Sunday, April 3, 2016

የፍኖተ ዲሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች

መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም.ዜና (April 01, 2016 NEWS)
#በደብረ ዘይት ከተማ የፈነዳው ቦምብ አንድ ሕጻን ሲገድል ሌሎች አራት ሰዎች አቆሰለ
#የወያኔው አሸከር ብአዴን በወልቃይት የሃይማኖት አባቶች ውግዘት እንዲያደርጉ ስብሰባ ጠራ
#መሀመድ አላሙዲ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር እንዲከፍል ተወሰነበት
#በህንድ ካልከታ ከተማ ከመንገድ በላይ የተሰራ ድልድይ ፈርሶ ጉዳት አደረሰ
#የሊቢያ የአንድነት መንግስት ስልጣን ከያዘ የተያዘው የሊቢያ ገንዘብ እንደሚለቀቀ ተመድ ገለጸ
#ተመድ በብሩንዲ የፖሊስ ኃይል ለመላክ ይወስናል ተባለ
#የጂቡቲው ገለህ በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው የይስሙላ ምርጫ ያሸንፋሉ ተባለ



Ø መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ያደረገው ላንሴት የህክምና ጆርናል የዘንድሮውን የሰውነት ክብደትና ይዘት መለኪያ (Body Mass Index) ይፋ አድርጓል። ሰንጠረዡ እንደሚያሳየው የዓለም ሕዝብ ውፍረት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል። በ1967 በተደረገው ተመሳሳይ ጥናት 105 ሚሊዮን ሕዝብ ወፍራም ተብሎ እንደተፈረጀና ባለፈው ዓመት የተጠናቀቀው ና በ200 አገሮች በተካሄደው ጥናት 647 ሚሊዮን ሕዝብ ወፍራም መሆናቸው አስደንጋጭ ነው ተብሏል። ወፍራም የተባሉት አብዛኞቹ የሚገኙት በበለፀጉና ሀብታም በተባሉ አገሮች ውስጥ ሲሆን አሜሪካ ወፍራሞችን በብዛት በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን ስታሳይ ጃፓን ደግሞ የበለጸገችና ሀብታም ሆና የወፍራሞችን ቁጥር አነስተኛ ቁጥር አነስተኛ የሆኑባት አገር ሆናለች። ከአሜሪካ ቀጥሎ አውስትራሊያ፣ ካናዳ ፣አየር ላንድ፣ኒውዚላንድና ብሪታኒያ ወፍራሞችን በብዛት እንደቅድመ ተከተላቸው ያስመዘገቡ ሲሆን በቀጫጫነት ደግሞ ምስራቅ ቲሞር ኢትዮጵያና የሻዕቢያዋ ኤርትራ አነስተኛ ቁጥር ያለው ወፍራሞችን አስመዝግበዋል፡፤ የሕክምና ባለሙያዎች ወፍራምነትን ተከትለው የሚመጡ በርካታ የጤና ችግሮች መኖራቸውን በመግለጽ ተመጣጣኝ የሰውነት አቋም  ከክብደትና ከቁመት ጋር እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አነስተኛ ክብደት መኖርም ለጤንነት አስጊ መሆኑን ይገልጻሉ። የሰውነት ክብደት የሚያሰጋቸው ሰዎች ከመጡበት አካባቢና ከኑሮ ደረጃቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል።

Ø የወያኔ ቡድን ጠፍጥፎ የሠራው ብአዴን የተባለው ቡድን እወክለዋለሁ በሚለው የአማራ ሕዝብ ላይ በየወቅቱና በየጊዜው አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆየቱ ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ የወልቃይት ሕዝብ ለማንነቱና ለመብቱ ያነሳውን ጥያቄ በግድያ በአፈናና በእስር ምላሽ እየሰጠ ባለበት ሰዓት በሁመራ የሃይማኖት አባቶች የተባሉት የወልቃይትን ነዋሪ ሃሳብ እንዲቃወሙ ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል። የሃይማኖት አባት የተባሉት ስብሰባ የተጠሩት የወልቃይት ሕዝብን እንዲያወግዙ መሆኑ ተገልጿል። የወያኔው ተላላኪ ብአዴን ለወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ የወያኔን ነፍሰ ገዳይ ጦር አግአዚ በመጥራት የጥይት ምላሽ ሲሰጥ የውግዘትና የተቃውሞ ድምጻቸውን ያላሰሙት የሃይማኖት አባት የተባሉት ዛሬ ከወያኔ ጋር በመሆን ለውግዘት መሰልፋቸው የሃይማኖት አባት የሀገር ሽማግሌ ሳይሆኑ ተራ ተላላኪ መሆናቸውን አሳይተዋል። የጎንደር ነዋሪዎች የሃይማኖት አባቶቹ ከወያኔ ጎን በመቆም ይህን ዓይነት ወራዳና ሕዝብ የሚጎዳ ተግባር መፈጸማቸው ከሃይማኖት አባት የማይጠበቅ የተራ ቀበሌ ካድሬ ስራ ነው በማለት ለመብትና ለማንነት የሚደርገው ትግል ይቀጥላል ይላሉ።

