Wednesday, May 18, 2016

የአዲስ አበባ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች በቅርቡ የፀደቀውን መመርያ በመቃወም አቤቱታ አቀረቡ


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ተሰብስቦ፣ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየውን ምትክ ቦታ ስለመስጠት የሚደነግገው መመርያ ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡
ካቢኔው ከዚህ መመርያ በተጨማሪ የካሳ ክፍያ አሰጣጥ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና ፍትሕ ቢሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ፣ በማሳ ላይ ለሚገኙ ሰብሎችና ዛፎች ስለሚሰጥ ካሳ የከተማ ግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ፣ አርሶ አደሮች የሚያካሂዱትን ምትክ ግንባታ በተመለከተ የኮንስትራክሽንና ግንባታ ፈቃድ ቢሮና የንግድ ቢሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በዕለቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ነገር ግን በልማት ምክንያት እየተፈናቀሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ያቋቋሙት ኮሚቴ ካቢኔው ባፀደቀው መመርያ ላይ ተቃውሞ አቅርቧል፡፡
የአርሶ አደሮች ኮሚቴ በቅርቡ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባቀረበው ደብዳቤ፣ አዲስ የወጣው መመርያ ጠቃሚ ማሻሻያ ያደረገባቸው ነጥቦች ቢኖሩም መሠረታዊውን ግን ስቷል ብሏል፡፡ አዲስ በወጣው መመርያም ሆነ በ2004 እና በ2006 ዓ.ም. በወጡት መመርያዎች እንደሚሉት ለአንድ አርሶ አደር 500 ካሬ ሜትር ቦታ፣ ለአንድ አርሶ አደር ልጅ ደግሞ 250 ካሬ ሜትር ቦታ ምትክ እንዲሰጥ ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን ይህ ቦታ በምትክ እንዲሰጥ ቢደነገግም እስካሁን ተፈጻሚ አለመሆኑን፣ ይህ ተፈጻሚ ቢሆን እንኳ አነስተኛ መሆኑን የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች በካሳ ክፍያና በምትክ ቦታ አሰጣጥ የዘለቄታ ማቋቋሚያን በሚመለከት ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ አቤቱታ ቀደም ሲል አሰምተዋል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ይህንን አቤቱታ በመቀበል በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር ኮሚቴ አዋቅረው የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በመመርኮዝ ማሻሻያ በማድረግ መመርያውን ካቢኔው በካቲት 2008 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡
የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ተስፋ ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመመርያው የተወሰኑ ጠቃሚ ማሻሻያዎች ቢደረጉም መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ መመርያው ፀድቋል፡፡
በአርሶ አደር ተስፋ ረጋሳ የሚመራው የአርሶ አደሮች ኮሚቴ በጻፈው ደብዳቤ ለሦስት ቤተሰብ አባላት እየተሰጠ የሚገኘው ምትክ ቦታ 250 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ከሰባት እስከ አሥር ቤተሰብ አባላት ያሉዋቸው አርሶ አደሮች 400 ካሬ ሜትር ቦታ ምትክ ይሰጣቸዋል፡፡
ይህ የቤተሰብ ቁጥርን መሠረት ያደረገ ሥሌት ፈጽሞ አግባብ አለመሆኑን ደብዳቤው ያትታል፡፡ ደብዳቤው እንደሚገልጸው የመሀል ከተማ ተነሺ ቤተሰቡ ምንም ይሁን ጂአይኤስ ላይ ሰፍሮና ይዞታው 500 ካሬ ሜትር ቦታ ሆኖ ከተገኘ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ይሰጠዋል፡፡
‹‹በከተማ ነዋሪ የይዞታ ባለቤትና በአርሶ አደሩ የይዞታ ባለቤትነት መካከል ልዩነት የፈጠረ፣ አልፎም ተርፎም ተመሳሳይ ኑሮ ሲኖር በነበረ አርሶ አደር መካከል ልዩነት የፈጠረ ነው፤›› በማለት የአርሶ አደሮቹ የተቃውሞ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ 54 ሺሕ ሔክታር ስፋት ያላት ሲሆን፣ በስድስቱ ክፍላተ ከተሞች (ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ የካ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ጉለሌ) 18,174 ሔክታር መሬት ላይ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡
እነዚህ አርሶ አደሮች ለኢንዲስትሪ፣ ለስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለመንገድ አውታሮች ግንባታና ለመሳሰሉት ግንባታዎች ከነበሩበት ቦታ እየተነሱ ይገኛሉ፡፡
አርሶ አደሮቹ ለከተማው አስተዳደር በጻፉት ደብዳቤ የተሟላ የካሳ ክፍያ፣ የተሟላ መኖርያ ሥፍራ (ምትክ ቦታ) እና ቋሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መሬታችን የማይነጥፍ ቋሚ የሀብት ምንጭና ሲወርድ ሲዋረድ በውርስ ይዘን የቆየነው የኑሮ መሠረታችን ነው፤›› በማለት አርሶ አደሮቹ ገልጸው፣ ‹‹ከግብርና ሥራ ውጪ ምንም ሙያ የሌለንና በመሆናችን እናገኝ የነበረው የሰብል፣ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የጓሮ አትክልት፣ ዛፍ በሙሉ ገቢው የሚቋረጥ በመሆኑ፣ ማኅበራዊ ትስስራችን የሚቋረጥና በቂ ካሳ ሊሰጠን ይገባል፤›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
‹‹አጠቃላይ ለአንድ ገበሬ መከፈል ያለበት ካሳ ከሁለት ሚሊዮን ብር ማነስ የለበትም፤›› በማለት የአርሶ አደሮች ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ተፈናቅይ አርሶ አደሮች የሚከፈላቸው ካሳና ምትክ ቦታ አነስተኛ በመሆኑ ለችግር እየተጋለጡ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ችግር ለመፍታት ከወር በፊት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment