Tuesday, May 31, 2016

በእንደራሴ ምደባ ጉዳይ: ፓትርያርኩ እስከ ነገ አቋማቸውን የሚያሳውቁበት የማሰላሰያ ጊዜ ተሰጣቸው


Abune Mathias perplexed
  • ከንግግራቸው በተፃራሪ በአማሳኞችና በተሐድሶ መናፍቃን ተጽዕኖ ውስጥ ወድቀዋል
  • የተጽዕኖው አስጊነት ምደባውን አስፈላጊ እንዳደረገው በምልዓተ ጉባኤው ታምኖበታል
  • ፓትርያርኩ፣ “ሌላ አለቃ ልታስቀምጡብኝ ነው ወይ?” በሚለው ተቃውሟቸው ውለዋል
  • በተቃውሞ ከጸኑ፣ ጉባኤው በአብላጫ ድምፅ ወስኖበት ሌላ ሰብሳቢ በመምረጥ ይቀጥላል
*           *           *
  • ቅ/ሲኖዶስ፣ የመጨረሻው መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭ እና ወሳኝ አካል ነው
  • ሕጎችን ያወጣል፤ ያሻሽላል፤ ይሽራል፤ የአስተዳደር መዋቅርን ደረጃና ተጠሪነት ይወስናል
  • በእንደራሴ ምደባ ጉዳይ የሚያሳልፈው ውሳኔም፣ የሕገ ቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ይኾናል
  • ፓትርያርኩን በአመራር ለማገዝ ለሚሾመው እንደራሴ ምደባ፣ ዝርዝር ደንብ ይወጣል
*           *           *
  • ፓትርያርክ የሚባሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ የቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን አባት ናቸው
  • የፓትርያርክነት/ርእሰ ሊቃነ ጳጳስነት ሥልጣናቸው የአመራር እንጂ የክህነት ደረጃ አይደለም
  • ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ያለአድልዎ የማስተዳደር እና የመምራት ሓላፊነት አለባቸው
  • ቤተ ክርስቲያንን ማስነቀፋቸውና ታማኝነት ማጣታቸው ከተረጋገጠ ከሥልጣናቸው ይወርዳሉ
*           *           *
በዛሬ፣ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ከምደባው ጋር በተያያዘ ከምልዓተ ጉባኤው ውይይት የሚጠቀሱ፡-
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፡-
  • “በሕጉ እንደራሴ ይመደብ የሚል ሕግ የለም፤ ከሕጉ ውጭ ነው፤ ሕጉ ይከበር፤ እኔስ ምን አደረግኋችኹ? እየሠራኹ አይደለም ወይ? ከእኔ በላይ ሌላ አለቃ፣ ሌላ ባለሥልጣን ልታስቀምጡ ነው ወይ?”
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡-
  • “ምልዓተ ጉባኤው÷ ሕግ የማውጣት፣ የወጣውን የማሻሻልና የመሻር ከፍተኛ ሥልጣን አለው፤ ውሳኔውም እንደ ሕግ ይሠራል፤ የቅዱስነትዎም ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ ሓላፊነትዎ ከባድና ክፍተቱ ብዙ ቢኾንም የተሰጠዎትን ከመናገር በቀር ምንም አልሠሩም፤ ምክርዎም ከአማሳኞችና ከመናፍቃን ጋር ነው፤ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ እስከ ሀገረ ስብከትና አጥቢያ ድረስ ወርደው ሥራ አስኪያጅ፣ ጸሐፊ እና ሒሳብ ሹም ይመድባሉ፤የምንሾመው የሚያግዝ እንደራሴ ነው፤ አንድ ብቻ ሳይኾን ብዙ ሊያስፈልግ ይችላል፤ ከዚኽ በፊትም በየዘመነ ፕትርክናው ሠርተንበታል፤”
  • እንደ ጉባኤው ሕግና ደንብ፣ አጀንዳው በድምፅ ብልጫ ሊወሰንበት ይገባል፤ ምልዓተ ጉባኤው 50 ለ1 ኾኖ መቀጠል የለበትም፤
  • ፕትርክናዎን ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ለቤተ ክርስቲያን ከሚያስቡ ጋር ሊሠሩበት እንጂ ከማይመለከታቸውና ከሚያበጣብጡን ጋር ሊመክሩበት አይገባም፤ ካልኾነ ሥልጣኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤
  • ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር መሥራትዎ ግድ ነው፤ ሕዝብ ይግባ፤ መንግሥት ይግባ ማለት ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሕገ መንግሥቱን አለማወቅ ነው፤ ማንም በማንም መግባት አይችልም፤ እኛም አንፈልግም፤
  • ቤተ ክርስቲያን በሕዝብ መካከል ኾና ኹሉንም በአንድነት የምትጠብቅ ችግር ፈቺና አስታራቂ ተቋም ናት፤ እነእገሌ ይግቡ፤ እነእገሌ ይምጡ የሚለው አስተሳሰብ የመከፋፈል አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ከውጭ የሚረጩት ነው፤
  • ለረጅም ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና በብፁዓን አባቶች ላይ ሲዘምቱ የቆዩ መናፍቃን፣ ስለአጀንዳው የሚያሰራጯቸው አሉባልታዎች፣ ፍጹም ሐሰትና ኾነ ተብሎ የጉባኤውን አቅጣጫ ለማስለወጥ የሚያናፍሷቸው ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment