Tuesday, July 12, 2016

ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ!


ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ
በቅርቡ የግንቦት ሰባት የውጪ ጉዳይ ግንኙነት ዋና ሹም ነአምን ዘለቀ ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፤ ከ1991 ዓ.ም እ.ኤ.አ ጀምሮ ፤ የኤርትራው ሻእቢያዊ መንግስት ፤ በኤርትራ ህዝብ ላይ የሚፈፀመውን ኢ ሰብአዊ የመብት ረገጣ አስመልክቶ ፤ በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ አለማቀፋዊ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ አቅርቦት የነበረውን መጠይቅ በተመለከተ ፤ የድርጅታቸው አባላት የሆኑትንና ያልሆኑትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፤ የመቃወሚያ ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ ጠይቀው ነበር ። “አርበኛው” ነአምን ዘለቀ ፤ ለወዳጃችን የሻእቢያ መንግስትና ባለስልጣናት ስንል ፤ የማንሆነው የለም በሚል መርህ ይመስላል ፤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለማስረገጥ ውሃ ባይቋጥርም ፤ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ፤ ያላቀረቡት ሰበብ አልነበረም ።
ሰሞኑን ደግሞ የኸው የተባበሩት መግስታት ድርጅት ፤ ኤርትራ በህዝቧ ላይ የምትፈፅመውን የመብት ረገጣ አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ፤ አቋም ይይዝ ዘንድ ጠይቋል ። እንደተለመደው ነአምን ዘለቀ ፤ ለወዳጃቸው ሻእቢያ ሲሉ ፤ “ከገሙ አይቀር ጥንብት” እንደሚባለው፤ ለአፍሪካ ህብረትም ፐቲሽን የማስፈረም ዘመቻቸውን ይጀምራሉ ተብሎም ይጠበቃል ። ይህን ካላደረጉ ደግሞ ፤ ራሳቸው “በደብል ስታንዳርድ” መታማታቸው የማይቀር ይሆናል ። አለበለዚያ ደግሞ የፐትሽኑ ፊርማ ፤ አቧራ ከማስነሳት ሌላ ፋይዳ እንዳልነበረው ማሳያ ከመሆን አይዘልም ። ሁሉንም በመቆየት እናየዋለን ፤ እያየነውም ነው ።
ወደ ዋናው ነጥቤ ልግባ ። “ኢሳኢያስ ሌላ መታወቂያቸው ሌላ ብየ ልጀምረው” ። ፕሬዚደንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ የሚታወቁት ፤ የአሜሪካውን አምባሳደርና አገራቸውን ዩናይትድ ስቴትስን በአደባባይ በመዝለፍ ፤ የጣሊያኑን ኤምባሲ አንደኛ ፀኃፊ ከምፅዋ አስሮ አምጥቶ አስመራም በካቴና አስሮ ሁለት ቀናት አሳድሮ ከአገር ማባረር ፤ ብሎም የቀድሞውን የተባበሩት መንግስታት ፤ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ፤ ዋና ፀኃፊ የነበሩትን ኮፊ አናንን ፤ በማዋረድ መዝለፍና በመሳሰሉት ድርጊቶቻቸው ነው ። የአለማችን ዲፕሎማሲያዊ መድረክና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች ፤ ለእያንዳንዳቸው የአገር መሪዎች ፤ ደረጃና መለኪያ አላቸው ። ስለዚህም ኢሳኢያስ አፈወርቂን የዲፕሎማሲው ማሕበረ-ሰብ የሚመለከቷቸው ፤ ለአለም ህግ የማይገዙ ፤ ጋጠወጥ ፤ ባለጌና ስርአት አልባ የሃገር መሪ አድርጎ ነው ።
እነ ነአምን ደግሞ ስለ ኢሳኢያስ ሊያሳዩን የሚከጅሉት ስእል ለየት ያለነው ። መከራከሪያ ነጥቦቻቸው “ኢሳኢያስ ፤ ሌባ መሪ አይደሉም” ፤ “ኢሳኢያስ ሃገራቸውን ይወዳሉ” ፤ በዚህ ላይ “ለኛ ለግንቦቶች ብቸኛ ወዳጃችን ናቸው” ፤ የሚል ነው ። እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር እመለስባቸዋለሁ ።
አለም አቀፉ ድርጅት ደግሞ ኢሳኢያስንና ባለስልጣኖቻቸውን ፤ እየከሰሰ ያለው ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ።
ክርክራችን ሁሉ የባዶ ቆርቆሮ ጩኸት እንዳይሆን ፤ የክሶቹን አቢይ ጭብጦች ፤ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ በአጭሩ ላስቀምጥ ። አንደኛ የኤርትራው መሪና ባለስልጣናቱ የአገሪቱን ህዝብ በባርነት ስርአት ውስጥ በማማቀቅ ፤ ሁለተኛ በቶርቸር በማሰቃያት ፤ ሶስተኛ የእምነት ነፃነትን በመግፈፍ ፤ አራተኛ በአስገድዶ መድፈር ፤ አምስተኛ ህዝቡን እንዳሻው በመግደል ፤ ስድስተኛ ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ህዝብን በገፍ በማሰርና ፤ ሰባተኛ ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን መፈፀም ናቸው ።
ነአምንና ካምፓኒያቸው ግን የክርክራቸው ማጠንጠኛ ነጥቦች ፤ ከላይ የተጠቀሱት ክሶች አይደሉም ። ኢሳኢያስ አፈወርቂ አገራቸውን ይወዳሉ ነው የሚሉን ። አለም አቀፉ ድርጅት እኮ በኤርትራው ፕሬዝደንት ላይ የአገር ፍቅር ክስ አልመሰረተም ። ኢሳኢያስ ኤርትራን ቢወዱ ባይወዱ የራሳቸው ጉዳይ ነው ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደግሞ አንድ መሪና ግብረአበሮቹ አገራቸውን ወደዱ አልወደዱ የሚከስበት ህግም ሆነ መለኪያ የለውም ። ፈፅሞም አያገባውም ። “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ።
ለማንኛውም ግን በአጭሩ የነነአምንን የመጀመሪያ መከራከሪያ ነጥብ ፤ በሰው ልጅ መለኪያ እንመልከተው ። አንድ መሪ አገሩን መውደዱን የምናይበት የቀን ተቀን ተግባራት አሉት ። አገሩን የሚወድ መሪ ፤ ህዝቡን በኑሮው አስመርሮ ለባሕር አሳ ሲሳይ አይዳርግም ፤ አገሩን የሚወድ መሪ የአገሪቱን ወጣቶች ህይወት ፤ የምድር ሲኦል አያደርግም ፤ አገሩን የሚወድ መሪ ፤ የህዝቡን ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች አይንድም ። በሱዳን “ሸገራብ” በኢትዮጵያ “ሽመልባ” ወይም ህፃናትና እስከ አስራ ስምንት አመት ታዳጊዎችን የሚቀበለውን የUNHCR መጠለያ ጣቢያ “እንዳባጉናን” አስመልክቶ UNHCR የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች መመልከት ኤርትራዊ ሁሉ የሚቀበለውን መከራ ለማሳየት በቂ ማርጋገጫዎች ናቸው ። ከአስመራ ጉዞዎቼ ባንዱ ላይ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ገጠመኝ ተመልክቻለሁ ።
ፕሬዚደንት ኢሳኢያስ ለህዝባቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲህ ነበር የገለፁት ። ከአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደርጋሉ ። ጠያቂው “የኤርትራ ወጣቶች በድንበር እየወጡ በብዛት እየተሰደዱ ነው” በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎ ? ሲል ጥያቄውን ያቀርባል ። የኢሳኢያስ መልስ ፤ “ድሮስ ቢሆን “ድርብ ጥርስ ፡ አያምር ወይ አይነክስ” በራሱ ወልቆ ከሄደልህ እፎይ ነው”፤ ነበር ያሉት ። ይህ ነው እንግዲህ አገር መውደድ ? የራሱ ህዝብ ላይ እንዲህ የመረረ ንቀት ያለው ሰው ነው አገሩን የሚወድ ? ታዲያ እንግዲህ ፤ እነ ነአምን የኢሳኢያስን አገራቸውን መውደድ በምን ለክተውት ይሆን ?
