ወያኔ እያደረገው እንዳለው በወልቃይት የአማራ ማንነት ሕዝባዊ ጥያቄና እንቅስቃሴ ዙሪያ ሕገወጥ የሆነ የኃይል ወይም የአፈሙዝ ምላሽ እንጅ የገዛ ሕገመንግሥቱ በሰጠውና በደነገገው መብት መሠረት ፈጽሞ ሊያስተናግደው እንደማይችልና እንደማይፈልግም እስከአሁን ከፈጸማቸው ሕገወጥ ድርጊቶቹ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ወያኔ ለዚህ ሕዝባዊና ሕጋዊ የማንነት ጥያቄና እንቅስቃሴ ፍጹም አሳፋሪ በሆነ መልኩ ከሕግ አግባብ ውጭ በተደጋጋሚ  ወገኖቹን የተቃውሞ ሰልፍ በማስወጣትና ሕገወጥ መፈክር በማስተጋባት በሕግ አግባብ ተይዞ በዚሁ አግባብ ብቻ ሊታይ በሚገባው ጉዳይ ላይ በዚህ ሕጋዊ ሒደት ላይ ሕገወጥ የሆነ ጣልቃገብነት በመፈጸም በሕጉ መሠረት ሊገኝ ከሚገባው መፍትሔ አስቀድሞ የራሱን ሕገወጥ ጥቅም የሚያስጠብቅ ምላሽ በመስጠት ፍትሐዊና ሕጋዊ ውጤት እንዳይገኝ ሲያደናቅፍና ሲያሰናክል መቆየቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
እሱ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ለሕዝባዊ የማንነት ጥያቄ መንግሥት ነኝ ከሚል አካል ፈጽሞ በማይጠበቅና እግጅ በወረደ መልኩ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ሕጋዊውን ጥያቄ ለማዳፈን ለማሰናከል የሕዝብ የብዙኃን መገናኛውንም አላግባብ በመጠቀም በሰፊው እየተንቀሳቀሰ እያለ መቸም ሐፍረት የሚባል ነገር ፈጽሞ አያውቃቸውምና ትንሽም ሳያፍሩና ሳይሸማቀቁ ሌላውን ወገን ሕግንና ሕግን ብቻ በተከተለ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚገባ በተደጋጋሚ አበክረው ለማሳሰብ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ወያኔ ሊያውቀው የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር የጨዋታው ሕግ በተሻረበትና በፈረሰበት ሜዳ ላይ ሕግ አክብሬ ልንቀሳቀስ በማለት ጭዳ የሚሆንና ከንቱ መሥዋዕትነት ሊከፍል የሚችል ወይም የሚገደድ ቂል የትም ቦታ ሊኖርና ሊገደድ የማይችል መሆኑን ነው፡፡
እነሱ ሕግን አክብረው ለመንቀሳቀስ ቅንጣት ታክል እንኳ ፍላጎቱና ፈቃደኝነቱ ሳይኖራቸው እጅግ ትዝብት ላይ ሊጥል በሚችል ደረጃ የሕዝብ የብዙኃን መገናኛን ሕገወጥ ለሆነ እንቅስቃሴያቸው ፍጹም ሚዛናዊነትንና ሌሎች መርሖዎችን ፍጹም ባልጠበቀ መልኩ አላግባብ እየተጠቀሙ ሌላው አካል ሕግን ብቻ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ መጠየቃቸው የሰዎቹን ገደብ የለሽ ራስ ወዳድነት ግፈኝነትና ድንቁርናን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነውረኛ የወንበዴ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ ሒደት የምንረዳው ሀቅ ቢኖር ወያኔ ለዚህ ሕዝባዊና ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሐዊ ምላሽ ለመስጠት ፍጹም ፈቃደኛ አለመሆኑን ነው፡፡
ለዚህም ነው ይሔንን ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ከሽግግር መንግሥትነት ዘመኑ ጊዜ ጀምረው ባነሡ ወገኖች ላይ ሕገወጥና ግፍ የተሞላበት ምላሽ ሲሰጥ በሐሰት እየወነጀለም በግፍ እርምጃ ሲቀጣ የኖረው፡፡ እንዲሁም ያለ አካባቢው ሕዝብ ፈቃድ ፍላጎትና ይሁንታ በአንባገነናዊ እርምጃ የወልቃይት ጠገዴን አና የጠለምን ሑመራን የጎንደር መሬቶችን ወደ ትግራይ ከልሎ ሲያበቃ “ይህ የምትሉት የማንነት ጥያቄ በ1983ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ምላሽ አግኝቷል! አሁን አናስተናግድም” ሲል ሕጋዊ የሕዝብ የማንነት ጥያቄውን ሊያስተናግደው እንደማይፈልግ በመግለፅ ላይ የሚገኘው፡፡
አሁን በዚህ ሰሞን ሲያደርገው እንደተስተዋለውም የሕዝባዊ የማንነት ጥያቄውን አስፈጻሚ ወኪል አባላት ላይና በእነዚያ አካባቢዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ባሉ በርካታ ወገኖች ላይ ሐሰተኛ ስም ሰጥቶ በአሸባሪነት እየወነጀለ እነሱን ወኅኒ በማውረድ ሕዝባዊና ሕጋዊ የማንነት ጥያቄውን አዳፍኖ ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ወገኖች ወያኔ ያነሣባቸው ክስ እንኳን ሐሰተኛ መሆኑን በሚገባ እያወቅነው ይቅርና ያነሣባቸው ክስ እውነት ቢሆንም እንኳ ለዚህ ተጠቃቂው ያንን ሕገወጥ ውሳኔ ወስኖ እነኝህ ቦታዎችን ወደ ትግራይ ከከለለበት ጊዜ ጀምሮ ከ25 ዓመታት በላይ ብዙ መራራ ዋጋ እያስከፈለ ሲቀርብ ለቆየ ሕዝባዊና ሕጋዊው የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሐዊ ምላሽ ለመስጠት በፍጹም ፈቃደኛ ሊሆን ያልቻለው ወያኔ እንጅ በምንም ተአምር ሕገ መንግሥታዊ፣ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) እና ሰብአዊ የማንነት ጥያቄያቸውን ሕጋዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ለማሰጠት በግፍ መብቱና ዕድሉ ስለተነፈጋቸው ስለተከለከሉ ለሕዝባዊና ሕጋዊ የማንነት ጥያቄያቸው ፍትሐዊና ሕጋዊ ምላሽ ለማግኘት ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ የተገደዱት ወገኖች አይደሉም፡፡
ስለሆነም ወያኔ ለዚህ ሕዝባዊና ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሐዊ ምላሽ በፍጹም የማይሰጥ መሆኑን አረጋግጧልና ወያኔ ለሕዝባዊው የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሐዊ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቅ በከንቱ ወርቃማ ጊዜያችንን ማባከን ነውና በተሻረና በፈረሰ የጨዋታ ሕግ መጫወታችንን ትተን በቦታው በተተካው የጨዋታ ሕግ በመጫወት ወያኔን አንበርክከን ለሕጋዊና ፍትሐዊ የማንነት ጥያቄያችን እኛው እራሳችን አግባብ የሆነውን ምላሽ በመስጠት የሚያስከፍለውን መሥዋዕትነት በመክፈል መብታችንን ማስከበሩ ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ፈጥነን እንነሣ!!!
ልብ በሉ! ልበ በሉ! አሁንም ልብ በሉ! ይሄንን ዕድል ሳንጠቀምበት ቆራጥ ወገኖቻችንን አሳልፈን ሰጥተን ለአውሬ አስበልተን አርፈን ለመቀመጥ ከዳዳን ወያኔ ይሄንን ጊዜ እንደምንም ተቅለስልሶ ካሳለፈና የተነሣበትን እሳት አታሎና አባብሎ ካጠፋ በኋላ ነገ እጅግ ከፍቶ በመምጣት ዳግም ቀና ልትል በማትችልበት አኳሃን እጅግ አዋራጅና አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዳትሆን አድርጎ በሰብእናህ ላይ ተጫውቶ እንደሚያጠፋህ ልታውቀው ይገባል፡፡
ወገኔ ሆይ! ከዚህስ እንኳንና አንድ ሞት ሽህ ሞትን ልንመርጥ ይገባናልና አሁኑኑ ደፍረንና ቆርጠን ብንነሣ የትንኝ ያህል ቀሎ የምናገኘውን ወያኔን በቀላሉ ጨፍልቀን በመጣል ይህችን ሀገር ከነቀርሳዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንገላግላት!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው