Tuesday, July 26, 2016

መሪ (ሪዳ) እና ገዥ (ሐጉካይ-ሻ) “ገዥ ጉልበት ይፈልጋል፤ መሪ ግን ጥበብ ይፈልጋል” – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት


የሩቅ ምሥራቆቹ ጃፓኖች እንዲህ የሚል ለዓለም የተረፈ ታሪክ አላቸው፡፡
በ17ኛው (መክዘ) ላይ በዓይን ሕመም የሚሰቃይ ጎ- ሳይ የተባለ አንድ የጃፓን ንጉሥ ነበረ፡፡ በሀገረ ጃፓን የሚገኙ ሐኪሞችን ሁሉ ጠርቶ ለስቃዩ መድኃኒት እንዲፈልጉለት ቢያዝም ሊያገኙ ግን አልቻሉም፡፡ በኮርያ፣ በቻይና፣ በሞንጎልያና በሩሲያ ሳይቀር ታዋቂ የሆኑ ባለ መድኃኒተኞችን እየጠራ፣ ገንዘብና ሥልጣን ለመሸለምም ቃል እየገባ፣ ሕመሙን ለማዳን ሞከረ፡፡ ግን አልተቻለውም። በመጨረሻም ሞንጎልያ ውስጥ በኡውስ ሐይቅ አጠገብ፣ ዑላንጎም በተባለ መንደር እጅግ የታወቀ ባለ መድኃኒት መኖሩ ተሰማ፡፡
ንጉሥ ጎ- ሳይም ኦይራት የተባሉትን የሞንጎልያ ሲራራ ነጋዴዎች፤ ይህን ባለመድኃኒት እንዲያመጡለት ወርቅ ሰጥቶ ላካቸው፡፡ ከአራት ወራት በኋላም ኦይራት የሚባሉት ሲራራ ነጋዴዎች፤ ባለመድኃኒቱን በድንክየዎቹና ፀጉራሞቹ ግመሎች ጭነው አመጡለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ ባለ መድኃኒቱ መምጣቱን ሲሰማ የመዳን ተስፋው ለመለመ፡፡
ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ንጉሡን አገኘው፡፡ ንጉሡም ከሚያሰቃየው የዓይን ሕመም ከፈወሰው የፈለገውን ሁሉ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ፤ የንጉሡን ሕመም ለማዳን የሚችል መድኃኒት እንዳለው ነገር ግን ንጉሡ መዳን የሚችለው አንድ ነገር ሲያሟላ መሆኑን ተናገረ። ንጉሥ ጎ-ሳይ የተባለውን ሁሉ ለማሟላት ቃል ገባ፡፡ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒትም ‹‹ሐኩጋይ-ሻ› (ገዥ) ከሆንክ አትድንም፤ ‹ሪዳ› (መሪ) ከሆንክ ግን ትድናለህ› ሲል ነገረው፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ የባለመድኃኒቱ ነገር ስለገረመው በገዥና በመሪ መካከል ያለውን ልዩነት ጠየቀው፡፡ ባለመድኃኒቱም፤ ‹ገዥ ጉልበቱንና ሀብቱን ብቻ የሚጠቀም አለቃ ነው፤ መሪ ግን አእምሮውንና ክሂሎቱን የሚጠቀም አለቃ ነው› ሲል በአጭሩ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይም መሪ መሆኑን አረጋገጠለት፡፡
ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ለዓይን ሕመም የሚሆነውንና በየቀኑ የሚቀባውን መድኃኒት ከሰጠው በኋላ እንዲህ ሲል አዘዘው፡- ‹ሕመሙ እስኪሻልህ ድረስ የምታየው ነገር ሁሉ አረንጓዴ መሆን አለበት፡፡ ከአረንጓዴ ቀለም ውጭ የምታይ ከሆነ ያገረሽብሃል› ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይም ያን ማድረግ ቀላል መሆኑን ነግሮት ተለያዩ። ሞንጎልያዊው ባለ መድኃኒትም ከ3 ወር በኋላ ተመልሶ ሊመጣ ቃል ገብቶ፣ ኦይራት ከተባሉት ሲራራ ነጋዴዎች ጋር ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
ንጉሥ ጎ-ሳይ ባለሟሎቹን ሁሉ ጠራ፡፡ ባለመድኃኒቱ የነገራቸውን በማስታወስም ከቤተ መንግሥቱ ጀምሮ ያሉ ዕቃዎች፣ ግድግዳዎች፣ ዛፎች፣ ተራሮችና ኮረብቶች ሁሉ አረንጓዴ ቀለም እንዲቀቡ አዘዘ፡፡ የከተማው ነዋሪም ቤቶቹን ሁሉ አረንጓዴ እንዲቀባ ዐዋጅ ወጣ፡፡ ከአረንጓዴ ልብስ ውጭ መልበስም ተከለከለ፡፡ እንስሳትም አረንጓዴ ቀለም እንዲቀቡ ተለፈፈ፡፡ ለዚህ ዐዋጅ የሚውል በሚሊዮን የሚቆጠር ወርቅ ወጭ ሆነ፡፡ ከኮርያ፣ ከቻይና፣ ከሩሲያና ከሕንድ ሳይቀር ቀለም በገፍ ወደ ጃፓን ገባ፡፡ ሰውና እንስሳውም መሬት ተተክሎ የበቀለ እስኪመስል ድረስ አረንጓዴ ሆነ፡፡
ከሦስት ወራት በኋላ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ቃል በገባው መሠረት ወደ ጃፓን መጣ፡፡ የንጉሥ ጎ-ሳይ የዓይን ሕመም ለውጥ አላመጣም፡፡ ሀገሪቱ ግን አረንጓዴ በአረንጓዴ ሆናለች፡፡ ባለመድኃኒቱም ወደ ጃፓን ከገባበት ቀን ጀምሮ ባለማቋረጥ ይስቅ ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲቃረብ የንጉሡ ልብሶች አረንጓዴ ቀለም ሲቀቡ ደረሰ። ይህንን ሲመለከትም ሳቁን ፈጽሞ መቆጣጠር አልቻለም ነበር፡፡ ንጉሡም የባለመድኃኒቱን ሁኔታ ተመልክቶ ግራ ተጋባ፡፡
ንጉሡ ለምን እንደዚያ እንደሚስቅ ባለመድኃኒቱን ጠየቀው፡፡ ሕመሙም እንዳልተሻለው ገለጠለት። ባለመድኃኒቱም እንደዚያ የሚያስቀው የንጉሡ ሞኝነት መሆኑን ገለጠለት፡፡ ሕመሙ ያልተሻለው ግን ገዥ እንጂ መሪ ባለመሆኑ እንደሆነ ነገረው። ንጉሡም ሞኝነቱንም ገዥነቱንም አብራርቶ እንዲነግረው ሞንጎልያዊውን ባለመድኃኒት ጠየቀው፡፡ ባለ መድኃኒቱም፤ ‹አንተ ሁሉን ነገር በሥልጣንና በገንዘብ ብቻ ነው የምታስበው። ይህ ደግሞ የ‹ሐኩጋይ-ሻ› (ገዥ) መለያ ጠባይ ነው። ሁሉንም በጉልበቱና በገንዘቡ ብቻ ማድረግ እንደሚችል ያስባል፡፡ በርግጥ የምታየው ነገር ሁሉ አረንጓዴ መሆን አለበት ብየ ነግሬህ ነበር፡፡ አንተም አገልጋዮችህንና ሕዝብህን እያስጨነቅህ አገሩን ሁሉ አረንጓዴ ቀለም ለመቀባት ሞከርክ፡፡ ለመሆኑ በዚህ አያያዝህ ቢበዛ ከዚህ ከተማ ውጭ ልትሻገር ትችላለህን? ዓለምንስ ሁሉ አረንጓዴ ቀብተህ ትጨርሳለህን? ሰማዩን፣ ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትንና ታላላቅ ተራሮችን ምን ልታደርጋቸው ነው? ከሁሉም በላይ እሳትን ምን ልታደርገው ነው? አየህ የገዥነት(‹ሐኩጋይ-ሻ›) ትልቁ ችግሩ ሁሉንም ነገር በጉልበቴና በገንዘቤ እቆጣጠረዋለሁ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ይህንን በተወሰኑ ነገሮች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ሲችል፣ ገዥ በዚያ ይታለላል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ይሳካልሃል፡፡ ያም የበለጠ ገዥነትህን ይጨምረዋል። እየቆየህ ስትሄድ ግን በገንዘብህና በጉልበትህ የማትደርስበት ኃይል መኖሩን ታውቃለህ፡፡ ልክ እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና እሳት፡፡
አእምሮ ቢኖርህ ኖሮ ‹ሪዳ› (መሪ) ትሆን ነበር፡፡ ሪዳ (መሪ) ብትሆን ኖሮ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ጉልበትህንና ገንዘብህን ለመጠቀም ከምትሮጥ ይልቅ አእምሮህን ትጠቀም ነበር፡፡ ዓይንህ አረንጓዴ ነገር ብቻ እንዲያይ ከፈለግህ ነገሩ በጣም ቀላል ነው። ያኔ እኔ አንተን ሳዝህ ‹በጣም ቀላል ነው› ስትለኝ፣ እውነትም አእምሮ ያለህ ‹ሪዳ› (መሪ) ነህ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ አሁን ግን ተሳስቼ እንደነበር ገባኝ።
‹ቀላሉ መንገድ ምን ነበር?› አለ ንጉሥ ጎ-ሳይ በሁኔታው እየተደነቀ፡፡
‹ቀላሉ መንገድ› አለ ሞንጎልያዊው ባለ መድኃኒት፡፡ ‹ቀላሉ መንገድ የምታየውን ነገር ሁሉ አረንጓዴ አድርጎ የሚያሳይ መነጽር በሁለት ‹ስየሶ ገንቦ› ገዝተህ ዓይንህ ላይ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን መነጽር ብታድርግ ኖሮ አገልጋዮችህንና ዜጎችህን ማስጨነቅ፣ ላንተ ሲባል ምድሩን ሁሉ አረንጓዴ ቀለም ማስቀባት፣ አረንጓዴ ልብስ ማስለበስና አገሩንም ማበላሸት አይጠበቅብህም ነበር፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ ለሀገርህና ለሕዝብህ ስትል አንተ ትሰቃያለህ እንጂ ለአንተ ስትል አገርህንና ሕዝብህን አታሰቃይም ነበር፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ አገርህን አረንጓዴ ለማድረግ ስታስብ፣ ሕዝብህን ማሳመን ይጠበቅብህ ነበር፡፡
ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ ያኔ እኔ ‹አረንጓዴ ነገር ብቻ ማየት አለብህ› ብዬ ሳዝህ ‹ቀላል ነው› ከምትል ይልቅ ‹እንዴት አድርጌ› ብለህ መጠየቅ ነበረብህ፡፡ ገዥ ተገዥ ይፈልጋል፡፡ መሪ ግን አማካሪ ይሻል፡፡ ገዥ ጉልበት ይፈልጋል፤ መሪ ግን ጥበብ ይፈልጋል። ገዥ ሁሉም ነገር ቀላል ነው ይላል፡፡ መሪ ግን እንዴት ቀላል ሊሆን እንደሚችል ያስባል፣ ይጠይቃል፡፡ ገዥ የሚመስለውንና የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። መፍትሔው ቢመጣ ባይመጣ፣ ችግሩ ቢፈታ ባይፈታ፣ ሌላ ችግር ቢመጣ ባይመጣ ግድ የለውም። መሪ ግን ማድረግ የሚችለውንና የሚመስለውን ሁሉ አያደርግም፡፡ ለውጥ የሚያመጣውን ነገር ብቻ እንጂ፡፡ ቢችልም፣ ዐቅም ቢኖረውም፣ ሥልጣን ቢኖረውም ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ካላረጋገጠ አያደርገውም፡፡ ለመሆኑ ይህንን ውሳኔ ስትወስን የሀገርህን ኬንጃ (ጠቢባን) አማክረሃቸዋል፡፡ ብታማክራቸው ኖሮ እንዲህ አገሩን ሁሉ አረንጓዴ አታደርገውም ነበር፡፡
ታድያ አንተ እንዴት ትድናለህ? ራስህን መቀየር ሲገባህ ዓለምን ልትቀይር ተነሣህ፡፡ መቀየር የነበረብህ የምታየውን ነገር ሳይሆን አንተ የምታይበትን መንገድ ነበር፡፡ አረንጓዴውን መነጽር ብትገዛ ኖሮ አንተ ዓለምን አረንጓዴ አድርገህ ታያታለህ። ሌላው ደግሞ እንደሚፈልገው ቀይም፣ ጥቁርም፣ ነጭም፣ ቢጫም አድርጎ ያያታል፡፡ አሁን ግን አንተ አረንጓዴ ስለምትፈልግ ብቻ ዜጎችህ ሁሉ አረንጓዴ እንዲያዩ፣ አረንጓዴ እንዲለብሱና አረንጓዴ እንዲበሉ አደረግካቸው፡፡ ካሚ(ፈጣሪ) ልዩ ልዩ አድርጎ የፈጠረውን ሕዝብ አንተ አንድ ዓይነት ልታደርገው ፈለግክ፡፡ ያውም ላንተ ሲባል፡፡
መሪ(ሪዳ) ለሕዝብ ነው፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስትሆን ግን ሕዝቡ ያንተ ነው፡፡ እንደፈለግክ ታደርገዋለህ፡፡ ለገዥ ሕዝብና ኪያሜሩ(ግመል) አንድ ነው፡፡ ለገዥ ሁለቱንም እንደፈለጉ ማድረግ ይቻላል። ለገዥ ሁለቱም ሀብት ናቸው፡፡ ገዥ ስለ ሕዝቡ እርሱ ያውቃል፡፡ የሕዝቡም ጭንቅላት በእርሱ ላይ ነው፡፡ እርሱ አሰበ ማለት፣ ሕዝቡ አሰበ ማለት ነው፡፡ እርሱ ፈለገ ማለት፣ ሕዝቡ ፈለገ ማለት ነው፡፡
ታድያ አንተ እንዴት ትድናለህ? ወርቅህን አልፈልግም፡፡ ሽልማትህም ለራስህ ይሁን? እንካ አረንዴውን መነጽር፡፡ ከቻልክ ያበላሸኸውን አስተካክለው፡፡ ያጠፋኸውን መልሰው፡፡ ካልቻልክ ሌላ ጥፋት ሳይደርስ ባለበት እንዲቆም አድርገው፡፡ እኔ ግን ወደ ሀገሬ ወደ ኡቭስ ሐይቅ፣ ወደ ዑላንጎም መንደር እሄዳለሁ፡፡ በረግረጉ ሥፍራም ይህንን ሞኝነትህን እያሰብኩ ስስቅ እኖራለሁ፡፡ ኮክ-ኦህ-ሩኽ (ልቡና) ካገኘህና ከገዥነት ወጥተህ መሪ መሆን ስትጀምር ጥራኝ፡፡ በሕይወት ካለሁ እመጣለሁ። ያኔ ሕመምህን ፈጽሞ እንዲድን አደርገዋለሁ፡፡ ላሁኑ ግን ገን-ኪ-ደ (ደኅና ሁን፣ ራስህን ጠብቅ)፡፡
ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ከጃፓን እስከ ሞንጎልያ፣ እስከ ኡቩስ ረግረጋማ ሥፍራ ድረስ በየደረሰበት ሁሉ ይህንን የንጉሡን ታሪክ እየተረከው ሄደ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ታሪክ ከኢራን እስከ ጃፓን ድረስ በየቋንቋው ይተረካል ይባላል፡፡

No comments:

Post a Comment