዳከመች ከሄደች ህልውናዋ ላይ ኣደጋ ማስከተሉ ኣይቀረውም።
የትግራይ የገጠር ኣብያተ ክርስትያን የህወሓት የስብሰባ ማካሄጃ ሁነዋል፣ ቄሶች በኣንድ ለ ኣምስት ተደራጅተው የህወሓት የፕሮፓጋንዳ መሳርያ ሁነዋል፣ የተቃዋሚ ድርጅት ዓረና ኣባላት ጥምቀት መከልከል፣ ኣባት ንስሃ መቋረጥ፣ መገዘት፣ ኣንቀብርም ማለት፣ የቤተ ክርስትያንዋ መሪዎች በታጋዮች ቁጥጥር መውደቅ ወዘተ የሚጠቀሱ ጥሰቶች ይፈፀማሉ።
ቤተ ክርስትያንዋ ነፃነትዋ በህወሓት ካድሬዎች እየተረገጠ፣ ኣማኞች ሳይወዱ በግድ እንዲርቋት እየተደረገ፣ ህወሓት እንደ የፖለቲካ መሳርያ እየተጠቀመችባት እስከ መቼ ነው? እንደ ተቋም ለምእመናን ኣገልግሎት ታላቅ ትኩረት መስጠት ኣላባት።
ሃይማኖት ከፖለቲካ፤ ፖለቲካ ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንደሚለዩ የሚሰብከው ህገ መንግስትስ የት ገባ?
የሃይማኖት ነፃነት ይከበር…!
ነፃነታችን በእጃችን ነው።

No comments:

Post a Comment