Ø የወያኔው የንግድ ሸሪክ የሆነው መሀመድ አላሙዲን ቤት ከዓመታት በፊት ግዥ የፈጸመባቸውን የንግድና የእርሻ ድርጅቶች ክፍያን በወቅቱ ባለመፈጸሙ ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር እንዲከፍል በወያኔው ፍርድ ተፈርዶበታል። ወያኔ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት የነበሩትን ጎጀብ  እርሻ ልማትን፤ አዲስ ጎማን የሊሙና የበበቃ የቡና እርሻን ለመሀመድ አላሙዲ ሜድሮክ ኩባንያ መሸጡ ይታወሳል። መሀመድ አላሙዲ የልማት እርሻዎቹን ሆርዘን ፕላንቴሽን በማለት ስያሜ ሰጥቶ ክፍያ ግን ባለመፈጸሙ ጊዜ ቢሰጠውም በገንዘብ ቀውስ ሊከፍል አለመቻሉ ታውቋል። የወያኔው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ችሎት ጉዳዩን ለወራት መርምሮ የልማት እርሻዎቹ ባለንብረት መሀመድ አላሙዲን ድርጅቶቹ ያላቸውን አጠቃላይ ዕዳ 433 ሚሊዮን 571 ሺህ 241 ብር በጊዜ ገደብ እንዲከፍል ካልከፈለ ከነወለዱ እንዲከፍል ወስኗል። የፖሊካ ተመልካቾች የወያኔ የፖለቲካ ፍርድ ቤት በወያኔ የንግድ ሸሪካ ላይ ይህን ውሳኔ የጣለው በቱጃሩና በውያኔ መካከል ያለው ፍቅር አልቆ ነው ወይስ ስግብግብና አልለጠግብ ባይ የሆኑት የወያኔ መሪዎች ውትሮችም በዘዴና በስልት የሰጡትን የሀገርና የሕዝብ ንብረት በህግና በፍርድ ቤት ስም ሊቀበሉት በማሰብ ነው በማለት ይጠይቃሉ።


Ø በህንድ አገር ካልከታ ከተማ ውስጥ ከመንገድ በላይ የተሰራ አንድ ድልድይ በመደርመሱ ከ 24 ሰዎች በላይ ሞተው በርካታ የቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል። ከተደመረሰው ድልድይ ስር ያሉትን ሰዎች ለማውጣት አስቸጋሪ በመሆኑ በዚህ ምክንያት ሊሞቱ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆኑ እንደሚችል ተሰግቷል። እስከ ዛሬ ድረስ 90 የሚሆኑ ሰዎችን ከተደረመሰው ድልድይ ስር በማውጣት ለማዳን የተቻለ ሲሆን አብዛኞቹ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተልከዋል።  2 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ ከተጀመሩ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የተደረመሰው በግምባታ ጥራት ጉድለት ነው ይባላል። ፖሊስ ድልድዩን ሲሰራ የነበረው ኩባንያ ኃይላፊዎችን በቁጥጥር ያደረገ ሲሆን በወንጀል ክስ የሚመሰርትባቸው መሆኑን ገልጿል። በአገራችንም አብዛኞቹ መንገዶች ድልድዮችና ህንጻዎች የሚሰሩት ጥራታቸውን ባልጠበቀ ሲሚንቶና ሌሎች የህንጻ መሳሪያዎች መሆኑን በመናገር እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች  ከተከሰቱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ለጉዳዩ እውቀት ያላቸው በርካታ መሀንዲሶች መምከር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

Ø የሊቢያ የአንድነት መንግስት ተቀባይነት አግኝቶ ሁኔታውን መቆጣጠር ከቻለ ሊቢያ የተያዘባት የአገሪቱ ገንዘብ ወዲያውኑ ሊለቀቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ላለፉት አምስት አመታት 67 ቢሊዮን ዶላር የአገሪቱ ገንዝብ እንዳይነቃነቅ በተመድ የተያዘ መሆኑ ይታወቃል። ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓም ትሪፖሊ ወደብ የገባው በተመድ ግፊት የተቋቋመው የሊቢያ የአንድነት መንግስት በከተማው ውስጥ ተኩሶች በመበርከታቸው እና የጸጥታው ሁኔታ ያልተረጋጋ በመሆኑ ምክንያት  ከወደቡ አካባቢ በመውጣት ወደ ሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ያልተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል።  በትሪፖሊ የራሱን መንግስት ያቋቋመው አካል  መሪ ካሊፋ ገዊል በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የውጭ መንግስት አስጠባቂና ሰርጎ ገብ የሆነው የአንድነት መንግስት የሚባለው አካል በእኛ አካባቢ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። አያይዘውም ወደ ትሪፖሊ የገቡት የአንድነት መንግስት የልኡካን ቡድን አባሎች ወይ እጃቸውን ለእኛ በሰላም ይስጡ ካለበለዚያም ይመለሱ የሚል መግልጫ ሰጥተዋል። በትሪፖሊም የአንድነት መንግስቱን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄደዋል።  ከአምስት ዓመት በፊት የጋዳፊ መንግስት ከተገለበጠ ጀምሮ በሊቢያ ምስራቅና ምዕራብ ሁለት ራሳቸውን መንግስት ነን ብለው የሚጠሩ የታጠቁ ክፍሎች መመስረታችው ይታወቃል። ባለፈው ታኅሳስ ወር በተመድ አማካይነት ከሁሉም የተውጣጣ መንግስት ለማቋቋም የተጠነሰሰው ሀሳብ በአንዳንድ ክፍሎች ስምምነት እንዲቋቋም ቢደረግም በምስራቅም ሆነ በምዕራብ የአንድነት መንግስቱን መቋቋም የሚቃወሙ ክፍሎች በማየላቸው መንግስቱ ተመስርቶ ሊንቀሳቀስ አልቻለም። ሰሞኑን ከዚህ ጋር በተያያዘ የአንድነት መንግስቱ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆነዋል ብሎ በሰየማቸው ሶስት የሊቢያ ባለስልጣኖች ላይ  የአውሮፓው ህብረት ማዕቀብ የጣለ መሆኑ ገልጿል። ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰቦች አጊላህ ሳላህ በምስራቅ ሊቢያ የሚገኘው መንግስት የፓርላማ መሪ፤ ካሊፋ ገዊል የትሪፖሊ መንግስት መሪ እና አቡ ሳህማን የጠቅላላ ብሔራዊ ኮንግሬስ መሪ መሆናቸውም ተነግሯል።  ሶስቱ ግለስቦች ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን በአውሮፓ ውስጥ የሚገኝ ገንዘብና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተጥሎበታል። የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የአሁኑን የሊቢያን ሁኔታ ፈጥሯል የሚል አስተያየት የሚሰጡ  ወገኖች የጋራ ስምምነት እስከሌለ ድረስ የሊቢያ ቀውስ ይቀጥላል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

Ø ከአስራ ሰባት ዓመት የስልጣን ጊዜ በኋላ የጅቡቲው ገለህ በሚቀጥለው ሳምንት መጋቢት 30 ቀን 2008  በሚካሄደው ምርጫ የሚመረጡ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው በማለት በርካታ ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። የዛሬ ስድስት ዓመት ፓርላማው የጂቡቲን ሕገ መንግስት በመቀየሩ ምክንያት ገለህ ለሶስተኛ ጊዜ የተመረጡ ሲሆን የአሁኑ አራተኛው የስልጣን ዘመናቸው ይሆናል።  የተቃዋሚዎች ህብረት በአንድ ላይ ለመቆም ችግር ያለበት ቢሆንም ከሰባት ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ሶስቱ የታቀደው ምርጫ መሰረታዊ የሆነ የነጻና ፍትሃዊ ምርጫ መመዘኛዎች ያላሟላ የይስሙላ ምርጫ  ስለሚሆን አንሳተፍም ብለዋል። ነጻና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ እንዲቋቋም የቀረበውን ጥያቄ የገለህ መንግስት ውድቅ አድርጎታል። ጅቡቲ ውስጥ አሜሪካ በየመን፤ በሶማሊያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጸረ ሽብር ጥቃቶችን የምታስተባብርበት የጦር ማዕከል ሲኖራት ፈረንሳይ፤ ጃፓን እና ቻይናም ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች የመሰረቱ መሆናቸው ይታወቃል። አገሪቱ ባለፉት አመታት የኢኮኖሚ እድገት አሳይታለች ተብሎ ብዙ ቢወራላትም በአግሪቱ ውስጥ የስራ አጡ ቁጥር 60 ከመቶ የደረሰ ከመሆኑም በላይ ቢያንስ አንድ አራተኛ የሚሆነው የጂቡቲ ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት ክልል እንደሚኖር ይታወቃል።

Ø ዛሬ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓም የተባበሩት መንግስት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት 100 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል አባላት  በብሩንዲ ስላም ለማስከበር ስለሚሰማሩበት ሁኔታ በፈረሳይ መንግስት በቀረበው ረቂቅ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጥበታል ተባለ። ቁጥራቸው ከ100 የማይበልጥ ፖሊሶች ወደ ጅቡቲ ተልከው በብሩንዲ የሰብአዊ መብትን ለማስከበር ስለሚቻልበት ሁኔታ እርዳታ ያደርጋሉ ተብሏል። በብሩንዲ የእርስ በርስ ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ዜጎች በገፍ የሚገደሉበት፤ የሚያዙበትና ተይዘውም በምርመራ ከፍተኛ ስየል የሚካሄድባቸው የዜና ምንጮችና የተመድ ባለስልጣኖች በየጊዜው መግለጻቸው ይታወቃል።  በቀረበው ሀሳብ መሰረት 100 ፖሊሶችን ለመላክ የታቀደ ሲሆን ጸጥታን ለማስከበር ቁጥሩን እንደማይበቃ ብዙዎች ይናገራሉ። የብሩንዲ ችግር በጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ400 በላይ የብሩንዲ ዜጎች ሲገደሉ ከ12 000 ሰዎች በላይ እንደተሰደዱ ተዘግቧል

No comments:

Post a Comment