የተቃውሞ ጎራውም ቢሆን ከዚህ ከፋፋይ የጥፋት ድግስ ያለመትረፉን ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚመለከት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በሚሰጡት ትንታኔና በሚያቀርቡት መፍትሄ በአብዛኛው መሰረታዊ ጉዳዮች ሳይለያዩ በጋራ አገራዊ አጀንዳ ላይ ተባብረው በመስራት ህወኃት የሰበረውን የግንኙነት ድልድይ ለመገንባትና አገርና ህዝብን ለመታደግ በቃላቸው ለመገኘት ባለመቻል ደጋግመው መክሸፋቸው በግልጽ ይታያል፡፡
ይሁን እንጂ ከዓመት በላይ የዘለቀው የሃመር ወጣቶች የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ ዓመት ሊደፍን የተቃረበው ኦሮሚያ -አቀፍ ህዝባዊ እምብተኝነትና የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ፣ በኮንሶ የተነሳው የማንነት ጥያቄ፣ በአሁኑ ወቅት ከወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በጎንደር ተነስቶ በአማራ ክልል በፍጥነት እየተዛመተ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ በሁሉም ክልል የሚታየው የህወኃት አድሎኣዊና አምባገነናዊ አገዛዝ ‹በቃኝ› በማለት በተናጠልና በተበጣጠሰ መልክ ፣ ግን በቆራጥነት፣ ያለማቋረጥና ማፈግፈግ እየተቀጣጠለ ነው ፡፡
ይህ አገር-አቀፍ የእምቢተኝነት ህዝባዊ እንቅስቃሴ ፣ እንዲሁም ከያቅጣጫው ከህዝቡ የሚሰማው የትግል አጋርነት ጥሪና በአንድ የጋራ ጥያቄ ዙሪያ የመሰባሰብ መንፈስ፣ ህዝቡ ከፓርቲዎች ቀድሞ ሄዷል የሚያስብል ነው፡፡ ለተቃዋሚ ጎራውም ትግሉን የማስተባበርና በአንድ አገር-አድን አጀንዳ ስር ለማሰለፍ አብሮ የመስራትን ወቅታዊነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግባራዊ ምላሽ እንደሚጠይቅ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል ፡፡ በእጅጉ የሚያበረታታ ነው፡፡
በተቃራኒው ህወኃት/ኢህአዴግ በአምባገነናዊ ተግባሩ ገፍቶበት የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት በጠብመንጃ ኃይል ለማፈን፣በዚህ የከፋ ወቅት ዜጎችን መኖሪያ አፍርሶ በኅልውናቸውና ሰብአዊ ክብራቸው ላይ መቀለዱንና… የተያያዘውን የግፍ መንገድ አጠናክሮ ለመቀጠል እየተንገታገተ ይገኛል፡፡ ሌሎች የቀድሞ ሕወኃታዊያንን ጨምሮ አምባገነናዊ አገዛዙ በሞት አፋፍ ላይ መሆኑን ገልጸው ለህገመንግስታዊ የምርጫ ስርዓት ምስረታ መወትወት ጀምረዋል፤ ይህም የተጨባጭ ሁኔታና በህወኃት ውስጥ ያለውን መከፋፈል አመላካች ነው፡፡ በአጭሩ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በጤናማ አዕምሮ ለሚመዝን ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመንግስት ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ያለው አምባገነናዊ አገዛዝ በያዘው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ፣ ወታደራዊ ኃይልና የአፈና ስልት ሊቀጥል የማይችል፣ ያለው የጥቂቶች ዘረኛ ቡድን ዕድገቱን ጨርሶ በጣረ-ሞት ላይ እንደሚገኝና ለውጡ አይቀሬ መሆኑን መረዳት አይቸገርም ፡፡ በዚህ ረገድ ከህዝባችን ፊት ሁለት ግልጽ አማራጮች ቀርበዋል፡፡
የመጀመሪያው ሁላችንን አሸናፊና ተጠቃሚ ከሚያደርግ ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሄ የሚያደርስ ሲሆን ሁለተኛው ያለውን አስተዳደር በአፈናና በኃይል ወደከፋ አምባገነናዊ ወታደራዊ አገዛዝ የሚያሸጋግር ወይም ባይወደድም በጠመንጃ ያለውን አምባገነናዊ አገዛዝ የሚያስወግድ አሉታዊ የኃይል አማራጭ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን በህዝቡ መካከከል የተሰራጨውና ህዝቡን የከፋፈለውን ህወኃት ሰራሽ የልዩነት ግንብ ለማፈራረስ፣ መርዙን ለማርከስ አደጋ የተደቀነበትን የአገርና ህዝብ አንድነትና ኅብረት ያስተሳሰሩ ታሪካዊና ባህላዊ ጠቃሚ እሴቶች ማስቀጠል የግድ ይለናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉን አሳታፊ ውይይት በማድረግ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ዕርቅ ማውረድና በአካታችና አሳታፊ የሽግግር ወቅት የተሰበረውን የአንድነት ድልድይ ገንብቶ ዘላቂ ሰላምና ፍትሃዊ ልማት የምንገነባበት የሁላችን ለሁላችን በእኩል የሚያገለግል፣ በቀደመው መቃብር ከሚገነባ በኃይል ላይ የተመሰረተ የሥልጣን ሽግግር በተለየ ፣ ወደ አዲስቱን ኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት ሂደት የሚያደርሰን የሽግግር ወቅት /መንግስት መመስረት ብቸኛው ዘላቂ መፍትሄ ነው፡፡
የድርጅታችን ምርጫ የመጀመሪያው ሰላማዊው መንገድ / አማራጭ በመሆኑ ለመንግስትና ደጋፊዎቹ፣ በአገር ቤትና በውጪ አገር ለሚገኙ የተደራጁና ያልተደራጁ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚከተለውን ጥሪ ያስተላልፋል ፡፡ ገዢው ፓርቲና መንግስት፡- ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ውጤት የሆነውና በስፋት የተሰራጨው የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲያበቃ፣ በታሪክና መንግስት ምስረታ ሂደት የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ እንዲበጅላቸው…. በአገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር…. የሚያስችል አገራዊ የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ‹‹ ማን ከማን ተጣላና ነው፣ ይህ የተቃዋሚዎች አቋራጭ የሥልጣን ጥያቄ ነው….›› በማለት በእብሪት ሲታሾፉ መቆየታችሁ ይታወቃል፡፡
አሁን ላይ ግን ሌላው ቀርቶ በህወኃት/ኢህአዴግ ውስጥና መካከል የተፈጠረው ልዩነት በለመዳችሁበት መንገድ ሊትሸፍኑትና ሊታለባብሱት ከሚችሉት በላይ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በመሆኑም እየተጠየቀ የቆየው አገራዊ የሰላምና እርቅ ጉባኤ የናንተም ጥያቄ ከሆነበት ደረጃ መድረሱን ተቀብላችሁ ከእብሪታችሁ ተላቃችሁ ጥሪውን እንድትቀበሉ፤ የመካከለኛውና ዝቅተኛው አመራርና ካድሬ፣ እንዲሁም ደጋፊዎች ጥሪያችን ከፓርቲና ጊዚያዊ ጥቅም በላይ የአገርና ህዝብ ህልውናና ቀጣይ ግንኙነት የሚወስን ስለሆነ ራሳችሁን ከህዝብ ጎን አሰልፋችሁ ታሪካዊ ገድል እንድትፈጽሙ ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡- ከዚህ በፊት በአገርቤት የሚገኙ ብዙዎች በጋራ ሆነን – ‹‹ አንድም አገራዊ ፣ አካባቢያዊ/ክልላዊ ወይም የብሄረሰብ የፖለቲካ ድርጅት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ለዚህች አገር ውስብስብ ችግሮች በተናጠል ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም ››ከሚል ድምዳሜ በመድረስ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች በኅብረት መስራት አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን በተደጋጋሚ ሰንገልጽ ፣ እንዲሁም በአገር-ቤትና በውጪ አገር ስለብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ስንሰብክ መቆየታችን ይታወቃል፡፡
ለዚህም በጋራ ለመስራት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገን ከተጠናወተን ‹‹ መጀመር እንጂ ከዳር ማድረስ የማያስችል ደዌ›› ሊንፈወስ ባለመቻላችን በተደጋጋሚ ከሽፈናል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ከእስከዛሬው ተሞክሮ ቀስመን፣ ያለንበትን ወቅታዊ አደጋ ተረድተን፣ ባለፈው መቃብር ላይ አዲሱን ከመገንባት አስተሳሰብና ልምዳችን ተፋተን፣ ከተናጠል ሩጫና የጎንዮሽ ፍትጊያ ወጥተን፣ የትግል ስልትና ሌሎች ልዩነቶችን እንዲሁም የፓርቲ ፕሮግራምና የሥልጣን ጥያቄን ወደኋላ አቆይተን ፣ ከመርዶ ነጋሪነትና መግለጫ ማውጣት ተሻግረን፣ከቢሮ ወጥተን ህዝባችን ውስጥ በተግባር በመድረስ በ ‹‹አገራዊ የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ›› ጥያቄ ዙሪያ ተሰባስበን ህዝቡን በጋራ ለማስተባበርና ለማታገል አመራር በመስጠት በገዢው ፓርቲ ላይ የምናሳርፈውን ተጽዕኖ እንድናጠናክር፤ በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በተለይም በዚህች በተፈጥሮ የታደለች ግን ደሃ አገር፣ በህዝብ ሃብት ቀለም የቆጠርን ‹ምሁራንና ልህቃን› ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ባህላዊ መሪዎች . . . የህዝቡ የትግል ተነሳሽነትና ዝግጁነት እንዲሁም አገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታና የተጠየቅነውን የማስተባበር ኃላፊነትና ተግባር በማገናዘብ – የተደራጀን በየተደራጀንበት የሲቪልና ሙያ ማኅበራት ፣ ያልተደራጀንም በየተሰማራንበት የሙያና የሥራ ዘርፍ፣ አገራችን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት፣ ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ብቸኛው መፍትሄ የብሄራዊ መግባባትና እርቅ መንገድ መሆኑን ህዝቡን በማስተማር ፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች- ገዢውም ተቃዋሚውም ወደ አገራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ እንዲመጡ – አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ፣ አገር የምትጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል እንድትወስኑ፣ በተግባር እንድታሳዩ፤ አገራዊ ጥሪያችንን ስናስተላልፍ ይህ ጥሪ የሚጠይቀው ተግባር የነገ ሳይሆን የዛሬ መሆኑን በአጽንኦት እናሳስባለን ፡፡ ለዚህ አማራጭ ተፈጻሚነት ድርጅታችን የሚቆጥበው አንዳችም እንደሌለና የቱንም መስዋዕትነት ለመክፈል ስላለው ዝግጁነት የገባውን ቃልኪዳን ደግመን እናረጋግጣለን፡፡ በሁሉም ልጆቿ ፣ ለሁሉም ልጆቿ የምትመች አዲስቱ ኢትዮጵያ ትገነባለች//
የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት/ኦሕዲኅ/ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ሃምሌ 22/ 2008 ፤ አዲስ አበባ