ግንቦቶች ሁለተኛው መከራከሪያ ነጥባቸውን ሲያቀርቡ ፤ “ኢሳኢያስ ሌባ መሪ አይደሉም” ፤ ይሉናል ። የሰባዊ መብት ተሟጋቹ ኮሚሽን ኢሳኢያስን በስርቆት አልከሰሰም ። ያም ሆኖ ግን ፤ አንድ መሪ ሰረቀ ወይም አልሰረቀም የሚባለው ፤ በአገሪቱ ህግና ስርአት ውስጥ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ሲኖር ነው ። ይህ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው ሰርቋል ወይም አልሰረቀም ሊባል የሚችለው ? ለኢሳኢያስና ባለስልጣኖቻቸው ፤ አገሪቷ ኤርትራም ሆነች ህዝቧ ፤ የግል ንብረቶቻቸው ናቸው ። በአገሪቱ ላይ ሰፍኖ ያለው ፤ የወታደር መሳፍንት አገዛዝ ሲሆን ፤ ኤርትራ በ5 ስሪቶች ተከፍላ በአምስት ጀነራሎች ትመራለች ። እንደዘመነ-መሳፍንት ዘመን ፤ አምስቱ ጀነራሎች በግዛቶቻቸው ላይ ምንም ተጠያቂነት የለባቸውም ። እንደልባቸው ያሻቸውን የማድራግ መብቶች አሏቸው ። ጀነራሎቹ የየራሳቸው እስር ቤቶች ፤ መመርመሪያ ጣቢያዎችና ፤ በጀት ሲኖራቸው ፤ ልባቸው በፈቀደ የኤርትራን ህዝብ እንዳሻቸው ይነዱታል ።
ሌላ ቦታ ሄደን ፤ እገሌ ሌባ ነው ወይም አይደለም ከማለታችን በፊት ፤ ትንሽም ይሁን ትልቅ ድርጅት ገንዘብን አስመልክቶ ፤ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ባህል ሊኖረው ይገባል ። ግንቦት ሰባትና ኢሳት ከህዝብ የሰበሰቡትንና የሚሰብስቡትን ገንዘብ ፤ ከተቋቋሙ ጀምረው አስቆጥረው ያውቃሉን ? የዋሁን ህዝብ እንተወውና ሌላው ቢቀር ፤ ግንቦትና ኢሳት ስለገንዘብ አውጣጥና አያያዛቸው ለአባሎቻቸው ይፋ አድርገው አሳይተዋልን ? በምን የሞራል የበላይነት ነው ፤ አto ነአምን እገሌ ሌባ ነው ወይም አይደለም ፤ ይሰርቃል ወይም አይሰርቅም የሚል ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉት ?
እነ ኢሳኢያስም የሻእቢያን ሃብት አለማስቆጠር የጀመሩት ገና በጧቱ “ሀ” ብለው ትግላቸውን ሲጀምሩ ነው ፤ “ከአህያ የዋለች እንደሚባለው……” ይኽው ልክ ግንቦት ሰባትና ኢሳትም ፤ ዛሬ በሰለጠነው በሃያ አንደኛው ዘመን ላይ እየኖሩ ፤ የሻእቢያን ፈለግ በመከተል ፤ ወጪና ገቢያቸው በታቦት ጨርቅ ተሸፍኖ ቁጭ ብሏል ። ስለዚህ ኢሳኢያስ ሌባ ነው ወይም አይደለም ለማለት ግልፅነትና ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል ።
ሌላውና ሶስተኛው መከራከሪያቸው ላይ ልምጣ ። ለአርበኞች ግንቦት ሰባት “ብቸኛ ወዳጆቻችን ኢሳኢያስና ባለስልጣኖቻቸው ናቸው” የሚል ነው ። ታዲያ ምን ይጠበስ ። ሻእቢያና መሪዎቹ የናንተ ወዳጆች ስለሆኑ አለም አቀፉ ድርጅት ፤ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ አይቶ እንዳላየ መሆን ነበረበት ? ምንም እንኳ ዛሬ ፤ ወደ አሜሪካ ኑሯቸው የተመለሱ ቢሆኑም ፤ አምና ፊሽካው ሲነፋ ከአሜሪካ የሄዱትን አርበኞች ፤ ኢሳኢያስና ባለስልጣናቱ ስላስጠለሏቸው ፤ የኤርትራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ አለም አቀፉ ድርጅት አይቶ እንዳላየ ማለፍ ነበረበት ? ለናንተ ሲባል የኤርትራ ህዝብ በባርነት መገዛት አለበት?
አንዴ በአስመራ ነዋሪ ላይ የተጣለ ቅጣት ትዝ ይለኛል ። ጊዜው 2011 እ.አ.አ. ነው ። አስመራ ከተማ ላይ የሚላስ የሚቀመሰ እህል ጠፋ ። ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባ ማንኛውም አይነት የእህልም ሆነ የጥራጥሬ ዘር በከተማ መውጫና መግቢያ ላይ ከህዝቡ ተወረሰ ። አላማው ባይታወቅና ፤ የአስመራ ነዋሪ እስካሁን መልስ ባያገኝለትም ፤ የከተማው ህዝብ በረሃብ እንዲቆላ ተደርጓል ። ይህ የሆነው ደግሞ በፕሬዚደንት ኢሳኢያስ ትአዛዝ ነበር ። የሰው ልጅ የመጀመሪያው ጥያቄ ደግሞ ምግብ ነው ። ህዝቡ ይህን በመሰለ ረሃብ እየተቀጣ የመኖር ዋስትናው ተገፎ ፤ ሰባዊ መብቱ ተደፍጥጧል ።
ይህን በተመለከተ ፤ ከምፅዋ በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ተሳፍሬ ወደ አስመራ ስመለስ ፤ ያጋጠመኝንና አንዲት ሴት ያደረጉትን ላውጋችሁ ። ነፋሲት ላይ ተሳፈሩ ። እንደገቡ ሴትዮዋ ሁሉንም ሰው በተለማማጭ አይኖቻቸው በንቃት ይመለከታሉ ። በኋላ ላይ እንደነገሩን ፤ የአስመራ ከተማ ነዋሪ ናቸው ፤ ነፋሲት አካባቢ ካለ ገጠር ዘመዶቻቸውን ጥየቃ ሄደው እየተመለሱ ነበር ። በግምት እያንዳንዳቸው ከሶስት ወይም ከአራት ኪሎ የማይበልጡ ሁለት ቋጠሮዎች በነጠላዎቻቸው ጫፎች ላይ አስረው በመቀመጫቸው ጀርባ ግራና ቀኝ ፤ ደብቀው አስቀመጡ ። የነፋሲትን ኬላ እንዴት እንዳለፉት ባላውቅም ፤ ቋጠሮዎቻቸው አስመራ ከተማ መግቢያ ላይ ተያዙባቸው ። የኬላው ፈታሽ ከሻእቢያ መንግስት የተሰጠውን ትእዛዝ ለማስፈፀም ቸኮለ ። የያዙትን የእህል ቋጠሯቸውን ፈትተው ለመንግስት ያስረክቡ ዘንድ ወተወተ ። ሴትዮዋ ልጄ “መአረይ” እባክህ ተውልኝ ። አራስ ልጅ እቤቴ ተኝታለች ከወለደች ገና ሳምንቷ ነው ። የሚላስ የሚቀመስ በቤቴ የለኝም እያሉ በገባኝም ባልገባኝም ትግርኛ ለመኑ ።
የኬላው ፈታሽ ፤ ወይ ፍንክች ያአባ ቢላዋ ልጅ ፤ ቋጠሮውን ያስረክቡ ብሎ ደረቀ ። ሴትዮዋ እህሉን ለማስረከብ ከአውቶቡሱ ወረዱ ። መሬት ላይ ቁጢጥ ብለው ተቀምጠው ሁለቱንም ቋጠሮዎቻቸውን ፈቷቸው ። በድንገት ብድግ አሉና ሁለቱንም የኩታቸውን ጫፎች ይዘው ፤ እህሉን ወደላይ በተኑት ። አብዛኛው እህል አንድ ቦታ መሬት ላይ ተዘረገፈ ። ላንተ ከማስረክብ ለወፎች ሰጥቼ ብፀድቅ ይሻለኛል አሉ ። መሬቱ ላይ የተዘረገፈውን እህል በእግራቸው በታተኑትና ወደ አውቶቡሱ ገቡ ። ሴትዮዋ ይህን ያደርጋሉ ብሎ የጠበቀ ባለመኖሩ ፤ አውቶቡሱ ውስጥ ያልነበረ ፀጥታ ሰፈነ ። የሁሉም ሰው አይኖች ሴትዮዋ ላይ አተኮሩ ። ሴትዮዋ ወደ አውቶቡሱ ሲገቡ ፊታቸው ላይ መረጋጋት ይታይ ነበር ። ፈታሾቹም ግራ ተጋብተው ተነጋገሩና ፤ አውቶቡሱ ቶሎ እንዲሄድ አደረጉ ። እኛም አስመራ ገባን ።
ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፤ የተለመደው ጋዜጠኛ ፕሬዚደንት ኢሳኢያስን የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ ጥያቄ ይጠይቃል ። ከጥያቄው መካከል አንዱ ፤ እህል ከገጠር እንዳይገባ የተደረገበት ጉዳይ ነበር ። ፕሬዚደንት ኢሳኢያስ ለክልከላው መልስ ከመስጠት ይልቅ እንዲህ በማለት ነበር የመለሱት ። ‘የአስመራ ሰዎች እንዴት አድርጋችሁ እህል ወደ አስመራ እንደምታስገቡ አውቃለሁ ። በጥሬ እህል ብንከለክላችሁ በወተት ላስቲክ እያደረጋችሁ በሊጥ መልክ እህል እንደምታስገቡ አውቃለሁ” ሲሉ ተናገሩ ። አሿፊው የአስመራ ሰው ሰውየው ኩሽና ገባ ብሎ አሾፈ ። ድኻው ደግሞ መፃኢው ኑሮና ተስፋው በምናቡ እየታየው ልቡን ሽብር ሞላው ። ምነው ይህ ህዝብ ከዚህ የማይሻል የለም ብሎ አይሰደድ ?
የኤርትራ ህዝብ እየተቀጣ ያለው በተለያየ መልኩ ነው ። ስለዚህ ሻእቢያ ፤ ለኔ ወዳጄ ነው ተብሎ ፤ የኤርትራ ህዝብ መከራ አይደፈጠጥም ። የኤርትራ ህዝብ ዛሬ መናገር ባይችልም ይታዘባል ።
ይህን የፐቲሽን ፊርማ አስመልክቶ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አስተያየቶቻቸውን ሰንዝረዋል ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ መሳይ ከበደ ናቸው ። መሳይ ከበደ እነ ነአምን ዘለቀ ያቀረቡትን ፐቲሽን ለምን እንዳልፈረሙ ምክንያታቸውን በሞራል ጥያቄ አስታከው ፤ መደረግ የነበረበትን ሲመክሩ እንዲህ ይላሉ ።
አለም አቀፉ ድርጅት በኤርትራ ላይ ከማተኮር ይልቅ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተመሳሳይ ክስ ማቅረብ ነበረበት ባይ ናቸው ። እንዴት ነው ነገሩ ዶ/ር መሳይ ? ዓለም አቀፉ ድርጅት ፤ ርስዎ ለኢትዮጵያውያን መልክትዎን ማስተላለፍ በሚወዱበት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በነጭ ወረቀት ላይ በጥቁር ቀለም ያሰፈረው መጠይቅ የሚለው ፤ “የኤርትራ መንግስት ፤ ወደኤርትራ ገብተን ፤ ምርመራችንን እንድናካሂድ ባለመፍቀዱ በ20 አገራት ውስጥ በስደት የሚኖሩ 42ሺህ ኤርትራውያንን አነጋግረን ባገኘነው መረጃ ላይ ተመርኩዘን ያወጣነው ሪፖርት ነው” ሲል አስረግጦ አስቀምጧል ።
ታዲያ ኮሚሽኑ በኤርትራውያኑ ላይ ያደረገውን ቃለ መጠይቅና ምርመራ ፤ ተመርኩዞ እንዴት የኢትዮጵያን መንግስት መክሰስ ይችላል ? “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ። አማርኛዬ ካልገባዎት በእንግሊዝኛ አስተርጉመው ያንብቡት ። ይህን ስል ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰባዊ መብት ችግር የለበትም እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ ።
ፅሁፍዎ እንደሚያስረዳው ፤ አንዱ መልእክትዎ እኔ ይህን ፐትሽን አልፈረምኩም የሚል ነው ። ጥሩ አደርገዋል ፤ በኢሳኢያስ ዳፋ ለምን የእርስዎ ስም ይቆሽሽ ። ያም ሆኖ ግን ፤ እርስዎ ፐቲሽኑን ፈረሙ አልፈረሙ የሚኖርዎ ድምፅ አንድ ብቻ ነው ። ስለዚህ ቋቱን አይሞላውም ወይ አይቀንሰውም ። ከዛሬ ሁለት ሺህ አመት በፊት ፤ ጲላጦስ ይሁዳውያኑ ፊት የተጠቀመበትን “አራድነት” ተጠቅመው የኢትዮጵያ መንግስት ለምን አልተከሰሰም በሚል ሰበብ ፤ ከታሪክ ተጠያቂነት ውልቅ ማለትዎን ደግሞ ፤ ታላቅ ጥበብ እንደሆነ ሳላደንቅልዎ ለማለፍ አልፈለኩም ።
የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት በሰብአዊ መብት ረገጣ መከሰሳቸውን አስመልክቶ ፍትህ ተዘናበለ ፤ ፍርድ ተገመደለ ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው ሰው ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ናቸው ።
