Black Market in Ethiopia : ጊዜው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ነው፡፡ ከረፋዱ 4 ሰዓት ሆኗል፡፡ ፈንጠር ፈንጠር ብለው መንገድ ዳር የቆሙ ወጣቶች አላፊ አግዳሚውን እየተጠጉ በሹክሹክታ ዶላር አለ ዶላር ከፈለጋችሁ ይላሉ፡፡ መንገደኞቹ እንዳልሰሙ ሆነው መንገዳቸውን ኮስተር ብለው ይቀጥላሉ፡፡ ወጣቶቹ ውትወታቸው እንዳልሰመረ  ሲያውቁ በዓይናቸው ሌላውን ሰው ማደን ይጀምራሉ፡፡ የሚፈልጉትንና መመዘንዘር የሚፈልግ ዓይነት ሰው ያገኙ ሲመሰላቸው አድራጎታቸው በሌላ ሦስተኛ አካል እንዳይስተዋል እየጣሩ ወደ መንገደኛው ይጣደፋሉ፡፡
በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ወጣት መሉቀን ግርማ (ስሙ ተቀይሯል) መተዳደሪያ ሥራው የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ሰዎችን መደለልና ከቀጣሪው መንዛሪ ድርጅት ጋር ማገናኘት ነው፡፡ ነገር ግን ሥራው ይህንን ያህል ገንዘብ የሚያስገኝለት አይመስልም፡፡ ድሬድ ፀጉሩ ቆሽሿል፡፡ የለበሰው ተቀዷል፡፡ መንችኳል፡፡ ጠየም ያለ ፊቱም  በፀሐይ ተጎድቷል፡፡ ወደ ሥራው ከገባ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ሥራው ከድህነት ባያላቅቀውም አያስርበውም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ብሔራዊ አካባቢ የጥቁር ገበያ የዶላር መግዣ ዋጋው 23 ብር ከ80 ሳንቲም ደርሶ ነበር፡፡ 22 ብር ከ30 ሳንቲም ደግሞ መሸጫው ነው፡፡ እንደ ሙሉ ቀን ያሉ ደላሎች የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማሻቀቡ ጥሩ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ደንበኛ ባመጡ ቁጥር ኮሚሽን ይታሰብላቸዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽን የሚታሰብልን በያዝነው ፈርቅ (ሳንቲም) መጠን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከአንድ ዶላር አምስት ሳንቲም ወይም አሥር ሳንቲም እናገኛለን፡፡ ደንበኞች የሚመነዝሩት የውጭ ገንዘብ መጠን ከፍ ባለ መጠን እኛም የምናገኘው ፈርቅ ይጨምራል፤›› በማለት በቀን እስከ 150 ብር ሠርቶ እንደሚያድር ይናገራል፡፡
በአካባቢው የሚገኙት የአልባሳትና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ህልውና የተመሠረተውም በውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ መሆኑን ሪፖርተር ካነጋገራቸው ደላሎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደነ ሙሉቀን ዓይነት አፈ ቀላጤ ደንበኞችን ተጠቅመው ኪሳቸውን የሚያደልቡ ግለሰቦች የየዕለቱን የባንኮች የውጭ ምንዛሪ መጠን  ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ደላሎቹም ቢሆኑ ደንበኞችን የሚያሳምኑት በጥቁር ገበያ የሚቀርበውን የገንዘብ ልዩነት ከባንኮች ምንዛሪ ዋጋ ጋር በማነፃፀር ነው፡፡
አገሮች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተገናኝተው ለመገበያየት አንድ ዓይነት መገበያያ ገንዘብ ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሠረት አብዛኞቹ ዶላርን ለመገበያየት መርጠው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዩሮ እና ሌሎችም መገበያያ ገንዘቦችም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡  ይህ ክስተት የገንዘቦቹን ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ከመጠን አልፎ የየአገሮቹ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ማድረግ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
ለዚህም መንግሥታት የየአገራቸውን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ፣ የወጪና የገቢ ንግዳቸውን እንዲሁም የሚመሩበትን ርዕዮተ ዓለም መሠረት አድርገው የገንዘቦቹን ዋጋ ይወስናሉ፡፡ በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መተመኛ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው ፊክስድ ኤክስቼንጅ ወይም ቋሚ የምንዛሪ ተመን ሲሆን፣ የምንዛሪ ሥርዓቱ የአገሪቱን የወጪና የገቢ ምጣኔን ባላገናዘበ  ሁኔታ ምንዛሪን የሚወስኑበት ሥርዓት ነው፡፡ በሌላው ጽንፍ የሚገኘው ፍሌክሰብል ወይም ተለዋዋጭ የምንዛሪ ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ሙሉ ለሙሉ በገበያ ላይ ማለትም የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ ምጣኔ እንዲሁም በምጣኔው ወቅታዊ ተለዋዋጪነት ላይ መሠረት በማድረግ የሚመራ ነው፡፡ ሌላኛው የሁለቱ የምንዛሪ ሥርዓቶች ድቅል የሆነው ማኔጅድ ፍሎቲንግ ወይም ቁጥጥር የሚደረግበት የምንዛሪ ሥርዓት ነው፡፡
እነዚህ ሥርዓቶች ለየአገሩ የኢኮኖሚና የውጭ ምንዛሪ የዶላር ቁጥጥር አመቺ ሁኔታን የሚፈጥሩ ቢሆንም፣ በትክክል በሥራ ላይ ካልዋሉ ግን የጎንዮሽ ችግሮች ያስከትላሉ፡፡ ይኸውም የወጪና የገቢ ንግዶችን ባላገናዘበ የውጭ ምንዛሪ ተመን የሚከሰት ጉዳት ነው፡፡ አንድ አገር ኤክስፖርት የምታደርጋቸው በርካታ ምርቶችና አገልግሎቶች ሲኖሯት ብዙ በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ማከማቸት ትችላለች፡፡ ዓለም አቀፍ የመገበያያ ገንዘቦቹም ከአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ጋር የሚኖራቸው ልዩነት የጠበበ ይሆናል፡፡ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት ያነሰ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የዚህ ተቃራኒው ይከሰታል፡፡
ይሁንና አንዳንድ መንግሥታት የአገራቸውን የገቢና የወጪ ንግድ መጠን ባላገናዘበ ሁኔታ ማለትም በፊክስድ የውጭ ምንዛሪ አተማመን ሥርዓት የዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች ዋጋ እንዲተመን ያደርጋሉ፡፡ ይህም ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ሲፈጥር ይታያል፡፡ ለምሳሌ በደርግ መንግሥት ወቅት በኢትዮጵያ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማንሳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የዶላር ዋጋ አምስት ብር ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተመኑ ግን ትክክለኛው የዶላር ዋጋ የሚያሳይ አልነበረም፡፡ አገሪቱ ኤክስፖርት የምታደርገው የምርት መጠን ከዛሬው በልጦም አይደለ፡፡ የአገዛዝ ሥርዓቱ የዕዝ ኢኮኖሚ በመሆኑ በገበያ ሁኔታ ባለመመራቱ እንጂ፡፡ ሁኔታው ትክክለኛውን የዶላር ዋጋ የሚያሳይ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ጥቁር ገበያዎች እንዲፈጠሩ መንገዱን ጠረገ፡፡ በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው የዋጋ ልዩነትም ብዙዎች ወደ ጥቁር ገበያው እንዲሳቡ አደረጋቸው፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አገሪቱ የኢኮኖሚ ሥርዓቷንና በገበያ በሚመራ የምንዛሪ ተመኗን ደግሞ ወደ ማኔጅድ ፍሎቲንግ ሥርዓት ቀየረችው፡፡ ይህም በጥቁር ገበያና በባንኮች የነበረው የዶላር ዋጋ ልዩነት እንዲጠብ አደረገው፡፡ በሌላ አገላለጽ መደበኛ የምንዛሪ ገበያው ትክክለኛውን የዶላር ዋጋ ማንፀባረቅ ቻለ፡፡ አሁን ላይ በጥቁር ገበያና በባንኮች መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ጠባብ ቢሆንም ብዙዎችን ግን ወደ ጥቁር ገበያ ከመሄድ አላገዳቸውም፡፡
በአንድ ተቋም ውስጥ የሒሳብ ሥራ ባለሙያ ሆኖ የሚሠራው የ28 ዓመቱ ሰለሞን (ስሙ ተቀይሯል) ጥቁር ገበያን ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል ነው፡፡ በሥራ አጋጣሚዎች ከአገር ሲወጣ ሙሉ ወጪውን መሥሪያ ቤቱ ይሸፍንለታል፡፡ ይሁንና በግሉ ውጭ የሚሄድበት ጉዳይ ሲኖረው ከባንክ የሚመነዝረው ዶላር አይበቃውም፡፡ ስለዚህ የጎደለውን ለመሙላት ወደ ጥቁር ገበያ መሄዱ አልቀረም፡፡
የኤሌክትሮኒክሶች ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ አልባሳት በርካሽ ገዝቶ አገር ውስጥ በማስገባት አትርፎ ለመሸጥ ሲል ከስድስት ወራት በፊት ዱባይ ሄዶ ነበር፡፡ ለዚህም ከሞላ ጎደል 10,000 ዶላር አስፈልጎት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከባንክ ማግኘት የቻለው 1,500 ዶላር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የተቀረውን ከጥቁር ገበያ በ23 ብር ሒሳብ ገዝቶ መሙላት ነበረበት፡፡
እንደ ሰለሞን ለንግድ ሲሉ የውጭ ምንዛሪ ከሚፈልጉ ሰዎች ባሻገርም ለሕክምና ወደ ውጭ የሚወጡ ሰዎች ከባንክ የሚያገኙት ምንዛሪ አነስተኛ በመሆኑ ወደ ጥቁር ገበያ ለመሄድ ይገደዳሉ፡፡
አቶ አስማማው (ስማቸው ተቀይሯል) በውጭ አገር የተደረገላቸውን ሕክምና ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ጥቁር ገበያን ከጎበኙ ሰዎች መካከል ናቸው፡፡ ለ15 ዓመታት ያህል የቆየባቸው የልብ ሕመም በአገር ውስጥ ሕክምና የሚድን አልነበረም፡፡ ህንድ  ሄደው እንዲታከሙ ተነገራቸው፡፡ ወጪውን የሚሸፍን አቅም አልነበራቸውም፡፡ ለሕክምናው የተጠየቁት ገንዘብ 30,000 ዶላር ነበር፡፡ ከመሞት መሰንበት ያሉት አቶ አስማማው ዕርዳታ አሰባስበው ለሕክምናው የሚያስፈልገውን 600,000 ብር አገኙ፡፡ ብሩን ወደ ዶላር መመንዘሩ ግን ሌላ ራስ ምታት ተከሰተ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ከ12,000 ዶላር በላይ ሊመነዘርላቸው አልቻለም፡፡ ምናልባት ሌሎች ባንኮች ይሰጡኝ ይሆናል በማለት ለመመንዘር ሞክረው ነበር፡፡ ይሁንና አሠራሩ ስለማይፈቅድ ሙከራቸው አልተሳካም፡፡ በመሆኑም ብቸኛ አማራጭ ወደሆነው ወደ ጥቁር ገበያ ለመሄድ ተገደዱ፡፡ በወቅቱ መደበኛው የዶላር ዋጋ 21 ብር ከ40 ሳንቲም ነበር፡፡ ከጥቁር ገበያ የገዙት  ግን በ22 ብር ከ80 ሳንቲም ነው፡፡
በንግድና በሕክምና ሰበብ ጥቁር ገበያን ለመጎብኘት ከሚገደዱት ባሻገር በአሁኑ ወቅት እየተለመደ የመጣ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ሐዋላ ከተለመደው በሐዋላ መላክ የተለየ ነው፡፡ ይኸውም አንድ ባህር ማዶ ያለ ግለሰብ አገር ውስጥ ላለ ወዳጁ ገንዘብ መላከ ቢሻ ባንኮችን ሳይጠቀም ዶላሩን የሚልክበት ሁኔታ ነው፡፡ ይኸኛው ዓይነት አካሄድ ገንዘቡን መላክ የሚፈልገው ግለሰብ እዚያው ለሚገኝ በጥቁር ገበያ ሥራ ለተሰማራ ሰው የሚፈልገውን ገንዘብ ይሰጠዋል፡፡ ተቀባዩም እዚህ ላለ ኔትወርከር (አብሮት ለሚሠራው ሰው) ደውሎ ያሳውቀውና የተቀበለው ዶላር በጥቁር ገበያ ዋጋ ተመንዝሮ አገር ውስጥ ላለው ተቀባይ ሰው እንዲሰጠው ያዘዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ገንዘቡ ለላኪው ወዳጅ ይደርሰዋል፡፡
ይህንን መንገድ የሚጠቀሙ ብዙዎቹ ሰዎች ሕገወጥ ሥራ ስለ መሥራታቸው ግንዛቤ አይኖራቸውም፡፡ ጥቂት የማይባሉት ግን ሕገወጥ መሆኑን እያወቁ በድፍረት መርጠው ይጠቀሙታል፡፡
‹‹ጥቁር ገበያ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል፤›› የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸ፣ ጥቁር ገበያ የሚፈጠረው መንግሥት የምንዛሪ ተመን ሲያወጣ፣ ሕዝቡ በአገሩ ገንዘብ ሳይተማመን ሲቀርና በዶላር እጥረት ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፣ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ቢመጡም ዋና ዋና የሚባሉ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴና የመሳሰሉትን ከውጭ ማስገብቷ አልቀረም፡፡  ወደ ውጭ ከሚላከው ይልቅ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በርካታ ሸቀጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከፍ እንዳይል የሚደረገውን ጥረት ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ ሁኔታው የብርን የመግዛት አቅም በየዓመቱ በአምስት በመቶ እንዲቀንስ እያደረገው ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህ ክስተት አገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ ጥቁር  ገበያ አገሪቱ በየዓመቱ ልታገኝ የሚገባትን ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ አድርጓታል የሚሉ ጥናቶችም እየወጡ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ በባንኮች የአሠራር ክፍተት የተፈጠረ ችግር እንደሆነና የጥቁር ገበያ መፈጠር የባንኮቹን አቅም ይበልጥ እንዳዳከመው የሚናገሩት፣ በወጋገን ባንክ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ክፍል ባለሙያ ናቸው፡፡
ከጥቂት ጊዜያት በፊት 50 በመቶ የሚሆነው የባንኩ ትርፍ ከውጭ ምንዛሪ የሚገኝ ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባለው የጥቁር ገበያ መንሰራፋት እውነታው ተቀይሯል፡፡ ‹‹ጥቁር ገበያ የባንኩን ግማሽ ድርሻ እየተካፈለ ነው፤›› ያሉት እኝህ ባለሙያ፣ ባንኩ የደንበኞችን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማሟላት በብዙ እየተቸገረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከየካቲት ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ካቀረቡ ባለሀብቶች መካከልም ምላሽ ያገኙት አሥር በመቶ ብቻ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
የጥቁር ገበያው እንቅስቃሴ  የሚፈጥረው ተፅዕኖ በውጭ ምንዛሪ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በየባንኩ ያለውን የብር ክምችትም አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ‹‹ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ሰዎች ብር ከባንክ ያወጣሉ፡፡ ይህም በባንክ ውስጥ ያለውን የብር ክምችት በተዘዋዋሪ መንገድ ይጎዳዋል፤›› ሲሉ የጉዳዩ አሳሳቢነት በብር ላይም እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከመቼውም በላይ ማሻቀቡን የሚናገሩት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ ጥቁር ገበያ በመደበኛው አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ፈልገው ወደ ባንኩ የሚሄዱ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ባንኩም ደንበኞቹን ማስተናገድ የሚችለው ባለው ክምችት መሠረት እንደሆነ ገልጸው፣ ለአንድ ሰው ይህንን ያህል ተብሎ የተወሰነ የዶላር መጠን ባይኖርም እንደደንበኞቹ ሁኔታ የሚጠሰው የዶላር መጠን ከፍና ዝቅ ይላል ብለዋል፡፡ ይሁንና ካለው የዶላር ክምችት አንፃር ለደንበኞቹ የጠየቁትን ያህል ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ለዚህም ጥቁር ገበያ ላይ ያለው የውጭ ምንዛሪ በመደበኛው አገልግሎት በባንኮች በኩል ቢካሄድ፣ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ መልኩ መቀነስ እንደሚቻል አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ በሆነው ጥቁር ገበያ ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ከባህር ማዶ ከመደበኛው አገልግሎት ውጪ በሰው በኩል ገንዘብ የሚልኩ አንዳንዶች መደበኛው አገልግሎት የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ ውድ በመሆኑ በሰዎች በኩል በእጅ መላኩን እንደሚመርጡት ይናገራሉ፡፡ እነሱ ይህንን ቢሉም መደበኛው አገልግሎት ዌስተርን ዩኒየን፣ ደሀብሽል፣ ትራንስፋስት ወዘተ. ያሉት የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ሐዋላ ያሉት ከሚሰጡት ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት አንፃር የሚጠይቁት ዋጋ ውድ እንደማይባል የሚገልጹም አሉ፡፡
‹‹የውጭ ምንዛሪ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ በሰው በኩል የሚተላለፍበት ሁኔታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የዓለም ክፍሎች የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በርካቶች መደበኛውን አገልግሎት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፤›› የሚሉት የ251 ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲስ ዓለማየሁ ናቸው፡፡ አቶ አዲስ እንደሚሉት፣ መደበኛ ባልሆነ መልኩ ወደ አገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦች አስተማማኝ አይደሉም፡፡ ከዚህም ሌላ በተባለበት ወቅት ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ መደበኛዎቹ የውጭ ገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎቶች ግን ከዚህ የፀዱና ለሚሰጡት አገልግሎት የሚጠይቁት ዋጋም ምክንያታዊ እንደሆኑ ይሞግታሉ፡፡
ምንም እንኳ ጥቁር ገበያ ቢኖርም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የባንክ ተጠቃሚ መሆናቸው ለመደበኛው አሠራር አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ አቶ አዲስ ያምናሉ፡፡ ‹‹ጦርነቱ የሚሸነፈው በዳኝነቱ ነው፤›› የሚሉት አቶ አዲስ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2025 በጥሬ ገንዘብ የማይገበያ (ካሽለስ) ማኅበረሰብ እንደሚፈጠር፣ ይህም ለጥቁር ገበያ መጥፋት መንስዔ እንደሚሆን አክለዋል፡፡
ከተለያዩ አገሮች ጋር የሚደረገው የንግድ ትስስር፣ አገሪቱ የጀመረቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችና ሌሎችም ጉዳዮች የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከመቼውም በበለጠ አሳድጎታል፡፡ ይህም ከመደበኛው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ጎን ለጎን ጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ እያደረገውም ይገኛል፡፡
ኢኮኖሚው የበለጠ ነፃ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲበዛ፣ የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ዋጋው እየጨመረ ሲሄድ ጥቁር ገበያ ድራሹ ይጠፋል ሲሉ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የጥቁር ገበያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያብራራሉ፡፡ ለዚህም አሠራሯን በገበያ መር  ኢኮኖሚ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ 295 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ የቻለችውን ህንድ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ ባለሙያዎች የምንዛሪ ገበያ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ይሆናል ብሎ ማሰብና ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ ታሟላለች ማለት የዋህነት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ለዚህም አገሪቱ ካለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታና ሙሉ ለሙሉ ኢኮኖሚን ነፃ ማድረግ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ አደጋን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ ህልውና ምንም እንኳን ቢዳከምም እንደሚቀጥል ያምናሉ፡፡
ባንኮች ባለው የዋጋ ልዩነት ከጥቁር ገበያ ጋር መወዳደር አይችሉም፡፡ የየዕለቱን የውጭ ምንዛሪ ተመን የሚያወጣላቸውም ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ያወጣውን ተመን መተላለፍም ሕገወጥ ነው፡፡ በመሆኑም የባንኮችን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥለውን የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ መከላከል የሕግ አስከባሪው ኃላፊነት ይሆናል፡፡