Friday, May 13, 2016

“በሊቢያ ዳግም አንገታቸውን የተቀሉ ኢትዮጵያውያን አናውቅም ! ” ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ

በአለም ላይ ማንም የማይስተካከለው ጨካኙ ISIS በሊቢያ ዳግም ኢትዮጵያውያን ክርስትያኖች ለይቶ መቅላቱን በሚመለከት የተሰራጨው መረጃ መሰረት የሌለው መሆኑን ካደረግኩት ማጣራት ለመረዳት ችያለሁ ። ከትናንት ምሽት እስከ ዛሬ ማለዳ ትክክለኛ መረጃውን ለማግኘት ካደረግኳቸው ቀዳሚ ማጣራቶች መካከል ከወደ ሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማነጋገርና እዚህ በአረቡ ሀገር ለመረጃው ከቀረቡት መረጃ ማፈላለግ ነበር ።
ኢትዮጵያውያን በሊቢያ …
================
በዋና ከተማዋ በትሪፖሊ ያገኘኋቸው ወገኖቸን መረጃውን ሰምተው እነሱም ግራ መጋባታቸውን ገልጸው ፣ ወደ ኋላ አጣርተው ስለደረሱበት መረጃ በሰጡኝ መላሽ እንዲህ ብለዋል ” እርግጥ ነው ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለን ኢትዮጵያውያን ለተሻለ ኑሮና በፖለቲካው ግፊት ከሀገር እየተሰደድን ነው ፣ በስደቱ መከራ እየተንገላታን ያለበት ሁኔታ የከፋ ነው … ከዚህ ውጭ 16 ኢትዮጵያውያውን አንገታቸው ተቀላ ተብሎ በ Press Tv የቀረበው መረጃ ምንም ማረጋገጫ የለውም ፣ ዳግም አንገቱን የተቀላ ኢትዮጵያዊ አናውቅም !” በማለት በዝርዝር ስለ ስደቱ ሰቆቃ ሲናገሩት አንገት ከመቀላት በላይ የሚያመውን የስደት ሰቆቃ በተጎዳ ስሜት አውግተውኛል ! እኒሁ ኢትዮጵያውያንን ትናንት ምሽት አግኝቸ አንገታቸው ተቀላ ስለተባሉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንዲያጣሩልኝ በጠየቅኳቸው መሰረት የደረሱበትን ሁኔታ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አድርሰውኛል። በተለይም በሁለተኛዋ የሊቢያ መዲና በጠረፍ ከተማዋ በቢንጋዚና በተለያዩ ከተማዎች ያሉ ኢትዮጵያውንን ስልክ በመደወልና በማጣራት ባደረሱኝ መረጃ መሰረት ” በእስከ አሁኗ ሰዓት ባለን መረጃ በሊቢያ በ ISIS አንገታቸው የተቀላ ኢትዮጵያውያን የሉም !” በማለት አስረግጠው ነግረውኛል !
የድረ ገጽ ባለሙያዎችና የአረብ መገናኛ ብዙሃን …
=================================
ሌላው መረጃውን ያጣራሁት በአሸባሪው ISIS ድረ ገጽ የተቀሉትን ኢትዮጵያውያን በሚመለከት መረጃ ተላልፎ እንደሁ ማጣራት ነበር። በዚህ ዙሪያ ጥልቅ ፍተሻ ያደረጉ የዘርፉ ባለሙያዎች በየትኛውም የአሸባሪው ISIS ቡድን ድረ ገጾችና የመረጃ ማቀበያ መንገዶች ” በሊቢያ 16 ኢትዮጵያውያን አንገት ቀልቻለሁ !” የሚል መረጃ አለማሰራጨቱን ከባለሙያዎች አረጋግጫለሁ ። ከዚህ ጋር በተያያዝ ዜናውን ለማጣራት እስከ እኩለ ሌሊት ጥረት ተደርጎ ማረጋገጥ አለመቻሉን አንድ ከፍተኛ የአረብ ኒውስ ጋዜጣ አዘጋጅ ወዳጀ ገልጸውልኛል ። የተሰጨውን መረጃ ማረጋገጥ ባለመቻሉም አረብ ኒውስ በዛሬው የማለዳ እትሙ መጨበጫ የሌለውን ዜና ይዞ ለመውጣት አለመፍቀዱን አስረግጠው ነግረውኛል !
ይህም ሰናይ መረጃ ነው !
የእኛ ስጋት ፣ ጭንቀትና የመንግስት የሀዘን መግለጫ …
====================================
ትናንት ከቀትር በኋላ የመረጃ ግብአት ” ISIS በሊቢያ 16 ኢትዮጵያውያን አረደ !” የሚለው ስጋትና ጭንቀት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበር ፣ እናም ” ያልተረጋገጠ ዜና ነው!” የሚል አንድምታ ያለው መረጃ እኔም ሆንኩ በርካቶች ያገባናል ያልን ወገኖች ሰፋ ያሉ መረጃዎችን ከነማስረጃቸው አቅርበን ነበር ። በተለይም የኢራኑ Press TV እና የብሪታንያው Express የዜና አውታሮች ያሰራጩት መረጃ ብዙዎችን ማጋባቱን አውስተን ከዚህ በኢትዮጵያውያን ላይ ከዚህ በፊት በሊቢያ የተፈጸመውን ግድያ የሚያሳይ ፎቶ ይዘው ከወጡት የዜና አውታሮች ባለፈ መረጃውን እስካሁን ያረጋገጠ አለመኖሩን ጠቁመንም እንደነበር አይዘነጋም ። በግል እዚህ ሳውዲ ሳውዲ ከሚገኙ የአል አረቢያና የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ዘጋቢዎችና ከሳውዲ አረብ ኒውስና ሳውዲ ጋዜጥ ታዋቂ ጋዜጣ አዘጋጆች ለማጣራት ሙከራ አድርጌ መረጃው ያልተረጋገጠ ተባራሪ ሊሆን እንደሚችል መጠቆማቸው አይዘነጋም !
በኢራኑ የ Press Tv የተሰራጨውን መሰረት የሌለው ዜና በመመርኮዝ በሊቢያ ውስጥ ዳግም በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጸመ የተባለውን ግድያ በሚመለከት የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የሀዘን መግለጫ ለኢትዮጵያውያንና ህዝብና ለሟች ቤተሰቦች ማስተላለፋቸው ይጠቀሳል ፣ ሳሩ ግን የሀዘን መግለጫው ከተጨበጠ መረጃ ጋር የተገናዘበ አይደለም በሚል ብዙዎችን ግራ ማጋባቱ ይጠቀሳል !
የእስካሁኑ የተጨበጠ መረጃ ይህ ነው …ለሁሉም በሊቢያው ስደት በጭንቅ ላይ ያሉት ወገኖች መከራና ጻዕር ከባድ ነው …” አንድ ፊቱን አንገቴ ተቀልቶ ሰማዕት በሆንኩ ይሻል ነበር … ” ያለኝን ወንድም መከራ የመስማት ህመምን ያማል ፣ ያማል ብሎ መግለጽ አይቻለኝም ! አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ አውጭ ሆኛለሁ … frown emoticonለሁሉም ከአገር አልባ ስሜት ያድነን ፣ ለሁሉም በጸሎት መትጋት ይመከራል …
አቤቱ ! የከፋውን መርዶ አታሰማን … አቤቱ ! በምህረትህ ጎብኘን … አቤቱ ! የተባረከ የተቀደሰ ቀን ያድርግልን … !
ነቢዩ ሲራክ
ግንቦት 5 ቀን 2008 ዓም

No comments:

Post a Comment