ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ከቤታቸው እየወሰዳቸው ነው]

  • ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምንድን?
  • ምን ሆነዋል?
  • ተቃጠልኩ ባክህ፡፡
  • እሳት ነው ያቃጠልዎት?
  • ምን ይቀባጥራል ይኼ?
  • ታዲያ ኑሮ ነው ያቃጠልዎት?
  • ኧረ እዛው አንተ ራስህ ተቃጠል፡፡
  • ታዲያ ምን ሆነው ነው?
  • ኳስ ነው ባክህ፡፡
  • የምን ኳስ?
  • ኮፓ አሜሪካ፡፡
  • የአውሮፓ ዋንጫ ማለትዎ ነው?
  • የአውሮፓ ዋንጫ ማን ያያል? ኮፓ አሜሪካ ነው የማየው፡፡
  • ምንድን ነው እሱ?
  • የደቡብ አሜሪካ አገሮች የሚፎካከሩበት የእግር ኳስ ውድድር ነው፡፡
  • በኢቢሲ ይተላለፋል?
  • እኔ ምን አውቅልሃለው?
  • ታዲያ በምንድን ነው የሚያዩት?
  • እኔ ኢቢሲ ላይ?
  • ምን አለበት?
  • ሥራም አላጣሁ፡፡
  • ታዲያ በምንድን ነው የሚያዩት?
  • በዲኤስቲቪ ነዋ፡፡
  • ወይ ዲኤስቲቪ?
  • የለህም እንዴ?
  • የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
  • ምን አልከኝ?
  • እኔ ዲኤስቲቪ ከማስገባ አገሪቱ ሳተላይት ብታመጥቅ ይቀላል፡፡
  • ልናመጥቅ አይደል እንዴ?
  • ምን?
  • ሳተላይት ነዋ፡፡
  • በቃ ያኔ ዲኤስቲቪ ማየት እችላለሁ፡፡
  • አንተ ግን የኳስ ፍቅር የለህም?
  • እኔ የአገር ፍቅር ነው ያለኝ፡፡
  • አገር ፍቅር ቴአትር ቤቱን ትወደዋለህ?
  • እርሶ ግን የአገር ፍቅር አልዎት?
  • ማን እኔ?
  • እህሳ?
  • ከባድ ጥያቄ ነው፡፡
  • የእንትን ፍቅር እንዳልዎት ግን አውቃለሁ፡፡
  • የምን ፍቅር?
  • የንዋይ ፍቅር፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • ዘፋኙን እኮ ማለቴ ነው፡፡
  • እ… እሱን እወደዋለሁ፡፡
  • ምኑ ነው ያናደድዎት ግን?
  • አርጀንቲና መሸነፏ ነዋ፡፡
  • መሸነፍ አልነበረባትም?
  • ሲጀመር ጠንካራ ቡድን አላት፣ በዛ ላይ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታ ነበር፡፡
  • እና እናንተም የመሸነፍ ዕድል አላችሁ ማለት ነው?
  • እንዴት ማለት?
  • ያው እንደ አርጀንቲና ጠንካራ ናችሁ በዛ ላይ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ትመስሉኛላችሁ፡፡
  • ወሬማ ማን ብሎህ?
  • ያው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ብዬ ነው፡፡
  • ስማ ምን እንዳሳዘነኝ ታውቃለህ?
  • ምንድን ነው ያሳዘንዎት?
  • ሜሲ ማልቀሱ ነዋ፡፡
  • ይኼ ምን ያሳዝናል?
  • እንዴት አያሳዝንም?
  • ይኸው ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ ያለቅሳል አይደል እንዴ?
  • ምን ሆኖ ነው የሚያለቅሰው?
  • ለምን እንደሚያለቅስም አያውቁም?
  • ግድብ ተሠራለት፣ ባቡር ተሠራለት ታዲያ ለምን ያለቅሳል?
  • አባት ሞቶበት!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
  • ይኸው ሪፖርቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የምን ሪፖርት ነው?
  • የአፈጻጸም ሪፖርት ይዘጋጅ ብለውኝ ነበር፡፡
  • ስማ አሁን ከባድ ሥራ ላይ ነኝ፡፡
  • የምን ሥራ?
  • ጨረታ እያየሁ ነኝ፡፡
  • የምን ጨረታ?
  • ሁሉንም ነው እኔ የምመለከተው፡፡
  • እና ምን ልርዳዎት?
  • እስቲ እዚህ ጋዜጣ ላይ ፈልግልኝ፡፡
  • እርሶ ምን እያዩ ነው ኮምፒዩተሩ ላይ?
  • በኢሜይል ራሱ ጨረታ ይመጣልኛል፡፡
  • ይኸው አንድ ጨረታ አገኘው እዚህ ጋ፡፡
  • የምን ጨረታ ነው?
  • ሐራጅ የወጣበትን መጋዘን ባንኩ አጫርቶ መሸጥ ይፈልጋል ነው የሚለው፡፡
  • እስቲ አምጣው፡፡
  • ይኸው ይዩት፡፡
  • ጉድ ጉድ ጉድ፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • አይ ምንም፡፡
  • ያውቁታል እንዴ?
  • የአንድ ዘመዴ ነው፡፡
  • የሚያውቁት ሰው?
  • እኔ ነኝ ከገጠር ያመጣሁት ስልህ፡፡
  • ከገጠር መጥቶ ነው መጋዘን ያለው?
  • በመቶ ብር ጀምሮ አሁን መቶ ሚሊዮን ብር አለው፡፡
  • ምን እያሉኝ ነው?
  • ተግተህ ከሠራህ አገሪቷ ውስጥ በርካታ ዕድል እኮ አለ፡፡
  • እና በ25 ዓመት ውስጥ ከመቶ ብር ተነስቶ መቶ ሚሊዮን ብር መድረስ ይቻላል?
  • ይቻላል፡፡
  • ለዛውም ሳይማር?
  • ይቻላል ስልህ?
  • እኔ እኮ ሁለተኛ ዲግሪዬን ከያዝኩ 10 ዓመት አለፈኝ፤ ግን…
  • ግን ምን?
  • እንኳን መጋዘን ሊኖረኝ ከወር ወር መድረስ አቅቶኛል፡፡
  • እንግዲያው እንትን ድረስ፡፡
  • ምን?
  • መጽሐፍ!
[ክቡር ሚኒስትር መጋዘኑን ሐራጅ ያወጣው ባንክ ኃላፊ ጋ ደወሉ]
  • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምነው አበጥክ?
  • ምን አሉኝ?
  • ምንድን ነው እንደዚህ ያጠገበህ?
  • ምን አደረኩኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • እኮ ምንድን ነው እንደዚህ ያሳበጠህ?
  • ምን ሆነው ነው?
  • የእኔን መጋዘን ለሐራጅ?
  • የምን መጋዘን ነው?
  • ጋዜጣ ላይ ያወጣኸውን ማስታወቂያ አይተኸዋል?
  • ብዙ ማስታወቂያ ነው እኮ የሚወጣው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እና እንዴት ብንደፋፈር ነው?
  • በእርስዎ ስም ያለ መጋዘን ነው?
  • በዘመዴ ስም ነው ያለው፡፡
  • ለዛ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እዚህ የደረሳችሁት በማን ነው?
  • ይኼማ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
  • አሁን ግን ረስታችሁታል፡፡
  • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይኸው ባንካችን ከእርስዎ ጋር ትልቅ ሥራ አይደል እንዴ የሚሠራው?
  • እኮ እንዴት መጋዘኔ ሐራጅ ይወጣበታል?
  • በቃ መልሰው ይገዙታል፡፡
  • ድጋሚ ገንዘብ ላወጣ?
  • በቃ መልሰው ይበደሩናል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ኢንተርኔት ሲያስቸግራቸው የአይቲ ክፍል ኃላፊውን አስጠሩት]
  • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን እየሠራችሁ ነው?
  • ምን ሠራን አለቃ?
  • ኢንተርኔት የለም እኮ፡፡
  • የእኛ አይደለም እኮ ችግሩ፡፡
  • እና የማን ነው?
  • የቴሌ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቴሌ ደወሉ]
  • ጤና ይስጥልኝ፡፡
  • ጤና ይንሳህ ለማለት ፈልገህ ነው?
  • ምን አሉኝ?
  • ጤና እየነሳችሁን ጤና ይስጥልኝ ትላላችሁ?
  • ማን ልበል?
  • እኔ ጠፋሁ፤ ጭራሽ?
  • ይቅርታ አላወኩም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
  • በጣም ይቅርታ አለቃዬ፡፡
  • ምን እየሠራችሁ ነው?
  • ምን አጠፋን?
  • እኔ ከጠፋውብህ ከዚህ ሌላ ምን ጥፋት አለ?
  • ይቅርታ በጣም፡፡
  • ኢንተርኔት እኮ ከጠፋ ቆየ፡፡
  • አስመዝግበዋል፡፡
  • እኔ ጠፋሁ? እኔ ላስመዝግብ?
  • ያው አሠራሩ እንደዛ ነው ብዬ ነው፡፡
  • እና እኔ እንደሌላው ሰው ላስመዝግብ?
  • ምን አለበት?
  • ለምን ሥራችሁን አትለቁም?
  • ምን አሉኝ?
  • ይኸው በኢንተርኔት ምክንያት ኢሜይል ቼክ ማድረግ አቅቶኛል፡፡
  • እንዴ ስልክዎት ምንድን ነው?
  • Iphone ነዋ፡፡
  • እና ታዲያ በስልክዎት ለምን አያደርጉም?
  • ይቻላል እንዴ?
  • ይኼንንም አያውቁም?
  • እኔ እንደእናንተ ጊዜ አልተረፈኝም፡፡
  • ገንዘብ ነው የተረፍዎት?
  • ምን አልክ አንተ ሞላጫ?
  • ምንም፡፡
  • ሰሞኑን ዜና አልተመለከትክም፡፡
  • ተመልክቻለሁ፡፡
  • ስለዚህ እናንተም እንደ ዴቪድ ካሜሮን…
  • ምን?
  • ሥራችሁን ልቀቁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
  • ምን ሆነሃል?
  • ሲያቃጥሉኝ ነው የዋሉት፡፡
  • እነማን ናቸው?
  • እነዚህ ቴሌዎች፡፡
  • ለምን?
  • ምንም ሥራ መሥራት አልቻልኩም፡፡
  • ለምን?
  • በቃ ኢንተርኔት የለም፤ ብዙ ሥራ ተበላሸብኝ፡፡
  • ምን ታደርገዋለህ?
  • እኔማ ከሥራ ልቀቁ አልኳቸው፡፡
  • ልክ እንደ ዴቪድ ካሜሮን?
  • እህሳ፡፡
  • አሁን እናንተ ጋ እንደዚህ ዓይነት ባህል አለ?
  • የምን ባህል?
  • የሕዝቡን ፍላጎት ካላረካሁ ከሥልጣን እለቃለሁ የሚል ነው፡፡
  • እሱ ባክሽ ጅል ነው፡፡
  • እንዴት?
  • አይደለም ከአውሮፓ ኅብረት ከዓለም ብትወጣም ሥልጣኑን መልቀቅ የለበት፡፡
  • እንዴ ለምን?
  • ሥልጣን በቀላሉ አይገኝም፡፡
  • እና አንተ ብትሆን አትለቅም ነበር?
  • ስሚ እዚህ አገር እንኳን ከሥልጣን ከባልኮኒ ወንበር ላይ መውረድ ከባድ ነው፡፡
  • እና እኔ ከሥልጣን አልወርድም እያልክ ነው?
  • እኔ ከሥልጣን ከምወርድ…
  • እ…
  • ሕዝቡ እስክስታ ቢወርድ ይቀላል!