አንዳንድ የምዕራብ መንግሥታት በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ባላቸው ጥቅምና ቀዝቃዛ ጦርነት በወለደው ፉክክር ተገፋፍተው፣ በወያኔ ስም የሚጠራውን የድሮውን የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር በአፄ ምኒልክ ዙፋን ካስቀመጧቸው ጊዜ ጀምረው፣ መሪዎቹ በስመ የብሔር ብሔረ-ሰቦች ነፃነትና እኩልነት ከፍተኛ ያስተዳደር ክልል ለውጥ አድርገዋል። ከነዚህ ለውጦች መካክል ቀንደኛ ቦታ ይዞ የሚገኘው የኢትዮጵያን መሬት እነሱ ላመኑበት ዓላማና ዕቅድ በሚመቻቸው መንገድ፣ ዘርማንዘርን መሠረትና መስፈርት ባደረገ መልኩ ሸንሽኖ በመከለል፣ በዚህ መንገድ የተፈጠረው እያንዳንዱ ጐሣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የሚትባል አገር ከተፈጠረች ጀምሮ በልዩ ልዩ መልክና መንገድ በመወላለድና በመቀላቀል የተዋሐደውንና የተሳሰረውን ሕዝብ፣ በዚህ ወያኔ በፈጠረው የምናብና የልበወለድ ምሥል ያገሪቷን ሕዝብ መከፋፈሉ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን አጨቃጫቂም ሁኗል ማለት ነገሩን በጣም አቅልሎ ማየት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በተወሰኑት አካባቢዎች ወደ ታላቅ ሽብርና ጦርነትም መርቷል።
ወያኔ እንደ አውሮጳ አቈጣጠር (አ. አ.) በሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹና ሰባዎቹ መኻል አብዛኛውን ዓለምንም ሆነ፣ ኢትዮጵያን ያናውጥ የነበረ የወጣቱ ተማሪ እንቅስቃሴ ርዝራዥ መሆኑ መረሳት የለበትም። ይሁንና ወጣትነት በዐዋቂነት፣ ከዚያም በሽማግሌነት ሲተካ ገጠመኛቸው እየሰፋ፣ ያስተሳሰብ ችሎታቸውም እየረቀቀና እየተሻሻለ ሄዶ፣ ከነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ አሁን አድገውና በስለው ወደኋላ ተመልሰው ያኔ ይሠሩት የነበሩትን ድርጊቶች ሲመለከቱ፣ አንዳንዶቻቸው ሲስቁበት፣ ሌሎቹ ሲጸጸቱበት ይታያል። ወያኔዎች ግን ለዚህ የታደሉ አይመስሉም። ከልጅነት እምነታቸውና ግትርነታቸው ፈቀቅም አላሉም። በቅዱስ መጽሐፍ አነጋገር፣ እንደግብጻዊው ፈርዖን ልባቸው እንደነደነ፣ አንገታቸው እንደገዘፈ፣ ርእዮታቸው በቅዠትና በምናብ ዓለም እንደተሰቀለ ቀርቷል። ከዕድሜና ከትዝብት ማለትም ከገጠመኝ የሚመጣው የአእምሮና የአስተሳሰብ ብስለት ሳይጐበኛቸው ወደሕይወታቸው መጨረሻ እየቀረቡ ናችው። ሥልጣናቸውን ያገኙት እንደአብዛኞቹ አላንዳች ዕፍረት እንደሚወቅሷቸው የድሮዎቹ አጤዎች በጒልበትና በጦር ኀይል ሲሆን፣ ግን እንደነሱ ሕዝቡን በማስደሰትና ጥቅሙን በመጠበቅ የማስተዳደር ችሎታም ብቃትም ከቶ አላሳዩም ብቻ ሳይሆን አገሩን የብዝበዛና የወረራ ምድር እንጂ እንደእናትና እንደትውልድ አገራቸው አድርገው አላዩትም ማለቱ ስሕተት አይመስለኝም። ይኸ ሁናቴ ግን ከፍተኛና ሰፋ ያለ የታሪክ፣ የኅብረተሰባዊና የሥነልቡና ትንተናና ጥናት የሚፈልግ ራሱን የቻለ ርእስ ስለሚፈልግ ለጊዜው አልፈዋአለሁ።
የዛሬ ጽሑፌ የሚያተኩረው ለብዙ ጊዜ አነታራኪ ሁኖ ቈይቶ፣ አሁን ግን እየከፋ መጥቶ፣ ወደጥኑ ጦርና ደም መፋሰስ ደረጃ ሊያደርስ የቀረበውን፣ በትግራይና በኩታገጠም አገሮች፣ በተለይም ጥንት በጌምድር፣ አሁን ደግሞ ጐንደር ተብሎ በሚጠራው ግዛት መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ላይ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ነገሩ የተነሣው በወያኔዎች የሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሞክራሲያዊ ግንባር መንግሥት የዘረጋው በዘርማንዘር ላይ የተመሠረተው የክልል መንግሥት ሥርዐት፣ ከማንኛውም ክልል ይበልጥ ትግራይን የሚበድል ሁኖ ስለተገኘ ይመስላል። ይኸንን ለመረዳት ብዙም መመራመር አይጠይቅም። ገና ወጣት ልጅ ሳለሁ ዕድል ገጥሞኝ ወደኤርትራ ለትምህርት ስሄድ፣ በጣም የገረመኝና በጭንቅላቴ ውስጥ እስካሁን ተቀርጾ የቀረ ነገር ቢኖር፣ እግሬ ትግራይን እንደነካ መሬቱ ከልክ በላይ ከመበላቱ የተነሣ ከድንጋይ ውጭ አፈር ማየት ብርቅ ነበር። ሕዝቡ በጣም የሚደነቅ፣ ጨዋና እጅግ በጣም በኢትዮጵያዊነቱ የሚኰራ ሁኖ ሳለ፣ መሬቱ ግን አሳዛኝ ነበር። እርሻው የጠጠርና ያፈር ድብልቅ፣ ጭንጫ መሬት ነው። ገና በልጅ እግርነቴም ቢሆን፣ ይኸ ምንድር ነው ብዬ ስጠይቅ እየተዘራ ያለ ማሳ ነው ሲሉኝ እጅግ ደነገጥሁኝ፤ እንዴት አባቱን እህል እዚህ መሬት ላይ ሊበቅል ይችላል ብዬ ላምን አልቻልኩም ነበር።
በተደጋጋሚ በተለያየ ቦታ እንደተጻፈውና እንደተገለጠው ወያኔ ገና የሽምቅ ጦርነቱን ሲያካሂድ ያለመውና የፀነሰው ዓላማ፣ ከኢትዮጵያ ነፃነቷን አግኝታ፣ ሀብታምና ኀያል የሆነች የትግራይን መንግሥት መፍጠር ነው። ይኸ ነገር እስካሁን ግቡን ባይመታም የወያኔ መሪዎች አሳቡ ስሕተት መሆኑንና፣ አሁን ግን እንደማይቀበሉት የገለጹትና የተናገሩት ነገር የለም። የረጅም ጊዜ ዓላማችን አይደለም ብለውም አልተናዘዙም። ይልቅስ የተያያዙት በጦር ሜዳ ላይ የጠነሰሱትን ዕቅድ በተግባር በማዋል ላይ መስሎ ይታያል። ዕቅዱም የሚከተለውን ይመስላል።
በነሱ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የትግራይ መልክዐ ምድር፣ የተወሰነ ቅርጽና ይዘት ኑሮት አያውቅም። በየጊዜው ይቀያየር ነበር። ከመላ ጐደል ግን፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በምሥራቅ ከቀይ ባሕር ሲካለል፣ በሰሜን በአሁኑ የኤርትራ መንግሥት ውስጥ የተጠቃለሉትን አብዛኞቹን አገሮች፣ በደቡብ ደግሞ አያሌውን የወሎን ክፍሎች ያካትት ነበር ባዮች ናቸው። ከዚህም የተነሣ የትግራይን የተፈጥሮ ሀብትና የአፈር ድኽነት፣ ከወሎና ከበጌምድር መሬቶች በመውሰድ ሊክሡ ፈለጉ። መንግሥት እንደመሆናቸው ሥልጣናቸውን በመጠቀም እንዳሉት መተገበር ጀመሩ። አንዳንድ የተማርን ዐዋቂዎች ነን ባዮች የአካባቢያቸው ምሁራንም የፈበረኩትን የታሪክ ማስረጃ በማቅረብ ድጋፋቸውን አበረከቱላቸው። እንደነዚህ እኔ ጥራዝ-ነጠቅ በምላቸው የታሪክ ምሁራን አባባል በሰሜን በጌምድር (በአሁኑ ቋንቋ ጐንደር) የሚገኙ ወልቃይት፤ ጸገዴ፣ ጸለምትና ሌሎችም እነሱን የመሳሰሉ አገሮች በተለያየ ጊዜ በትግራይ ገዢዎች አስተዳደር ሥር ነበሩ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል[1]።
ሐቁ ግን እጅግ ከዚህ የራቀ ነው። በእጃችን ያሉት የታሪክ ሰነዶች የሚነግሩንም ሆነ አገሩን ያስተዳድሩት የነበሩት ገዢዎች የሚሰጡን ማስረጃዎች በፍጹም ይኸንን አቋም አይደግፉም። ከውጭ አገር ጸሓፊዎች መካከል እንደ አ. አ. በሺ ስድስት መቶ ኻያ ዐራት ዓ. ም. ገደማ ወደኢትዮጵያ መጥቶ አገሩን ለረጅም ዓመታት ያህል ዙሮ የጐበኘው የጶርትጓሉ የማኅበረ ኢየሱሳውያን ቄስ አባ ማኑኤል ዳልሜይዳ፣ “የደጋው ኢትዮጵያ ወይንም የሐበሻ ታሪክ (Historia de Ethiopia a alta ou Abassia[2])” በተባለው መጽሐፉ የትግራይን ግዛት ርዝመትና ስፋት በመጠኑ ይገልጥልናል። እንዲሁም እንደ አ. አ. በሺ ስድስት መቶ ኻያ ዐራት ዓ. ም. ኢትዮጵያ ሄዶ መቀመጫውን ትግራይ ውስጥ አድርጎ ላሥር ዓመት ያኽል ባገሩ የኖረው አባ ማኖኤል ባራዳስ (Manoel Barradas) የተባለው ሌላ ኢየሱሳዊ፣ “በኢትዮጵያ ስለትግራይና አስተዳደሯ ዳግማዊ ሐተታ(Tratado secondo do regno de Tegre’ e seus mandos em Ethiopia[3])” በሚለው መጽሐፉ፣ የትግራይን ግዛት ክልልና ስፋት በደምብ አድርጎ ይተነትናል። ለናሙና ያህል የጠቀስኳቸውን የውጩን አገር ማስረጃዎች እዚሁ አቁሜ፣ ወዳገር ቤት ብገሠግሥ የነገሥታቱ ታሪኮች አሉ። እነሱም ደጋግመው የሚነግሩን ከጶርትጓሎቹ ማስረጃ የተለየ አይደለም።
በእነዚህ መረጃዎች መሠረት የትግራይ የሹመት ወይንም የግዛት ክፍሎች በተናጠል ሲዘረዘሩ፣ አክሱም ካለበት ትግሬ ከተባለው አውራጃ ራሱ፣ ቦራ፣ ሐዋዜን፣ መንበርታ፣ ሰለዋ፣ ሰሐርት፣ ሠራዬ (ሠራዌ)፣ ሺሬ፣ ተምቤን፣ ናግና፣ አበርጌሌ፣ አጋሜ፣ እንደርታ፣ ዐረብ፣ ዋጅራትና ገራልታ ናቸው። በጥንት እነዚህ ክፍለ-ግዛቶች በየራሳቸው ሹም ሲተዳደሩ፣ የመላው አገሩ የበላይ አስተዳደሪ ሁኖ የሚታወቀው “ትግሬ መኰንን” በሚል ማዕርግ የሚጠራው ሹም ነው። በቀረው ከትግራይ ማዶ ባለው አሁን ኤርትራ በመባል በሚታወቀው አገር ውስጥ ያሉት ክፍለ አገሮች የበላይ አስተዳዳሪ ባሕርነጋሽ ነበር። ግን በሺ ዐምስት መቶ ሰማንያ ዓ. ም. ላይ ባሕርነጋሽ ይስሐቅ ምፅዋን ይቈጣጠር ከነበረው ከቱርክ መንግሥት ጋር ጐን ሁኖ በመሰለፍ ቢሽፍትና፣ እናት አገሩን አብሮ ወግቶ ቢሸነፍ፣ ግዛቱ ለትግሬ መኰንን ተሰጥቶ ቀረ። ይኸም ሁናቴ ኢጣሊያን የድሮውን የባሕርነጋሽ ግዛት በጉልበት ወስዳ ኤርትራ ብላ አዲስ ስም አወጥታ በቅኝ ግዛት እስከያዘችበት ጊዜ ድረስ አልተለወጠም።
በኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ መንግሥቱ በዘመነ-መሳፍንት ወድቆ ከነበረበት፣ መልሶ በሦስቱ ነገሥታት (አፄዎቹ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምኒልክ) ጥረት በዘመናዊ መልኩ ከተቋቋመ በኋላም ቢሆን፣ ይኸ ያስተዳደር ክልል አልተቀየረም። በአፄ ኀይሌሥላሴም ዘመን የትግራይ ክልል በምዕራብ ከተከዜ ወንዝ፣ በደቡብ ከአላማጣ የማይሻገር እንደነበር፣ በጊዜው ጠቅላይ ግዛቱን የበላይ ሹም ሁነው ያስተዳድሩ የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ለአሜሪቃ የሬድዮ ድምፅ [Voice of America] በሰጡት መጠይቅ በይፋ በማያወላውል መንገድ ገልጠውታል[4]።
እንግዴህ የሰሜን ጐንደርም ሆነ የወሎ ክፍለ አገሮች የትግራይ ግዛት ክፍል ሁነው የሚገኙት በወያኔ መሪዎች ጭንቅላትና እነሱ በተጠናወታቸው ልማዳቸው መሠረት በቅርቡ በፈበረኩት ልበወለድ ታሪክ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። አፈታሪክም ሆነ የጽሑፍ ማስረጃዎች ግን በምንም መልክ አይደግፉም።
No comments:
Post a Comment