Sunday, July 24, 2016

የዘር ፖለቲካ መዘዙ (ትግሬዎች ላይ ደረሰ በተባለው ጥቃት ላይ) – ግርማ ካሳ


የዘር ፖለቲካ መዘዙ (ትግሬዎች ላይ ደረሰ በተባለው ጥቃት ላይ) – ግርማ ካሳ
የሪፖርተሩ የማነ ነጋሽ አንድ ጽሁፍ አስነብቦናል። “የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ ችግሮች ጀርባ ስሙ ለምን ይነሳል?” በሚል ርእስ ሥር። ጽሁፉ ብዙ የተካተቱ ሐሳቦች አሉበት። አገዛዙ ኤርትራ፣ ኤርትራ ለምን እንደሚል የማነ ባቀረባቸው ነጥቦች ላይ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ። አሁን ግን በትግራይ ተወላጆች ላይ ደረሰ በተባለው ጥቃት ላይ፣ የማነ በጻፈው ላይ አንዳንድ ያሉኝ ሐሳቦች እንዳጋራ ይፈቀድልኝ።
“….በአካባቢው በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ተገልጿል፡፡ቀደም ሲል የቅማንትን የማንነት ጥያቄ አስመልክቶ በተነሳው ሁከትም በተመሳሳይ በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸሙን፣ የአማራ ክልል መንግሥት በቂ ከለላ አላደረገም ተብሎ በፓርላማ በቀረበበት ጥያቄ መሠረት ይቅርታ ጠይቋል” በማለት ነው የማነ ነጋሽ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሩን ለማሳየት የሞከረው።
ከሚወጡት መረጃዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ በማንም የትግራይ ተወላጅ ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ያለ አይመስለኝም። እርግጥ ነው በአንዳንድ ሰዎች ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ሁላችንም ተመልክተናል። የአካባቢው ሰዎች “ የትግራይ ተወላጆች ላይ ሳይሆን የሕወሃት ካድሬ ሆነው ሕዝቡን ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች ንብረት ላይ ጥፋት የደረሰው”የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። እንደዚያም ቢሆንም ድርጊቱ ግን ትክክል ነው ማለት አይደለም። ማንም ዜጋ (የአገዛዙ ካድሬ ይሁን አይሁን) በሕይወቱ ላይም ሆነ በንብረቱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሊደርስበት አይገባም። ማንም ዜጋ በማናቸዉም የአገሪቷ ክፍሎች በሰላም የመኖር፣ ንብረት የማፍራት መብቱ መረጋገጥ አለበት። ማንም ዜጋ የሕግና የሕግ አስጠባቂዎች ከለላ ማግኘት መቻል አለበት።
ይሄን ብዬ ሁለት ነጥቦችን ላንሳ። ከየትኛው የአገሪቷ ክፍል ይልቅ የትግራይ ተወላጆች በብዛት የሚኖሩት በጎንደር (በጌምድር) ነው። ለዘመናት ተዋልደው፣ ተፋቅረው የኖሩ ናቸው። ጎንደሬዎች፣ “አማራ” እየተባሉ በሕወሃት ህዝቡ ከፍተኛ በደልና ግፍ ላለፉት 25 አመታት ቢፈጸምባቸውም ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ፣ አንድ ጊዜም፣ ጥቃት ተፈጸም ሲባል የተሰማበት ሁኔታ የለም። (በቅርቡ ተፈጸመ ከተባለው ዉጭ )። ያም የሚያሳየው የሕዝቡ ጨዋነትና ስው አፍቃሪነት ነው። እነ ጀነራል ሳሞራ “የትግራይ ህዝብ ማለት ሕወሃት ማለት ነው” ይላሉ። የጎንደርም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የትግራይን ህዝብ ከሕወሃት ለይቶ ነው የሚያየው። ሕወሃት ለትግራይ ህዝብ ከሚጠነቀቀ፩ው በላይ የተቀረው ጎንደሬው ለትግራይ ወንድሞቹ የሚጠነቀቅ ነው። አብሯቸው ተዋልዷልና። ከነጌታቸው ረዳ ምክር አያስፈልገውም።
ወደ ሌሎች ክልሎች፣ ወደ ደቡብ ክልል፣ ወደቤነሻንጉል እና ኦሮሚያ ስንሄድ ግን የተለየ ነገር ነው የምናየው። በኦሮሚያ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች ፣ “አማራ ናችሁ፣ መሬታችሁ አይደለም” ተብለው ተፈናቅለዋል፡፡መፈናቀል ብቻ አይደለም ኢሰብአዊ ጭፍጨፋና ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ቤቶቻቸው በእሳት ጋይተዋል። ከሁለት አመት በፊት እንኳን ፣ በማስተር ፕላኑ ዙሪይ ተነስቶ በነበረው ግጭት፣ “አማራ ናችሁ” ተብለው እንደ አምቦ ፣ ጊምቢ ባሉ ቦታዎች ብዙ ሆቴል ቤቶች፣ የግል ባንኮች ፣ የግለሰቦች ቤቶች ጋይተዋል። በብዙ የኦሮሚያ ትናንሽ ከተሞች የሚኖሩ “ኦሮሞ” ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያን እየለቀቁ ወደ ድረዳዋ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ ፈልሰዋል። መኖር ስላልቻሉ። በደቡብ ክልል ጉሩ ፈርዳ በመሳሰሉ አካባቢዎች እንዲሁም በበርካታ የቤኔሻንጉል ወረዳዎች የደረሰዉን የዘር ማጽዳት ወንጀል ሁላችንም በቅርበት የምናውቀው ነው። በሁሉም አቅጣጫዎች ማለት ይቻላል፣ “አማርኛ ተናጋሪዎች” ላይ ሲስተማቲክ የሆነ ጥቃት ሲፈጸም ነው የነበረው። በሕወሃት ተእዛዝ፣ በክልሉ አስተዳዳሪዎች እውቅና። በደቡብ ክልል አስተዳዳሪ የነበረው፣ ሽፈራው ሽጉጤ ፣ “አማራዎችን እንድናስወጣ በመለስ ዜናዊ ታዘን ነው” ሲል የተናገረዉን ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው። (ከታችን የቀረበውን ሊንክ በመጫን አማራ ናችሁ በሚል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰዉን ከፍተኛ ስቃይና እንግልት፣ ከተፈናቃዮች ከራሳቸው አፍ መስማት እንችላለን)
የዘር ማጽዳቱ ወንጀል ሳይቋረጥ፣ በሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል፣ ላለፉት 25 አመታት የነበረ ቢሆንም፣ የኦሮሚያ፣ የቤኔነሻንጉል እና የደቡብ ክልል መንግስታት ይቅርታ እንዲጠይቁና ለተፈናቃዮችና ለሟቾች ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፍሉ የተደረገበት ሁኔታ የለም።
በሰላም በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ለደረሰው ጉዳት ብአዴን ካሳ እንዲከፍልና ይቅርታ እንዲጠይቅ መደረጉ ተገቢ ነው። ብአዴን ጥበቃ ማድረግ ነበረበት። በሕወሃት ሐጢያት ምክንያት፣ ሰላማዊው የትግራይ ተወላጅ ለምን ይጠቃል ? ማንም ሰው በማንም ላይ ጉዳት ማድርስ የለበትም። ሆኖም ግን የትግራይ ሰዎች ሲበደሉ መንግስትና ፓርላማው ሲቆምላቸው፣ ለ”አማራው” የሚቆረቆር አካል አለመኖሩ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ የአንድ ዘር የበላይነት መኖሩን በገሃድ የሚያረጋግጥ ነው። ያ መቆም አለበት።
አንድ ሰው የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ ምን እንደሚባሉ ነገረኝ። “ዜጎች ነው የሚባሉት” አለኝ። ያ ማለት ሌሎች “ዜጎች” አይደሉም እንደማለት ነው። ትግሬው እንደ “ዜጋ” ሲቆጠር ሌላውም እንደ “ዜጋ” የማይቆጠርበት ምክንያቱ ምንድን ነው ? የሌላው ሕይወት ከትግሬው ሕይወት ያነሰ ተደርጎስ ለምን ይታያል ? እንግዲህ ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው።
የአብዛኛው ሕዝብ ጥያቄ “ጸረ-ትግሬ” ጥያቄ አይደለም። ትግሬዎች “ዜጎች” እንደሆኑት እኛም ዜጎች እንሁን የሚል ነው። ታዲያ በአንዳንድ የትግራይ ወገኖቻችን ዘንድ “እኛም ከትግሬው እኩል መሆን አለብን” መባሉንስ ለምን ይጠሉታል ? ለምንስ ትግሬዎች ላይ እንዳነጣጣረ አድርገው ይወስዱታል ? በትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጸመ የተባለው እንዳስቆጣቸው፣ (ሊያስቆጣቸውም ይገባል) ለምን በሌላው ላይ የሚደርሰውስ አስያቆጣቸውም ?
