ይህ ሁሉ ገንዘብ ከየት መጣ? በሙስና በኪራይ ሰብሳቢነት ሚሊየነር ቢሊየነር ተኮነ፡፡ (በጌታቸው አስፋው)
አምና መርካቶ በርበሬ ተራ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ጨረታ ሦስት መቶ ሰላሳ ሺሕ ብር ተሰጠ ተባለ፡፡ ዘንድሮ አቃቂ ቃሊቲ አንድ ካሬ ሜትር ቦታ በሰባ አምስት ሺሕ ብር ሒሳብ ተሸጠ፡፡ በሙስና ሚሊኒየር ቢሊኒየር ተኮነ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ሚሊየነር ቢሊየነር ተኮነ፡፡
ደላሎች በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ያንቀሳቅሳሉ ተብሎ በፓርላማ ውይይት ተካሄደ፣ አንድ ፍሬ ልጆች ሃምሳ ሺሕ፣ መቶ ሺሕ ለደላላ ከፍለው በበረሃ አሸዋና በባህር ለመበላት ይሰደዳሉ፡፡ የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ድርሻው ከአሥራ አምስት በመቶ የማይበልጥ መንግሥት በግብር እስከ ሁለት መቶ ቢሊዮን ብር ይሰበስባል፡፡ ባለበጀት መሥሪያ ቤት ያልሆኑ የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች የሚያንቀሳቀሱት የገንዘብ መጠንስ ከፈጣሪ በቀር ማን ያውቀዋል?
ስልሳ ብር የነበረ ኩንታል ጤፍ ሁለት ሺሕ ብር ገብቶም እንደ ልብ ይሸጣል፡፡ አሥር ብር የነበረ አንድ ኪሎ ሥጋ ሁለት መቶ ብር ገብቶም እንደ ልብ ይሸጣል፡፡ ቢራ በቧንቧ ቤታቸው ሊያስገቡ ያሰቡ ሰዎችም አይጠፉም፡፡ በዚህ ዓመት መደበኛ ገቢና ቋሚ ሥራ ሳይኖራቸው መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች ቁጥር የእጥፍ እጥፍ ሳይጨምር አልቀረም፡፡
ሚጥሚጣ እንኳ ለማቃጠል በኪሎ ሁለት መቶ ብር ተሽጣለች፡፡ የሁለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየም ቤት መሸጫ ዋጋ ከሚሊዮን ብር በላይ ዘሏል፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ይህ ሁሉ ገንዘብ ከየት ነው የሚመጣው? ብዙዎቻችን የማናውቀው የገንዘብ ማዕድን ይኖረን ይሆን እንዴ? ካለም የሚኖረው ቦሌ አካባቢ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግ ነው ለፈረንጆች እውቀትን ሰጠ፣ ለዓረቦች የነዳጅ ማዕድን ሰጠ፡፡ ለእኛም የገንዘብ ማዕድን ሰጥቶን ይሆናል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ማወቅ ለሚፈልግ መናገር ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ ያነበበም በብሔራዊ ባንክ የሚዘጋጁ የጥሬ ገንዘብና ሌሎች የኢኮኖሚ ሪፖርቶችን በቀላሉ ሊረዳና ሊተነትን ይችላል፡፡
አንዳንዴ ሳስበው ጥቂት የመንግሥት ሰነዶችን ከማስተዳደር በቀር አብዛኛው ሥራው እንደ ቀድሞው ስሙ የግምጃ ቤት ሥራ ወይም የጓዳ ሚኒስቴርን ሥራ የመሰለ፣ የመንግሥትን ጥሬ ገንዘብ ገቢና ወጪ በጀት ማስተዳደር የሆነው የምወደው ትልቁ የቀድሞው መሥሪያ ቤቴ የገንዘብ ሚኒስቴር የሚለው ስያሜ ይገባዋል ወይ እላለሁ፡፡
የገንዘብ ዓይነቶችና ትርጉሞች
ደሃውም፣ ሀብታሙም፣ መሪውም፣ የተማረውም፣ ያልተማረውም፣ ፖሊሲ አውጪውም፣ ፖሊሲ አስፈጻሚውም፣ ሕግ አውጪውም፣ ሕግ ተርጓሚውም፣ ሕግ አስፈጻሚውም፣ ሸማቹም፣ ነጋዴውም… ገንዘብ ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አለማወቃቸውን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች በኢኮኖሚያችን ውስጥ በግልጽ ይታያሉ፡፡
ከእነዚህ ሁኔታዎችም ዋናው የገንዘብ ዓይነቶችን በሚያውቁት በአገርኛ ቋንቋ በጥሬነት ደረጃ ለይተው ሲጠሩ አለመሰማታቸውና ሁሉንም በጥቅሉ ጨፍልቀው ገንዘብ ብለው መጥራታቸው ነው፡፡ እኔም ለአንባቢ እንዲገባው ብዬ የጽሑፌን ርዕስ ጥሬ ገንዘብ ማለት ሲገባኝ ጨፍልቄ ገንዘብ ብዬአለሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን ትክክለኛውን ስያሜ በትክክለኛው ቦታ እጥቀማለሁ፡፡
በተለይም ስለኢኮኖሚ ጉዳይና ስለዋጋ ንረት ለሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን ንግግር የሚያደርጉ ፖለቲከኞችና የኢኮኖሚ ባለሟሎች፣ የኢኮኖሚውንና የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ተዛምዶን ለመግለጽ ትክክለኛውን ስያሜ አለመናገራቸው ለኢኮኖሚ ባለሙያ አደናጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ቋንቋችን በቂ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም፡፡ የቃላት እጥረትም የለበትም፡፡ ቢኖርበትም እንኳ ሐሳብን በሁለትና በሦስት የቃላት ሐረግ መግለጽ ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚ ሙያ ቃላትንና ሐሳቦችን በራሱ ቋንቋ የሚናገርና አሳውቆ እንዲናገሩና እንዲጽፉ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ባለሟል ነው የጠፋው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንስ ምን እየሠሩ ይሆን ያንኑ ፈረንጅ የነገራቸውን መልሰው መላልሰው ማስተጋባት ብቻ ሆነ እንዴ ሥራቸው?
በዩኒቨርሲቲዎቻቸው እንግሊዝኛን በአማርኛ የሚማሩት የሰላሳ ስንት ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቃን እንኳ ሐሳቡ በደንብ ሳይገባቸው በእንግሊዝኛ የተጻፈውን ቃል ከሌላው የሰሙትን ይደግማሉ እንጂ፣ ምንነቱን መርምረው በራሳቸው ቋንቋ መናገር አይችሉም፡፡ ለነገሩ የቀድሞዎቹ ያልመረመሩትን አዲሶቹ እንዴት ይመረምሩታል?
ገንዘብን ሀብት ለማለትም፣ ገንዘብ ለማለትም፣ ጥሬ ገንዘብ ለማለትም፣ እርሾ ጥሬ ገንዘብ ለማለትም፣ ምንዛሪ ለማለትም፣ ሁሉንም በአንድ ላይ ጨፍልቀን በአንድ ቃል ገንዘብ ስለምንል ሐሳቦች አይገቡንም፣ ይምታቱብናል፡፡ በዚህ የጥቅል ስም የኢኮኖሚ አማካሪዎች ባለሟሎችም ሆኑ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች ምኑን ተረድተውና አውቀው እንዴት የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ እንደሚነድፉ እግዜር ይወቀው፡፡
በዚህ ጽሑፍ የገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ ዘርዝረን እንመለከታለን፡፡ ከዝርዝሩ ወደ ጥቅሉ ወደ ላይ ስንወጣ የተሰራጨ ምንዛሪ ማለት በገበያ ውስጥ የሚዘዋወሩትንም ሆነ በባንክ ካዝና የተቀመጡ ብርና ሳንቲሞችንም ማለት ነው፡፡ እርሾ ጥሬ ገንዘብ ማለት ምንዛሪዎችንና የንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የግዴታና የውዴታ ተቀማጮችን ማለት ነው፡፡
እርሾ ጥሬ ገንዘብንና በንግድ ባንኮች ውስጥ የተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባና የጊዜ ተቀማጮችን በአንድነት ጥሬ ገንዘብ እንላለን፡፡ እርሾ ጥሬ ገንዘብና በንግድ ባንኮች ውስጥ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ጠባብ ጥሬ ገንዘብ ሲሆኑ፣ የቁጠባና የጊዜ ተቀማጮች ጥሬ ገንዘብ አካሎች ከጠባብ ጥሬ ገንዘብ ጋር ሲደመሩ ሰፊ ጥሬ ገንዘብን ይሰጡናል፡፡ ጥሬ ገንዘብንና የአክሲዮን ሰነዶችን ብድሮችን ውሎችን በአንድነት ገንዘብ እንላለን፡፡
ፈረንጆች ሐሳቡ የሚገባ መሆኑ እንጂ ቃላት የመገጣሙ ጉዳይ ስለማያሳስባቸው እርሾ ጥሬ ገንዘብን በሦስት ዓይነት ሐረጐች (Reserve Money) ወይም (High Powered Money) ወይም (Monetary Base) ብለው በሦስት አማራጮች ይጠራሉ፡፡
እኔም ሐሳቡ ብቻ ለአንባቢ ይግባ በማለት የቃላት ምርጫው ሳያሳስበኝ እርሾ ቡኮን ኩፍ አድርጎ አንስቶ ትልቅ እንደሚያደርገው፣ እንደዚሁ እርሾ ጥሬ ገንዘብ በአርቢዎች ረብቶ የጥሬ ገንዘብ ክምችት መጠን ወይም የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ስለሚሆን ከላይ የሰጠሁትን ስያሜ ተጠቅሜአለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የገንዘብ ገበያ ስለሌለና ለግብይት የምንጠቀመው ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ በጥሬ ገንዘብ ስለሆነ፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ጥሬ ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ማሳየት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ሙያ ትንታኔ ደረጃና በፖሊሲ ወይም በኢኮኖሚ ዕቅድ አገላለጽ አንዱን ቃል በሌላው ተክቶ መናገርና መጻፍ ፈጽሞ አላዋቂነት ሲሆን፣ ተናጋሪ የሚናገረውን እንደማያውቅ የሚያሳብቅም ነው፡፡
የጥሬ ገንዘብ አሠራጮች
የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን በመወሰን በማሠራጨትና በመጠቀም ረገድ የራሳቸውን ድርሻ የሚጫወቱ አካላት አንደኛ ብሔራዊ ባንክ እርሾ ጥሬ ገንዘብን በማሰራጨት፣ ሁለተኛ ኅብረተሰቡ ከሸመታ የተረፈውን ጥሬ ገንዘብ ባንክ በማስቀመጥና ሦስተኛ ንግድ ባንኮች ኅብረተሰቡ ያስቀመጠውን ጥሬ ገንዘብ አርብቶ በማበደር ስለሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ለጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምን ዓይነት ሚና እንደሚጫወቱ እንመለከታለን፡፡
በ1985 ዓ.ም. አሥር ቢሊዮን ብር የነበረ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን አርባ እጥፍ አድጎ ዛሬ ወደ አራት መቶ ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ማን ነው የገንዘቡን መጠን እንደዚህ የሚያሳድገው? ለምንስ ነው የሚያሳድገው? ትክክለኛው ተፈላጊ የገንዘብ መጠን እንዴት ያውቃል? ይህ በእርግጥ ኢኮኖሚውን ያሳድጋል ወይም ማስመሰያ ዕድገት ነው? ከእንግዲህ ዕድገቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ቢቀጥል እንደታሰበው በቅርብ ጊዜ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ በፍጥነት ያስገባናል? ወይስ የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈጥራል?
በኅብረተሰቡ ጥሬ ገንዘብ ለምን ለምን ጉዳዮች እንደሚፈለግና የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት ተጣጥመው ኢኮኖሚውን እንደሚያሳድጉ ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡ ከዚህ ቀጥለን ጥሬ ገንዘብን ማን እንደሚያቀርብ፣ የገንዘብ አቅርቦትን የሚወስኑ ጉዳዮች ምንና ምን ያህል እንደሆኑ እንመለከታለን፡፡
ብሔራዊ ባንክ
