Thursday, May 26, 2016

የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ሕዝባዊ ውይይት ሊደረግበት ነው


  • ማስተር ፕላኑ ሦስት ክፍላተ ከተሞች ለሁለት እንዲከፈሉ ሐሳብ አቀረበ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅት ራሱን በማግለሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን ማስተር ፕላን ለይቶ ለሕዝብ ውይይት ሊያቀርብ መሆኑ ታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱ ክልል በሆነው በ54 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን ማስተር ፕላን ከግንቦት ወር በኋላ በማዕከል፣ በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ደረጃ ለሕዝብ ውይይት እንደሚያቀርብ የከተማው ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በማስተር ፕላኑ ላይ ከመከሩ በኋላ የሚሰነዝሩት ጠቃሚ ሐሳብ ተካቶ ካቢኔውም ከተቀበለው፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የኢንዱስትሪ ልማት፣ የገበያ ሥፍራዎች፣ የትራንስፖርት፣ የመንገድ አውታሮች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ የሕንፃ ከፍታ፣ የታሪካዊ ቦታዎች፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ፕላን፣ የከተማ መዋቅር ዕድገት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የአካባቢ ልማትና የፍሳሽ ማስወገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ተለይቶ የተዘጋጀውን ማስተር ፕላን በየጊዜው እየተሰበሰበ በማብላላት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ካቀረባቸው የተለዩ ሐሳቦች መካከል በአዲስ አበባ የሚገኙ ሦስት ክፍላተ ከተሞች ለሁለት እንዲከፈሉ የሚለው ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ ለሁለት እንዲከፈሉ ሐሳብ የቀረበባቸው ቦሌ፣ አቃቂና የካ ክፍላተ ከተሞች ናቸው፡፡
እነዚህ ክፍላተ ከተሞች ለሁለት ከተከፈሉ አዲስ አበባ 13 ክፍላተ ከተሞች ይኖሯታል፡፡ ክፍላተ ከተሞቹ እንዲከፈሉ ሐሳብ የቀረበው እጅግ ሰፊ በመሆናቸው ለአስተዳደርና ለቁጥጥር አልተመቹም በሚል ነው ተብሏል፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ በአጠቃላይ 12 ሺሕ ሔክታር ስፋት አለው፡፡ ልደታ ክፍለ ከተማ ደግሞ 800 ሔክታር ብቻ ስፋት አለው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ወረዳ 10  ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር እኩል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራርና ሠራተኛ ሲመደብ ለሁሉም ክፍላተ ከተሞች እኩል ነው፡፡ ሃያ መኪና ገዝቶ ቢያከፋፍል አሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚደርሳቸው ሁለት ሁለት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የክፍለ ከተማው አመራሮች ክፍለ ከተማውን ለማስተዳደርም ሆነ ለመቆጣጠር መቸገራቸውን በተለያየ ጊዜ ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱም ሁኔታውን በመረዳት ሦስቱ ክፍላተ ከተሞች እንዲከፋፈሉ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
በዚህ ሐሳብ የከተማው አስተዳደር ተነጋግሮ ስምምነት ላይ የደረሰ በመሆኑ፣ ማስተር ፕላኑ ሲፀድቅ ሦስቱ ክፍላተ ከተሞች ለሁለት እንደሚከፈሉ ተገልጿል፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ ነባሩን መንደር ይዞ ሲቀጥል፣ አዲስ የሚቋቋመው ቦሌ አራብሳ ክፍለ ከተማ ደግሞ ማስፋፊያ አካባቢዎችን ይዞ ክፍለ ከተማ ሆኖ እንደሚደራጅ የሪፖርተር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ማስተር ፕላን በ2005 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል፡፡ አዲስ ማስተር ፕላን ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ቢባልም፣ አዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር ተጣጥሞ መሄድ አለበት በሚል የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡
ነገር ግን ሥራው በተገባደደበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል በማስተር ፕላኑ ምክንያት ሁከትና ተቃውሞ በመነሳቱ፣ የኦሮሚያ ክልል በተፈጠረበት ጫና ራሱን አግልሏል፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ለሦስት ዓመታት ያለ ማስተር ፕላን መጓዝ ግድ ብሏታል፡፡

No comments:

Post a Comment