- ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኝቷል
- ጊዜው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች ለዜጎች እየተሸጡ ነው
- ሊብሬ ያላቸው ተሽከርካሪዎች በአካል የት እንደገቡ አይታወቅም
- የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ዩኒቨርሲቲዎች ተወቀሱ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2007 የበጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲት ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት፣ አብዛኞቹ በጀት ተቀባይ የመንግሥት ተቋማት አስደንጋጭ የተባለ የሕግ ጥሰት የተገኘባቸው መሆኑን አስታወቀ፡፡ በዚህ ሪፖርት መነሻም ፓርላማው በአስፈጻሚ አካላት ላይ ቁጣውን ገልጿል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በምክር ቤቱ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ብዛት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ በየዓመቱ የሚሰጣቸውን አስተያየት ተግባራዊ በማድረግ ከማሻሻል ይልቅ፣ ወደባሰ ጥፋት እየገቡ መሆናቸውንና ለዚህም ዋና ምክንያቱ ተጠያቂ ያለመደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር በሁሉም መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡ ዋና ዋና የተባሉና ልዩ ትኩረት የሚሹ የኦዲት ግኝቶችን ዋና ኦዲተር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አጠቃላይ ሪፖርታቸው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት፣ በክዋኔ ኦዲትና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ድጋፍ (PBS) ላይ ባተኮሩ ሦስት ክፍሎች የቀረበ ነበር፡፡
ምንም እንኳ ተጠያቂ መደረግ አለባቸው የተባሉ የተለያዩ ተቋማት በዝርዝር ሪፖርቱ የተካተቱ ቢሆንም፣ በኦዲት ግኝቱ ስማቸው የተነሳው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና አሥር ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡
በሕግ በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱን ለማጣራት በተደረገው የኦዲት ሥራ፣ በ94 መሥሪያ ቤቶችና በ11 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 2.079 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ መወራረድ አለመቻሉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ከዚህ ውዝፍ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ የታዩ ዋና ዋና የአሠራር ችግሮች ያሉትን አቶ ገመቹ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ በአራት መሥሪያ ቤቶች የተሰብሳቢ ሒሳብ ተቀፅላ ሌጀር ያልተዘጋጀላቸው ሒሳብ ከ174 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ባሉ ሦስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በሌሎች ሁለት መሥሪያ ቤቶች ከ15.9 ሚሊዮን ብር በላይ በወጪ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረግ ሲገባው፣ ያላግባብ በተሰብሳቢ ሒሳብ ተይዞ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የመንግሥት ገቢ በወጡት ሕጎች መሠረት በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት፣ በ34 መሥሪያ ቤቶችና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ባሉ አሥራ አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ 118.7 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በአንድ መሥሪያ ቤት ተማሪዎች በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ያልተሰበሰበ 211,930 ዶላር ግብር፣ ቀረጥና ታክስ አለመሰብሰቡንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ከፍተኛ የሚባሉ ገንዘቦች አለመሰብሰባቸውን የዋና ኦዲተር ሪፖርት በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ለአብነትም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከ689 ሚሊዮን ብር በላይ በበጀት ዓመቱ አለመሰብሰቡን አሳይቷል፡፡
የገቢ ሒሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተተ ገቢን አስመልክቶ የኦዲት ግኝቱ እንደሚያስረዳው፣ ገቢ እንዲሰበሰቡ በተፈቀደላቸው ተቋማት በትክክል ተመዝግቦ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መቅረቡን ለማረጋገጥ በተደረገ የኦዲት ሥራ በስድስት መሥሪያ ቤቶች ከ76.7 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በሌሎች አምስት መሥሪያ ቤቶች በገንዘብ መጠን ያልተገለጸ የውስጥ ገቢ ባቀረቡት ዓመታዊ የገቢ ሒሳብ ሪፖርት ሳይካተት መገኘቱን አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡
የገቢ ሒሳብ በሪፖርት ከማያካትቱት መሥሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ፣ ይህ አሠራር በገቢ ሒሳብ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማላላት ለምዝበራ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ፣ መሥሪያ ቤቶቹ በራሳቸው የሚያዘጋጁዋቸው የሒሳብ መግለጫዎች የመንግሥት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሒሳብ ትክክለኛ ገጽታ እንዳያሳዩ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በወጪ ሒሳብ አያያዝ፣ በግንባታ ኮንትራት ውል፣ በግዢና ንብረት አወጋገድና አስተዳደር ከፍተኛ የሕግ ጥሰትና አግባብነት የጎደለው አሠራር በአብዛኞቹ መሥሪያ ቤት ቢታዩም፣ ከፍተኛ ችግር የታየባቸውም ሆነ በተከታታይ ዓመታት መሻሻል ያላሳዩት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡
የወጪ ሒሳብን በተመለከተ በ24 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ ከ221.8 ሚሊዮን ብር በላይ በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከመዘገቡት መሥሪያ ቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር 95,526,864.83 ብር፣ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 26,417,436.86 ብር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 10,000,000 ብር፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 8,601,445.18 ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 5,100,434.00 ብር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ 4,646,850.00 ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
እንዲሁም ኦዲት በተደረጉ 56 መሥሪያ ቤቶችና አራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያላግባብ 61,397,293.70 ብር ተከፍሎ መገኘቱን የዋናው ኦዲተሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ማንኛውም ግንባታ ሲከናወን ሥራው በትክክል ስለመሠራቱ ብቃቱ ተረጋጋጦ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ፈቃድ በተሰጠው አማካሪ ድርጅት ሲረጋገጥ ብቻ፣ ክፍያዎች ሊፈጽሙ እንደሚገባ የሕግ አግባቡን ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በአራት መሥሪያ ቤቶች የፕሮጀክቶችን ሥራ እንዲከታተሉ የተቋቋሙ፣ ነገር ግን የማማከር ፈቃድ በሌላቸው የግንባታ ጽሕፈት ቤቶች በኮንትራክተሮች የተሠራው ሥራ ትክክለኛነት እየተረጋገጠ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ 717,312,735.03 ብር፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ 74,495,345.59 ብር፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 35,419,596.22 ብር እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ 7,428,032.90 ብር በድምሩ 834,655,709.74 ብር ገንዘብ ወጪ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የእነዚህን ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ በተመለከተ ተጠያቂ የማድረግ ዕርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳብ ያሉትንም አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከዓመት ዓመት የሚፈጸሙት ስህተት እየተባባሰ በመሆኑ በትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ ግዢ፣ ግንባታንና መሰል ሥራዎችን በተመለከተ ሌላ ተቋም ማቋቋም እንደሚገባ፣ ወይም በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ለዚህ ዓላማ አንድ ዘርፍ እንዲቋቋም በማለት ለምክር ቤቱ አሳስበዋል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ብዙ የኦዲት ችግር ከተገኘባቸው መሥሪያ ቤቶች አንዱ በመሆኑ፣ ይህንን ሥራ በአግባቡ ስለመፈጸሙ በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡
በሌላ በኩል የምክር ቤቱን አባላት ያስደነገጠው ሌላው ጉዳይ በግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች ለአርሶ አደሮች የሚሸጡ መሆናቸው በዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ሲቀርብ ነው፡፡ የተለያዩ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች በዝርዝር የተጠቀሱ ሲሆን፣ በኦዲት ሥራው ወቅት ኬሚካሎቹ ከሁለት ወራት እስከ ሁለት ዓመታት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ቢያልፍም በቀጥታ ለአርሶ አደሮች ሲሸጡ መታየታቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በተጨማሪም በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የተገዙ ግምታቸው 570 ሚሊዮን ብር የሚሆኑ መድኃኒቶች፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመጋዘን ተቀምጠው የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ መገኘቱንም አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ሕፃናትን በጉዲፈቻ መልክ ወደ ውጭ መላክን በተመለከተ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ግኝቱንም አመላክቷል፡፡ በተለይ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ከ2004 እስከ 2007 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ በናሙና ተመርጠው በታዩት የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች፣ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሕፃናትን በላኩባቸው አገሮች ጉብኝት ማድረጋቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን ኃላፊዎቹ በሄዱባቸው አገሮች ያገኙዋቸው በጉዲፈቻ የተሰጡ ሕፃናት ደኅንነታቸው መጠበቁንና የጉዲፈቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን የጉብኝት ዝርዝር ሪፖርት ቢያቀርቡም፣ እንዲሁም ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድና ግብረ መልስ ሊሰጡ የሚገባ ቢሆንም ይህ የማይፈጸም መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የገቢና ወጪ ዕቃዎችን በተመለከተ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ወይም እንዳይወጡ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የላብራቶሪ ውጤት፣ ወይም ዓለም አቀፍ የሦስተኛ ወገን ሠርተፊኬት አምጥተው ትክክለኛነቱ ተረጋግጦ ደረጃቸውን የሚያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጦ፣ ንግድ ሚኒስቴር ከሕግ አግባብ ውጪ በተቃራኒው ደብዳቤ በመጻፍ እንዲለቀቁ ማድረጉን የኦዲተሩ ሪፖርት አጋልጧል፡፡ እንዲሁም በሦስተኛ ወገን ሳይረጋገጡና የላቦራቶሪ ውጤት ሳይገለጽ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በንብረት አስተዳደርም በርካታ የኦዲት ግኝቶች ለምክር ቤቱ የቀረቡ ሲሆን፣ የፓርላማ አባላቱን በቁጭት ፈገግ ያሰኘው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በስሙ ከተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ አሥሩ ሊብሬ ቢኖራቸውም፣ ተሽከርካሪዎቹ የት እንደደረሱ ምንም የማይታወቅ መሆኑን አቶ ገመቹ ሲገልጹ ነው፡፡
ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በኋላም የት እንዳሉ የማይታወቁትን አሥሩን የኢንስቲትዩቱ ተሽከርካሪዎች አስመልክተው አስተያየት የሰጡት የምክር ቤቱ አባል አቶ ዱቤ ጂሎ፣ ‹‹ባለፉት ቀናት ከ88 በላይ የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ጠፉ ተባልን፡፡ ዛሬ ደግሞ አሥር ተሽከርካሪዎች ከአንድ ተቋም ከጠፉ ነገ የተገነባ መንገድ ጠፋ የማንባልበት ምክንያት ላይኖር ነው?›› በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ አስተያየትና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላት ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹን ላቀረቡት ሪፖርት ውዳሴና አድናቆት ሲያቀርቡላቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ አስፈጻሚውን አካል ሲተቹ ውለዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ የምክር ቤት አባል በሪፖርቱ ማዘናቸውን ገልጸው እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በሕግ ሊጠየቅ ይገባዋል ካሉ በኋላ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ አንላቀቅም፡፡ ከማንኛውም አካል ጋር እንጠያየቃለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እኚሁ አባል፣ ‹‹ለብዙ ዓመታት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከተዘፈቀበት መውጣት አለመቻሉን ስመለከት ለእኔ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ እስከ መክሰስ የሚያደርስ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችንም በተለመከተ ሕግ፣ አካውንቲንግ ወይም ማንኛውንም የትምህርት ዓይነት የሚያስተምር ተቋም እንዴት የራሱን ስህተት ሊያርም አይችልም በማለት ጠይቀዋል፡፡
አቶ መሐሪ ዘለቀ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች የሚሸጥ ተቋምን በአስተያየት ብቻ ማለፍ የለብንም፡፡ በሕግ ጭምር የግድ መጠየቅ አለበት፡፡ በሰው ሕይወት የራሱን ትርፍ ለማጋበስ የሚሞክር ተቋም ዝም ሊባል አይገባውም፤›› ብለዋል፡፡
በተደጋጋሚ ዓመታት ተመሳሳይ የኦዲት ግኝት ቀርቦባቸው መሻሻል በማያሳዩ ላይ በምክር ቤቱ በኩልም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት፣ በርከት ያሉ የምክር ቤቱ አባላት ተመሳሳይ አቋማቸውን ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ የመንግሥት ተቋማቱ በተደጋጋሚ የሕግ ጥሰት የሚፈጽሙት ተጠያቂ ባለመሆናቸው ምክንያት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በምክር ቤቱ አሠራር መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ ዋናው ኦዲተሩ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፣ የኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ሪፖርቱን እንዲከታተሉ በአፈ ጉባዔው ጥሪ ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን ከሰዓት በኋላ በነበረው የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ አብዛኛዎቹ የተቋማቱ ኃላፊዎች ባለመገኘታቸው በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡
Reproter Amharic
No comments:
Post a Comment