ኮለኔል ጎሹ እንደሳቸዉ ትዉልድ በጥሩ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ታንጸዉ ለሀገራቸዉ አንድነትና ለባንድራቸዉ የማሉ መኮንን ነበሩ። ከዉትድርና ተቋሙ በብቃትና በጥራት የፈጸሙ ለመሆናቸዉ አዉሮፓ በነበርኩበት ጊዜ በአንድ ስብሰባ ከአስልጣኛቸዉ ከጄነራል ነጋ ተገኝ አፍ ሰምቻለሁ ተከታታይ ስራቸዉም ይህንኑ ያንጸባረቀም ነበር።ኮለኔሉ በወቅቱ የአዉሮፓ ጉዟቸዉ ወያኔን በሀይል ለመናጥ ያዘጋጁትን ድርጂት ለማስተዋወቅ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ኮለኔል ጎሹ ከተናገሩት መሪ ቃል “ይህ ወጣት ምንም ማድረግ ቢያቅተዉ ስለ ሀገሩ እንዴት መቆጨትና መናደድ ያንሰዋል” ብለዉ የተናገሩት ለረጂም ጊዜ የመወያያ አርስት ሁኖ ሰንብቷል። በእርግጥም ጥሩ አባባል ነበር።
ኮለኔል ጎሹ ወታደር ፤ ምሁር እና ዲፕሎማት ናቸዉ በዋሉበት ቦታ ሁሉ ድምቀት የተሞላባቸዉ ፡ በቆሙበት ቦታ ረትተዉ ፤ተደምጠዉ፤ ተደንቀዉ ፤መክተዉ የሚመለሱ ታላቅ ኢትዮጵዮጵያዊ ነበሩ። አንባቢ ለአንድ አፍታ በስዩም መስፍን እግር የባድሜንና ሌሎች ለሻቢያ የተሰጡትን መሬቶቻችንን ክርክር ኮለኔል ጎሹ ይዘዉት ቢሆን ኑሮ ብሎ በምናቡ ያስብ። ስዩም መስፍን ከጠበቅነዉ በላይ ተሰጠን ብሎ ህዝቡን አስጨብጭቦ እሱም አጨብጭቦ በዛ በተዛባ ድርድር ምክንያት የ70 ሺህ ኢትዮጵያዊ ህይወት ተቀጠፈ ወላድ በየቤቱ ይላቀሳል አዝማቾቹ እነ ስዩም መስፍን ስብሀት ነጋ እና ሌሎቹም በየቤቱ ይስቃሉ። ስለዚህ ጉዳይ ታሪክ ወደፊት በሚገባ ያወጣዋል። በስዩም መስፍን ስንገረም ሌላዉ ትያትረኛ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የ9 አመት ልጂ 8 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ አደረገችልን ብሎ ባለም ያሳቀብንን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተራችንንም ከኮለኔል ጎሹ አንጻር አንባቢ ደምሮ ይመልከትልን :: ታድያ ወደ ጉዳዬ ስመለስ ኮለኔል ጎሹ አገልግሎታቸዉን በብቃት፤በድፍረት እንዲሁም ፕሮፌሺናል ኤቲክስ በሚፈቅደዉ መስፈርት በጥራት የተወጡ ዜጋ እንደነበሩ ኢትዮጵያን እንዲህ ያለ ችግር በገጠማት ጊዜ ጉዳዩን እሳቸዉ ይዘዉት ቢሆን ኑሮ ዉጤቱ ሌላ ይሆን ነበር።
ኮለኔል ጎሹ በእዉቀት ደረጃም በሁለት እጂ የማይነሱ ምሁር እንደነበሩና እስከ አሁንም አስመዝገበዉ ያለፉት ነጥብ ያልተደፈረ መሆኑን እናዉቃለን ከሚሉ ሰዎች ይደመጣል። ወደ ሗላም ወደ ባህር ማዶ ተሻገረዉ ከስመ ጥሩዉ ዬል ዩኒቨርስቲም አድናቆት የተቸራቸዉ እንደነበረ ድርሳናት ያሳያሉ። ከዉትድርና ትምህርት ባሻገር በህግ የረቀቀ እዉቀትና ችሎታ ያላቸዉ ኮለኔል ጎሹ እራሳቸዉን ከአንድ አርእስት ወደ ሌላዉ አርስት በመወረወር በተነሳዉ ነጥብ ሁሉ በሳል አስተያየትን ሰጥተዉና አስተምረዉ የሚመለሱ ዜጋ በመሆናቸዉ ለዲፕሎማቲክ ስራ ተቀራራቢ ሰዉ ሊገኝላቸዉ የማይችሉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
