ኮሎኔል ደመቀን የማውቀውን ያክል፤
‹‹ዐማራን በመሣሪያ ማስፈራራት ልጅ ለእናቷ ምጥ እንደማስተማር ነው›› ኮ/ል ደመቀ
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን የማውቀው ከሕዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ አጋጣሚው ይኼ ነው፤ አንድ ቀን ማለዳ የወልቃይት ዐማራ የማንነት አስተባባሪ ኮሚቴዎች ደወሉልኝ፡፡ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አገኘዋቸው፡፡ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያስገቡትን ደብዳቤ ሰጡኝ፤ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዝርዝር ዘገባ ሠራሁት፡፡ ያገኘዋቸው ወጣቶች (ስማቸውን ዘልየዋለሁ) የኮሎኔል ደመቀንና የአቶ አታላይ ዛፌን ስልክ ሰጡኝ፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ጎንደር እንደሆነና አዲስ አበባ ሲመጣ እንደሚያገኘኝ ገለጸልኝ፤ ትሁት ነው፡፡
በሚቀጥለው ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የትግራይ ልዩ ኃይል የሆነው የፌደራል ፖሊስ እንጦጦ ላይ ለእናንተ አዲስ አበባ የተገባ አይደለም ሲል መለሳቸው፡፡ ከወልቃይትም የተባረሩት ወልቃይት ዐማሮች አዲስ አበባ መከልከላቸው ብዙም የሚገርም አልነበረም፡፡
(ዕሁድ ቀን) በቀጣዩ ቀን ወደ አረፉበት ጫንጮ ከተማ ከሰዓት ሔድኩ፡፡ ከ60 በላይ ከሚሆኑት የኮሚቴ አባላትና የማኅበረሰቡ ተወካዮች ጋር ተገናኘን፡፡ ኮሎኔል ደመቀ፣ አቶ አታላይ ዛፌ፣ ወጣት ሸፈቀ፣ ወጣት አደራጀውንና ሌሎችንም እስከ ምሽት 2›30 ድረስ በዝርዝር ስረዳ ቆይቼ ተመለስኩ፡፡ ማክሰኞ አዲስ አበባ ገብተው ሸበሌ ሆቴል ተገናኘን፡፡
ኮሎኔል ደመቀ ከ18 ዓመቱ ጀምሮ ከሕወሓት ጋር አብሮ የደርግን ሥርዓት ታግሏል፡፡ ቃል በቃል እንዲህ አለኝ፤ ‹‹እኔ የደርግን ሥርዓት ለመጣል እንጅ ትግሬ ልሆን አልታገልኩም፤ ልብ አድርግ እንዴት ዐማራ ትግሬ ይሆናል? ይህ እንደሚሆን ባውቅ ኖሮ እኔ ራሴ እነሱን እታገላቸው ነበር›› አለኝ፡፡ ዕውነቱን ነው እንዴት ዐማራ በግዴታ ትግሬ ይሆናል? ይህን መሸከም ኮሎኔልን የሚያክል ጀግና ቀርቶ ማንም አይሆንለትም፡፡
ከኮሎኔል ጋር ብዙ ተጨዋወትን፡፡ ሌላም ጊዜ ሃያ ሁለት ተገናኘን፤ ግሎባል አካባቢ ደጋገምን፡፡ ጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል ስብሰባ ሲደረግ ተደወለልኝ፡፡ ከአዲስ አበባ ከች አልኩ፡፡ እንዴት ይታለፋል?
ጥይት የተሰጣቸው የትግራይ ሰፋሪዎች በዳንሻና ኹመራ ‹‹እኛ ትግሬ ነን!›› የሚል መፈክር ይዘው ወጥተው ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶ ‹‹አዎ እነርሱ ትግሬ ናቸው፤ ማንም በዚህ ጉዳይ ላይ አይከራከርም! እኛ ያልነው እኛ ዐማራ ነን እንጅ እናንተ ትግሬ አይደላችሁም አይደለም›› አለ፤ ቤቱ በጭብጨባ ተናጋ፡፡
ኮሎኔል ደመቀ ተናገረ፤ ‹‹መሣሪያ በመያዝ ዐማራን ማስፈራራት እኮ ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች ማለት ነው››፡፡ ዕውነቱን ነበር፤ የተናገረውን የፈጸመ፤ የዘመናችን አጼ ቴዎድሮስ፣ በላይ ዘለቀ እርሱ ነው፡፡ ጓዶቹ መታሠራቸው ያሳዝናል፡፡ ከተሰውት ውስጥም ብዙዎቹን አውቃቸው ነበር፡፡
ከዚያን ቀን ጀምሮ እኔና ኮሎኔል ቤተሰብ ነበርን፤ በዚህ ሰዓት ከእርሱ ጎን ባለመቆሜ ሀዘኔ የበረታ ነው፡፡ የወለቃይት ዐማሮች ሆይ ቃሌን እጠብቃለሁ፤ ማህላየን ባለሁበት አጸናለሁ፡፡ ኮሎኔል ደመቀ በሚችለው ሁሉ የዐማራውን ጦር እንደሚመራ አውቃለሁ፡፡ ይህን በደንብ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡ በመላው የዐማራ ሕዝብ ሙሉ እምነት አለው፤ የአርማጭሆና የጠገዴ ገበሬም አብሮት እንደሚሰልፍ ግልጽ ነው፡፡ መላው የዐማራ ሕዝብ ከጀግና ጋር በጋራ መዋጋቱን መቀጠል አለበት፡፡
ኮሎኔል ደመቀ ባለበት ይህች መልክት እንደምትደርሰህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንተ ለምንም የማትሳሳ፣ ቃልህን የምታከብር ጀግና ነህ! መላው የዐማራ ሕዝብ ከጎንህ ነው፤ ታሪክህን በቀይ ደማቅ ቀለም እንጽፋለን፡፡
ወንድምህ!
ማሳሰቢያ፤ የኮሎኔሉንና የኮሚቴውን ሙሉ ቃለ ምልልስ እዚህ ላይ አቀርባለሁ፡፡
#ዐማራ-ተጋድሎ
No comments:
Post a Comment