Friday, July 8, 2016

ተወዳዳሪ ዕጩዎችንና የሚሾሙባቸውን አህጉረ ስብከት ቁጥር ለመጨመር በአስመራጭ ኮሚቴው የቀረበው ጥያቄ ውሳኔ የሚያገኘው፣ በዛሬው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ እንደኾነ ተገልጧል፡፡


  • ካህናት እና ምእመናን መረጃዎችንና አቤቱታዎችን ወደ አስመራጭ ኮሚቴው እያጎረፉ ነው
  • የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት እና የሚሾሙባቸው አህጉረ ስብከት ቁጥር እንደሚጨምር ተጠቁሟል
  • የኑፋቄው ሕዋስና የአማሳኙ ቡድን፥ ምልምሉን ለማሾምና ‘ስጋቱን’ ለማስወገድ እየሠራ ነው
  • ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ሢመቱ፣ ከዘመን መለወጫ በፊት እንዲከናወን ፍላጎት አላቸው
  • ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ እንጂ ሕዝብን የሚያሳዝን እንዳይኾን ማሳሰቢያዎች እየተሰጡ ነው
 ኮሚቴው፣ ተጠቋሚዎቹን በመመርመር፣ በማጥናትና በማጣራት ውጤቱን እስከ ትላንት፣ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲያቀርብ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው ወስኖ የነበረ ቢኾንም፤ የተጠቋሚዎቹ ብዛትና ሒደቱ የሚጠይቀው ከፍ ያለ ጥንቃቄ የቀነ ገደቡን መራዘም አስፈላጊ አድርጎታል፡፡
ቀደም ሲል ለሹመት የሚያስፈልጉት ሐዲሳን ኤጲስ ቆጶሳት ከ14 – 16 እንደሚኾኑ ቢገለጽም፤ በሞተ ዕረፍት በተለዩትና በእርግና በሚገኙት አባቶች ምክንያት ክፍት ከኾኑት መንበረ ጵጵስናዎች ብዛት አንፃር፣ በኮሚቴው የሚቀርቡ ዕጩዎችና የሚሾሙባቸው አህጉረ ስብከት ቁጥርየተወሰነ ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ተጠቋሚዎችን አጣርቶ ለውድድር የሚቀርቡትን ዕጩዎች ቁጥር ለማሳወቅ የሚያስፈልገው ጊዜ ከሰንበት ዕለታት ውጭ በ15 የሥራ ቀናት ቢራዘምም፤ ተወዳዳሪ ዕጩዎችንና የሚሾሙባቸውን አህጉረ ስብከት ቁጥር ለመጨመር በአስመራጭ ኮሚቴው የቀረበው ጥያቄ ውሳኔ የሚያገኘው፣ በዛሬው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ እንደኾነ ተገልጧል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ ዋና ጸሐፊን በአስረጅነት የያዘውና ሰባት አባላት ያሉበት አስመራጭ ኮሚቴ፣ በምልአተ ጉባኤው የተሰጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን አስመልክቶ፤ ትላንት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ተወያይቷል፡፡ ቅዱስነታቸው፣ ሥርዓተ ሢመቱ ከዘመን መለወጫ በፊት እንዲካሔድ ያላቸውን ፍላጎት የገለጹ ሲኾን፣ ኮሚቴው በጀመረው መንገድ፣ ተጠቋሚዎቹን አጣርቶ ዕጩዎቹን በየአካባቢው የመለየቱ ሥራ በከፍተኛ ጥንቃቄ የማካሔዱ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡
ሥራውን በይፋ ከጀመረ ኹለት ሳምንታትን ያስቆጠረው አስመራጭ ኮሚቴው፣ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተቀበላቸውን ከ118 ያላነሱ ተጠቋሚዎችን በመያዝ፥ የመመርመር፣ የማጥናትና የማጣራት ሥራውን በከፍተኛ ትጋትና ግልጽነት በተመላበት ውይይት እያካሔደ ይገኛል፡፡
የተጠቋሚዎች ስም ዝርዝር፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች ይፋ መኾኑን ተከትሎ፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን፣ መረጃዎችንና አቤቱታዎችን በተለያዩ መንገዶች ለአስመራጭ ኮሚቴው እያጎረፉ እንደሚገኙና ይህም ለማጣራት ሥራው አዎንታዊ እገዛና ድጋፍ እያደረገ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡
ድጋፍም ተቃውሞም የሚታይባቸውን የካህናትና የምእመናን መረጃዎችና አቤቱታዎች፣ እንደ ግብአት ከመጠቀም አንፃር፣ በኮሚቴው የመጀመሪያዎቹ የሥራ ቀናት በብርቱ አከራክሮ እንደነበር ታውቋል፡፡ ማጣራቱ፥ ተጠቋሚዎቹ በቤተ ክህነት ባላቸው ማኅደር ላይ ብቻ ተመሥርቶ መካሔድ አለበት፤ በሚል የተንጸባረቀው አቋም፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንና በምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቡ፣ የካህናትንና የምእመናን ተሳትፎ አስፈላጊና ግድ የሚያደርጉትን ድንጋጌዎች ያላገነዘበና ተቀባይነት ያለው የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ከማካሔድ አኳያም የሚያገለግል ባለመኾኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የመረጃዎቹንና የአቤቱታዎችን ይዘትና መግፍኤ በጥንቃቄ በማንጠር መጠቀም እንደሚገባም የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
ኮሚቴው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የተጣለበትን ሓላፊነት ክብደት ተረድቶ፣ ከማንኛውም አሉታዊ ግፊትና ተጽዕኖ ተጠብቆ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አባት ለማስመረጥ እንጂ ሕዝብን የሚያሳዝን ሥራ እንዳይሠራ የተለያዩ አካላት እያሳሰቡ ሲኾን፤ አጋጣሚውን የሞት ሽረት ያደረገው የተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋስና የአማሳኙ ቡድን በበኩሉ፥ ግንባር ፈጥሮ፣ምልምሎቹን ለማሾምና ስጋቴ ናቸው የሚላቸው ንጹሐንና ቀናዕያን ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ከዕጩዎች እንዳይገቡ በብርቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በጠቅላይ ጽ/ቤት በመምሪያ ሓላፊነትና ጸሐፊነት፣ በሀገረ ስብከትና በክፍለ ከተማ ሓላፊነት፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በስብከተ ወንጌል ሓላፊነትና ሠራተኝነት የሚገኙት የኑፋቄው ሕዋስ አባሎች፤ ሥራቸውን ትተው ጠዋትና ማታ በብፁዓን አባቶች ማረፊያዎች በማንዣበብ፣ ከተጠቋሚዎቹ መሀል ለጥፋታቸው ከለላ የሚሰጧቸውንና እንዲሾሙላቸው የሚፈልጓቸውን በመለየት ውትወታቸውን ማጠናከራቸው ተገልጿል፡፡
በተጠቋሚዎችና በብፁዓን አባቶች መካከል በአንድ ወቅት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን እያስታወሱ፣ ምልምሎቻቸውን የሚልቁ፣ ከዓላማቸውና ከጥቅሞቻቸው አንፃርም እንደ ዕንቅፋት የሚያዩዋቸውን ተጠቋሚ አባቶች ማጥቆርና ቅራኔን ማባባስ፤ እንዲኹም፣ በጎጠኝነት መከፋፈል ዓይነተኛ ስልቶቻቸው ሲኾኑ፤ ዳጎስ ያለና አማላይ ገንዘብ፣ የቤት፣ የተሽከርካሪና መሰል የቁሳቁስ ስጦታዎችም እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
በምዝበራ ሰንሰለቱ ያሉ የአንዳንድ አድባራት አለቆች፣ በአማሳኝነት ካከበቱት የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እንዲያዋጡ ሲጠየቁ፤ የተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋሱም፣ ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ኃይሎች በሚያገኘው ድጋፍ ሲሞናዊነቱን አጠናክሮ፣ ወኪሎቹን ለከፍተኛው ማዕርገ ክህነት በማድረስ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ሰርጎ ለመግባት በማሰፍሰፉ አስመራጭ ኮሚቴውና ብፁዓን አባቶች በአጠቃላይ እንዲያውቁበት ያስፈልጋል፡፡
በየአጥቢያው ሙስናን ኑፋቄን በመዋጋት፥ ለዕቅበተ እምነት፣ ለፍትሕና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሲጋደሉ የቆዩ ወገኖች፤ የኑፋቄውንና የአማሳኝ ቡድኑን ኅቡእ እንቅስቃሴ፣ በፀረ ኑፋቄና በፀረ ሙስና ስልቶች በንቃት እየተከታተለ በማጋለጥ፣ የሤራውን ባሕርይና አስፈላጊ መረጃዎችን ለአስመራጭ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እያሳወቀ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment