Sunday, July 17, 2016

ታሪክ ተዛብቶ ሲቀርብ በጣም እናደዳለሁ” 50 ዓመታት በፎቶግራፍ ባለሙያነት


• ጃንሆይ አምላክ መባላቸውን በመቃወም፣ጃማይካ ውስጥ የቤተ-ክርስቲያን ማሰሪያ ገንዘብ ሰጥተዋል
• በሻሸመኔ መጀመሪያ መሬት የተሰጣቸው ጥቁር አሜሪካውያን እንጂ ራስ ተፈሪያን አይደሉም
• መስፍን አበበ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጊታር ተጫዋች ነኝ” ማለቱ ውሸት ነው
የፎቶግራፍ ባለሙያው ንጉሴ ተሾመ ደጀኔ የተወለዱት በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በኤርትራ ደቀመሀሪ ለተወሰኑ ዓመታት ተቀምጠው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ሲሆን ለአንድ ዓመት በሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ተምረው እንደገና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሻሸመኔ በማቅናት፣ በአፄ ናኦድ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል መማራቸውን ይናገራሉ፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት በፎቶግራፍ ባለሙያነት የሰሩት አቶ ንጉሴ፤ ፎቶግራፍ የተጻፈ ታሪክን ተጨባጭና ተዓማኒ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ በተለይ እውነቱን የማውቀው ታሪክ ተጣሞና ተዛብቶ ሲቀርብ በጣም እናደዳለሁ የሚሉት ባለሙያው፤ በፎቶግራፎች ማስረጃነት የተዛቡ ታሪኮች እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ “ራስ ተፈሪና የራስ ተፈሪያን ማንነት” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሃፍም የህትመት ብርሃን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ለመሆኑ ወደ ፎቶግራፍ ባለሙያነት እንዴት ገቡ? ፎቶግራፍና ታሪክን እንዴት አስተሳሰሩት? እስካሁን ምን ያህል የተዛቡ ታሪኮችን በፎቶግራፎች ማስረጃነት ለማረም ሞከሩ? ሥራና ኑሮአቸውስ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለስራ አዳማ በሄደችበት ወቅት፣ የፎቶግራፍ ባለሙያውን አቶ ንጉሴ ተሾመን አግኝታ በሙያቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡ እንዲህ ተጠናቅሯል፡-
ቤተሰቦችዎ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በምን ምክንያት ነበር?
በወቅቱ አባቴ ሹፌር ስለነበሩ የተለያየ ቦታ ይጓዛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተሰባችን ተረጋግቶ አይቀመጥም ነበር፡፡ በኋላ ላይ አባቴ ማዕከላቸውን ሻሸመኔ አደረጉና፣ እኛም ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ እዚያ መኖር ጀመርን፡፡ አፄ ናኦድ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተማርኩኝ፤ አባቴም ዲላ ወላይታ እየሄዱ በሹፍርና ይሰሩ ነበር፡፡ በቃ እዚያው አደግሁኝ፡፡ ስለ ሻሸመኔ ብዙ ነገር አውቃለሁ፤ ብዙ የፎቶግራፍ ማስረጃዎችም አሉኝ፡፡
እንዴት ወደ ፎቶግራፍ አንሺነት ሙያ ሊገቡ ቻሉ? ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶግራፍ ያነሱትና ካሜራ የጨበጡት መቼ ነበር?
በ1963 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ በ27 ብር “ሉቢቴልቱ” የተባለች የራሺያ ካሜራ ከነማኑዋሏ ገዝቼ፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከተማ እየዞርኩ ታሪክ ማስቀረት ጀመርኩ። ፍላጎቱ ያደረብኝ በአሰብ መንገድ አንድ ተኮላ የሚባል ኢንጂነር መንገድ እያሰራ ፎቶ ያነሳና ስዕል ይሰራል፤ ስዕሉን ከፎቶው ላይ ነበር አስመስሎ በትልቁ የሚስለው፡፡ እሱ በወቅቱ ያቀረበውን የስዕል ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየሁኝ፡፡ በካሜራ ካነሳሁ በኋላ ነው የምስለው ብሎ ሲናገርም ሰማሁ፤ ለምን እኔስ በካሜራ እያነሳሁ አልስልም በሚል ካሜራውን ገዛሁ፤ከዚያ በኋላ ማንሳቱን ቀጠልኩኝ ማለት ነው፡፡
እስከ ዛሬ ከ200 ሺህ በላይ ፎቶዎችን አንስተዋል ይባላል፡፡ እውነት ነው?
አይበልጥም ብለሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ዲጂታል ካሜራ ከመጣ ያነሳሁት እንኳን ብዙ ስለሆነ ያለኝ የፎቶ ብዛት ወደ 300 ሺህ ሳይጠጋ አይቀርም፡፡ የካሴት ከቨር የሆኑ ወደ 300 አልበም ፎቶዎች አሉኝ። የቀድሞው ቱሪዝም ኮሚሽን የሚያሳትመውን ፖስተርና ፖስት ካርድ ሰብስቤ ከ400 በላይ አለኝ፡፡ እነሱ ጋ አንድም የለም፤ሸጠው ሸጠው ጨርሰውታል፤የተሳሳተ ነገር ሲያወጡ እየፃፍኩ አርማቸዋለሁ፡፡
በሻሸመኔ መጀመሪያ መሬት የተሰጠው ለራስ ተፈሪያን አይደለም፤የሚለውን ማስረጃ ከየት ነው ያገኙት?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ እኛ ሻሸመኔ በቋሚነት መኖር የጀመርነው በ1949 ዓ.ም ነው፡፡ በ1942 ግን በጃንሆይ በጎ ፈቃድ መሬት የተሰጠው ለሶስት አፍሮ አሜሪካዊያን ነው፡፡ እነሱም፡- ግላድስተን ሮቢንሰን፣ ጀምስ ፓይፐር እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ፓይፐር ብቻ ነበሩ፡፡
እነዚህ አፍሪካ አሜሪካዊያን እንዴት ከጃንሆይ መሬቱ ሊሰጣቸው ቻለ?
በጣም ጥሩ፡፡ ፋሽስት ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ አገራችንን በ1928 ዓ.ም በወረረ ጊዜ ጃንሆይ ለአምስት አመታት ለንደን ነበሩ፡፡ ያኔ ጥቁር አሜሪካውያን ኒውዮርክ ሀርለም ላይ ኢትዮጵያን ለማገዝና ለመዋጋት 17 ሺህ ያህል ሆነው ተመዝግበው ነበር፡፡ ነገር ግን ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና እንግሊዝ ዙሪያውን ከበው ስለነበር መግባት አይቻልም ነበር፡፡ ስለዚህ ሶስት ተደማጭነት ያላቸው አፍሮ አሜሪካዊያን ተመርጠውና ተወክለው ጃንሆይ የሚኖሩበት ለንደን ድረስ ሄደው አነጋገሯቸው፡፡ የጥቁር አሜሪካዊያኑንም ኢትዮጵያን የማገዝ ፍላጎት አስረዷቸው፡፡ ከህዝቡ ማለትም ከአሜሪካውያኑ የተውጣጣውን አራት ሚሊዮን ብርም ሰጧቸው፤ ምክንያቱም ኒውዮርክ ላይ “የምኒሊክ ክበብ” የሚል አቋቁመው የእርዳታ ገንዘብ ያሰባስቡ ነበር፤ ጥቁር አሜሪካውያኑ፡፡ በኋላ ጃንሆይ “ወደ ኢትዮጵያ መግባት አትችሉም፤ዙሪያውን በቅኝ ገዢዎች የተከበበ ነው፤ ለስንቅና ትጥቅም አይመቻችሁም፤ እዛው ሆናችሁ ታገሉልን” አሏቸው “እንግዲያውስ አንድ አስተባባሪ ስጡን; ብለው ጠየቁ፡፡ ከዚያ ዶክተር መላኩ አማኑኤል በያን የተባለውን የአጎታቸውን ልጅ፣ ጃንሆይ በአስተባባሪነት ሰጧቸው፡፡ ዶ/ር መላኩ በአሜሪካ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ነው፡፡ ዶ/ር መላኩም አሜሪካ ሄዶ “Ethiopian World Federation” የተባለ ማህበር እ.ኤ.አ በ1937 አቋቋመ፡፡ ከዚያም እርዳታውን እያስተባበረ ለአርበኞች ትጥቅና ስንቅ፣ መድሀኒት፣ ለጃንሆይ መኖሪያ ሁሉን ማሟላት ጀመረ፡፡
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጃንሆይ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ለጥቁር አሜሪካዊያኑ ደብዳቤ ፃፉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ላደረጉት ውለታ ለማመስገን፣ ሻሸመኔ ላይ መጥተው እንዲኖሩ የሚጋብዝ ደብዳቤ ነው፡፡ በዚህ ግብዣ መሰረት ሚስተር ጀምስ ፓይፐር፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ፓይፐርና ግላድስተን ሮቢንሰን በ1942 ዓ.ም ወደ ኢትዮጰያ መጥተው ሻሸመኔ መኖር ጀመሩ፡፡ የሚገርምሽ ወ/ሮ ፓይፐር ለንደን ውስጥ ለጃንሆይ ምግብ ያበስሉላቸው ነበር፡፡ እንዲያውም በወቅቱ የሻሸመኔ አካባቢ ባላባትና ሹም ፊታውራሪ ጁላ ሾቤ ይባሉ ነበር፡፡ ከዚያም ጃንሆይ ለፊታውራሪው፤“እነዚህ ባለውለታችን ስለሆኑ አምስት ጋሻ መሬት ፈልገህ ለአውራ ጎዳናው ቅርብ የሆነ ቦታ ስጣቸው” ብለው አዘዙ፡፡ ፊታውራሪውም፤ “ጃንሆይ፤ የመንግስት መሬት አውራ ጎዳናው ላይ የለም፤ መሬት ያለው ከከተማው ርቆ ወደ ኮፈሌ ገጠሩ ውስጥ ነው፤እዚያ ደግሞ አውሬዎች በብዛት ስላሉ ለመኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ወላይታ ይሂዱና እዚያ ይኑሩ” የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ጃንሆይ ደግሞ “አይ አንዴ አዝዤሀለሁ፤ከየትኛውም ሰው ላይ ቀምተህ ስጣቸውና ቤተ-መንግስት መጥተህ ሪፖርት አድርግ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ በዚህ መሰረት ፊታውራሪ ጁላ፤ ከቄስ ገመኔ ላይ ሶስት ጋሻ መሬት፣ ከዋቻሞው ባላባት ላይ ሁለት ጋሻ ቀምተው አውራ ጎዳናው ላይ ያለ መሬት ሰጧቸው፡፡ ከዚያ ጀምስ ፓይፐርና ባለቤታቸው ወይዘሮ ፓይፐር እንዲሁም ግላድስተን ሮቢንሰን ከ1942 ጀምሮ መኖር ጀመሩ፡፡ ባልና ሚስቱ የአይሁድ እምነት ተከታይ ሲሆኑ ግላድስተን ሮቢንሰን የኦርቶዶክስ እምነትን ተቀብሎ ተጠምቆ በኋላ ስሙ ፍቅረ ስላሴ ይባል ነበር፡፡ ስምህ ማን ነው ሲባል እንኳን የባርነት ስሜ ግላድስተን ሮቢንሰን፣ የነፃነት ስሜ ፍቅረ ሥላሴ እያለ ይመልስ ነበር፡፡ በቅርብ ከአራት አመት በፊት ነው ፍቅረ ስላሴ የሞተው፤ እንቀራረብ ነበር፡፡
ታዲያ ጃማይካዊያን መቼ ነው ወደ ሻሸመኔ የመጡት?
ጃማይካዊያኑ በ1962 ዓ.ም ማለትም አፍሮ አሜሪካኑ ከመጡ ከ20 ዓመታት በኋላ ነው ስምንት ሆነው ወደ ሻሸመኔ የመጡት፡፡ አፍሮ አሜሪካኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ጃማይካዊያን በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ስለነበሩ ሻይቅጠልና ትምባሆ እያስተከሏቸው ነበር፡፡ ያን  ጊዜ ለራሳቸውም ነፃነት ስላልነበራቸው ኢትዮጵያን እንደ አሜሪካዊያን ሊያግዙ አልቻሉም ነበር፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላ በ1962 ዓ.ም ስምንት ጃማይካዊያን መጡ፤በወቅቱ የግቢ ሚኒስትር በነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ፣ ከቤተ መንግስት፤ “በሉ እንግዲህ ከእናንተ ጋር ይኑሩ” ብለው ወደ ሻሸመኔ ላኳቸው፡፡ አፍሮ አሜሪካኖቹ ተቃወሙ፡፡
ምን ብለው ተቃወሙ?
“እኛ አፍሮ አሜሪካዊያን ነን፤እነሱ ጃማይካዊያን ናቸው፤ በምንም አንገናኝም እንዴት አብረን እንኖራለን፤ይሄ መሬት የተሰጠው በኢትዮጵያ ወርልድ ፌደሬሽን ስም ለእኛ ነው” የሚል ነበር ተቃውሞው፡፡ ከዚያም የላኳቸው ፀሀፌ ትዕዛዝ፤“መልካችሁ አንድ አይነት ነው የአገራችሁ ርቀትም እንደዚያው፤በዚያ ላይ ለኢትዮጵያም ያላችሁ ፍቅር አንድ አይነት ነው ስለዚህ አብራችሁ ኑሩ” ሲባል “አብረን አንኖርም” ብለው አሻፈረኝ ሲሉ፣ የጃንሆይ ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅ ጣልቃ ገብተው፤ “ለወደፊቱ እኔ ወንዶገነት ወዳለኝ መሬት እወስዳቸዋለሁ፤ አሁን አምስት አምስት ሄክታር ይሰጣቸውና ይቀመጡ; ተብሎ የዝዋይ አውራጃ ገዢ በተገኙበት (ፊታውራሪ ጁላ በወቅቱ ሞተው ስለነበር) ልጃቸው ነጌሶ ጁላ እየለካ፣ አምስት አምስት ሄክታር ሰጥቷቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ሲደረግ የተፈረመው ደብዳቤ በእጄ ላይ ስላለ ማስረጃ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ለምን እንደሚቆለምሙት አይገባኝም፡፡
ጃንሆይ ጃማይካን ለመጎብኘት በሄዱ ቀን ሲዘንብ ያደረ ዝናብ ቆመ እንጂ እሳቸው እዚያ ሲደርሱ ዝናብ አልዘነበም ብለው እንደሚከራከሩም ሰምቻለሁ—–
አዎ እከራከራለሁ፡፡ ለምን መሰለሽ—-ጃንሆይ በጃማይካዎቹ አምላክ የተባሉት በ1923 ገና ዘውድ እንደጫኑ ነው፡፡ ጃማይካን የጎበኙት እ.ኤ.አ በ1958 ሊወርዱ ሲሉ ነው፡፡ ጉብኝቱም በጃማይካ መንግስት ግብዣ የተደረገ ነው፡፡ የዝናቡን ጉዳይ በተመለከተ ጃንሆይ እዚያ ከመድረሳቸው ከአንድ ቀን በፊት ሲዘንብ አደረና፣ ከገጠር ከአገሪቱ ጥግ ሁሉ ኪንግስተን ከተማ አምላኩን ለመቀበል የመጣውን የጃማይካ ህዝብ ሲቀጠቅጥ አድሮ፣ በነጋታው ጃንሆይ እዚያ ሲደርሱ ዝናብ አልነበረም፡፡ ፊልሙ እኔ ጋር ይገኛል፤ላሳይሽ እችላለሁ፤በዕለቱ በአቀባበሉ ላይ ጃንጥላም አልተያዘም፡፡
ጃንሆይን አምላክ ብሎ የተቀበለውም ያልተቀበለውም የጃማይካ ህዝብ እሳቸውን ለማየት ኪንግስተን ከተማ ወጥቶ ዝናብ እየቀጠቀጠው ስለነበር ጃንሆይ ከአውሮፕላን ሳይወርዱ አየር ላይ ለሶስት ሰዓት ያህል ቆይተዋል የሚባለውስ—-?
ትክክለኛውን ስሚኝ፡፡ አየር ላይ አልቆዩም፤እንደውም ከአውሮፕላን ሲወርዱ ህዝቡ አጥሩን ሰብሮ ክቡር ዘበኛውን ጥሶ፣ አውሮፕላኑ ስር ይፍለከለክ ነበር፤ ይሄ ነው የሆነው፡፡
ታዲያ የታሪክ መፋለሱ የመጣው ከታሪክ ፀሐፊዎች ነው ወይስ በጃንሆይ ወገን የተወራ ነው?
እንደውም ጃንሆይ ስለ ራሳቸው አጋንነው የሚያወሩት ነገር የለም፡፡ አንድ ጊዜ ማርከስ ጋርቬይ እንግሊዝ ሊጎበኛቸው ሄዶ እንኳን አልተቀበሉትም፡፡
ማርከስ ጋርቬይ በ1890ዎቹ መጨረሻ “ከኢትዮጵያ አምላክ ይወጣል ወደ አፍሪካ ተመለሱ” እያለ የነበረና አሜሪካ የሚኖር ጃማይካዊ አይደለም እንዴ?
አዎ፤ እሱ ጃንሆይን አምላክ ነው ብሎ የሚናገር፣ በጃማይካዊያን ዘንድ እንደ ትንቢት ተናጋሪ የሚቆጠር ስለነበር፣ እኔ አምላክ ሳልሆን አምላክ እያለ ያወራል ብለው አልተቀበሉትም ነበር። በኋላ ጃንሆይ “ህዝባቸውን ለጣሊያን ትተው ወደ እንግሊዝ ሄደዋል” እያለ ሲከሰሳቸው ዶ/ር መላኩ አማኑኤል በያን ያልኩሽ የጃንሆይ የአጎት ልጅ፣ ክሱን በመቃወም መልስ ይሰጠው ነበር። ስለዚህ ጃንሆይ አምላክ መባላቸውን አጥብቀው ከመቃወማቸው የተነሳ ጃማይካ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ ሰጥተዋል፤ ትልልቅ የሀይማኖት መሪዎቻቸውን ሰብስበው፡፡ አባ ላዕከ ማሪያም የተባሉ የኦርቶዶክስ ቄስ በአጥማቂነት መድበው፣ “እኛ የምንከተለውን የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከተሉ፤ እኛ አምላክ አይደለንም” ነው ያሉት ጃንሆይ። ጃማይካዎች “እናውቃለን ይሄ የትህትና ንግግር ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም እኔ ክርስቶስ መሆኔን ለማንም እንዳትናገሩ ብሏል በመፅሀፍ ቅዱስ፤ ስለዚህ እኛ እርሶ አምላክ እንደሆኑ እናምናለን” አሉ፡፡ ኦርቶዶክስን የተቀበሉ ተጠመቁ፤ ያልተቀበሉ እርሳቸውን አምላክ ናቸው ብለው ቀጠሉ፤ ይሄው ነው፡፡ ወሬው ግን ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ ተመልከቺ፡፡ ለምሳሌ የሻሸመኔ ልጆች ማህበር አለን፡፡ ከመሃላችን ትልልቅ የመንግስት ኃላፊዎችም አሉ፤የአካባቢው ተወላጆች የሆኑ—-ስንሰበሰብና ራስ ተፈሪያን መጀመሪያ መሬት እንዳልተሰጣቸው፣ ለጥቁር አሜሪካውያኑ የተሰጠ የምስጋና መሬት እንደሆነ በፊት ለፊታቸው ስንናገር፣ ትንፍሽ አይሉም፤ እውነታውን ያውቁታላ፡፡
እርስዎ እንግዲህ የፎግራፍ ባለሙያ እንጂ የታሪክ ተመራማሪ አይደሉም፡፡ ይህን ሁሉ ታሪክ ያወቁት አካባቢው ላይ ስለኖሩ ብቻ ነው ወይስ ታሪክ የመሰነድ ፍላጎትም አለዎት?
በነገራችን ላይ ፎቶግራፍ ስታነሺም ታሪክ ነው የምታሰባስቢው፡፡ አንዳንድ ታሪኮች ተፅፈው በፎቶግራፍ ሲደገፉ ታሪክን የበለጠ ተጨባጭና ተዓማኒ ያደርጉታል፡፡ በዚያ ላይ ፎቶግራፍ ስታነሺ ገብቶሽ አንድን ነገር መሰረት አድርገሽ ስለምታነሺ፣በመረጃነት በአዕምሮሽም በወረቀትም ይቀመጣል፡፡ ታዲያ ታሪክ ሲዛባ ስትመለከቺ፣ ለምን የሚለውን ጥያቄ ታነሺና ፎቶዎቹን በማስረጃነት ታቀርቢያለሽ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የጊታር ተጫዋቹ መስፍን አበበ በሰይፉ በኢቢኤስ ላይ ቀርቦ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጊታር ተጫዋች ነኝ ብሎ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ውሸት ነው፤አሁን በእርግጥ በህይወት የለም እንጂ ፊት ለፊት እንነጋገር ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ ዘንድ በርካታ መረጃ አለ፡፡ መስፍን አበበ አምስተኛ ጊታር ተጫዋች ነው፡፡ ለዚህም “የጊታር አጀማመር በኢትዮጵያ” በሚል 60 ገፅ ፅሁፍ ፅፌ፣ 120 ያህል ፎቶግራፎች አስገብቼበት ተቀምጧል፡፡ በቅርቡ ይፋ ይሆናል፡፡
የመጀመሪያዎቹን ማለትም ከመስፍን አበበ በፊት ጊታር ተጫውተዋል የሚሏቸውን በቅደም ተከተል ሊነግሩኝ ይችላሉ?
አንደኛ የክቡር ዘበኛው ተዘራ ሃይለሚካኤል በ1952 ዓ.ም ተጫውቷል፣ ሁለተኛው የጅማው ግርማ ምንተስኖት በ1962 ጊታር ይጫወት ነበር፤ በኢቲቪ ሁሉ ይታይ ነበር፡፡ ሶስተኛው በ1968 የዘፈነው ፀጋዬ መርጊያ ነው፣ ሙሉጌታ ረታ አለሙ በ1970 በጊታር ዘፍኗል፡፡ መስፍን አበበ ከአራቱ በኋላ በ1972 ነው የመጣው፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፤ በሚል በመረጃ አስደግፌ በቅርቡ እለቀዋለሁ ብያለሁ፡፡
ሌላው የአርሲዋ ሴት ጉደቱ ካዎ ጉዳይ ነው። ይህቺ የአርሲ ሴት የቀድሞው ቱሪዝም ኮሚሽን ፎቶዋን በፖስት ካርድነት ይጠቀመው የነበረች ሴት ናት፡፡ ስለዚህች ሴት እኔ በ1981 ዓ.ም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ፣ “አባቴን አፈላልጉኝ” በሚል ርዕስ ከአስር በላይ መጣጥፍ ፅፌ ነበር፡፡
ምክንያቱም ፎቶውን ያነሳሁት እኔ ነኝ በሚሉ ሰዎች መሀል ጭቅጭቅ ተነስቶ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በ2000 ዓ.ም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት መሀመድ ድሪር፣ የግብርና ሚኒስትር የነበሩት ሰው፣ የኦሮሚያ ባህል ቢሮ ኃላፊው እሷም አሀራ ተቀምጣ፣ ትልቅ ዝግጅት ተዘጋጅቶ አዳማ ላይ 105 ካ.ሜ ቦታ ተሸልማለች፡፡ የሀራምቤ ኮሌጅ ባለቤት ለ10 ዓመት በየወሩ 300 ብር እንድትወስድ ቃል ሲገባ በቦታው ተገኝቼ ፎቶ አንስቻለሁ፤ ስትወስድም አውቃለሁ፡፡ ቦታውን 45 ሺህ ብር መሸጧንም አውቃለሁ፤ነገር ግን በ2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምንም እንዳልተደረገላት ክዳለች፡፡
ጋዜጠኛውን ስለ ራሷ የተፃፉ 10 የጋዜጣ ኮፒና 15 ፎቶግራፎች ሰጥተነው፣ 15 ቀን ስጡኝ አስተካክላለሁ ብሎ ሁለት ወር ተጠበቀ፤ አልመለሰም፡፡ ከዚያ እውነታውን በፌስቡክ “የኢቲቪ ጋዜጠኛ የቀደዳ አርበኛ” በሚል ለቀቅኩት፡፡ ይሄው እዚህ አዳራሽ ውስጥ ለጥፌዋለሁ፤ አንብቢው፡፡ እውነተኛ ማስረጃ ስላለኝ አንድም ሰው አልተቃወመም፡፡ ለምን ታሪክ ይዛባል። አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰስ መዋሸት ነበረባቸው?
አቶ ሀብተስላሴ—–?
አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ናቸው፡፡ እኔ በግሌ ለቱሪዝም መበልፀግ በሰሩት ትልቅ ስራ ክብር አለኝ፤ ነገር ግን በዚች ሴት ፖስት ካርድ ላይ አሻጥር ሰርተዋል። ፎቶውን ያነሳት አንቶኒዮ ቪራኖ የተባለው ጣሊያናዊ ነው፡፡ ክሪያዚዝ ዜርፎዝ የተባለ ፎቶ ቤት የነበረው አርመን፣ አሁን ፒያሳ ክሪያዚዝ ኬክ ቤት አጠገብ የነበረ ፎቶ ቤት ባለቤት “ከለር ማተም ጀምሬያለሁና ስጠኝ ጥሩ አድርጌ ላትምልህ” ይልና ከአንቶኒዮ ይቀበላል፡፡ ኮሚሽነሩ የክሪያዚዝ ጓደኛ ስለነበሩ፣እሳቸው ጋ ወስዶ በራሱ ስም አሳተማት፡፡
አንቶኒዮና ክሪያዚዝ አቶ ሀብተስላሴ ጋ ሄደው ይካሰሳሉ፡፡ ለክሪያዚዝ አግዘው ፍርድ ሳይሰጡ ፎቶዋን እንደያዙ ደርግ መጣና እስር ቤት ከተታቸው፡፡ ከዚያ ራሱ ደርግ ፈታና መልሶ የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አደረጋቸው፡፡ ፊልሟን አገኟትና በራሳቸው ስም፤ “Girl On the Baro River Gambella” ብለው አወጥዋት፡፡ ይሄንን ታሪክ ከራሷ ከጉዳቱ ካዎ መስማት ትችያለሽ፤ አርሲ ነገሌ በህይወት ያለች ሴት ናት፤ ታገኚያታለሽ፡፡ ላገናኝሽ እችላለሁ፡፡
ይህን ሁሉ ውሸት ለማጋለጥ ነው በ1981 በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ “አባቴን አፈላልጉኝ” በሚል ርዕስ በተከታታይ 10 መጣጥፍ ያወጣሁት፡፡ ያኔ ቱሪዝም ኮሚሽን “ስህተቱን እናርማለን” በሚል የፃፈልኝ ደብዳቤ በእጄ ላይ አለ፡፡
የኢቲቪው ጋዜጠኛ ይህን ሁሉ ማስረጃ ካሰባሰበ በኋላ ነው ያልሆነ ታሪክ ያወጣው፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ በተለይ እውነታውን እያወቅሁት ተጣሞና ተዛብቶ ሲቀርብ በጣም እናደዳለሁ፡፡
ሌላው ሰው ጋ የማይገኝና እኔ ብቻ አለኝ የሚሉት ፎቶ አለዎት?
እኔ ከሌላው የምለየው በአንድ ወቅት በምንም ሁኔታ ያነሳሁትን ፎቶ አልጥልም፤ ምክኒያቱም ፎቶ ቅርስ ነው፣ማስረጃ መፅሀፍ ነው፡፡ ሌላው ያነሳና ይጥለዋል፡፡ እኔ  በማንኛውም ጉዳይ ላይ መረጃ ስፈልግ አቀርባለሁ፤ልክ አሁን ለተዛቡ ታሪኮች መረጃ እንደማቀርበው ማለት ነው፡፡ ለፎቶግራፎች ክብር ሰጥቼ በማስቀመጤ ነው ከሌላው የምለየው፡፡ ስለዚህ አንቺ ፎቶ አንስተሸ ከጣልሽ እኔ ጋ አለ፤አንቺ ጋ የለም ማለት ነው፡፡
የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አቅርበው ያውቃሉ?
በጣም ብዙ ጊዜ በተለያየ ቦታ አቅርቤያለሁ። በጣሊያን ካልቸር፣ በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ፣ በፑሽኪን አዳራሽ —- በበርካታ ቦታዎች አቅርቤያለሁ፡፡
በራስ ተፈሪያን ላይ የጻፉት መጽሀፍ በምን ደረጃ ላይ ነው?
ተፅፎ ካለቀ ቆይቷል፡፡ ታሪኩን በትክክል እንዲቀመጥ ለማድረግ ነው እንጂ ብር የለኝም። አሁን ግን የኔ የፎቶ ተማሪ የነበረ፣ እንደገና እኔን ኤዲቲንግ ያስተማረኝ በኃይሉ ግርማ የተባለ ልጅ፣እንደሚያሳትምልኝ ቃል ገብቷል፤እግዚአብሔር ይርዳው እንግዲህ፡፡
እስኪ ስለ ራስዎ ይንገሩኝ—በምን ሁኔታ ነው የሚኖሩት?
አሁን በቋሚነት የምኖረው አዳማ ነው፡፡ 45 ዓመት እዚህ የኖርንበትን ቤት፣ “ለእናታችሁ ነው ያከራየነው አናቅህም” ተብዬ ሰባት ዓመት ተከራክሬ አሸንፌ፣እዚሁ ቤት ውስጥ ብቻዬን እኖራለሁ። በትዳር በኩል የመጀመሪያዋ ባለቤቴ ከመላዕክና ከሰው የተፈጠረች ነበረች፤ በጣም ትረዳኝ ነበር ፈጣሪ ወሰዳት፤ አላመሰገንኩትም መሰለኝ፡፡
ሁለተኛዋ ባለቤቴ፣ ጥሩ ጥሩ ልጆች ሰጥታኛለች፤ሶ ስት ልጆች ከሰጠችኝ በኋላ እራሴ እንደመጣሁ እራሴ እሄዳለሁ አለች፤ ሸኘሁ መቼስ ምን አደርጋለሁ፡፡ አሁን ብቻዬን ነው የምኖረው፡፡
ልጆችዎ የት ነው ያሉት?
ልጆቹን ወስዳቸዋለች፡፡ ከአባት እናት ይበልጣል በሚል ሀዋሳ ይዛቸው ትኖራለች፡፡ ከሟች ሚስቴ የወለድኳት የመጀመሪያ ልጄ ትዝታ ንጉሴ፣ ራሷን ችላ እየሰራች ነው፡፡ እኔም ራሴን ችዬ እየኖርኩ ነው።

No comments:

Post a Comment