አዲሱ ትውልድና የቀድሞው ትውልድ መንገዳቸው
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 ዓም ጥቂት ዘመናት ቀደም ብለው የተወለዱትንና በአሁኑ ዘመን እስከ 30ዎቹ እድሜዎች ያሉትን ትውልዶች ሺአውያን (Millennials) ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ በአሜሪካ ሻውያን (ሺአውያን) እጅግ የተጠኑና ብዙ የተወራላቸው ትውልዶች መሆናቸው ይነገራል፡፡
አንዳንዶችም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ተወልደው፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ አድገው፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ለወግ ለማዕረግ የሚደርሱ ትውልድ ይሏቸዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያና ትሥሥር መንደሮችን ሁሉ ባዳረሰበት፣ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ግለሰባዊ ተደራሽነትን በያዙበት፣ ወላጆች ለትምህርት ይበልጥ ትኩረት በሰጡበት ዘመን የተፈጠሩ ትውልዶች በመሆናቸው እነዚህ ነገሮች በአስተሳሰባቸው፣ አነዋወር ዘያቸውና ፍልስፍናዎቻቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድረውባቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የእንስሳት፣ የተመሳሳይ ጾታ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ጉዳዮች በሚቀነቀኑበት ዘመን የሚገኙ ናቸውና የእነዚህ ነጸብራቅ ይታይባቸዋል፡፡ ዓለም ተያያዥና በቀላሉ ተደራሽ በሆነችበት የሉላዊነት ወቅትም ስለሚገኙ ክፉውንም ሆነ ደጉን የመካፈል ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ልጅን ተገንዝቦና አስገንዝቦ እንጂ ጠብቆ ማዳን የማይቻልበት ዘመን ነው፡፡
በሀገራችን ጥናት ባይደረግም በምዕራቡ ዓለም ግን ሻውያን አጥለቅላቂው ትውልድ ተብሎላቸዋል፡፡ በአሜሪካና በእንግሊዝ የተደረጉ ጥናቶች ሻውያን ከቀደምት ትውልዶች ይልቅ ብዛትና ስብጥር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የ2012 (እኤአ) ጥናት፤ 80 ሚሊዮን ሻውያን በአሜሪካ፣ 14.6 ሻውያን ደግሞ በእንግሊዝ መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ በ2015 ይሄ ትውልድ ‹ፍንዳታ› (baby boomers) የተባለውን ትውልድ ተክቶ በአሜሪካ ዋናው የሥራ ኃይል እንደሚሆን በአሜሪካ ቆጠራ ቢሮ (U.S. Census Bureau) ጥናት ተመልክቶ ነበር፡፡ በ2048 እኤአ ደግሞ ከመራጩ ሕዝብ መካከል 39 በመቶውን እንደሚይዙ ተተንብዮአል፡፡ እኤአ በ2008 ዓም በነበረው የባራክ ኦባማ ምርጫ ወቅት ሻውያን ወሳኝ ድርሻ እንደነበራቸው ታምኗል፡፡
ሻውያን ካለፉት ትውልዶች ሁሉ በተሻለ የትምህርት ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ምንም እንኳን የትምህርት ጥራት ጉዳይ አነጋጋሪ እየሆነ ቢመጣም በሻውያን ትውልድ ውስጥ ብዙ ልጆችና ወጣቶች በትምህርት ላይ ናቸው፡፡ ዲፕሎማ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ በመያዝ ሻውያን ካለፉት ትውልዶች የበዛ ቁጥር አላቸው፡፡ የትምህርት ተቋማት በየአካባቢያቸው እየተከፈቱ ነው፡፡ የግል፣ የመንግሥትና የሌሎች ድርጅቶች የትምህርት ተቋማት ካለፉት ትውልዶች በተሻለ ቁጥር ተመቻችተውላቸዋል፡፡ መጻሕፍትን፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችንና የመርጃ መሣሪያዎችን የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡ አንድ የሂሳብ መጽሐፍ ለዐሥር፣ አንድ የአማርኛ መጽሐፍ ለአራት ከሚለው ተሻግረዋል፡፡ ወላጆቻቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ካለፉት ትውልድ ወላጆች በተሻለ ዐቅም፣ ንቃትና ፍላጎት ላይ ይገኛሉ፡፡
በሀገራችን ከተማሩ ወላጆች በመወለድና በማደግ ረገድ ሻውያን ካለፉት ትውልዶች የተሻለ ዕድል ላይ የሚገኙ ይመስለኛል፡፡ ሳይማር ካስተማረ ወላጅ ተምሮ ወደሚያስተምር ወላጅ ሽግግር እየተደረገ ነው፡፡ ‹አልተማሩም› የሚባሉት ወላጆች እንኳን ቢሆኑ ስለ ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ ‹ተማሩ› ከሚባሉት ጋር የሚመጣጠን እየሆነ ነው፡፡ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርሱና ከትምህርት ቤት የሚያወጡ ወላጆች ቁጥር ካለፉት ዘመናት ይልቅ እየጨመረ መምጣቱን ለረዥም ዓመታት በትምህርት ቤት ያሳለፉ መምህራንን በጠየቅኩ ጊዜ ገልጠውልኛል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ዘመናት ወላጆችን ለማግኘት የግድ ‹ወላጅ አምጡ› ተብሎ መጠራት ያስፈልግ ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ለማድረስም ሆነ የልጆቻቸውን ጉዳይ ለመከታተል ትምህርት ቤት ራሳቸው ይመጣሉ፡፡
ምንም እንኳን በሀገራችን ያለው መረጃ ምን እንደሚመስል ለማግኘት ቢያዳግተኝም በአዲስ አበባ 10 (አምስት የግልና አምስት የመንግሥት) ትምህርት ቤቶች ከሚያስተምሩ መምህራን ጋር ባደረግሁት ውይይት እንደተረዳሁት ግን በየትምህርት ቤቶቹ የሴት ተማሪዎች ቁጥር ካለፉት ዘመናት በበለጠ ጨምሯል፡፡ በአንዳንድ ክፍሎች እንዲያውም የሴት ተማሪዎች ቁጥር ከወንዶቹ በልጦ ይገኛል፡፡ በምዕራቡ ዓለም በ2014 ዓም በአሜሪካ ይገኙ ከነበሩ የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል 57 በመቶዎቹ ሴቶች ነበሩ፡፡ በ1970ዎቹ ሴቶች ከሕክምና ተማሪዎች መካከል 10 በመቶ፣ ከሕግ ተማሪዎች መካከል ደግሞ 4 በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከሕግና ከሕክምና ተማሪዎች መካከል ወደ 50 በመቶውን ሲይዙ ከአሜሪካ የባለሞያዎች (professionals) ቁጥር ውስጥ 55 በመቶውን እየሸፈኑ ነው፡፡
ሻውያን ካለፉት ትውልዶች በበለጠ ቴክኖሎጂ ቀመስ ናቸው፡፡ በኮምፒውተር፣ በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በዲጂታል ካሜራ፣ በዲጂታል ቴሌቭዥንና በሳተላይት ዲሾች ዘመን ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ ወላጆቻቸው የማያውቋቸውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች፣ አፕሊኬሽኖች፣ ግንኙነቶችና አሠራሮች ሻውያን ያውቋቸዋል፡፡ ወላጆቻቸው ከመሐል እድሜ ላይ ያገኙትን፣ አንዳንዶቹም ተጠቅመውበት የማያውቁትን ኮምፒውተር ሻውያን በትምህርት ቤቶቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የመማርና የመጠቀም ዕድል አላቸው፡፡ በ2014 በተደረገ ጥናት 80 በመቶ የአሜሪካ ሻውያን (ከ18 እስከ 30 ዓመት) ስማርት ስልክ ሲኖራቸው 45 በመቶዎቹ ደግሞ ታብሌቶች አሏቸው፡፡ በብዙ ሀገሮች የሚገኙ ወላጆች በሻውያን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግራ እንደሚጋቡ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ መከልከል ወይስ መስጠት? ‹ሻውያን ለቴክኖሎጂ ቅርብ፣ ነገሩን ለመረዳት ፈጣንና በተለያየ መንገድ ለቴክኖሎጂው ተጋላጭ በመሆናቸው መከልከሉ የበለጠ ጉጉት ይጨምርባቸዋል፤ በሌሎች ጓደኞቻቸው የተበለጡ ይመስላቸዋል፤ ከትውልዳቸው ጉዞ ወደ ኋላ ያስቀራቸዋል ስለዚህ መስጠቱ ይሻላል› ብለው የሚያስቡ ወላጆች እንዳሉ ሁሉ ‹ቴክኖሎጂው የሰው ለሰው ግንኙነታቸውን ያበላሸዋል፣ ለባህላቸውና ለእምነታቸው ትኩረት እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል፤ ቁጥጥር ሳይደረግባቸው ለሚለቀቁ ነገሮች ያጋልጣቸዋል፤ ለጨዋታና ለቀልድ በማዋል አእምሯቸውንና ጊዜያቸው ይወስድባቸዋል፤ አካላዊ እንቅስቃሴን በማቀብ ሰነፎችና ደካሞች ያደርጋቸዋል› ብለው የሚፈሩም አሉ፡፡
በተለይ ደግሞ የሻውያን የቴክኖሎጂና የመገናኛ መሣሪያዎች ዕውቀት ከቀደመው ትውልድ ዕውቀት የፈጠነ በመሆኑ፤ ብዙ ወላጆችም የተለያዩ መሣሪያዎችን አጠቃቀም የሻውያንን ያህል ስለማያውቁ፣ ለአፕሊኬሽኖችና ለአጠቃቀም መንገዶች የሻውያንን ያህል ወላጆች ቅርበት ስለሌላቸው የመቆጣጠር አቅማቸው አናሳ ሆኗል፡፡ ሻውያን ለቴክኖሎጂ ያላቸውን ቅርበትና ዕውቀት፤ ብሎም ከጓደኞቻቸው በቀላሉ የሚያገኟቸውን ልምዶች ተጠቅመው ወላጆቻቸውን የማታለል ዕድላቸው ሰፊ መሆኑ ይነገራል፡፡ አንዱ የወላጆች ሥጋትም ይሄ ነው፡፡ የሽብር ድርጅቶች እነዚህን ልጆች በቀላሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲመለምሉ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑም ይነገራል፡፡
እንደ ሊቃውንቱ ምክር፤ ይህንን የሻውያንን የቴክኖሎጂ ለመድነት ጠባይ ተጠቅሞ ለጥናት፣ ለዕውቀት ማገዣነት፣ ለመረጃ መሰብሰቢያነትና ማኅበራዊ መስተጋብርን ለመፍጠር እንዲጠቀሙበት ማበረታታት ይቻላል፡፡ በ2014 ቴሎፎኒካ በተሰኘ ኩባንያ የተደረገ ጥናት፤ 60 በመቶ የላቲን አሜሪካ ሻውያን የሞባይል ስልካቸውን ለጥናት እንደሚጠቀሙበት ገልጠዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ካልተቻለ ግን ልጆችን ለከፋ ዓለም ዐቀፋዊ ተጽዕኖ ያለ እድሜያቸው ያጋልጣቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሳተላይት በሚለቀቁ የቴሌቭዥን ሥርጭቶች ላይ ወላጆች ዕውቀታቸውን ካላሳደጉ፣ ቴክኖሎጂውን በሚገባ ካላወቁትና የማስተዳደር ዐቅማቸው ከደከመ ልጆቻቸው ቴክኖሎጂውን ለበጎ እንዲጠቀሙበት ለማገዝ ይሳናቸዋል፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት ከሆነ፤ ሻውያን መብት ዐወቅ (civic-minded) ትውልዶች ናቸው፡፡ በሀገራችን እንኳን የአብዮቱ ትውልድ የሌሎች ሀገሮችን የአብዮትና የለውጥ እንቅስቃሴዎች በታሪክ መዛግብት፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ነበር ይረዱ የነበሩት፡፡ ሻውያን ግን በቴሌቭዥን፣ በጡመራ መድረኮች፣ በገጸ ድሮች፣ በማኅበራዊ ገጾችና በፊልሞች አማካኝነት በቀላሉና በፍጥነት የማወቅ ዕድል አላቸው፡፡ የመብት ጉዳዮችን ከትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ከየአቅጣጫው ከሚያገኟቸው መረጃዎችም ይገነዘቧቸዋል፡፡
አንድን ጉዳይ ነውር ነው፣ ባህል ነው፣ ኃጢአት ነው፣ ጽድቅ ነው፣ መመሪያ ነው፣ ትእዛዝ ነው፣ ተገቢ ነው፣ ስለተባሉ ብቻ ለመቀበል ያዳግታቸዋል፡፤ ለምን? ብለው መጠየቅ ያዘወትራሉ፡፡ ለመስማት ትዕግሥቱ ቢያንሳቸውም መሰማት ግን ይፈልጋሉ፡፡ ስለ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጾታዊ፣ ዜጋዊና ሌሎች መብቶች የተሻለ ዕውቀቱ አላቸው፡፡ ጭቆናን፣ የተበላሸ አስተዳደርን፣ የመብት ረገጣን፣ ያረጀ አሠራርን፣ ዘገምተኛነትን፣ አምባገነንነትንና ግፍን ለመቀበል የሚችል ኅሊና የላቸውም፡፡ አስተሳሰባቸው፣ መረጃቸውና ግንኙነታቸው በፈጣን ሁኔታ እንደሚቀየረው ሁሉ አካባቢያቸው በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡
ሻውያን ጭንቅ የማይችሉ ትውልድ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ቢሮክራሲ አይስማማቸውም፡፡ በ2013 የተደረገ የታይም መጽሔት ጥናት ሊቀያየር በማይችል የሥራ መርሐ ግብር(non- flexible work schedule) መሥራትን አይወዱም ይላል፡፡ ነገሮችን በቶሎና በአቋራጭ የሚያገኙበት መንገድ ካለ ያንን ይሞክራሉ፡፡ የመገናኛ ቴክኖሎጂውን በጣም ከሚፈልጉበት ምክንያት አንዱ ይሄ ነገሮችን በፍጥነት ለማግኘት ካለ ጉጉት ነው፡፡ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ የሚባለውን ተረት አይወዱትም፡፡ ‹ሄዱ› ይበቃቸዋል፡፡
ፎርሙላዎችን ወስደው በእነዚያ አማካኝነት ሂደቱን ተጉዘው መልስ ፍለጋ አይንከራተቱም፡፡ ማሽኖችን የሚፈልጉት ቶሎ መልስ ስለሚሰጧቸው ነው፡፡ ሻውያን ትእዛዝ ተቀብለው ከ30 ደቂቃ በኋላ ምግብ የሚያመጡትን ምግብ ቤቶች ማዘውተር አይፈልጉም፡፡ የፈጣን ምግቦች ጥገኛ የሆኑትና ከምግብ ቤቶች ይልቅ ካፍቴሪያዎቹን የሚወዱት ለዚህ ነው ይባላል፡፡
ከረዥም ልቦለዶች ይልቅ አጫጭር ወጎችን፤ ከረዣዥም ፊልሞች ይልቅ ቅንጭብጭቦችን ይመርጣሉ፡፡ የቀድሞው ትውልድ በወታደራዊ ግዳጆቻቸው ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖችን ያደንቅና ስለ እነርሱ የተሠሩትን ፊልሞች፣ የተጻፉትንም መጻሕፍት ይመርጥ ነበር፡፡ ሻውያን ግን እነ “ባትማን”፣ “ሱፐር ማን”ና እነ “ስፓይደር ማን” ከ90 ደቂቃ በኢንተቤና ከየኛ ሰው በደማስቆ በላይ ይማርኳቸዋል፡፡ በግንኙነቶች ጊዜም አጫጭር ሐሳቦችን፣ ኮዶችን፣ አሕጽሮቶችን፣ ይወዳሉ፡፡ በሻውያን ዘንድ ‹የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ነገር ማሳጠር ነው›፡፡ ሻውያን ዘላኑ ትውልድ እየተባሉም ይነገርላቸዋል፡፡ አንድ ቦታ ረግቶ መቀመጥ አይፈልጉም፡፡ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል፤ ድኻ ቀብራሬ ሞቱን ይመኛል› ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ዘመን የብዙ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ችግር ለረዥም ጊዜ ሠርቶ፣ ልምድ አዳብሮ፣ የድርጅቱን ባህልና እሴት ዐውቆ የሚኖር ሠራተኛ ማጣት ነው፡፡ ይመጣሉ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ይሠራሉ፤ እየሠሩ ሌላ ሥራ ይፈልጋሉ፤ ይሄዳሉ፡፡