አብዛኞቻችን ከጅምሩ “ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ መባባል አይኑር። ሰው በሰብአናዉና በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ይመዘን። ማንም በየትኛው የአገሪቷ ክፍሎች ዘሩ ሳይጠየቅ በሰላም ይኑር” ስንል ነበር።
ጎንደሬዋ አስቴር አወቀ “አንድ አርገን” በሚል ዜማዋ
“ድሮ መች ነበር ዘር ቆጥሮ ጎረቤት
በጠዋቱበጥንቱ በነአባብዬ ቤት
እድር መሃበሩ ሲያሰባስባቸው
መች ይጠየቅ ነበር የዘር ሃረጋችው? “
እንዳለች በወልቃይት ጠገዴም ሆነ በሌላው የአገሪቷ ክፍሎች በዘር ሳንለያያ ተፋቅረን ነበር የምንኖርው። አሁን ግን ህወሃት ያመጣው መርዛማ ዘረኛ ፖሊሲና ፖለቲካ እርስ በርስ በጎሪጥ እንድንተያይ አደረገን። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማርኛ ይናገራል፤ ትግሪኛ ይናገራል። ሲያሻው ሽሬ ሄዶ ይነግዳል፤ ሲያሻው ጎንደር ይሄዳል። በደርግ፣ በአጼዎቹ፣ በዘመነ መሳፍንት በነ ሚካኤል ስሁል ጊዜ ሳይቀር አማራ፣ ትግሬ እየተባበላ ተጣልቶ ተከፋፍሎ አያውቅም ነበር። አሁን ግን ይኸው ትላንትና የመጡ ሕወሃቶች በመካከሉ እሳት ለኮሱበት።
እንግዲህ መፍትሄ ወደ ፍቅር ወደ አንድነት ፖለቲካ መመለስ ነው። መፍትሄው ዘረኝነትን ከፖለቲካችን፣ ከሕግ መንግስቱና ከመንግስት መዋቅር ማስውጣት ነው። የአንድ ዘር የበላየነትን አስቆሙ ሁሉም ዜጎች እኩል የሆኑባት፣ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በሰላም የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መመስረት ነው። አንድ ዘር የበላይ የሆነበት አገር አይደለም፣ ወረዳ መኖር የለበትም። ኢትዮያውያን በቀላማቸው፣ በኃይማኖታቸው፣ በዘራቸው ሳይሆን መመምዘን ያለባቸው በስራቸው መሆን አለበት።
አሁን ለሁልጊዜ እንደምለው የሚበጀን ፍቅር ነው። የሚበጀን ወንድማማችነት ነው። የሚበጀን መከባበር ነው። ሕወሃት በሚሰጠን አጀንዳ መወሰድ የለብንም። ዘረኝነትን ከነርሱ መማር የለብንም። ሕወሃትን ከትግራይ ህዝብ ለይተን ማየት አለብን። ሕወሃት ባደረገው የትግራይን ህዝብ መዉቀስ በጀመርን ጊዜ አሸናፊ የሚሆነው ሕወሃት ራሱ ነው። ሕወሃት እንድናስብና እንድንሆን የሚፈልገውን ካሰብንና ከሆንን አንደኛ ራሳችንን እናሳንሳለን፤ ሁለተኛም የሰለጠነ ፖለቲካ አይደለም።
የሕወሃት የንቀት፣ የጥጋብ፣ የጭካኔ፣ የእልህ ፣ የጥላቻና የዘረኝነት ፖለቲካና መፈንስ መቆም አለበት። ከአሁን ለአሁን የኛ ዘር ናችው ብለን፣ ህወሃትን የምናስታምም ወገኖች መረዳት አለብን። የህወሃት ፖለቲካ ትግሬዉንም የሚጎዳ የክፋት ፖለቲካ ነው። የሕወሃት ዘረኛ ፖለቲካ የትግሬ ማህበረሰብን፣ ለዘመናት አብሮና ተፋቆሮ ከኖረው ሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር እያቃቃረው ነው።

No comments:

Post a Comment