Friday, July 15, 2016

ከአውሬ ጋር ትግል


ነፃነት ዘለቀ
(“ኢትዮጵያ ዛሬ”ድረ ገጽ)
ትግል ከሰው ጋር እንጂ ከዐውሬ ጋር ከሆነ አደገኛ ነው። ህወሓት ከጥንስሱ ጀምሮ መቼም ቢሆን በሰዎች ተመርቶ አያውቅም። ይህ ድርጅት ከመነሻው በሰው መሰል አራዊት እንደሚመራ የታወቀ ሆኖ ሳለ ከእባብ ዕንቁላል ዕርግብ ይፈለፈል ይመስል ከዚህ ቡድን መልካም ነገርን የሚጠብቁ ሞኛ ሞኝ ፍጡራን ሲስተዋሉ የሚገርም ነው። እነዚህ የህወሓት ሰዎች የራሳቸው ጠባብ የአስተሳሰብ አድማስ ከፈጠረላቸው የትግሬ ዘር ውጪ ሌላውን ሰው በሰውነት ሊቀበሉ አይፈልጉም።
ከትግሬ ዘር እንኳን ከነሱ ጎጠኛ አመለካከት ባለፈ ሰው ልሁን ብለው የሚፍጨረጨሩ ትግራውያንን ሳይቀር ከማሰርና ከማሰቃየት ብሎም ከመግደል እንደማይመለሱ በቅርብ ከረሸኑት የአረና አባል መረዳት ይቻላል። ይህ ሰሞኑን የገደሉት ኢትዮጵያዊ ትግሬ ለድርጅቱ አራተኛ መስዋዕት ሲሆን አብርሃ ደስታም በእሥር የሚማቅቅ ፀረ-ህወሓት የሆነ ትግራይ በቀል ድንቅ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው ለጥቅምና ለዘረኝነት ያልተምበረከኩ፣ ከነፃነት ትግሉም ጎን የተሠለፉ ብዙ ተጋሩ መኖራቸውን ማወቅ አለብን። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው።
በዚህች ማለዳ የሰማነው አሳዛኝ ዜና አለ። ይሄውም ሀብታሙ አያሌው ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር እንዳይሄድ በወያኔው ፍርድ ቤት መጓተቱን ተመርኩዞ ባለቤቱ በድንጋጤ ራሷን ስታ መውደቋ ነው። ይህን ግፍ እግዚአብሔር እየመዘገበው ነው። “ዳኛው አልተገኙም” ብሎ ጣር ላይ በሚገኝ ዜጋ ላይ መቀለድ ከሰው ቢቀር ከፈጣሪ ምን መቅሰፍት ሊያመጣ እንደሚችል እነዚህ ደናቁርት የወያኔ ባለሥልጣናት አልገባቸውም ማለት ነው። በጥይት መግደል – ምክንያት ኖረውም አልኖረውም – “ጀግንነት”ና ለሰውም የመራራት ያህል ነው። በራስ የወደፊት ዕድል ላይም አለመጨከን ማለት ነው። በገዛ የወደፊት ትውልድ ላይም መጥፎ ጠባሳ አለማሰቀመጥ ማለት ነው – በጥቅሉ በእጃችን ውስጥ በሚገኙ ምሥኪን ዜጎች ላይ መጨከንና አለመጨከን በራስ ሕይወት ላይ ሣይቀር ብዙ አንድምታ አለው። እነዚህ የሰይጣን ልጆች ግን በእግዚአብሔር ፍጡር እንዴት እንደሚጫወቱ በአግራሞት እያየን ነው። የነዚህን አጋንንት መጨረሻ የሚያይ የታደለ ነው – በፈጣሪ ፍርድ ብዙ ይማርበታልና። ሬሣቸውን ውሻና ጅብ ሲጫወትበት ይታየኛል። በጣም ክፉዎችና የክፉ ክፉዎች እንደመሆናቸው የፈጣሪ ቅጣት ከዚህ መልስ የሚባል አይሆንም። ከነሱ የበለጠ ዐረመኔ ልኮ ኢትዮጵያን የወረሳትን የጠነባና የከረፋ የማፊያና የአፓርታይድ ሥርዓት እንደሚያጸዳ አለአንዳች ጥርጥር አምናለሁ።
ምድሪቱን በዘረኝነት አረንቋ ስላጨቀዩዋት የእግዚአብሔር ቁጣ ከአፎቱ ሲወጣ በሚፈጠረው መብረቃዊ መቅሰፍት አንድም ወያኔ ለወሬ ነጋሪ የሚተርፍ አይመስለኝም – አያያዛቸው ወደዚህ ዓይነቱ አርማጌዴዎናዊ ኹነት የሚያመራ ነው፤ ምሕረትን ለማያውቅ ፈርዖን የሚታዘዘው ተኩሶ የማይስት ሳዖል ወይም በአህያ መንጋጋ ድባቅ የሚመታ ሦምሶን ነው። ነገረ ሥራቸው ሁሉ “ፈጣሪ ሆይ! አባታችን ዲያብሎስን ለማስደሰት የምንሠራው ግፍና በደል ሁሉ ቋቱን አልሞላ ብሎ ይሆን ወይ እስከዚህ ጨክነህ ዕድሜያችንን በማንዘላዘል አሣራችንን የምታበዛው? ለምን ከዚህ የእሳት ወንበር በቶሎ አንስተህ አትገላግለንም? ለምን ወንጀላችንን ታበዛህ?” እያሉ እግዜር ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እንዲያስወጣቸው የሚለምኑ ይመስላሉ። እንጂ በነሱው ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆነን ዜጋ ለህክምና ከሀገር አትወጣም ብሎ መጨከን ቢቻል በምድር ያ ቢቀር በሰማይ የሚያስጠይቅ መሆኑን አጥተውት አይደለም። ዛሬ ባይሆን ነገ፣ ነገም ባይሆን ከነገ ወዲያ እነሱም በተፈጥሮ ወይም በአደጋ ወይም በጦርነት እንደሚሞቱ ማወቅ ነበረባቸው። ሞት ለማንም የማይቀር ርስት ነው። እንደ አጠቃላይ ሕግ ሞትን ማታለልና ማዘግየት ወይም ከነጭራሹ ማስቀረት አይቻልም። ትልቁ ጸሎት መሆን ያለበት አሟሟትን እንዲያሣምርልን ፈጣሪን መለመን ነው – እንደወያኔ ለይቶልን ካልታወርን።
ሰዎች ከሰዎች ጋር ቢታገሉና ቢሸናነፉ ያለ ነው። ኃይለኛው ደካማውን ያሸንፋል። ደካማውም ልባም ከሆነ አሸናፊውን ኃይል በማክበር መሸነፉን አምኖ ይገዛል። ኃይለኛው አሸነፍኩ ብሎ ግፍና በደል ቢፈጽም ለራሱ ዕዳ እያስቀመጠ ነውና ከዚህ መጥፎ ድርጊት መታቀብ ይኖርበታል። ማሸነፍ ብርቁ የሚሆንበት አሸናፊ ኃይል ወደማማው ከወጣ ግን ተሸናፊው መፈጠሩን እስኪራገም የግፍ ጽዋን ይጨልጣል።
በሀገራችን አሁን የምናየው አሸናፊ ማሸነፍ ብርቁ የሆነ ፈሪ ኃይል ነው። ለምን ቢባል የጀግና አሸናፊ ቢሆን ኖሮ ፍቅርና ትዕግስት ተፈጥሯዊ ባሕርያቱ ይሆኑና ታጋሽና በፍቅር የሚያስተዳድር ኃይል ይሆን ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይህ ኃይል ማሸነፉን እንኳን ለማመን 25 ዓመታት ያልበቁት ገና ጦርነቱን ያልጀመረ ያህል የሚሰማው እጅግ ቦቅቧቃና ጥላውን ሣይቀር የሚጠራጠር ፈሪ ኃይል ሆነና ተቸገርን። እኛ መሸነፋችንን ለመግለጥና ሆዱን ለማራራት ብንሰግድለትም አላምነን አለና ባጎነበስንበት ጦሩን በጀርባችን ይወደውድብን ገባ። ሽንፈታችንን ለማሳመን ምን እናድርግ? የፈሪ አሸናፊ ለጠላትም አይስጥ። መከራ ነው።
ይህን ዓይነቱን ጠላት ለመርታት ልዩ ሥልት መቀየስ ሲገባ በሰላማዊ መንገድ ታግዬ እጥለዋለሁ የሚሉትን የጅሎች ፈሊጥ መከተል ተራ በተራ ግን በሂደት ሁሉንም ታጋይ ለሽንፈትና ለሥልታዊ ዕልቂት የሚዳርግ ነው። ይህንን እውነት ደግሞ ባለፉት ከ40 የማያንሱ ዓመታት ውስጥ በተግባር አረጋግጠናል።
በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚመከርና በሁሉም ረገድ የሚታገዝ ወያኔን የመሰለ ኃይል እንዴትና እነማንን ማጥፋት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህም ሰዎችን ብቻ ሣይሆን ተቋማትንና ተስፋን ራሱን ጭምር ድምጥማጣቸውን ማጥፋት ዋና ዓላማው ነው። የኢትዮጵያ አንድነት አንዱ ምሰሶ የነበረውን የዐማራን ብሔር ከመነሻው ጀምሮ እንደሚያጠፋው በፕሮግራም ቀርፆ ለመሰሎቹ ሲሰብክላቸውና ሲታገል የነበረው፣ ለተግባራዊነቱም ላለፉት 40 ዓመታት ሲታክት የቆየው በተጨማሪም የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ድራሹን ለማጥፋት በካህን መሣይ ጳጳሣትና ኤጲስ ቆጶሣት ተጋዳላዮቹ ቤተ አምልኮውን ወርሮ ኦና ማስቀረቱ፣ ምዕመናኑንም ለቀበሮና ለተኩላዎች ማስረከቡ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ትልቁ ግብ አካል እንደነበር ተደጋግሞ የተነገረ ነው – የገባውና የነቃ አካል ተገኝቶ ይህን ሸውራራ ጉዞ ለመግታት ባይቻልም ሃቁ ይሄው ነው።
ሌላው የወያኔ ጥቃት ሰለባ ደግሞ ተስፋ ነው። ተስፋ ትልቅ ስንቅ ነው። አንድ ሰው ተስፋ ሲያጣ ነው መሞት የሚጀምረው። ፈረንጆች The last thing to lose is hope የሚሉት ወደው አይደለም። ልትሞት ደቂቃዎች ቀርተው በጠና ታመህ ሳለ በተስፋ ድነህ ያጣሃውን ነገር ሁሉ ስታገኝ የምታየው በተስፋ ነው። ቤሣ ቤስቲን አጥተህ በመደህየትህ የማዘጋጃ ቤት ቱቦ ሥር እያደርክ ሳለ ነገ ከብረህ ቪታራና ቪ8 መኪና ይዘህ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች ስትዘማነን የምታየው በተስፋ ነው። ልጅ የማትወልጅ መካን መሆንሽ በሀኪሞች ተነግሮሽ ሳለ አንድ ቀን እግዜር ብሎልሽ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አድርገሽ ስሜቱ የጎፈነነውን ባልሽን አስደስተሸ በአዲስ መልክ ከባልሽ ጋር የፍቅር ቄጤማ እንደምትቀነጥሽ የምታልሚው በተስፋ ነው። ተስፋ ብዙ ነገር ነው። ከመኖር ወዳለመኖር የሚመልስ ዋና የሕይወት ቅመም ነው። ለዚህም ነው ሰው ተስፋ ካጣ ሁሉንም ነገረ እንዳጣ የሚቆጠረው። ለዚህም ነው ሰው ተስፋ ሲያጣ መሰቀያ ገመዱን ይዞ ወደሚቀርበው ዛፍ በመሮጥ የሚንጠለጠለው ወይም ወዳንዱ ፎቅ ወጥቶ የሚፈጠፈጠው ወይም ብልቃጥ መርዙን ጨልጦ ባዶነት ከወረሰው የቀቢፀ ተስፋ ዓለም የሚገላገለው። የተስፋ ወርድና ቁመት በሦስት ሆሄያት ይወሰን እንጂ ትርጓሜው ጥልቅና የዓለማችን ኑባሬ ዓይነተኛው ግብኣት ነው። ካለ ተስፋ ቢዋል አይታደርም ወይም ቢታደር አይዋልም። እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር የሕይወት ቋሚ ምሰሦና ወጋግራ መሆናቸው የሚነገረውም ለዚህ ነው።
ወያኔዎችና ላኪዎቻቻው ይህንን እውነት በደንብ ይረዳሉ። የገጠመን ጠላት ቀላል አይደለም። ያለህን ማናቸውንም ነገር ቀምቶ ባዶ የሚያስቀር ከባድ ጠላት ነው ከጥልቁ የእሳት ባሕር ወደምድራችን የተላከብን፤ ግን አላወቅነውም። ሁሉን ነገር ተቀምተን ከተስፋ ጋር እንኳን እንዳንኖር እያደረጉን ነው። ታች አምና አንዳርጋቸውን ለመጥለፍ ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት – ያው የኛው ሀብትና ንብረት ቢሆንም – አንድን የሕዝብ ተስፋ ለማንጠፍ ነው። ሀብታሙን የሚያጠፉት ተስፋችንን ለማጥፋት ነው። ፕሮፌሰር ዐሥራትንና ሌሎች ዕንቁ ዜጎቻችንን