የሚያግዳቸው፣ የሚወስናቸውና የሚከለክላቸው ሕግና አሠራር አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች በረዥም ጊዜ ቆይታ መሥሪያ ቤቱን ያወቀ ኃላፊ ለመሾም የማይችሉበት ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ በተለይም የአየር መንገዶች የሰው ኃይል ፍልሰቱን የሚሸከሙበት ትከሻቸው እየጎበጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቦታዎችን፣ ከተማዎችን፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ክበቦችን መቀየር ለእነርሱ ጣጣ የለውም፡፡ እምነታቸውን፣ ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ሀገራቸውን፣ ስማቸውን፣ ትዳራቸውንና ሌላውንም ለመቀየር የቀድሞውን ትውልድ ያህል ጽኑዕ አይደሉም፡፡ ድንበሮችን በቀላሉ መሻገር ስለሚወዱና ስለሚችሉ ሻውያን እጅግ የተሣሠሩ (Networked) ትውልድ ናቸው ይባላል፡፡ በጓደኛነት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ በቡድኖችና ማኅበራት ይበልጥ መተዋወቅን፣ መገናኘትን፣ መተሣሠርን፣ ሐሳብ መለዋወጥን፣ ይወዳሉ፡፡ ከአለቆቻቸው ይልቅ ለትሥሥሮቻቸው (Networks) ይታዘዛሉ፡፡ አንድ ድርጅት ውስጥ ሲገቡ ስለ መሥሪያ ቤቱ አሠራር፣ ሕግና ዓላማ ከማወቃቸው በፊት ‹ኔትወርክ› ይዘረጋሉ፡፡ ቶሎ ይተዋወቃሉ፣ ይላመዳሉ፣ ከዚያም ይተሣሠራሉ፡፡ በመጨረሻም ‹ኔትወርካቸው› ትተው ይወጣሉ፡፡
ሻውያን ገንዘብን በቀላሉ እናገኘዋለን ብለው ያስባሉ፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ ቢቀጠሩም እንኳን በ‹ኔትወርካቸው› አማካኝነት የጎን ሥራዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ቶሎ ተሠርተው ጠቀም ያሉ ብሮችን የሚያመጡ ጉዳዮች ውስጥ ይሠማራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት እነርሱን በየድርጅቱ በደመወዝ ብቻ አጽንቶ መያዝ ከባድ ነው፡፡ ይሄ ገንዘብ በቀላሉ ይገኛል የሚለው አመለካከታቸው አንዳንዶቹን ለትምህርት ትኩረት እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡
ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ ፍላጎት፣ የራሱ መንገድ፣ የራሱ እሴትና የራሱ ጀግና አለው፡፡
በተለይ ደግሞ ዘመኑ መረጃ በቀላሉ የሚገኝበት፣ የዓለም ተፈጥሯዊ ድንበሮች በመገናኛ መንገዶች የፈረሱበት፣ ድንበር ተሻጋሪ እሴቶች የሀገሮችን ነባር እሴቶች የሚፈትኑበት ወቅት በመሆኑ ትውልዱም የዚሁ ነጸብራቅ ነው፡፡ መንግሥት፣ ድርጅቶች፣ ማኅበረሰቦች፣ የእምነት ተቋምት፣ የትምህርት ማዕከላት፣ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ መስተጋብሮች እየመጣ ያለውን ትውልድ ተገንዝበውና ተቀብለው ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ለማስተናገድ ካልተዘጋጁ፣ አዲሱ ትውልድ በአዲሱ የራሱ መንገድ ብቻ ሲጓዝ፣ ነባሮቹ የነበረንን ብቻችንን ይዘን መቅረታችን ነው፡፡

No comments:
Post a Comment