ኮለኔሉ በዲፕሎማሲያዊ ስራ እና ለህዝብ ይፋ ካልወጣዉ አስተዋጽዋቸዉ ሌላ ምን ሰርተዉ ነበር ብሎ መጠየቅ የዜጋ መብት ነዉ ኮለኔል ጎሹም የህዝብ ሰዉ በመሆናቸዉ ይህ ቅር የሚላቸዉ አይመሰለኝም።
የትግራይ ነጻ አዉጭ ድርጅትና ሻቢያ አገሪቱን ከተቆጣጠሩ በሗላ ሊደርስ የሚችለዉ አደጋ ቀደም ሲል ስለገባቸዉ ጠንካራ ድርጅት አቋቁመዉ ኢትዮጵያን ከነዚህ ክፉ ጠላቶች ለማዳን ጥረት አድርገዉ ነበር:: ታዲያ እንደ ኮለኔል ጎሹ፤ፖል ትዋት፤ኢንጂነር ቅጣዉ፤ኮለኔል ታደሰ አይነት ዜጋ የሚመራዉ ድርጅት ፈተናዉ ብዙ በመሆኑ የኮለኔል ጎሹንም ድርጅት የኢትዮጵያ ጠላቶች ከዉስጥና ከዉጭ ተረባርበዉ በለጋነቱ ጣሉት የኮለኔል ጎሹም ሀሳብ ዉጥን ብቻ ሁኖ ቀረ እንደ አንድ መሪ ግን የሚቻላቸዉን አደረጉ በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል።
ኮለኔል ጎሹ አገር ከፈረሰ በሗላ በእጂጉ ከሚታወቁበት ትልቁ ስራቸዉ የአሜሪካን ሴናተር በጠራዉ ስብሰባ ላይ ከሻቢያና ከወያኔ ጋር ያደረጉት ፍልሚያ ነበር። ይህ ህዝብ የጣለዉን መንግስት ጣልን ብለዉ በለስ ቀንቷቸዉ ሸብ ረብ በሚሉበትና እንደ መንትዬ ልጆች ሻቢያ የጀመረዉን ወያኔ በሚጨርስበት የስብሰባ ስርአት ያደረጉት ንግግር በታሪክ ዘወትር ሲታወስ ይኖራል። ኮለኔል ጎሹ ብቻቸዉን ያለአንዳች ረዳት ይህን የበታኝ መንጋ ሲለበልቡት አብረዋቸዉ የተቀመጡት ትንፍሺ ሳይሉ ወጥተዉ ሂደዋል የዛን ቀን ሁኔታቸዉም ከአንዱ የአፍሪካ ሀገር ለታዛቢነት የመጡም አስመስሏቸዋል። ምክንያቱም በለስ ከቀናዉ ሀይል ጥቅም አይጠፋም በሚል ምክንያት በስብሰባዉ ላይ አድፍጠዉ ተቀምጠዉ ነበር:: በሗላም እንደ አምቦ ወንድሞቻችን የኢትዮጵያ ህዝብ ጨክኖ ወያኔንና ሻቢያን እንዳይፋለም አንዴ ጊዜ ስጧቸዉ አንዴም የኛዉ ናቸዉ እያሉ ሲያጃጂሉን ከርመዉ ዛሬ ዉቃቤ ርቋቸዉ ከአንዱ ጎል ወደ ሌላዉ ጎል እራሳቸዉን እየለጉ እለተ ሞታቸዉን ይጠብቃሉ።
ታዲያ አድር ባይነትን ባእጂጉ የተጠየፈዉ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ልጅ ጎሹ ወልዴ ግን በዛን ስብሰባ ብቻዉን ግዳይ ጥሎ ገብቷል።
ጎሹ በዛን ቀን በሰራዉ ስራ ስሙና ተጋድሎዉ ሀገሩን በሚወድ ዜጋ እስከ ወዲያኛዉ ሲታሰብ ይኖራል። ዛሬ ነገር አልፎ ቀላል ቢመስልም በዛን በቀዉጢ ጊዜ አባሎቻቸዉ መረን በወጡበት ዘመን ደፍሮ ሀገሩን ብቻዉን መክላከሉ ሀገሩን በሚወድ ዜጋ ዘወትር ሲታሰብ ይኖራል። እንደዉም የእዉቀቱን ጥልቀት የተረዳዉ የስብሰባዉ ሊቀ መንበር ምን ብናደርግ ይሻላልም ብሎ ሀሳብ ጠይቆ ጎሹም ጥራት ያለዉ መልስ ሰጥቶ ነበር።በዛን ቀን ኮለኔል ጎሹ ባሳየዉ ወታደራዊ መንፈስ፤ የነገር አወራረድ፤ የሃሳብ ብስለት፤ የቋንቋ ጥራትና የታሪክ እዉቀት የተገረመዉ ሴናተር በተመስጦ ሲመለከተዉ ደናቁርቱ ባላንጣዎቹ ደግሞ በክንድ ጠምዝ ምልልስ የጀግናዉ ጎሹን ወልዴን ሀሳብ ሊመክቱ ሲታገሉ በእጅጉ ያሳዝኑ ነበር። በዛን ቀን በተሰራዉ ስራ ኮለኔል ጎሹ ያለምንም ተቀናቃኝ እራሱን ከታላላቁ ጎራ ቀላቅሏል። ያም ስራዉ ተቀራራቢነቱ ለሀገራቸዉ ታላቅ ስራ ሰርተዉ ካሸለቡት ዜጎች እንደ አንዱ ሊሆን ይገባዋል። ድልንና ታላቅ ስራን የምንመዝነዉ እንደ ዘመኑ በመሆኑ ጀግናዉ ጎሹ ወልዴም በዛን ቀን በሰራዉ ስራ ታሪክ እስከ ወዲያኛዉ ሲያስታዉሰዉ ይኖራል። (እዚህ ላይ ነሸጥ አድርጎኝ አንተ ብያለሁ መቼም ጀግና እርሶ አይባልምና)
እንግዲህ ከአንድነት ሐይሎች ሰፈር ኮለኔል ለመገለላቸዉ ምን ምክንያት ሊሰጥበት ይችላል? በእርግጥ ዘመኑ የጨረባ ተዝካር የሆነበት፤ ከአዋቂ ይልቅ ተናጋሪ የተደመጠበት፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት የተመረጠበት ፤ያለዉን ከመያዝ መበተን የተያዘበት፤ ከሀቅ ይልቅ ትርፍ በሚያመጣ ነገር ላይ ማተኮር የተመረጠበት በመሆኑ ይህ ደግሞ ለኮለኔል ጎሹ ስብእና የሚስማማ ባለመሆኑ ዳር ሁነዉ መመልከትን መርጠዉ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ትላንት በካድሬነት ሲያገልግሉ የነበሩ የሶሻሊስት ደቀ መዛሙርት ዛሬ ተገልብጠዉ የዘዉግ አስተዳደር ለኢትዮጵያ መፍትሄ ነዉ ብለዉ የሚሰብኩትንም ላለማየት ፈልገዉም ይሆናል ወይም ደግሞ ኤርትራ በሀይል ተገንጥላ ስትሄድ ፓርላማ ቁጭ ብለዉ ሲያጨብጭቡ ከነበሩ ፓርላሜንታሪያንም ጋር በአንድ መድረክ ላለመቀመጥም መንፈሳቸዉ ተጠይፎም ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ 100,000 ጦር ኢሳይያስ አፈወርቀ ላይ አዝምቶ ዛሬ ኢሳይያስ አፈወርቅ የኢትዮጵያ ወዳጂ ነዉ የሚለዉን ላለመስማት ፈልገዉም ሊሆን ይችላል። ምሁር ተብየዎችም ኢትዮጵያ የማትጠቀምበት እምቅ ሀብት አላት ኑና ዉሰዱ ብለዉ የጥንት አፍራሺ ጓደኞቻቸዉን መታረቂያ ያደረጉት ስብሰባም ሳይመቻቸዉ ቀርቶ ይሆናል።
እንግዲህ ዛሬም እንደ ትላንቱ ለሌላ ጥፋት በየቦታዉ በሚደረገዉ ስብሰባም መገኘት ያልፈለጉበት ታሪክ እራሱን ሲደገም ድንጋይ አላቃብለም ብለዉም ሊሆን ይችላል። ከዚህ ታክኮ የዘር ድርጅቶች በየምክንያቱ በራቸዉን ሲያንኳኩም የለም ይህ እኔን አይመለከትም ዘሬ ኢትዮጵያዊ ነዉ በጽናት እስከ ኢትዮጵያዊነቴ በክብር እንደ አንድ ወታደር እሞታለሁ ብለዉ እንደሚመልሱም ጥርጥር የለኝም። የተለያዩ የሚዲያ ተቋማትም ጎትተዉ ባልፈለጉትና በማይመቻቸዉ አርእሰት አስገብተዉ እንዲያዘላብዷቸዉ ሳይፈቀዱም ቀርተዉ ይሆናል።
ኮለኔል ጎሹ ኢሳይያስን ነጻ አዉጣኝ ብለዉ ያልተማጠኑ፤ለኢትዮጵያ የሚጠቅመዉ በዘር መከፋፈሏ ነዉ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ዘራችን ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል ታሪካችንም 100 አመት አይበልጠዉም ከሚለዉ ዘመን አመጣሺ በሺታ ተከልለዉ መቀመጣቸዉ መልካም ቢሆንም ለተተኪዉ ትዉልድ የሚጠቅም ብዙ ደጎስ ያሉ መጻፍቶችን ቢያስነብቡን በሪፈረንስ መልክ አጠገባችን ይቀመጥ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ለማንኛዉም በኔ በኩል መልካም ጤንነትና እድሜ እየተመኘሁ ከግራ ቀኝ የሚላተሙ የእርሶ ዘመን ሰዎችም የኢትዮጵያዊነትና አንድነት ማተባቸዉን ጠብቀዉ በክብር ወደማይቀረዉ ለመሄድ ቢዘጋጁ መልካም ነዉ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
No comments:
Post a Comment