የገደሉብን ተስፋችንን ለማጨለም ነው፤ እሥር ቤቶችን በተስፋዎቻችን የሞሉት ተስፋችንን ለማደብዘዝና በሂደትም ለመግደል ነው። ይህን አባባል ልብ በል፡- “ከጓደኞቿ ወጣ ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ”። አዎ፣ ሁላችንም በግ ሆነን “ባባእ” እያልን እነሱ እንዳደረጉን ከሆን ለተወሰነ ጊዜ ይታገሱን ይሆናል፤ “አይ፣ አገዛዛችሁን በቅጡ አድርጉት፤ ለሰሚ ሣይቀር የሚሰቀጥጠውን ግፍና በደል መፈጸማችሁን አቁማችሁ በወጉ አስተዳድሩን። ግዴለም በለስ ቀንቷችኋልና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ባህል ኖሮን ባንመርጣችሁም መግዛቱን ግዙ – ግን ሁለመናችሁን አሳውራችሁ የለየላችሁ ዘረኞችና ነፍሰ በላዎች አትሁኑ። ሀገሪቱ የሁላችንም ናት፤ ደግሞም ጠባይ ካለን ለሁላችንም ትበቃናለች….” ብለህ ሃሳብና ምክር የምትሰጥ ከሆነ ከጓደኞችህ በልጠህ ነቅተሃልና ለወፍ ወይ ለወንጭፍ ትዳረጋለሁ። ስለዚህ አንተም በዚህ አባባልህ የወደፊት የሕዝብ አለኝታና የነገ ተስፋ ነህና የሕዝብን ተስፋ ለማቀጨጭ ሲባል ጭዳ ትሆናለህ። ደናቁርቱ ወያኔዎች ያልገባቸውና የማይገባቸው ትልቅ ነገር ደግሞ በሠይፍ የሰው አንገት የሚቀነጥሱ የነሱም አንገት በሠይፍ የሚቀነጠስ መሆኑን ነው – “የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ” ይባላል።
ነገር ግን ይህን ልብ በል! መግደል መቼም ቢሆን መፍትሔ አምጥቶ አያውቅም። ለተወሰነ ጊዜ እውነተኛ ሰላም የሌለበት እፎይታ ያመጣ እንደሆነ እንጂ መግደል ዘላቂ ሰላምን ያመጣበት ሁኔታ እስካሁን የለም – መግደል መግደልን ይተካልና። ፍቅርና መተዛዘን ግን የሚተካው ሌላ ፍቅርንና መተዛዘንን ስለሆነ የዘላቂ መፍትሔ ዋና መሠረት መሆኑ አይካድም።
ወያኔዎች ግን ሥጋና ጅማታቸው ከምን ተበጅቶ ይሆን እንዲህ በግድያ የሚደሰቱት? የአንጎላቸው ሥሪት ከምን ይሆን? እርግጥ ነው እነዚህን መሰል ወንጀለኞች የኤክስና ዋይ ክሮሞሶሞቻቸው ተፈጥሯዊ ስብጥርና ውህደት በተገቢው መንገድ ያልተሰደረና ባሕርያቸው ለወንጀለኝነት የቀረበ እንደሆነ አንብቤያለሁ፤ የሚገርመኝ ግን ይህ ሁሉ የወያኔ ጀሌ እንዴት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ግድፈት (ደፊሸንሲ) ሊኖርበትና ግም ለግም ተያይዞ ሊያዘግም እንደቻለ መረዳት ያቃተኝ መሆኔ ነው። በአመራርም በተመሪም ቦታ የሚገኙ ብዙዎቹ ወያኔዎች ከሕጻንነት ጀምሮ የተሰበኩበትና አእምሯቸውን ያንሻፈፉበት አንዳች ጠማማ ስብከት እንዳለ አምናለሁ። ግን ያ መርዘኛ ስብከትና ሥነ ልቦናዊ ጥመት በማኅበራዊ ተራክቦና በጊዜ ሂደት ሊሰክን ያልቻለው ለምን ይሆን? ብዬ ብዙውን ጊዜ እጨነቅላቸዋለሁ። ለተበዳይ ብቻ ሣይሆን ለበዳይም መጨነቅ ይገባል – እርሱም ከተበዳዩ ባልተናነሰ ያሳዝናልና፤ ሰው መቼም ወዶ አይደለም ሰውን ከመሬት ተነስቶ የሚገድለው ወይም የሚያሰቃየው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ትግሬ ወንድምና እህቶቻችን ይህን ያህል የለወጣቸው ቀደም ሲል ሌሎቻችን ምን በደልና ጥፋት አድርሰን ይሆን? ብዬም አስባለሁ። በርግጥ ይህን ያህል ሊያስቀይማቸውና በኛ ላይ ክፉ እንዲሆኑ ያስቻለ በደል ፈጽመን ከሆነ እናስታውስና ይቅርታ እንጠይቅ፤ ከዚያም ይቅር ተባብለን ይህን አስጠሊታ ታሪክ እንለውጠው። ይቻላልም። በዚህ ጉዞ ግን የትም አንደርም።
ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ተስፋም ይገደላል፤ ተስፋም ይሞታል። ተስፋ ሲገደል ሕዝብ አንገቱን ይደፋል። ተስፋ ሲያንሠራራ ሕዝብ አንገቱን ቀና ያደርጋል። አንገቱን ቀና ያደረገ ሕዝብ ለአገዛዝ አይመችም። ለአገዛዝ የማያመች ሕዝብ ውስጡ ተስፋ ያረገዘ እንደሆነ መገመት አይከብድም። የሕዝብ እውነተኛ ተስፋ መሆን ደግሞ ብፁዕነት ነው። ከብዙ ትንንሽ ተስፋዎች ደግሞ አንድ ትልቅ ተስፋ የተሻለ ነው። በብዙ ትንንሽ ተስፋዎች ውስጥ ብዙ ሣንካዎች ሊኖሩና ተስፋን ወደ ቀቢፀ ተስፋነት ሊለውጡ እንደሚችሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። የብዙ ተስፋዎች የጋራ ሕልም በብዙ የተናጠል ምኞቶችና የማይቀራረቡ ፍላጎቶች ምክንያት ሊጨነግፍ እንደሚችልም መረዳት ብልህነት ነው። ስለዚህ ተስፋን ከተስፋነት ወደ እውንነት ለማሸጋገር ብዙ ትግል አለ። በዋናነት ግን ብዙ ተስፋዎችን ወደአንድ የተማከለ ተስፋነት መለወጥ ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆን ይርበታል። በብዙ ኩይሣዎች ሥር ብዙ የምሥጥ ነገሥታት አሉ። በብዙ ተስፋ ፈንጣቂ ንቅናቄዎችና ማኅበራዊ ስብስቦች ውስጥም ብዙ ፕሬዝደንቶች አሉ።… ችግር ነው። …
ለመሆኑ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሕዝብ ተስፋ ልትሆኑ የምትችሉ ሻማ ልጆቻችን ወዴት አላችሁ? ተስፋነታችሁስ እስከመቼ ነው? ልብ አድርጉ፣ ተስፋ እንደማንኛውም ሕይወት ያለው ፍጡር ይጸነሳል፤ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ እንደየሁኔታውም ታሞ ወይም በድንገተኛ አደጋ ይሞታል። የጫጫ ተስፋን ለማዳን ከባድ የመሆኑን ያህል የተወለደ ተስፋን ተንከባክቦ በማሳደግ ለፍሬ ማብቃትም አስቸጋሪ ነው። ሁሉ ነገር ለጊዜ ተገዢ መሆኑን ልብ ማለትም ተገቢ ነው። ሕዝብ ባህር ነው፤ ሕዝብ ሁሉን ያውቃል። ሕዝብን ዝም ማሰኘት እንጂ እንዳያስብና እንዳያውቅ ማድረግ ግን አይቻልም። ሕዝብ ሆን ብሎ ይታለላል እንጂ ባለማወቅ ተጭበርብሮ አያውቅም። ሕዝብ ዕድሉን ካገኘ አገርን አፍርሶ መገንባት የሚያስችል እምቅ ኃይል አለው። ሕዝብን ንቆ መጓዝ የት እንደሚያደርስ ለማወቅ ቀ.ኃ.ሥንና ደርግን ማስታወስ ብቻ ይበቃል።
በነገራችን ላይ የአቶ አሰፋ ጫቦን “ትቼው ረስቼው” ክፍል አንድ መጣጥፍ ካነበብኩ ወዲህ እነፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ነፍሴ ተፀየፈቻቸውና እንዴት ሊያስጠሉኝ እንደጀመሩ አትጠይቁኝ። የሥልጣን ሱስና ፍቅር እንዲህ ያደርጋል? በስማም!!!! ሀገራችን እንዴቱን ያህል ተረግማለች እባካችሁን?

No comments:

Post a Comment