Thursday, May 26, 2016

‹‹ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ መብትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረጋገጡት ድርጊት ልከሰስ አይገባም›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ


በፌስቡክ አድራሻቸው አመፁና ብጥብጥ ቀስቃሽ ጽሑፎችን በማሠራጨት፣ የኦነግን ዓላማ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ የቀረበባቸውን ክስ ተቃወሙ፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና በክሱ የተጠቀሰው ብጥብጥና አመፅ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረጋገጡበት ሁኔታ ልከሰስ አይገባም፤›› ሲሉም ተቃውሞአቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ብጥብጥና አመፅ ‹‹የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግር ነው፡፡ የሌላ ሦስተኛ አካል ተሳትፎ የለበትም፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማረጋገጣቸውን ያስረዱት ተከሳሹ አቶ ዮናታን፣ የተለያዩ የፌደራልና የክልል ሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በማጠናከር፣ ዕርምጃ የወሰዱበትና በርካታ ሹማምንትም ከኃላፊነት መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሚያውቀውና ከማንም ያልተደበቀ በመሆኑ፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ግምት (Judicial Notice) የሚወስድበት ጉዳይ መሆኑን አቶ ዮናታን አክለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተደረገው አመፅና ብጥብጥ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑ ተረጋግጦ ሳለ፣ በቀረበባቸው ክስ ላይ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንደተጀመረና እሳቸው በፌስቡክ ገጻቸው ባሠራጩት መጣጥፍ ለማስቀጠል የተደረገ እንደሆነ መገለጹ፣ ከአዋጁ መንፈስ ውጪ መሆኑን በመጠቆም ክሱ ውድቅ ተደርጐ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ዮናታን በክስ መቃሚያቸው ላይ እንዳብራሩት፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን መተላለፋቸው ተገልጿል፡፡ በአንቀጹ እንደተገለጸው ተላልፈዋል የተባለው ድርጊት ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳትና መሞከር የሚል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በክሱ ያሰፈረው አቶ ዮናታን ኦነግ ያስጀመረውን አመፅና ብጥብጥ ለማስቀጠል በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የተለያዩ ቀስቃሽ ጽሑፎችን ማሠራጨታቸውን የሚገልጽ በመሆኑ፣ በአዋጁ አንቀጽ ሥር ከተመለከቱት ውስጥ በአንዱም የማይሸፈን መሆኑን በመግለጽ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግ ክስ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 የተደነገገውን ማለትም ‹‹… ወንጀለኛው የፈጸመው ተግባር፣ ወንጀል ከሚያደርገው የሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን አለበት፤›› ከሚለው ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ዮናታን ፈጽመውታል ለተባለው ክስ በማስረጃነት የቀረበው የሰነድ ማስረጃ በፌስቡክ ገጻቸው ተሠራጨ የተባለው መጣጥፍ መሆኑን ገልጸው፣ ፌስቡክ ደግሞ ዘመናዊ የመልዕክት መለዋወጫ ዘዴ መሆኑን፣ ይኼም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ድንጋጌ ከመሆኑ አንፃር፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በየትኛውም ሕግ ገደብና ክልከላ ያልተደረገባቸውና በቀረበባቸው ክስ በተጠቀሰው አንቀጽ ሥር የማይሸፈንና የሽብርተኝነት ተግባር አለመሆኑንም አቶ ዮናታን አክለዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር የተቀመጡ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን የማያሟላ ክስ መሆኑን ገልጸው፣ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስ ሐሳቡና ይዘቱ አርትኦትና የቃላት ማስተካከል የጎደለው ከመሆኑም በተጨማሪ ለመረዳት የሚያስቸግር፣ በረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችና አባባሎች አሳሳች ሆኖ የቀረበ በመሆኑ በወንጀል መዝገብ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 111 ድንጋጌን ማለትም፣ ‹‹… የክስ ማመልከቻ ቀን፣ ዓመተ ምሕረት የተጻፈበትና የተፈረመበት…›› የሚለውን የማያሟላ መሆኑን አቶ ዮናታን ጠቁመው፣ ክሱ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የሚያሻሽል ከሆነም በሕጉ አግባብ ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ በሚያቀርበው ክስ ላይ የሚጠቅሰው የሕግ አንቀጽ፣ ከክሱ ጋር የሚቀራረብና የተከሳሹን የመከራከር መብት የማያጣብብ አድርጐ እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ጉዳዩን ለሚከታተለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment