Sunday, July 17, 2016

የወያኔ ማጎሪያ ካምፕ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚባል እስረኛ የለም ሲል ካደ::


የወያኔ ማጎሪያ ካምፕ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚባል እስረኛ የለም ሲል ካደ:: …………
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው የመጨረሻ ትዕዛዝ መሠረት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚባሉ ታራሚ እንደሌሉት ለፍርድ ቤቱ በድጋሚ በደብዳቤ አስታወቀ፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸውና ‹‹ተከላከሉ›› የተባሉት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ አቶ አንዳርጋቸው የመጨረሻ መከላከያ ምስክር መሆናቸውን አሳውቀው ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚያሰሙ እርግጠኛ እንደነበሩ ገልጸው፣ ምስክሩ በማረሚያ ቤት የሉም መባሉ እንዳሳዘናቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸውን የክሱ ምሰሶ በማድረግ እነሱን (ተከሳሾቹን) እንዳሠለጠኑ፣ ተልዕኮ እንደሰጡና እንዳስታጠቁ አድርጐ የሐሰት ክስ የመሠረተባቸው፣ አቶ አንዳርጋቸው እንደማይገኙ (እንደማይያዙ) አስቦ እንደነበር ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አቶ አንዳርጋቸው ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ በመናገራቸው ምክንያት እነሱ (ተከሳሾቹ) በመከላከያ ምስክርነት እንደቆጠሯቸው አስታውሰዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የዕድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ በመሆናቸው መከላከያ ምስክር ሆነው መቅረብ እንደሌለባቸው በመጥቀስ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ እስከ ሰበር ድረስ በመሄድ ሊያስከለክል ቢጥርም፣ ሰበር ሰሚው ችሎት ይግባኙን ውድቅ አድርጐ ቀርበው እንዲሰሙ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የደረሰው ማረሚያ ቤት ‹‹እኔ ጋ የሉም›› ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ እንዳልገባቸው ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አቶ አንዳርጋቸው የት እንዳሉ ዓቃቤ ሕግ ያውቃል›› የሚሉት ተከሳሾቹ፣ ማረሚያ ቤቱ የት እንዳሉ የማያውቅ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡
ያለምንም ምክንያት በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው መበታተናቸውን የሚናገሩት ተከሳሾቹ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ከሕግ አንፃር ምን ይላል? የታሰረ ሰው በማረሚያ ቤት የለም ሲባል ምን ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት ማረሚያ ቤቱ ምስክሩ እሱ ዘንድ እንደሌሉ በተደጋጋሚ ስለገለጸና ፈጣን ፍትሕ መስጠት ተገቢ በመሆኑ፣ ተከሳሾቹ ቀደም ብለው ያሰሟቸው ምስክሮች በቂ ሆኖ ፍርድ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን አስተያየት ከሰማ በኋላ ተወያይቶ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment