Wednesday, July 6, 2016

ለንደን፤ የኢራቁን ጦርነት የመረመረዉ ዘገባ በብሪታንያ


የቀድሞዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በጎርጎርዮሳዊዉ 2003 ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ላይ በከፈተችዉ በወጉ ያልታቀደ ጦርነት ሀገራቸዉ እንድትሳተፍ ማድረጋቸዉ ከፍተኛ ጥያቄ አስነሳ።
Großbritannien Chilcot-Bericht - PK Tony Blair
ረዥም ጊዜ የወሰደዉ ይህን ጉዳይ የተመለከተ ምርመራ ዉጤት ዛሬ ይፋ የተደረገ ሲሆን ጦርነቱ ከሕግ አኳያ የሚያጠያይቅ እና በመጥፎ ሁኔታ የተፈጸመ ተብሏል። የያኔዉን የኢራቅ ጦርነት የመረመረዉ ዘገባ በወቅቱ ብሪታንያ አሜሪካን መራሹን ወረራ የተቀላቀለችዉ ሌሎች አማራጮች በሙሉ ተሟጠዉ ሳይሞከሩ እና የቀድሞዉ የኢራቅ ፕሬዝደንት ሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ አላቸዉ በሚል የሀሰት የስለላ መረጃ ምክንያት መሆኑን ግልጽ አድርጓል። ብሌየር ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአንድ ዓመት በፊት ለያኔዉ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ጆርጅ W ቡሽ «ምንም ቢሆን ከጎንህ ነኝ» የሚል ቃላቸዉን በመስጠታቸዉም ትችት ደርሶባቸዋል። ምርመራዉ በስማቸዉ የተሰየመዉ የመርማሪዉ ቡድን መሪ ጆን ቺልኮት ያኔ ብሌየር የተሰጣቸዉን ምክር አለመቀበላቸዉን ነዉ የተናገሩት።
«ሚስተር ብሌየር ወታደራዊዉ ርምጃ አልቃይዳ በብሪታኒያ እና በብሪታኒያ ፍላጎት ላይ ስጋቱን ከፍ እንደሚያደርገዉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዉ ነበር። በተጨማሪም ወረራዉ የኢራቅ መሣሪያም ሆነ አቅም ወደአሸባሪዎች እጅ እንዲገባ ሊያደርገዉ እንደሚችልም ተነግሯቸዉ ነበር። አሁን ኢራቅ ላይ የነበረዉ መመሪያ ባልተጨበጠ የስለላ መረጃ እና ቅኝት ላይ የተመሠረተ እንደነበር ግልፅ ሆኗል።»
Großbritannien Chilcot-Bericht Anhörung und Ergebnis des Ausschusses
ለድርጊቱ ሙሉ ኃላፊነትን እንደሚወስዱ የገለፁት ቶኒ ብሌየር በበኩላቸዉ በእሳቸዉ መሪነት የተደረገዉ ሁሉ ዉሸትም ሆነ ማጭበር በር ሳይሆን የዉሳኔ ጉዳይ ነዉ ይላሉ።
«ይህ የሀሰት፤ የማጭበር በር ወይም የመመሳጠር ሳይሆን ጉዳይ ሳይሆን ዉሳኔ ነዉ። መወሰን ነበረብኝ፤ አምኜበት በመጨረሻም ምክር ቤቱም ሆነ ካቢኔዉ ሊከተል የሚችለዉን መዘዝ ችላ አለማለቱ ትክክል ነዉ።»
ዛሬ የቀረበዉ የምርመራ ዘገባ ሰባት ዓመታት ፈጅቷል። በወቅቱ ከ150 ሺህ የሚበልጡ የኢራቅ ዜጎች አልቀዋል። ኢራቅ የዘመቱ 178 የብሪታንያ ወታደሮች የሞቱ ሲሆን ሀገሪቱ ጦሯን በ2009 ዓ,ም ነዉ ከዚያ ያሰወጣችዉ። ከዚያ ወዲህ ኢራቅ በተለያዩ ግጭትና የሽብር ጥቃቶች እየተናጠች ሲሆን ባለፈዉ እሁድ በደረሰዉ የቦምብ ፍንዳታ ብቻ 250 ሰዎች ተገድለዋል። ለድርጊቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ኃላፊነት ወስዷል። በመቶ የተቆጠሩ የጦርነቱ ተቃዋሚዎች ዘገባዉ ዛሬ ከቀረበበት የስብሰባ ማዕከል ፊት ለፊት ተሰልፈዉ «ብሌየር በዋሹት ሺዎች ተገደሉ»፤ ብሌየር የጦር ወንጀለኛ የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ መዋላቸዉም ተገልጿል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ

No comments:

Post a Comment