Monday, May 16, 2016

1.3 ሚሊየን ብር የነፈግናቸው ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

(ዘ-ሐበሻ) በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 2005 ዓ.ም አካባቢ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታላቁ ባለውለታ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ለሕክምና 1.3 ሚሊዮን ብር አስፈለጋቸው:: ወልደመስቀል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ የጣሉት አሻራ የማይሻር ነው:: በርካታ አትሌቶችን ከጃንሜዳ ሃገር አቋራጭ እስከ ኦሎምፒክ ድረስ አፍርተዋል:: ውለታቸውን ግን የቆጠርልናቸው አይመስለኝም:: እንዴት? እዘረዝረዋለሁ:-
በ1990 ዓ.ም ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ እግራቸው ላይ የደረሰባቸው ጉዳት ከ እድሜ መግፋት ጋርም ተያይዞ በ2005 አካባቢ አላስቆም አላስቀምጥ የሚል ህመም አስከተለባቸው:: ይህ የ እግር ህመም በሃገር ውስጥ ብቻ ታክሞ ለመዳን የማይቻል ባይሆንም ለመታከም የሚያስፈልገው ወጪ 1.3 ሆነ:: ዶክተሩ ለሃገራችን በአትሌቲክሱ ዘርፍ የሰሩትን ታላቅ ገድል በማውሳት አንዳንድ ግለሰቦች ለህክምና የሚሆነውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ተንቀሳቀሱ:: ሰሚ ግን አልነበረም:: ጥቂቶች ጥቂት ገንዘብ ቢያሰባስቡም 1.3 ሚሊዮን ብር ሊደርስ አልቻለም:: ዶክተሩ በከዘራ እስኪሄዱ በመኪና አደጋው በደረሰባቸው አደጋ ለ15 ዓመታት ቢሰቃዩም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባቅሙ ከ200 ሺህ ብር የዘለለ እርዳታ ማድረግ አልቻለም ነበር:: ፌዴሬሽኑ ይህን ልገሳ ያደረገውም እኚህ ታላቅ ባለውለታ ብዙ ልመና ካደረጉ በኋላ እንጂ እንደው አዝኖም አልነበረም::
የሚገርመው ለዓለም አቀፍ ዝና ያበቋቸው ታላላቅ አትሌቶች እንኳ በታመሙ ጊዜ አልደረሱላቸውም:: 1.3 ሚሊዮን ብር ያላዋጣንላቸውና ያላሳከምናቸው ዶክተር ወልደመስቀል የመኪና አደጋው ከደረሰባቸው ከ13 ዓመታት በኋላ ዛሬ ሕይወታቸው በሌላ ህመም አልፏል::
ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን! ለሃገራችን ውለታ የዋሉ ሰዎችን በቁም የምንረዳና የምናስባቸው ያድርገን::

No comments:

Post a Comment