[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
  • ዓየህ አይደል?
  • የአውሮፓ ዋንጫን ነው?
  • በዓለም ላይ ጐልተን ልንታይ ነው፡፡
  • ለዓለም ዋንጫ አለፍን እንዴ?
  • ምን ይላል ይኼ? 15ቱ ውስጥ ገባን ነው የምልህ፡፡
  • ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነው?
  • አንተ ያለኳስ አታውቅም እንዴ?
  • ተመስገን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምኑ ነው ተመስገን?
  • እርሶ እንዲህ ማለትዎ ነዋ፡፡
  • እንዴት ማለቴ?
  • አይ እርሶ ከኳስ ሌላ መቼ ያወራሉ ብዬ ነዋ?
  • እሱማ ኳስን ጠልቼ አይደለም እንደዚህ የምልህ?
  • ለማንኛውም ዓለም ላይ ጐልተን ልንታይ ነው ያሉኝ በምንድን ነው?
  • የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆንን አይደል እንዴ?
  • እ…እሱን ነው እንዴ የሚሉኝ?
  • በቃ ዓለምን ልናንቀጠቅጣት ነው፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • የዓለም መሪ ሆንን እኮ፡፡
  • ብለው ነው?
  • አሁን ምን እንደምናደርግ ታውቃለህ?
  • ምን ልታደርጉ ነው?
  • የመጀመሪያ ጠላታችን ማን ነው?
  • ድህነት ነዋ፡፡
  • በቃ እሱን ማጥፋት የመጀመሪያ ሥራችን ነው፡፡
  • የተመድ ዋነኛ ጠላት ግን ድህነት ነው እንዴ?
  • ምን ነካህ? ከእኛ ሊጋባባቸው ስለሚችል በመጀመሪያ እሱን ማጥፋት አለብን፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከዛ ደግሞ ሽብርተኝነትን ድራሹን ነው የምናጠፋው፡፡
  • ምን አሉኝ?
  • በቃ እያንዳንዱን ሽብርተኛ ሕግ ፊት ነው የምናቀርበው፡፡
  • ሌላስ?
  • ሌላማ ይኼ ጐረቤታችን ያለውን ኢሳያስ እንነቅለዋለን፡፡
  • ይቻላል ብለው ነው?
  • ስማ ነገርኩህ እኮ ዓለምን በእጃችን ይዘናታል፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • እነአሜሪካ ሦስት መቶ ዓመት ቢፈጅባቸውም፣ እኛ ግን በ25 ዓመታት ውስጥ በአቋራጭ ዓለምን መግዛት ጀምረናል፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግን ብዙ የገባዎት አልመሰለኝም?
  • ስማ ወደድክም ጠላህም ዓለም በእጃችን ላይ ናት፡፡
  • ይሁና፡፡
  • እኔ እኮ በፊትም እነግርህ ነበር፡፡
  • ምን ብለው?
  • ገና ይኼ ዕድገታችን ብዙ ቦታ ያደርሰናል ብዬ ነዋ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ግን የፀጥታው ምክር ቤት አባል ስንሆን ይኼ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ነው እኮ አባል ስንሆን፡፡
  • ይኼ የኪራይ ሰብሳቢዎች ወሬ ነው፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • አውቀው የደረስንበትን ስኬት ለማፍረስ የሚሠሩት ሴራ ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ብዙ አልገባዎትም ያልኩዎት ለዚህ ነበር፡፡
  • ስማ ዓለምን መግዛታችን ይቀጥላል፡፡
  • እንዴት ነው የምንገዛው?
  • የምንፈልገውን እንወስናለን፣ የማንፈልገውን እንጥለዋለን፡፡
  • እኮ እንዴት ሆኖ?
  • ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አለና፡፡
  • ኪኪኪ…
  • ምን ያስቅሃል?
  • ኧረ እንደዛ ማድረግ አንችልም፡፡
  • ለምን ሲባል?
