Thursday, July 7, 2016

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 19 ባቡሮች በቴክኒክ ችግር መቆማቸው ተጠቆመ


የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከጀመረ ገና ዘጠኝ ወራትን ብቻ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በአሁኑ ወቅት ካሉት 41 ቀላል ባቡሮች (Trams) ውስጥ 19 የሚሆኑት በቴክኒክ ብልሽት በቃሊቲ ዲፖ መቆማቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ካሉት 41 ቀላል ባቡሮች ውስጥ 28 ባቡሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና የቀሩት አብዛኞቹ በተጠባባቂነት እንደሚቆሙ፣ በጣም ጥቂት ባቡሮች የቴክኒክ ችግር ሲገጥማቸው ለጥገና እንደሚቆሙ በመግለጽ መረጃውን አስተባብሏል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ ባቡሮቹ የቆሙት በቴክኒክ ችግር መሆኑን፣ ተጠግነው ወደ ስምሪት ለመግባትም የመለዋወጫ አቅርቦት እንደሚያስፈልግና ይህንን አስመልክቶ ግን የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር ቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንም ሆነ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ማኔጅመንት ኮንትራክተር ጋር ሕጋዊ ስምምነት ባለመኖሩ ችግሩ ሊቀረፍ እንዳልቻለ ይጠቅሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የኮንትራት ስምምነት ዓይነት “EPC” (ኢንጂነሪንግ ግዥና ግንባታ አጠናቆ ማስረከብ) ሲሆን፣ ለዚህም 475 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በውሉ መሠረት ኩባንያው ከዲዛይን ጀምሮ መሠረተ ልማቱን በመገንባትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ 41 ቀላል ባቡሮችን አስገብቶ፣ አገልግሎቱ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን  የጀመረው የትራንስፖርት አገልግሎትና አስተዳደር ኮንትራት ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች ጋር በመፈራረም ነው፡፡
የመሠረተ ልማት ግንባታውን የፈጸመው ቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ሼንዞን ሜትሮ የተባሉት የቻይና ኩባንያዎች ተጣምረው ይህንን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን፣ ሼንዞን የተባለው ኩባንያ የትራንስፖርት አገልግሎቱንና አስተዳደሩን የማከናወን ኃላፊነትን ሲይዝ፣ መሠረተ ልማቱን የገነባው ኩባንያ ደግሞ የጥገና ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት በኮንትራቱ ተሰጥቶታል፡፡
ይህ ስምምነት ለሦስት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን፣ ስምምነቱ ግን በመሠረተ ልማቱ ላይም ሆነ በባቡሮቹ ላይ የሚከሰቱ የቴክኒክ ችግሮችን ከመጠገን ባለፈ መለዋወጫ የሚያስፈልጋቸው ወጪዎችን እንደማይመለከት ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
በመሆኑም ባቡሮቹ ላይ የተከሰተው የቴክኒክ ችግር መለዋወጫን የሚጠይቅ በመሆኑና ወጪውን ሸፍኖ መለዋወጫዎቹን የማስገባት ግዴታ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ላይ መውደቁ፣ ለኮርፖሬሽኑ ድንገተኛ እንደሆነበት ይጠቁማሉ፡፡
ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ከ“EPC” ኮንትራክተሩ ገና ባልተረከበበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከተጀመረ ዓመት ሳይሞላው የመለዋወጫ ግዥ ጥያቄ መቅረቡ ያልተጠበቀ መሆኑን ነው፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ከ41 ባቡሮች አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 28 ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የቆሙት በተጠባባቂነት ሲሆን፣ ለተሳታፊዎች ደኅንነት በምንሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ጥቃቅን ችግሮች ሲከሰቱ እንዲቆሙና እንዲጠገኑ ይደረጋል፤›› ሲሉ የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፣ ባቡሮች በተጠባባቂነት የሚቆሙበት ምክንያት አንድም በሥራ ላይ ያሉ ባቡሮች የቴክኒክ ችግር ሲገጥማቸው ለመተካት፣ እንዲሁም  አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን ባቡር ለመተካት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የትራንስፖርት አስተዳደር አገልግሎቱን የሚሰጠው ሼንኮን ሜትሮ በአገሩም ተመሳሳይ አሠራር እንዳለውና ከኮርፖሬሽኑ ጋር በገባው ውል መሠረት፣ በሁለቱ የቃሊቲና የአያት ዴፖዎች ለእያንዳንዳቸው አራት ባቡሮችን በተጠባባቂነት እንዲቆሙ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
የቴክኒክ ችግር ለሚገጥማቸው ባቡሮች መለዋወጫ የሚያስፈልግ በሚሆንበት ወቅትም ሆነ ሌሎች ማናቸውም ወጪዎችን ደመወዝን ጨምሮ ራሱ ኮንትራክተሩ በመሸፈን ያመጣውን ወጪ ኮርፖሬሽኑ የሚተካበት የማኔጅመንት ውል መኖሩን፣ በመሆኑም በመለዋወጫ ወጪ አሸፋፈን ምክንያት የሚስተጓጎል ነገር አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡
በዋናነት ባቡሮቹ እያጋጠማቸው ያለው የሙቀት ማቀዝቀዣ ሲስተም ብልሽት መሆኑን፣ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ባቡሮቹ መጫን ከሚገባቸው 300 ሰው በላይ አጭቀው የሚጭኑ በመሆናቸው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወረቀት ትኬት አገልግሎቱ በመጀመሩና ይህ አሠራር ተሳፋሪን ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ፣ የሁለት ብር ትኬት ቆርጠው ከጫፍ ጫፍ መጓዝ ባቡሮቹ በተሳፋሪዎች እንዲጨናነቁ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ፡፡
በባቡር መስመሮቹ የመሳፈሪያ ጣቢያዎች የተገጠሙ ሊፍቶችና ኤስካሌተሮች ተንቀሳቃሽ መወጣጫዎችን አገልግሎት እንዳይጀምሩ የተደረበት ምክንያት አንድ ሊፍት ለመጠገን የሚያስፈልገው ወጪ ውድ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በባቡር መስመሮቹ ባሉ 22 ጣቢያዎች ላይ ሊፍትና ኤስካሌተሮች በግራና ቀኝ መገጠማቸውንም ያስታውሳሉ፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ መፍትሔው ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ካርድን ወደ ሥራ ማስገባት በመሆኑ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ካርድ የፕሮጀክቱ አካል ቢሆንም የ“EPC” ኮንትራቱ አካል አለመሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከከተማ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በቀን ከ350 ሺሕ እስከ 370 ሺሕ ብር ገቢ እየተገኘ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ደረጀ፣ ‹‹በዚህ ገቢ የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን ይቅርና የአገልግሎት ወጪውንም መሸፈን አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ አስተዳደር በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ድጎማ ለማድረግ ቀደም ሲል የተደረሰውን መግባባት ወደ ተግባር እንዲለውጥ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

No comments:

Post a Comment