ብሔራዊ ባንክ ምንዛሪ ያሠራጫል፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ይይዛል፣ ለውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የክፍያ ሚዛን ዓላማ ይበደራል፣ የመንግሥት ባንክ ሆኖ ይሠራል፣ የመንግሥት ሰነዶችን ግዢና ሽያጭ ያካሂዳል፣ ለመንግሥትና ለንግድ ባንኮች ያበድራል፣ የውጭ ምንዛሪ ይገዛል፣ ይሸጣል፣ የጥሬ ገንዘብን መጠን ለመቆጣጠር ሕግ ያወጣል፣ የባንኮች ባንክ ሆኖም ይሠራል፡፡
ብሔራዊ ባንኩ የጥሬ ገንዘብ መሠረት የሆነውን እርሾ ጥሬ ገንዘብ ይፈጥራል፡፡ የእርሾ ጥሬ ገንዘብ መጠንንም በመቆጣጠር የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን ይቆጣጠራል፡፡ ብቸኛ የእርሾ ጥሬ ገንዘብ አቅራቢ በመሆን ብሔራዊ ባንክ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ አውጪም ነው፡፡ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ሒደት መጀመሪያ ብሔራዊ ባንክ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ምንዛሪ ብሮችና ሳንቲሞች አሳትሞ ለሕዝብ ባለዕዳ ሆኖ ያሠራጫል፡፡
ለሕዝብ ባለዕዳ የሚሆንበትም ግለሰቦች ምንዛሪውን እንደ መገበያያ መሣሪያ የሚቀበሉት ምንዛሪው ዋጋ እንደማያጣ ብሔራዊ ባንክ ዋስትና ስለሚሰጣቸውና በእምነት መገበያየት እንደሚችሉ ስለሚረዱ ነው፡፡ ሻጭና ገዢ ተገበያዮች ለክፍያ እንዲቀበሉ በሕግም ያስገድዳል፡፡
ይህ በገበያ ውስጥ የሚዘዋወርና በንግድ ባንኮች ካዝና ውስጥ የሚገኝ በኢኮኖሚ ውስጥ የተሠራጨ ምንዛሪ የእርሾ ጥሬ ገንዘብ አንዱ ክፍል ሲሆን፣ ሌላው ብሔራዊ ባንኩ ለንግድ ባንኮች ባለዕዳ የሆነበት የመጠባበቂያ የግዴታና የውዴታ ተቀማጭ ነው፡፡
ይህ እርሾ ጥሬ ገንዘብ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምንጭ ነው፡፡ እርሾ ጥሬ ገንዘብ በአርቢ ተባዝቶ ወይም ረብቶ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ወይም ጠቅላላ ገበያ ውስጥ የቀረበ የጥሬ ገንዘብ ክምችት መጠን ይሆናል፡፡
የሕዝብ የጥሬ ገንዘብ አጠቃቀም
የጥሬ ገንዘብ አገልግሎቶች ብዙ ቢሆኑም ከዋነኞቹ ውስጥ ጥቂቱ የዕቃን ዋጋ ከመተመን ባሻገር ሸቀጦችን ማገበያየትና ንብረትን ለወደፊት በጥሬ ገንዘብ መልክ ለመያዝ ያገለግላል፡፡ የተለያዩ የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶች የተለያየ ትርፋማነት ወይም ወለድ መጠን ስላላቸውም ሰዎች ጥሬ ገንዘባቸውን በተለያየ የማስቀመጫ ዓይነት ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ምንም ዓይነት ወለድ አያስገኝም፡፡ የቁጠባ ተቀማጭና የጊዜ ተቀማጭ የተለያየ ወለድ መጠን አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ሰዎች ንብረታቸውን በአራት መልክ ይይዛሉ፡፡ እነሱም፣
- በምንዛሪ መልክ በኪሳቸው ውስጥ ወይም በባንክ ተቀማጮች መልክ በጥሬ ገንዘብነት፣
- ቦንድን በመሳሰሉ የብድር ሰነዶች፣
- አክሲዮኖችን በመሳሰሉ ሰነዳዊ ገንዘቦችና
- ቁሳዊ ንብረቶች ናቸው፡፡
ከእነዚህ የንብረት ዓይነቶች የትኞቹን እንደሚይዙ የሚወሰነው በሦስት ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡
- ከሌሎቹ የንብረት ዓይነቶች ጋር ሲመዛዘን ለወደፊት ያስገኛል ተብሎ የሚታሰበው ትርፋማነት፣
- የመክሰርና የአደጋ ሥጋትና
- የንብረቱ ጥሬነት ደረጃ ናቸው፡፡ ጥሬነት ማለት በግብይት ጉዳይ ሲፈለግ መሸጥ፣ መለወጥ፣ መሯሯጥ ሳያስፈልግ ወዲያው መገኘት ማለት ነው፡፡
የቁሳዊ ንብረቶች ገበያና ዋጋ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ ትኩረታችን በገንዘብ ንብረቶች ሁኔታ ላይ ብቻ ነው፡፡ የገንዘባዊ ንብረቶች ትርፋማነት ሁለት መልክ አለው፡፡ ከንብረቱ የሚገኝ ወለድ ወይም ዲቪደንድና የንብረቱ የገበያ ዋጋ መጨመርና መቀነስ ናቸው፡፡
በኪስ የሚያዙ ምንዛሪዎችና በባንክ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ (Demand Deposit) በጣም ጥሬ ገንዘቦች ሆነው ትርፋማነታቸው ግን ባዶ ነው፡፡ የተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ጥሬነት የሚገለጸው አስቀማጩ ባንክ መሄድ ሳይኖርበት ለሌላ ሰው ቼክ ጽፎ በመስጠት ብቻ ክፍያ መፈጸም መቻሉ ነው፡፡ ይህም የምንዛሪዎችን ያህል ጥሬ ያደርገዋል፡፡
ሰዎች ንብረታቸውን በምንዛሪና በተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ቢይዙ በቦንድ ወይም በቁጠባና በጊዜ ተቀማጭ ቢይዙ ኖሮ አሊያም አክሲዮን ቢገዙ ሊያገኙ የሚችሉትን ወለድ ወይም ዲቪደንድ ትርፋማነት ያጣሉ፡፡
ገንዘብ ራሱ እንደማንኛውም ሸቀጥ ፈላጊና አቅራቢ የገበያ ቦታና የገበያ ዋጋም ያለው ሸቀጥ ነው፡፡ ትርፍና ኪሳራም ያመጣል፡፡ የትርፋማነት ደረጃውም በጥሬነትና ጥሬ ባለመሆን ደረጃው ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
ንግድ ባንኮች
የጥሬ ገንዘብ ተቀማጮችን ከቆጣቢዎች በመቀበል ለተበዳሪዎች የማበደር የአስተላላፊነት ሥራ የመሥራት ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ንግድ ባንኮች ብቻ ናቸው፡፡
ንግድ ባንኮች አራት ዋና ኢኮኖሚያዊ ሚናዎችን ይጫወታሉ፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው ከቆጣቢዎች ተበድረው ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በማበደር በቆጣቢዎችና በመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መካከል የአስተላላፊነት ሚና ይጫወታሉ፡፡
ሁለተኛ ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንኩ የሚፈልግባቸውን መጠባበቂያ የግዴታ ተቀማጥ ሒሳብ ብቻ ይዘው፣ ሌላውን ከቆጣቢዎች የሰበሰቡትን ብርና ሳንቲም ምንዛሪ አርብተው በማበደር በኢኮኖሚው ውስጥ በርካታ ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ ወይም የብድር ጥሬ ገንዘብ ይፈጥራሉ፡፡
ሦስተኛ የንግድ ባንኮች ተቀማጭ በመቀበልና ብድር በመስጠት የውስጥ ፖሊሲያቸው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንንና ጥሬነትን ይወስናሉ፡፡ ለቆጣቢዎች የሚሰጧቸው ማነቃቂያዎችና ከተበዳሪዎች የሚሹዋቸው መያዣዎች የውስጥ ፖሊሲ ውሳኔዎቻቸው ናቸው፡፡
አራተኛ የብሔራዊ ባንኩ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን ለመቆጣጠር የሚያወጣቸውን ሕጐች ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ፣ አጠቃላዩን የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ወደ ሕዝብ ያስተላልፋሉ፡፡
የብድር ዕርባታ
ንግድ ባንኮች ከቆጣቢዎች ተቀማጭ ውስጥ በሕግ ለመጠበቂያ የሚፈልግባቸውንና በብድር የተረፋቸውን ወይም በራሳቸው ፈቃድ በጥንቃቄ ሊይዙ የሚፈልጉትን ምንዛሪ በብሔራዊ ባንክ አስቀምጠው፣ አብዛኛውን ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ደጋግመው ብድር በመስጠት ያረቡታል፡፡
ስለዚህም የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ወሳኞች አንደኛ ብሔራዊ ባንኩ ባለዕዳ በሆነበት እርሾ ጥሬ ገንዘብ መጠን፣ ሁለተኛ ኅብረተሰቡ በገቢ መልክ እጁ የገባውን ብርና ሳምንቲም ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ ቆጥቦ በተንቀሳቃሽ በቁጠባና በጊዜ ተቀማጭ ባንክ ለማስቀመጥ በመወሰንና ሦስተኛ ንግድ ባንኮች ኅብረተሰቡ ያስቀመጠውን ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ አራብተው በማበደር ናቸው፡፡
ንግድ ባንኮች ብድርን እንዴት እንደሚያረቡ ለመረዳት በምሳሌ መመልከት ይቻላል፡፡ አንድ ሰው አንድ ሺሕ ብር አቢሲኒያ ባንክ ቢያስቀምጥ ባንኩ ሁሉም አስቀማጮች በአንድ ጊዜ ገንዘባቸውን እንደማያወጡ ስለሚያውቅ ከተቀመጠው አንድ ሺሕ ብር ውስጥ አሥር በመቶውን አንድ መቶ ብር በብሔራዊ ባንክ ለሚፈለግበት መጠባበቂያ ተቀማጭ አስቀርቶ፣ ዘጠና በመቶውን ዘጠኝ መቶ ብር ለአንደኛ ተበዳሪ ሰው ያበድራል፡፡
አንደኛው ተበዳሪ ሰው በገንዘቡ ዕቃ ገዝቶ ዕቃውን ለሸጠለት ሰው ሲከፍል ዕቃውን የሸጠው ሰውም ዘጠኝ መቶ ብሩን ከገዢው ተቀብሎ ዳሸን ባንክ ቢያስቀምጥ፣ ዳሸን ባንክም የዘጠኝ መቶ ብሩን አሥር መቶኛ ዘጠና ብር በብሔራዊ ባንክ ለመጠባበቂያነት አስቀምጦ ስምንት መቶ አሥር ብሩን ለደንበኛው ሁለተኛ ተበዳሪ ሰው ያበድራል፡፡ ተበዳሪውም ዕቃ ገዝቶ ስምንት መቶ አሥሩን ብር ለዕቃ ሻጩ ይከፍለዋል፡፡
ተከፋዩም ስምንት መቶ አሥር ብሩን ንብ ባንክ ቢያስቀምጥና ንብ ባንክም የዚህን አሥር መቶኛ ሰማንያ አንድ ብር ለመጠባበቂያ ተቀማጭነት በብሔራዊ ባንክ አስቀምጦ ቀሪውን ሰባት መቶ ሃያ ዘጠኝ ብር ለደንበኛው ያበድራል፡፡ እንዲህም እያለ ሲቀጥል አንዷ ሺሕ የመጀመሪያ ተቀማጭ ረብታ 1000 + 900 +810 +729 + ለባንኮቹ የሦስት ሺሕ አራት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ብር ብድር ትፈጥራለች፡፡
ስለዚህም ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንኩ ያሰራጨውን ብርና ሳንቲም ምንዛሪ ብዙ ጊዜ አርብተው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱን ብዙ ያደርጋሉ፡፡
ንግድ ባንኮቹ የአስቀማጮቹን ገንዘብ ያለሥጋት ለሌሎች የሚያበድሩት ሁሉም አስቀማጮች ገንዘባቸውን ለማውጣት በአንድ ጊዜ ስለማይመጡ ችግር አይገጥመንም በሚል ተስፋና ቢመጡባቸውም ብሔራዊ ባንኩ እንደሚታደጋቸው፣ ወይም የጎደለበት ባንክ ከተረፈው ባንክ እየተበዳደሩ ለአስቀማጩ መክፈል እንደሚችሉ በማመን ነው፡፡
ሲጀምሩ በተከራዩት ደሳሳ ጎጆ ሲያገለግሉ የነበሩትና በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ያደጉት የግል ንግድ ባንኮች በአዲስ አበባ የሚያማምሩ ሕንፃዎችን ገንብተዋል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ ከየት አገኙ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሰው ቢኖር መልሱ ይህ የብድር ዕርባታና ለቆጣቢው አስቀማጭ የሚከፍሉት ወለድ መጣኝ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡
የእርሾ ጥሬ ገንዘብ ዕርባታ
በብሔራዊ ባንክ የቀረበው እርሾ ጥሬ ገንዘብ በቆጣቢዎች በባንክ አስቀማጭነትና በባንኮች አርብቶ አበዳሪነት ረብቶ አጠቃላዩን ለገበያ የቀረበ የጥሬ ገንዘብ መጠን ይሆናል፡፡ ስለዚህም ለገበያ የቀረበው ጠቅላላ የጥሬ ገንዘብ መጠን ለእርሾ ጥሬ ገንዘብ ሲካፈል የአርቢውን መጠን ይሰጠናል፡፡ ጥሬ ገንዘብም በአርቢ ዕድገት ወይም በእርሾ ጥሬ ገንዘቡ ዕድገት ምክንያት ያድጋል፡፡
የአርቢው መጠን ለውጥ የሦስት አካላትን ባህርይ ወይም ድርጊት ያመለክታል፡፡ አንደኛ ብሔራዊ ባንክ ምን ያህል የመጠባበቂያ ግዴታ በንግድ ባንኮች ላይ እንደሚጥል፣ ሁለተኛ የንግድ ባንኮች ምን ያህል ከመጠባበቂያ ግዴታ በላይ በገዛ ፈቃዳቸው የውዴታ ተቀማጭ መያዝ እንደሚፈልጉ፣ ሦስተኛ ሕዝቡ በወለድ መጣኝ ለውጦች ምክንያት የገንዘብ ይዞታውን ጥምረት ማለትም ምን ያህሉን በምንዛሪ መልክ ምን ያህሉን በተንቀሳቃሽ ተቀማጭና ምን ያህሉን በቁጠባና በጊዜ ተቀማጭ መልክ ለመያዝ በመፈለጋቸው ነው፡፡
በመሆኑም ብሔራዊ ባንኮች ብቻቸውን የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን መወሰን አይችሉም፡፡ ቢሆንም አርቢው ቋሚ ከሆነና ሊተነብዩት ከቻሉ ለኢኮኖሚው የሚያስፈልገው የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ለመድረስ የሚፈልገውን የእርሾ ጥሬ ገንዘብ መጠን መወሰን ይችላሉ፡፡
የሊስትሮው ተስፋ
በዚያን ሰሞን የኮንዶሚኒየም ቤት ታገኛላችሁ ተብለው ሊስትሮዎች ጫማ ጠርገው ያኙትን ብር በሚያከስር ወለድ በንግድ ባንክ አስቀምጡ ተባሉ፣ አስቀምጠው ከሰሩ፡፡ ሳልባጅ ነጋዴዎችም የቤት ውስጥ አገልጋዮችም የላባቸውን ፍሬ በኪሳራ ባንክ አስቀምጠው ዛሬ ብሮቻቸው ሸቀጥን የመግዛት አቅማቸው ከቀድሞ ያነሱ ሆነዋል፡፡
አካላቸውን ሸጠው ብዙ እህቶቻችን ያልፍልናል ብለው ይቆጥባሉ፡፡ የወላጆቻቸውን ውለታ ለመክፈል ሲሉ በበረሃና በባህር ለመጓዝ ያሰቡ ወጣቶች ይቆጥባሉ፡፡ ጠላ ጠምቀው ካቲካላ ቀቅለው ድሆች ይቆጥባሉ፡፡ ሽንኩርት ቸርችረው፣ ኩበት ለቅመው፣ እንጀራ ጋግረው፣ የማገዶ እንጨት ከዱር ለቅመው፣ ውኃ ከምንጭ ቀድተው ሰዎች ይቆጥባሉ፡፡
በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በኩራዝ ብርሃን እያዩ፣ በሳር ክዳን ጣሪያ ቤት ውስጥ እየኖሩ፣ በእንጨትና በፍም እያበሰሉ፣ ገበያ ለማግኘት አራትና አምስት ሰዓት እየተጓዙ ሰዎች ይቆጥባሉ፡፡
ግንቦት 3 ቀን 2008 በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹የቁምራ ዘመን ቁጠባ›› በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ በምሳሌ እንዳመለከትኩት፣ በአሥራ ሁለት በመቶ የዋጋ ንረት የገንዘብ ሸቀጦችን የመግዛት አቅም በአሥራ ሁለት በመቶ ስለሚወድቅ አምስት በመቶ የቁጠባ ወለድ እያገኘ ገንዘቡን ባንክ የሚያስቀምጥ ሰው ለተበዳሪው ሰባት በመቶ ከፍሎ እንዳበደረ ወይም ገንዘቡን በሰባት በመቶ ኪሳራ እንደሸጠ ይቆጠራል፡፡
በ25 ዓመታት ውስጥ በ34 በመቶ እና በ10 በመቶ መካከል የሚዋዥቀውን የዋጋ ንረት አማካይ 15 በመቶ አድርገን ብንወስድና በዚሁ ጊዜ በሦስት በመቶና በአምስት በመቶ መካከል የነበረውን የቁጠባ ወለድ መጣኝ አማካይ አራት አድርገን ብንወስድ፣ በ25 ዓመት ውስጥ በዓመት በአማካይ 11 በመቶ ቆጣቢ በተበዳሪው ተነጥቋል፡፡
የዘንድሮውን 216 ቢሊዮን የጊዜና የቁጠባ ተቀማጭ በ11 በመቶው ብናበዛ 24 ቢሊዮን ብር ገደማ ደሃ ቆጣቢው በተበዳሪው ሀብታም ተመዝብሯል፡፡ የሃያ አምስት ዓመቱን በተመሳሳይ መልክ ብናሰላ ስንት ዓባዮችን እንገድብ ነበር? ስንት የጎጆ ፋብሪካዎችን እንከፍት ነበር? ከድህነት የሚያወጡን ብዙ ሥራዎች እንሠራበት ነበር፡፡ ሀብታም መዝብሮ ፎቅ ብቻ ሠራበት እንጂ፡፡
ብድር እንደ ጥሬ ገንዘብ ይቆጠራልና ንግድ ባንኮች የቆጣቢውን ተቀማጭ ብዙ እጥፍ አርብተው በማበደር የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱን ከልክ በላይ አድርገው የሸቀጦች ዋጋ እንዲወደድ ከማድረጋቸውም በላይ፣ ለቆጣቢው የሚያከስረውን አምስት በመቶ ብቻ ወለድ እየከፈሉ እነሱ ግን ገንዘቡን እስከ አሥራ አምስት በመቶ ወለድ ስለሚያገኙበት ትርፋማነታቸው ምን ያህል እንደሆነ መገመት አያቅትም፡፡ ታዲያ በአዲስ አበባ ብዙ ሕንፃዎችን እነሱ ቢገነቡ ገንዘቡ ከየት እንደመጣ እስካወቅን ድረስ ምን ይገርማል?
