የወያኔ አፋኝ አገዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ በጫነው የጎሳ ሽንሸና ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የማንነት ጥያቄዎች ላይ ማለትም ቋንቋ፣ ባህል፣ ስነ-ልቡና የመሳሰሉት ላይ የተመረኮዙ ግጭቶች እየተከሰቱ ናቸው። ከነዚህ ግጭቶች ውስጥ ዋነኛውና ቀደምቱ በጎንደር ክፍለ ሐገር ውስጥ የሚገኘው ወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ነው። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነቱ እንዲጨፈለቅና ከፍላጎቱ ውጭ በጠመንጃ አፈሙዝ ተገዶ ወደ ትግራይ ክፍለ ሐገር ውስጥ እንዲጠቃለል በመደረጉ ምክንያት የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል። ወያኔ ጫካ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የአማራ ህዝብን ማንነት ለውጦ ወደ ትግራይነት ለመቀየር እየወሰዳቸው በሚገኘው ህገወጥና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ምክንያት በርካታ የአማራ ብሔር አባላት ላይ ጭፍጨፋዎችን፣ሰቆቃዎችንና ማፈናቀሎችን በማድረስ ላይ ይገኛል።
ይህንን በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ በመድረስ የሚገኘውን የማንነት ጭፍለቃና መሬት ነጠቃ ከታሪክና ከነበራቸው ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን አኳያ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ የዕድሜ ባለጸጋውን ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን የተለያዩ የዜና ማሳራጫዎች ቃለ ምልልስ አድርገውላቸዋል። በዚህም መሠረት ከጥቂት ወራት በፊት የኤሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸውና አውስትራሊያ ውስጥ የሚሰራጨው ኤስ.ቢ.ኤስ. ሬድዮ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ላይ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን አነጋግረዋቸው የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭ ምላሽ በአግባቡ እንዲብላላና አስፈላጊው ግንዛቤ እንዲሰጥ እዚህ ላይ አቅርበንላችኋል። ልዑል ራስ መንገሻ ከትዝታ በላቸው ጋር ባደረጉት ውይይት የትግራይና የጎንደር ወሰን ተከዜ ወንዝ መሆኑንና እሳቸው ሆኑ አባታቸውና አያታቸውም ጭምር ተከዜ ወንዝን ተሻግረው ጎንደርን አስተዳድረው እንደማያውቁ በማያሻማ ሁኔታ የገለጹ ቢሆንም ከጥቂት ቀናት በኋላ ከካሳሁን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የወልቃይት ጠገዴን አማራነት አደናግረውና አጨናብረው ለማለፍ ያደርጉት የነበረውን ዙሪያ ጥምጥምና የቃላት ድርደራ ትዝብት ላይ ጥሏቸው አልፏል።
No comments:
Post a Comment