ኤርትራ ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊት ጀምሮ ፤ በሻእቢያ ወዳጅነታቸው በሚታወቁት ሻለቃ ትንተና ፤ ግዙፏና ቱጃሯ ሳውዲት አረብ “በወሃቢ” ምንጭነት ሳትጠየቅ ፤ ብሎም በየመንና በአገሯ ውስጥ፤ በውጪ ዜጎች ላይ ለምታደርሰው ሰብአዊ መብት ጥሰት ሳትከሰስ ፤ ሚጢጢዋ ኤርትራ ተከሰሰች የሚል ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነው ። ስለዚህም የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ያቀረበው ክስ ፍትህ የጎደለው ነው ይላሉ ። ከሻለቃው ፅሁፍ ያልገባኝ ጉዳይ ፤ የኤርትራ ባለስልጣናት በህዝባቸው ላይ ላደረሱት ሰብአዊ መብት ረገጣ ፤ ግድያ ፤ ቶርችርና ፤ አስገድዶ መድፈር ፤ ሳውዲት አረብ እስክትጠየቅ ድረስ በፍፁም አይነሳ ነው? ወይስ የኤርትራ ባለስልጣናት እንደ ሳውዲት አረብ ጉቦ እየከፈሉ ከሰባዊ መብት ረገጣ መዝገብ ላይ ስማቸውን ያስፍቁ ነው ነገሩ ። ስለ 400 ሽዎቹ በባርነት ደረጃ እየማቀቁ ስላሉት የኤርትራ ዜጎች ፤ ሴቶች ልጆቹ ያለፈቃዳቸው በኤርትራ ከፍተኛ የጦርና የሲቪል ባለስልጣናት ስለሚደፈሩበት ሰላማዊ ዜጎች ግን ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም ።
ለእርስዎና ለወዳጆችዎ ለግንቦት ሰባት ድርጅት ፤ ሻእቢያ ምሽግ እስከሆነ ድረስ ፤ የኤርትራ ህዝብ የግፍና የመከራ ቀንበር እንደተሸከመ ይኑር ? የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርቱን ያቀረበው በነዚህ ነጥቦች ላይ ሆኖ ሳለ ሻለቃ ዳዊት እየነገሩን ያለው ስለሳውዲት አረብ ነው ። ሻለቃ ፤ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” የሚባለው ።
ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ፤ አንድ ጥያቄ ሻለቃውን መጠየቅ እፈልጋለሁ ። ይህ ፤ ሁሌ ፅሁፍዎ ስር የሚያስቀምጡት “Institute for strategic and Security Studies” የሚባለው መስሪያ ቤት ፤ የኤርትራ ፤ የግብፅ ፤ የሳውዲ ወይስ የሴኔጋል ነው ? የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከሆነ ደግሞ እንደዚያ መጠቀስ ነበረበት ብዬ ነው ። ይህቺን መስሪያ ቤት እንደርስዎ ሁሉ አንድ ሌላ የቀድሞው የደርግ መንግስት ባለስልጣን ሲጠቀምባት በማየቴ ፤ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ምሽግ መስላኝ ነውና አደራዎን ያብራሩልኝ ። የአሜሪካ ከሆነች ደግሞ የአሜሪካ ብለው ይግለጿት ። ካልሆነችም የማን መሆኗን ይንገሩን ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተሟጋች 47 አገሮች ያሉበት አካል በኮንሰንሱስ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተመርኩዞ ፤ የአፍሪካ ህብረትም የራሱን ምርመራ አድርጎ በሰባዊ መብት ረገጣ ተጠያቂ የሆኑትን የኤርትራ ባለስልጣናት ለይቶ በማውጣት ለፍርድ ያቀርብ ዘንድ ፤ ጥያቄ ቀርቦለታል ።
ግንቦት ሰባትና ነአምን ዘለቀ ለተባበሩት መንግስታት እንዳዘጋጁት ሁሉ ፤ ለአፍሪካ ህብረትም ሌላ ፐትሽን እንደሚያዘጋጁ በመተማመን ፤ የዚያ ሰው ይበለን እያልኩ ፤ በዚያ ሁኔታ ላይ አስከምንገናኝ በዚሁ ልሰናበታችሁ ።
ጁላይ 4 ቀን 2016 እ.ኤ.አ
ላስ ቬጋስ ፤ ኒቫዳ

No comments:

Post a Comment