Monday, May 30, 2016

ስኬት እና ተምሳሌት – “በዛሬው ዕለት በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር አኩሪ ድል በደማቅ ተጽፏል!!!” ይድነቃቸው ከበደ (እርገጤ)


ስኬት እና ተምሳሌት  ይድነቃቸው ከበደ (እርገጤ)
—-
“በዛሬው ዕለት በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር አኩሪ ድል በደማቅ ተጽፏል!!!”
——
Yidnekachew Kebede's Profile Photoብልህነት የተሞላበት ስትራቴጂ ከተነደፈ፣ አምባገነናዊ ሥርትዓት እና የሥራዓቱ አራማጆችን በአነስተኛ መሰዋዕትነት ትልቅ ድል ማስመዝገብ ይቻላል።ለዚህም በዛሬው ዕለት በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር አኩሪ ድል በደማቅ ተጽፏል። አምስት ወር ሙሉ ትምህራትቻውን ባአግባቡ ሳይከታተሉ፣ በአገዛዙ ጠባቂዎች ሲገደሉና ሲንገላቱ የነበረ ተማሪዎች፤ በግዳጅ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የብሔራዊ ፈተና እንዲፈተኑ የታቀደው እቅድ፣ በሰለጠነ የሰላማዊ ትግል ዜዴ ማስቀረት ተችሏል ።ይህን መሰል አኩሪ ድል ለፈጸሞት ምስጋና ሲያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም።
“የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን”የሚል ስያሜ የተሰጠው የመሬት ነጠቃ እና ወረራ ፤የህዝብ ጥቅም እና ፍላጎትን ያልጠበቀ መሆኑን ተከትሎ ፣በተደረገ ህዝባዊ ጥያቄ እና በገዢው መንግሥት በኩል በተሰጠው ምላሽ ፣ መተኪያ የሌለው የሰው ልጅ ሕይወት እንዲጠፋ ፣የንብረት ውድመትና ኪሳራ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።ለህዝብ አቤቱታ እና ተቃውሞ ፣ተገቢውን ክብርና ምላሽ የመስጠት የአቅም ውስንነት ብቻ ሳይሆን አፈጣጠሩ ጭምር የማይፈቅድለት የህውሓት/የኢህአዴግ አንባገነን መንግሥት ዓይኑን በጨው አጥቦ ፣ከሞትና ከእስራት የተረፉ ታዳጊ ወጣቶችን፣ በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በብሔራዊ ፈታና ለመቅጣት ሲዳክር ፣ የአገዛዙ ስርዓት ለብቀላ አንድም ሣይቀር ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ የሚያመላክት ነው።
የከፍተኛ ትምህርት የብሔራዊ ፈተና፣አንድ ተማሪ በቀጣይ የትምህርት ሂደቱ እና በወደፊት የስራ መስክ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ የሚወስንበት የዓመታት የልፋት ውጤት ነው። የፈተና ውጤቱ የሚያስከትለውን አሉታዊ እና አወንታዊ ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም ። በዚህ ላይ አሻሚነት እንደሌለው የጋራ እምነት ካለ፤በአንድ ተማሪ ላይ የዚህን ያህል ተፅእኖ ካለው፤ በአገራችን በተለያየ ክፍለ አገር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ላይ ድርጊት ቢፈጸም ፣የጉዳቱ መጠን ምን ያህል አስደንቃጭ ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡
አሁንም እየተጠየቀ ያለው ፣ተማሪዎች ለአምስት ወራት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ተደርጓል ፣ለዚህም የመንግስት እጅ አለበት።በመሆኑም ፈተናው አገር አቀፍ እንደመሆኑ መጠን ፣አመቱን ሙሉ ሲማር እና ለአምስት ወር የተማረ ተማሪ እኩል ፈተና ላይ መቀመጥ የለበትም ።ስለዚህም በቂ የፈተና ጊዜ እና የማካካሻ ት/ት ተሰጥቶ ፤ብሔራዊ ፈተና መካሄድ እንዳለበት ነው።ይህ ጥያቄ የማንም መብት የማይጋፋ፣ከምንም በላይ የፈተናው ሚዛናዊነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው፡፡
የህውሓት/የኢህአዴግ አንባገነን መንግሥት “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን” የሚል ስያሜ ሰጥቶ የነበረው እቅድ ተግባራዊነቱ እንዲቆም፣ በህውሓት የሞግዚት አስተዳደር የሚመራው ኦህዴድ መዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑ የሚታወቅ ነው። ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የህዝብ ተቃውሞና አለም አቀፍ ማህበረሰብና የውጪ መንግስታት ከፍተኛ ጫና ተከትሎ ነው።በተለይ በአገራችን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች የህይወት መሰዋዕትነት ሁሉ ከፍለውበታል።
አቶ ኃ/ማርያም ዳሳላኝ በተለያየ ወቅት በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ፣እሳቸውና እና መንግሥታቸው ፤የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን አስመልክቶ በተከሰተው ነገር ይቅርታ ከመጠየቃቸው በላይ ፣ለይስሙላ የተወሰኑ ባለስልጣናት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እና እንዲጠየቁ አስችለናል ሲሉ ተደምጠዋል።ይህን ማድረግ ከተቻለ መንግስት ነኝ ባዮም ኃላፊነት ወስጃለሁ ካለ ፣ለተማሪዎች ተጨማሪ የፈተና ጊዜ እና የማካካሻ ትምህርት ለምን አይስጥም ?! ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው።ተገቢውን መልስ የሚሰጥ የመንግስትነት ቅርጽ ያለው ስርዓት ስለመኖሩ ዋና መሰረታዊ ጥያቄ ነው።የሆነዉ ይሁንና ተብሎ የማይታለፈው ፣ዛሬ የሆነው ነገር ስኬቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተምሳሌታዊነቱ ለአማራጭ የሰላማዊ ትግል ዘዴ ትልቅ ቦታ ይኖሯዋል።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም
ይድነቃቸው ከበደ (እርገጤ)

No comments:

Post a Comment