  • ተራ አባል ስለሆንን፡፡
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ አፍሪካዊ ሚኒስትር ደወለላቸው]
  • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
  • እንዴት ነህ ወዳጄ?
  • እንኳን ደስ አልዎት፡፡
  • ለምኑ ነው?
  • የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆናችሁ አይደል?
  • በአምላክህ፣ በአምላክህ፡፡
  • በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
  • ስማ ገና በጣም ትልቅ ቦታ እንደርሳለን፡፡
  • የማይደረስበትማ ቦታ የለም፡፡
  • ዋናው ዓላማችን ለአፍሪካ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • እንዴ እኛ አገር የተመዘገበው የ11 በመቶ ዕድገት 54 አገሮች ላይ እንዲደገም ጠንክረን እንሠራለን፡፡
  • እ…
  • ከዛማ የአኅጉሪቱ ዕድገት 11×54 በመቶ ይሆናል ማለት ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ቁጥር ላይ እምብዛም አይደሉም መሰለኝ?
  • እንዴ እንደ ቁጥርማ የሚቀናኝ ነገር የለም፡፡
  • አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • ገንዘብ ስቆጥር አይደል እንዴ የምውለው?
  • እንግዲያው የምክር ቤት አባልነቱ ለዚህ በጣም ይጠቅማል፡፡
  • ስነግርህ አኅጉሪቷንም አገራችንንም የሚጠቅም ነገር እንሠራለን ስልህ?
  • ኧረ ራስዎትንም መጥቀም ይችላሉ፡፡
  • በምንድን ነው የምጠቅመው?
  • የእኛ አገር እኮ ከጥቂት ዓመታት በፊት የምክር ቤቱ አባል ነበረች፡፡
  • በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ አባል ስንሆን እኛ አይደለንም እንዴ?
  • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
  • አሁን ስንመረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም እንዴ?
  • አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ እኛም ከዓመታት በፊት የምክር ቤቱ አባል ነበርን፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • በነገራችን ላይ ኢትዮጵያም ስትመረጥ እኮ ይኼ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡
  • ይኼ የኪራይ ሰብሳቢዎች ወሬ ነው፡፡
  • ኪራይ ሰብሳቢ ማለት ምን ማለት ነው?
  • እሷን ትንሽ አንብቤ ሌላ ጊዜ እነግርሃለሁ፡፡
  • ለማንኛውም ራስዎትን በደንብ መጥቀም ይችላሉ፡፡
  • እኮ እንዴት አድርጌ?
  • እኔ አሜሪካ ውስጥ ሦስት ቤት አለኝ፡፡
  • የት የት ስቴት?
  • ኒውዮርክ፣ አትላንታና ላስቬጋስ ውስጥ፡፡
  • እሺ፡፡
  • ፈረንሳይ ውስጥ ፓሪስና ማርሴይ ቤቶች አሉኝ፡፡
  • ወይ ግሩም፡፡
  • ሚላን ውስጥ ደግሞ እየተገነባ ያለ ቤት አለኝ፡፡
  • ትቀልዳለህ?
  • ዱባይም ሌላ ቤት አለኝ፡፡
  • እሺ ቀጥል፡፡
  • በዓለማችን ባሉ ትላልቅ ባንኮች ደግሞ ከፍተኛ ሼሮች አሉኝ፡፡
  • እኮ እንዴት ሆኖ?
  • በቃ እነዚህ ምዕራባውያንም ሆኑ በነዳጅ ገንዘብ ያበጡ የዓረብ አገሮች የእነሱ አጀንዳ እንዲፈጸምላቸው ስለሚፈልጉ ለእኛ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡
  • እ…
  • በቃ አጀንዳቸውን እንዲልፍ ከላይ ያልኩዎትን ነገር ለሚኒስትሮቹ ያደርጋሉ፡፡
  • ከእኛ ታዲያ ምንድን ነው የሚጠበቀው?
  • በቃ እጅ እያወጡ ከእነሱ ጋር መስማማት፡፡
  • እጅ ማውጣቱንማ እዚህም ፓርላማ ለምደነው የለ?
  • በቃ እሱ ብቻ ነው የሚጠበቀው፡፡
  • የነዳጅ ቁፋሮ ውስጥ ነዋ የገባሁበት፡፡
  • ስነግርዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አገራችን ነዳጅ ሳታወጣ እኔ ላወጣ ነው ማለት ነው?
  • ከእርሶ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
  • ምንድን ነው የሚያስፈልገው?
  • ቅልጥፍና!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚኒስትር ጓደኛቸው ጋር ምሳ እየበሉ ነው]
  • ዛሬ ለምን እንደፈለኩህ ታውቃለህ?
  • ለምንድን ነው የፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ነዳጅ እናውጣ ልልህ ነው፡፡
  • ለአገሪቷ የህልም እንጀራ የሆነን ነዳጅ እኛ ከየት ልናመጣው?
  • በቃ ነዳጅ ተገኝቷል፤ እናውጣው ነው የምልህ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር በቃ ብዙ ልብ ወለዶች እያነበቡ ተቸገሩ አይደል?
  • ይኼ ልብ ወለድ አይደለም፡፡
  • ልብ ወለድ ካልሆነ እንዴት ነው ነዳጅ ማውጣት የምንችለው?
  • እሱን ልነግርህ እኮ ነው፡፡
  • እሺ ይንገሩኝ፡፡
  • የፀጥታው ምክር ቤት አባል በመሆናችን ብዙ እንጠቀማለን፡፡
  • በእሱማ ዓለማችን ላይ ያሉ ችግሮችን ስለምንቀርፍ ብዙ እንጠቀማለን፡፡
  • መጀመሪያማ እኔም እንደዛ ብቻ መስሎኝ ነበር፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ድህነትን ምናምን እናጠፋለን ስል ነበር፡፡
  • እሱንማ ማጥፋት አለብን፡፡
  • ስማ መጀመሪያ የራሳችንን ድህነት ነው ማጥፋት ያለብን፡፡
  • እንዴት አድርገን?
  • በቃ እነዚህ ምዕራባውያንና በነዳጅ የጠገቡ ዓረቦች የእነሱን አጀንዳ ለማስፈጸም ገንዘብ ይረጫሉ አሉ፡፡
  • ይቀልዳሉ?
  • እንዴ ይኸው አንድ የአፍሪካ ሚኒስትር በየቦታው ነው ቤት ያለው፡፡
  • ቤት?
  • አሜሪካ ሦስት፣ ፈረንሳይ ሁለት፣ ጣሊያን፣ ዱባይ ብቻ ምኑ ቅጡ፡፡
  • ምንድን ነው ከእኛ የሚጠበቀው?
  • በቃ እነሱ ለሚፈልጉት አጀንዳ እጃችንን ማውጣት ብቻ፡፡
  • እሱንማ እዚህስ ፓርላማ ለምደነው አይደል እንዴ?
  • ምን ላድርግህ? እኔም ያልኩት እሱን ነበር፡፡
  • ግን እዛ የምናስቀምጠው ሰው ወሳኝ ነው፡፡
  • ዓየህ እሱ ላይ ነው በደንብ መሥራት ያለብን፡፡
  • እኮ እዛው ያሉት ሰዎች የእኛን ውሳኔ ዝም ብለው ላይቀበሉት ይችላሉ፡፡
  • ታዲያ ምን እናድርግ?
  • እርሶ እዛ ይቀመጣሉዋ፡፡
  • እንዴ? እንዴት?
  • በቃ የእኛን ሐሳብ እዛ ላሉ ሰዎች እያስረዱ ያፀድቃሉ፡፡
  • እኔ የት ልቀመጥ?
  • ቤት ይገዛልዎታላ፡፡
  • የት?
  • ኒውዮርክ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የአውሮፓ ዲፕሎማት ጋር ደወሉ]
  • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ነህ?
  • እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
  • ሰማህ አይደል?
  • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
  • የፀጥታው ምክር ቤት አባል እንደሆንን፡፡
  • እኛም እኮ አባል ነን፡፡
  • በቃ ዓየህ ከምንጊዜውም በላይ ተቀራርበን መሥራት አለብን፡፡
  • ልክ ብለዋል፡፡
  • የዓለማችንን ችግር የምንቀርፍበት ጊዜ ነው፡፡
  • ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የእኛንም ችግር እንቀርፈዋለን አይደል?
  • የእኛ ሲሉ?
  • ማለቴ የግል ሕይወታችንንም ማሻሻል እንችልበታለን፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ይኼ እኮ ለአገር የሚሠሩበት ኃላፊነት ነው፡፡
  • እሱማ ነው፡፡
  • ታዲያ ምን እያሉ ነው?
  • ያው ተቀራርበን እንድንሠራ ለማለት ነው፡፡
  • እሱንማ ማድረግ አለብን፡፡
  • እንግዲህ በቀጣይ ብዙ አብረን የምንሠራቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡
  • ቦታው ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
  • እኔም የምልህ እሱን ነው፡፡
  • በሌላ በኩል ደግሞ ለሌላ ነገር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
  • ለምን?
  • ለኪራይ ሰብሳቢነት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
  • ምነው የደካከመህ ትመስላለህ?
  • ዛሬ ሥራ በዝቶብኝ ነው የዋልኩት፡፡
  • ምን ተገኘ?
  • ምን ያልተገኘ ነገር አለ?
  • ምን አዲስ ነገር ተገኘ?
  • የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆንን አይደል?
  • እሱማ ሰነባበተ፡፡
  • እኮ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልናል፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • በቃ ቦታው ለዘመናት ስንመኘው የነበረውን ነገር ሊሰጠን ይችላል፡፡
  • ማለት?
  • በአሜሪካና በአውሮፓ ቤት መሥራት ቀላል ሊሆን ነው፡፡
  • እየቀለድክ ነው?
  • በቃ እንደቀልድ ቤት ሊኖረን ነው ስልሽ?
  • እንዴት ሆኖ?
  • የምክር ቤቱ አባል መሆናችን ብዙ ዕድል ይከፍትልናል፡፡
  • በጣም ደስ ይላል፡፡
  • ትንሽ ሊያስቸግሩን የሚችሉት ምዕራባውያን ናቸው፡፡
  • ዓየሽ አንዳንዴ ብዙ መማር ጥሩ አይደለም፡፡
  • አልገባኝም፡፡
  • ብዙ መማር፣ ፈጽሞም አለመማር ጥሩ አይደለም፡፡ እንደ እኔ መካከል ላይ መሆን ነው የሚያዋጣው፡፡
  • አንተ ብዙ ማስተርስ አይደል እንዴ ያለህ?
  • ምን የእኔ ማስተርስ እኮ ቤት ድረስ ነው የሚመጣልኝ፡፡
  • እሱስ ልክ ነህ፡፡
  • ለአንቺስ ተርፌያለሁ አይደል እንዴ?
  • እግዚአብሔር ይስጥህ፣ በማስተርስ ከ12ኛ ክፍል ሰርተፍኬት ገላገልከኝ፡፡
  • እና እነዚህ ምዕራባውያን ትንሽ ሊያስቸግሩን ይችላሉ፡፡
  • አንተ ግን ከመቼ ጀምሮ ነው ከኒዮሊብራሎች ጋር መሥራት የጀመርከው?
  • ገንዘብ ካገኘሁበትማ አይደለም ከኒዮሊብራል ጋር ከሌላም ጋር እሠራለሁ፡፡
  • ከሌላ ከማን ጋር?
  • ከኒዮጋኔን!