Sunday, July 17, 2016

ፌስቡክ ከሽብር ጋር በተያያዘ በ 1 ቢ. ዶላር ተከሰሰ


ፌስቡክ ከሽብር ጋር በተያያዘ በ 1 ቢ. ዶላር ተከሰሰ
   ተቀማጭነቱ በእስራኤል የሆነው ሹራት ሃዲን የተባለ የመብቶች ተሟጋች ቡድን በቅርቡ በፍልስጤም ከተከሰቱ የሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ላይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ የሚጠይቅ ክስ መመስረቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በሽብር ጥቃቶች የተገደሉ አሜሪካውያን ግለሰቦችን ቤተሰቦች በመወከል ክሱን የመሰረተው ቡድኑ፣ የማህበራዊ ድረገጹ የአሜሪካን የጸረ ሽብር አዋጅ በመጣስ ለሽብርተኞች የጥፋት መልዕክቶችን ማሰራጫ መንገድ ሆኖ አገልግሏል በሚል ፌስቡክን ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ማድረጉን ዘገባው ገልጧል፡፡
የመብት ተሟጋች ቡድኑ ሃማስን የመሳሰሉ ቡድኖች አዳዲስ አባላትን እንዲመለምሉ፣ ጽንፈኛ አመለካከቶቻቸውን እንዲያራምዱና ለሽብር ለሚያሰማሯቸው ታጣቂዎች መመሪያ እንዲያስተላልፉ ምቹ ዕድል ፈጥሯል በሚል ባለፈው ሰኞ በኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት በፌስቡክ ላይ ክሱን እንደመሰረተ ተነግሯል፡፡
ቡድኑ በመሰረተው ክስ ላይ የተጠቀሱት የሽብር ጥቃት ሰለቦች የሆኑ አምስት ቤተሰቦች ሁሉም አሜሪካውያን እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህም መካከል ባለፈው መጋቢት ወር ላይ እስራኤልን ሲጎበኝ በፍልስጤማውያን ጥቃት የተገደለው ቴለር ፎርስ የተባለው የ28 አመት አሜሪካዊ ቤተሰቦች እንደሚገኙበት አክሎ ገልጧል።

No comments:

Post a Comment