የገንዘብ አገልገሎት ዋጋ የሆነው ወለድ ብዙ ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ጽንሰ ሐሳቦቻቸውን የተነተኑበት መሣሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ስሙ እስከዛሬ የገነነው ታላቁ ኢኮኖሚስት ጆን ሚናርድ ኬንስ ለኢኮኖሚ ትንታኔው መነሻ ያደረገው የቦንድ ገበያ ዋጋ ትርፋማነት ወለድ መጣኝን ነው፡፡
የወለድ መጣኝ ቁጠባንና መዋዕለ ንዋይን ስለሚወስን ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ቦታ አለው፡፡ በእኛ አገር የወለድን መጣኝ በገበያ ዋጋ እንዳይተመን በሕግ ደንግጎ ቆጣቢው እየተመዘበረ ባለበት ሁኔታ፣ ለመዋዕለ ንዋይ የሚሆን ገንዘብ ጠፋ ተብሎ ይጮሃል፡፡
በከዘራ የሚራመድ አዛውንትና በአርተፊሻል የድጋፍ ፖሊሲ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ አዛውንቱ ከዘራ የሚጨብጥ እጁ ላልቶ መራመድ ተስኖት አልጋ ላይ ይውላል፡፡ በድጋፍ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚም እንደዚሁ ነው እጁም እግሩም ይሽመደመዳል፡፡
በኢሕአዴግ ጥሬ ገንዘብ በብዛት ረጭቶ ገንዘብ ባህር ውስጥ ገብታችሁ ተንቦጫረቁ ወይም ተሻሙና ያሸነፈ ይውሰድ ፖሊሲ ጥቂቶች ተሻምተው ከብረዋል፡፡ በእርግጥ በሕዝብ መፍጨርጨር ኢኮኖሚውም ለጊዜው ተስፋፍቷል፣ አብጧል፡፡ አሁን ግን ፖሊሲው አርጅቷል፡፡ ከእንግዲህ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡
ዋጋን ያንራል፣ የውጭ ምንዛሪን ያሟጥጣል፣ ኢኮኖሚውንም እንደሚፈለገው አያሳድግም፡፡ የገንዘብ ባህሩ ጥልቀት ሲጨምር ጭነቱ እንደበዛበት መርከብ ሁላችንም ባህሩ ውስጥ ገብተን እንሰጥማለን፡፡ የዋጋ ንረቱ እንደ እስከዛሬው በሃያ አምስት በመቶ ካደገ አሥር በመቶው በአሥር በመቶ ለሚያድገው ኢኮኖሚው ሲሆን፣ ቀሪው አሥራ አምስት በመቶ ዋጋን ያንራል፡፡
የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት ባለሥልጣን የሆነው ብሔራዊ ባንኩ በሚያወጣቸው የቁጥጥር ሕጐች አማካይነትና በግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ አማካይነት የንግድ ባንክ ተቀማጮችን መቆጣጠር ተስኖት ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ጥሬ ገንዘብ ገበያ ውስጥ ገብቶ የሸቀጦችን ዋጋ ማስወደዱን ስናይ፣ በመጠባበቂያ ተቀማጭ አማካይነት ሊቆጣጠራቸው የማይችሉ የገንዘብ ገበያ ሰነዶች ግብይት ቢጀመር ኖሮ ምን ይውጠን እንደነበርም እንረዳለን፡፡
እኔን ለመሳሰሉ የካፒታል ገበያና የጥሬ ገንዘብ ገበያ በአጠቃላይ የገንዘብ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን አይቋቋምም ለምንል ሰዎች ብሔራዊ ባንኩ በቂ መልስ አለው፡፡ በማን አቅም ነው ይህ የሚሆነው? የጥሬ ገንዘብ ገበያውን እንቅስቃሴ መምራት አልቻልኩም ይለናል፡፡
ለነገሩማ የግብርና ኢኮኖሚ ምን ጣጣ አለው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦ ማረስ ነው፣ ከዚያም ሰብስቦ መብላት ነው፣ መጠጣት ነው፣ መጥገብ ነው፣ ከድህነት መላቀቅ ነው፣ በግብርና ባህር ተሳፍሮ መካከለኛ ገቢ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ይህን አይቼ ነው እኔም ከሁለቱም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቻችን በላይ ከተጻፈ መቶ ዓመት ገደማ የሆነው የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› መጽሐፍ በሳይንሳዊነቱና መንግሥት ምን እንደሚሠራ በዝርዝር በማቅረብ የተሻለ የዕቅድ ዶክመንት ይወጣዋል የምለው፡፡
No comments:
Post a Comment