Sunday, July 24, 2016

ኢሕአዴግ ሕገወጥና ሰርጐ ገብ በማለት በዜጐች ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ እንዲያቆም መድረክ ጠየቀ


የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ‹‹ሕገወጥ የቤት ግንባታ›› እና ‹‹ሰርጐ ገቦች›› በማለት ሰበብ እየፈጠረ በዜጐች ላይ እየወሰደ ያለውን ሕገወጥ ዕርምጃ እንዲያቆም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ጠየቀ፡፡
መድረክ ዓርብ ሐምሌ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢሕአዴግ በሰላም፣ በሠለጠነና ሕዝቡን አሳታፊ በሆነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ትቶ፣ በሰርጐ ገቦችና በሕገወጦች ላይ ዕርምጃ እንደወሰደ መናገሩ ስህተት መሆኑን አስረድቷል፡፡
ኢሕአዴግ ሰሞኑን በጎንደር ከተማ በሰርጐ ገቦች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን እንደገለጸ ያስታወሰው መድረክ፣ ኢሕአዴግ እንዳለው ብቻ ሳይሆን ብዙ ዜጐች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቋል፡፡
ኢሕአዴግ እየወሰዳቸው ያሉ አላስፈላጊ ዕርምጃዎች ለከረረ ግጭት ከመብቃታቸው በፊት፣ ከሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ አግባብ ፈጥኖ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
የሕግ የበላይነትንም በአግባቡ በመተግበር ችግሮችን በሰላም መፍታት እንዳለበትም አክሏል፡፡ ‹‹ሰርጐ ገቦች›› የተባሉት አካላት በታላቁ ጥንታዊ ጎንደር ከተማ ገብተውና በጦር መሣሪያ ተደራጅተው ፊልሚያ እስከሚጀምሩ ፖሊስ፣ ደኅንነቱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ የት እንደነበሩ የጠየቀው መድረክ፣ ኢሕአዴግ አላስፈላጊ መግለጫ መስጠቱን ትቶ ለሕዝቡ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ አንድምታ ያላቸው ሕገወጥ ግድያዎች እያሳሰበው መሆኑን የገለጸው መድረክ በቅርቡ በኢሕአዴግ ታጣቂዎች በኦሮሚያ፣ በደቡብና በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ እየተገደሉ መሆኑን ስም ዝርዝራቸውን ጠቅሶ አሳውቋል፡፡ በተለይ ወቅቱ የአዝመራ ወቅት መሆኑን የጠቆመው መድረክ፣ ደጋፊዎቹ ማዳበሪያ ሲጠይቁ ‹‹መድረክ ይስጣችሁ›› እየተባሉ እንደሚከለከሉና ‹‹መሬታችን ለም ስለሆነ ማዳበሪያ አንወሰድም›› የሚሉትን በግዳጅ እንዲወስዱ እየተደረገ በመሆኑ ኢሕአዴግ ይኼንን ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሃና ማርያም አካባቢ፣ በወረገኑና በሌሎችም አካባቢ ለዓመታት ቤት ሠርተው የሚኖሩ ዜጐችን ‹‹ሕገወጥ ግንባታ›› በማለት ቤታቸውን በዶዘርና በግሬደር በማፍረስ፣ ለዶፍና ጐርፍ ማጋለጡን አጥብቆ እንደሚያወግዝም መድረክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment