እመቤት ግርማ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዳ ያደገች ነች፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነች ማለት ነው፡፡ እመቤት ብቻ ሳትሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ እመቤት በዚህ ዕድሜዋ የአራት ዓመት ታላቋን ኢሕአዴግን “ታናሽ ታላቁን መጠየቁ ወግ ነውና” በማለት “ከቶ ምን ለውጥ አመጣህ ይሆን?” እያለች ትጠይቀዋለች፡፡ አንብቧት፡፡
“…ሕፃናት እጅግ ደስ ብሎናል፣ ግንቦት 20 ዛሬ ደርሶልናል፣ ግንቦት 20፣ ግንቦት 20፣ የሰላም ቡቃያ…”
ያኔ ነፍስ በማናውቅበት የሕፃንነት (የተማሪነት) ዕድሜያችን በአስተማሪዎቻችን መሪነት ይህን መዝሙር በኅብረት ሆነን እና ‹ግንቦት 20› የሚል የካርቶን ኮፍያ አድርገን በየአደባባዩ እየዞርን ዘምረናል፡፡ የመዝሙሩ መልዕክት ምን ማለት እንደነሆነ ባይገባንም ለካርቶን ኮፊያ እና ለመንገድ ላይ ሰልፍ ስንል በደመ ነፍስ ላንቃችን እስኪሰነጠቅ እንዘምር ነበር፡፡ ልክ የትግራይ ሕፃናት ምኑም ሳይገባቸው ‹መሥመርዩ መሓርያ› እንደሚሉት፤ ወይም አርቲስቶቻችን በቅጡ ሳይረዱት “ምነው ሞት እንዲህ ጨከነ” ብለው እንዳቀነቀኑት፡፡ እንዲሁ በደመ ነፍስ ዛሬ አድገን እንኳን ትርጉሙ ያልገባንን መዝሙር ከመዘመር ባለፈ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) ደርግ ይጠቀምበት የነበረ የሬዲዮ ጣቢያን ፣ ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም› ሲባል ከተቆጣጠረበት በኋላ የተወለድን የዘመነ ኢሕአዴግ ልጆች ነንና፡፡ ዛሬ እኔ 21 ኢሕአዴግ ደግሞ 25 ዓመታችንን ይዘናል፡፡. እናም ታናሽ ታላቁን ያልገባውን ጥያቄ እንዲያስረዳው እንደሚጠይቀው እኔም ለአራት ዓመታት ታላቄ ኢሕአዴግ 25ኛ የልደት በዓሉን በሚያከብርበት በዛሬው ዕለት ጥቂት ጥያቄዎችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ በርግጥ የጥያቄዎቼ መልስ “አትጨቅጭቂኝ ልማቴን ላፋጥንበት”’ አልያም “እነዚህን እኮ ከ25 ዓመታት በፊት መልሻቸዋለሁ” የሚሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባውቀውም በግንቦት 20 ‹በተረጋገጠው› ዴሞክራሲያዊ መብቴ ተጠቅሜ መጠየቄን እቀጥላለሁ፡፡
ታላቄ ኢሕአዴግ ሰፊው ሕዝብ ማነው? የሰፊው ሕዝብ ጥቅምስ ምንድነው? በየዓመቱ ለግንቦት 20 ዋዜማ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን የሚታየው አስከፊው የደርግ ስርዓት እና ዛሬ በእኛ ዘመን ያለው አገዛዝስ ልዩነታቸው ምንድን ነው? ግንቦት 20 ‹የነጻነት በዓል› የተባለበትስ ምክንያት ምንድን ነው? በርግጥ ጥያቄዎቼ የማያልቁ ቢሆኑም መልሱን ከኢሕአዴግ እንደማላገኝ አውቀዋለሁና በራሴ አረዳድ እና በጥቂት ተሞክሮዎቼ በመመርኮዝ ራሴ ለጠየኳቸው ጥያቄዎች እኔው ራሴው ምላሽ ለማግኘት እሞክራለሁ፡፡
ሰፊው ሕዝብ ማነው?
