Tuesday, May 31, 2016

ከብጹዐን ጳጳሳት በቀር ካህናትና ቆሞሳት እንኳን የማይገቡበት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝበት መጋበዙ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳየን ነው፡፡

‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› ማለት ሊቀር ነውን? .. ዲ/ን ዳንኤል ክብረት……..
ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩን እንደራሴ ሹመት በተመለከተ ለመወያት የያዘው አጀንዳ የመንግሥት ተወካይ ባለበት እንዲታይ መወሰኑን ዛሬ ጠዋት ሰማን፡፡ ከብጹዐን ጳጳሳት በቀር ካህናትና ቆሞሳት እንኳን የማይገቡበት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማኝ ይሁን ኢአማኒ፣ ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን የማይታወቅ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝበት መጋበዙ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳየን ነው፡፡
በአንድ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ወሳኝ አካል መሆኑን ስናስበው፤ በሌላ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚደረገው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው፤ ውሳኔውም በሐዋርያት ሥራ እንደተገለጠው ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› የሚባልበት ነው(የሐዋ. 15፣29) የሚለውን ስናየው ‹የመንግሥት ተወካይ ይኑርልን› የሚለውን ውሳኔ ኢሃይማኖታዊ ነው ያሰኘዋል፡፡ ለአንድ የሲኖዶስ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት አልበቃው ብሎ ነው የመንግሥትን ተወካይ የሚጋብዘው? ‹ሱባኤ ይዘን፣ ጸሎት አድርገን፤ አንድ ገዳም ወርደን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መክረን› አይደለም ይሉን አባቶቻችን፡፡ ‹የመንግሥትን ተወካይ ጋብዘን› ነው ያሉን፡፡ እንዲያውም ቀኖናው የሊቀ ጳጳሳቱ(ፓትርያርኩ) ጉዳይ ሲታይ ‹በመቀመጫቸው መካከል አንድ ወንበር አስቀምጠው፣ ቅዱስ ወንጌሉን በዚያ ላይ አኑረው፣ ሊቀ ጳጳሳቱ በፊታቸው ተቀምጦ፣ አንድነት ተነሥተው በሩን ዘግተው ይጸልዩ፤ የተሰበሰቡበትንም ጉዳይ በሥውር(በኅቡእ) ይመርምሩ› ነው የሚለው(ፍ.ነ. ዐ.168)፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው የመንግሥት ተወካይ ባለበት የሚታየው? አግዚአብሔር ያየናል የሚለው ጠፍቶ ታዛቢ ቢያስፈልግ እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለታዛቢነት አይበቁም? ቅዱስ ጳውሎስ ‹በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?› (1ኛቆሮ. 6፣5) ያለው ለዚህ ጊዜ አይሆነንም?
በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝ መጋበዙ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና የሚነካ በሌላ በኩልም ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ፤ በመጨረሻም ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትና ታዛቢነት የራስዋን ጉዳዮች በራስዋ ሕግጋት፣ ቀኖናና ሥርዓት መሠረት የመወሰን መብት አላት፡፡ አባቶቻችን ከንጉሥ ሐርቤ ዘመን ጀምረው ከግብጽ ሲኖዶስ ጋር ሲሟገቱ የኖሩት ይህን ሉዐላዊነት ለቤተ ክርስቲያናቸው ለማስገኘት ነው፡፡ ጳጳሳትን ለማግኘት የግብጽ ሡልጣኖች መለማመጥ፣ የግብጽንም ፓትርያርኮች መለመን ሰልችቷቸው፡፡ ከግብጽ ቀድማ ክርስትናና የተቀበለች ሀገር፣ የራስዋን ጉዳይ ለመወሰን አለመቻሏ አስደናቂ ስለሆነባቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያንዋ ታላቅነትና ከሀገሪቱ ክብር ጋር ስላልተመጣጠነላቸው፡፡
ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ መንግሥትን በገዛ ፈቃዳቸው ‹አንተ በመካከላችን ካልተገኘህ አንሰበሰብም› የሚሉ አባቶች መጡ፡፡ ቀደምት አበው ‹አንተ ከኛ ጋር ሁን› የሚሉት ፈጣሪያቸው ነበር፡፡ ዘመን ተቀየረ፡፡ በቀደመው ጊዜ ‹መንግሥት ለምን በጉዳያችን ውስጥ ይገባል?› ነበር ክርክሩ፡፡ ‹አሁን መንግሥት ከሌለ ይህንን አጀንዳ አናይም› የሚባልበት ዘመን ላይ ደረስን፡፡ የፓትርያርክ እንደራሴ ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ እንደራሴውም የሚፈጽመው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ነው፡፡ የሥልጣን ክልሉም በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን ክልል ነው፡፡ ታድያ ለምንድን ነው መንግሥት ያስፈለገው? ይህንን ጥያቄ ፓትርያርኩ ጠይቀውት ይሆናል፡፡ እንደመከራከሪያ ቢያቀርቡት አይገርምም፤ ቢያሳዝንም፡፡ የምልዐተ ጉባኤው መቀበል ግን ሕመም ነው፡፡
መንግሥትስ ቢሆን ምን ብሎ ነው ተወካይ የሚልከው? ምናልባት ‹ጠሩኝ፣ ሄድኩ› ካላለ በቀር፡፡ ሕገ መንግሥታችን መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በግልጽ እየደነገገ እንዴት አድርጎ ነው በቀኖናዊ ስብሰባ ላይ የሚገኘው? ውሳኔውንስ ከየትኞቹ የቀኖና መጻሕፍት ጋር ሊያገናዝብ ነው? በጉባኤው የሚኖረውስ ሚና ምን ሊሆን ነው? ምን ዓይነት ወኪልስ ነው የሚወክለው? በየትኛው ሥልጣንና ሕግ ነው የሚገኘው? የዚህ ዓይነቱ አሠራርስ መጨረሻው ምን ይሆናል? በጉባኤው ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ የማን ውሳኔ ነው? ‹የእኛና መንፈስ ቅዱስ› ወይስ ‹የእኛና የመንግሥት›? መንግሥትም ጉዳዩን ሊያስብበት ይገባል፤ ‹ሲጠሩት አቤት› ሳይሆን ‹ሲጠሩት ለምን?› መሆን አለበት፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ኤጲስ ቆጶስ በዚህ ዓለም መኳንንት ርዳታ አንዳይቆም ያዝዛል፡፡ በእምነቱና በእግዚአብሔር ቃል ብቻ እንዲጸና፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ 176፤ረስጠብ 21) በዲድስቅልያም ላይ ‹ከቤተ ክርስቲያን ሹሞች በቀር ሕዝባዊ አይፍረድ› ይላል (ዐንቀጽ 71)፡፡ ታድያ በምን ሕግ ነው የመንግሥት ተወካይ ባለበት የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤውን የሚያደርገው?
ዛሬ እንደዋዛ የሚከፈተው በር ነገ እንዝጋህ ቢሉት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ አባት የመንግሥት ተወካይ ይገኝልኝ ባለ ቁጥር የሚፈቀድ ከሆነ፤ ነገ ደግሞ ወንድሜ ባለበት፤ እናቴ ባለችበት፤ ሐኪሜ ባለበት፣ ፖሊስ በተገኘበት ይሄ አጀንዳ ይታይ የሚል ነገር መስማታችን አይቀሬ ነው፡፡ ጋባዡም፤ ተጋባዡም ቆመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ መቼም እንደዘንድሮ የእንጦንስና ጳውሊ ራእይ በተግባር የታየበት ዘመን የለም፡፡

No comments:

Post a Comment