Thursday, July 28, 2016

አንድ ህዝብ አንድ ሀገር! (አብርሃ ደስታ)


ሰው ነፃነት ይፈልጋል። ነፃነት ላለመፈለግ ራሱ ነፃነት ይጠይቃል። ስለዚህ ነፃነቱን የሚቃወም አይኖርም። ምክንያቱም ነፃነትን በራስ መቃወም በራሱ ነፃነት ነው። ሰው ነፃ ለመሆንም ላለመሆንም ነፃ መሆን አለበት። ሰው ነፃ ላለመሆን የመወሰን ነፃነት አለው። ዋናው ጉዳይ ዉሳኔው የራስ መሆን አለበት፤ የሌላ አካል ጣልቃ ገብነት ሊኖረው አይገባም።
ነፃነት የሰው ነው፤ የራሳችን ሃብት ነው። በሌሎች ጣልቃ ገብነት ሊገደብ ግን ይችላል። ስለዚህ ነፃነታትችን ከፈለግን መጠበቅ ይኖርብናል። ነፃነታችንን ለመጠበቅ ፈፃሚ ተቋም ያስፈልጋል። ፈፃሚ ተቋም ወይ ስርዓት የሚኖረው መንግስት ሲኖር ነው። መንግስት የሚኖረው ሀገር ሲኖር ነው። ሀገር የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው።
የምንፈልገው ነፃ ህዝብ ነው። ነፃ ህዝብ የሚኖረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖር ነው። ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚኖረው የዴሞክራሲ ግንዛቤ ያለው ህዝብ ሲኖር ነው። ግንዛቤ ያለው ህዝብ መብቱ ያውቃል፤ መንግስት አገልጋይ እንጂ ጌታ አለመሆኑ ይረዳል።
ባጠቃላይ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሲሆን ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይኖራል። እናም ነፃነቱን ያረጋግጣል። ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆነው መንግስትን መቆጣጠር ሲችል ነው። መንግስትን መቆጣጠር ስልጣን መስጠትንና መንጠቅን ይጨምራል።
ህዝብ መንግስትን መቆጣጠር የሚያስችል ዓቅም የሚፈጥረው አንድነት ሲኖረው ነው። ሰለማዊ ህዝብ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በአከባቢ ወዘተ ሳይከፋፈል በአንድነት ሲቆም መንግስትን ይቆጣጠራል። በአንድነት መቆም ማለት የግድ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ኣቋም መያዝ አይደለም። የራሱ የመሰለውን አመለካከት ይኖረዋል። የሚወሰነውም በአብዛሃ (አብላጫ) ድምፅ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ነፃ ነው።
ስለዚህ ነፃ ህዝብ እንዲኖረን ነፃ መንግስት ያስፈልጋል። ነፃ መንግስት እንዲኖረን የህዝቦች አንድነት ያስፈልገናል። የህዝቦች አንድነት እንዲኖር የሀገር አንድነት መኖር አለበት። ምክንያቱም የሀገር አንድነት ከሌለ የህዝብ አንድነት አይኖርም። የህዝብ አንድነት ከሌለ የህዝብ ስልጣን አይኖርም። የህዝብ ስልጣን ከሌለ ዴሞክራሲ አይኖርም። ዴሞክራሲ ከሌለ ነፃነት አይኖርም። ነፃነት ከሌለ እኩልነት አይኖርም። እኩልነት ከሌለ ፍትሕ አይኖርም። ፍትሕ ከሌለ የህዝቦች አንድነት አይኖርም። የህዝቦች አንድነት ከሌለ የእርስበርስ ችግር ይኖራል። የእርስበርስ ችግር ሀገርን ያፈርሳል። ሀገር ከፈረሰ ምንም አይኖርም።
ስለዚህ ነፃነት ከፈለግን ሀገር ያስፈልገናል። ሀገር ከፈለግን አንድ ህዝብ (የሚተባበር ህዝብ) ያስፈልገናል። አንድ ህዝብ ከፈለግን ነፃነት ያለው መሆን አለበት። ነፃነት የሌለው ህዝብ ወይ ሀገር አይቆምም። ስለዚህ ሀገር እንዲቆም ነፃነት ያስፈልጋል። ነፃነት እንዲከበር አንድ ሀገር፣ አንድ ህዝብ አስፈላጊ ነው።
ጨቋኝ ገዢዎች ግን የህዝቦችን አንድነት አይፈልጉም። ምክንያቱም ህዝብ አንድ ከሆነ፣ ከተባበረ ከስልጣን ያስወግዳቸዋል። ለዚህም ነው ብዙ ግዜ “የከፋፍለህ ግዛ” ስትራተጂ የሚጠቀሙ። ስለዚህ ነፃነት ፈላጊዎች እንዲያሸንፉና የህዝብና የሀገር አንድነት እንዲጠብቁ የህዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር አንስራ። መከፋፈል ለገዢዎች ይጠቅማል።
አዎ! አንድ ህዝብ አንድ ሀገር ለነፃነት።
It is so!!!

No comments:

Post a Comment