በኢሕአዴጋውያን አነጋገር የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው፣ በትግሉ ወቅት ብዙ ወጣቶች የተሰዉት፣ አስከፊው የደርግ ስርዓት የተገረሰሰው፣ ኢሕአዴግ ለ25 ዓመታት በብቸኝነት፣ በመንግሥትነት ሥልጣን መንበር ላይ የኖረ ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል› ነው፡፡ ታዲያ፣ ‹ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት ነው ‹ሰፊው ሕዝብ› የተረጋገጠለት ጥቅምስ ምንድን ነው?› ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ የኢሕአዴግ የ‹ሰፊው ሕዝብ› ትርጓሜ ከተለመደው ትርጉማችን በተቃራኒ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በቀጥተኛ ትርጓሜው ሰፊው ‹ሕዝብ› ማለት፡ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ብዝኻውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክለው ታላቅ ክፋይ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ክፋይ ማለትም ተማሪው፣ ምሁሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ወታደሩ… ከግንቦት 1983 ጀምሮ ጥቅማቸው ተከብሮ ሳይሆን ተረግጦ የሚገኝ መሆኑን ስንመለከት ‹ሰፊው ሕዝብ› በኢሕአዴግ መዝገበ ቃላት ሌላ ትርጉም የሚይዝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እዚህ ላይ የኢሕአዴግ ነባር ታጋይ የነበረው ኅላዌ ዮሴፍ ‹እያወገዙ መሆን› በሚል ርዕስ ለደርግ ባለሥልጣናት “‹ሕዝብ› ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ለዛሬዎቹ ኢሕአዴግዎች በልክ የተሰፋ በሚመስል መልኩ ምላሽ የሰጠበትን ግጥም በቅንጭቡ እንመልከት፡-
በርሶ ትርጉም ትንታኔ ሕዝብ ማለት ምን ማለት ነው ለአገር ለጎረቤትዎ በሬዲዮ የሚሉትን የሚያወሩትን በትርጉም ሳይሆን በልብ በሚያምኑበት በራስዎ የሚስጢር ኪስ በማስታወሻዎ በያዝዋት ምንም ሳያንገራግሩ ገለጥለጥ አድርገው ያጫውቱን እባክዎ ሕዝብ ማለት ወዛደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ … ናቸው አይበሉን የለም የለም ይህ አይደለምስንተዋወቅ! በርሶ ትርጉም በምናውቀው በሚወራው ሳይሆን በሚሰራው …በእናንተ እምነት ሕዝብ ማለት ከበርቴ ፋሸስቶቹ በላኤ-ሰቦች ጨፍጫፊዎቹ የድርጅት ክቡር ሰዎች የሥርዓቱ ባለሟሎች እና ጓዶች … እነዚህ ብቻ ናቸው፤እናንተ ሕዝብ የምትሏቸው …
እናም የትናንት ደርግን አውጋዦቹ ኢሕአዴጋውያን ዛሬም እነሱ በደርግ ፈለግ ተጉዘው ‹ሰፊው ሕዝብ› የሚለውን ቃል ልማታዊ ባለሀብቶች፣ የድርጅት አባላት፣ የጊዜው ባለሥልጣኖች፣ የስርዓቱ ባለሟሎች… የሚል ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ በአገራችን ውስጥ የአብዛኛውን ሕዝብ የሰቆቃ ኑሮና የጥቂት የስርዓቱ ባለሟሎች የቅንጦት ኑሮ መመልከት በቂ ነው፡፡ እናም ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም› ሲል ደርግን የተፋለመው ኢሕአዴግ ዛሬም ‹በሰፊው ሕዝብ› ፍላጎት እና ድጋፍ እነሆ 25ኛ የልደት በዓሉን በማክበር ላይ ነው፡፡ ‹ብራቮ› ‹ሰፊው ሕዝብ›!
በግንቦት 20 ምን ተለወጠ?
የግንቦት 20 ሰሞን ‹ዶክመንተሪዎች ሁሉ ወደ ደርግ ያመራሉ› በሚል ያልተጻፈ መርሕ፤ በኢሕአዴግ ሚዲያዎች የደርግን ገዳይነት፣ የደርግን ገራፊነት፣ የደርግን አምባገነንነት… በጊዜው ምሁራን የሚያስተነትኑበትና የሚያስወግዙበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ የሁሉም ‹ዘጋቢ ፊልሞች› መደምደሚያ የኢሕአዴግን ዴሞክራሲያዊነት፣ ልማታዊነት፣ ሆደ ሰፊነት… የሚናገሩ ‹አንዳንድ የኅብረተሰባችን ክፍሎች› አስተያየት ነው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ዘጋቢ ፊልሞች እና የምሁራንም ሆነ ‹አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች› አስተያየት ባሻገር የኢሕአዲግ እውነተኛ ባሕሪይ ሲፈተሸ ከ’83 በፊት ከነበረው እና ዛሬ ገዢዎቻችን ከሚኮንኑት ከደርግ በባሰ መልኩ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጣሱ፤ በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዜጎች ሞትን እየደፈሩ ከአገራቸው ሲሰደዱ፤ ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸውና ልዩነታቸው ምክንያት መኖሪያቸው እስር ቤት ሲሆን መመልከት የተለመደ የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል፡፡
በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የደርግን ስርዓት በመጽሐፍት ከማንበብና ከሰዎች ከመስማት ውጪ ያልኖርኩበት እና የማላውቀው ቢሆንም፣ አሁን ባለሁበት የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን ግን ንፁኃን ጓደኞቼ ያለምንም ጥፋት በተደጋጋሚ ለእስር ሲዳረጉ ተመልክቻለሁ፡፡ በ17 ዓመቴ በ‹ማርች 8› የተዘጋጀ የሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ ‹መፈክር አሰምተሻል› በሚል ተልካሻ ምክንያት የሽጉጥ አፈሙዝ በተመርማሪ አፍ ውስጥ ከቶ ማስፈራራትን እንደ መዝናኛ ሥራ በሚቆጥር ‹ጋጠወጥ› የደኅንነት አባል ተመርምሬያለሁ፡፡ ሳሙኤል አወቀን የመሰሉ ከሠላማዊ ትግል በስተቀር ምንም ዓላማ የሌላቸው ወጣቶች በሞት ሲቀጠፉ ተመልክቻለሁ፡፡ እና ስለዚህ ስርዓት ለኔ ከኔ በላይ ምስክር አይኖርም፡፡
እናም በእኔ አመለካከት “ግንቦት 20 ምን ለወጠ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሹ “አምባገነን ግለሰቦችን ከሥልጣን አውርዶ ሌሎች አምባገነኖችን ወደ ሥልጣን ከማምጣት በስተቀር ሌላ ያመጣው ለውጥ የለም” የሚል ነው፡፡ ይህንን ንፅፅር በግርድፉ ስንመለከተው በቀይ ሽብር ሰማ㙀ታት ሙዚየም የደርግ ዘመን ወጣቶች እንዴት ይገረፉ እንደነበር ከሚያሳየው ፎቶ ባልተለየ መልኩ ዛሬም ማዕከላዊን በመሰሉ የአገሪቱ እስር ቤት ወጣቶች ይገረፋሉ፡፡
በደርግ ዘመን ወጣቶች በአደባባይ እንደሚገደሉ ሁሉ ዛሬም ወጣቶች በአደባባይ ይገደላሉ፡፡ የነጻነት እና ፍትሓዊ ምርጫ ጉዳይም ‹እንዲያው ዝም› የሚባል ጨዋታ ከሆነ ዋለ አደረ፡፡ ለዚህም ነው ለኔ የግንቦት 20 ለውጥ የግለሰቦች ለውጥ እንጅ የስርዓት የማይሆነው፡፡
No comments:
Post a Comment